Saturday, 14 December 2013 12:45

ድፍረት፣ ጥልቀት እና ቁጥብነት “የኢትዮጵያ ኮከብ” ደራሲ መገለጫዎች

Written by  በብርሃኑ ገብረጊዮርጊስ
Rate this item
(16 votes)

መግቢያ
ከ”የኢትዮጵያ ኮከብ” መፅሐፍ ደራሲ ከአብነት ስሜ ጋር ያለን እውቂያ ከሁለት አስርታት ይልቃል። በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ - ፅሁፍ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪያችንን አብረን ስንማር ጀምሮ እንተዋወቃለን፡፡ ይህንን መጽሐፍም ሳውቀው ያንኑ ያህል ጊዜ የቆየ ይመስለኛል፡፡ አሁን ባለው መልኩ ባይሆንም። በመጽሐፉ በተነሱ በርካታ ርእሰ ነገሮች ዙሪያ ያኔም እንወያይ ነበረና፡፡
ከደራሲው ጋር ከአንድ እጅ ጣቶች ላልበለጡ አመታት ተለያይተን ቆይተን ዳግም በተገናኘንበት አጋጣሚ የህትመት ብርሃን ያየውን ይህን መጽሐፍ “የእንኳን ደህና መጣህ” ገፀ በረከት ሆኖ እንደቀረበልኝ ስለሚሰማኝ ጭምር ነው መጽሐፉን ሳነበውና አንብቤ እንደጨረስኩ ስላሳደረብኝ ስሜት ጥቂት ልል የወደድኩት፡፡
በመጀመሪያ ግን በርዕሴ “ድፍረት፣ ጥልቀትና ቁጥብነት” የደራሲው መገለጫዎች ናቸው፤ ስል ምን ማለት ፈልጌ እንደሆነ ትንሽ ላብራራ፡፡ ድፍረት ስል፡- ሌሎቻችን ዳር ዳር ብለን የምናልፋቸውን ጥያቄዎች መጠየቅንና አጥብቆ መመርመርን ብቻ ሳይሆን፤ ያገኘውን መልስም ወይም የጥያቄዎቹን መልስ አልቦነት አፍን ሞልቶ መናገር መቻልን ማለቴ ሲሆን፣ ጥልቀት ስል ደግሞ፤ የሚያነሳውን ርዕሰ ነገር ከሁሉም ማዕዘናት አኳያ ብትንትን አድርጐ የማየትንና ለሌሎችም የማሳየት አቅምን ማለቴ ነው።
ቁጥብነትም ይህንን በድፍረት የተነሳውን ርዕስና በርዕሱ ዙሪያ ከሰፊ ንባብና ልምድ ተፈልፍለው፣ ነጥረው የወጡ አያሌ ሀሳቦችን ክሽን አድርጐ፣ አሳጥሮና አጣፍጦ የማቅረብ አቅምን ማለቴ ነው፡፡

ድፍረት
ለአንድ ህፃን “ፈጣሪ ሰማይና ምድርን፤ እንስሳትን፣ እፅዋትንና እኛንም ፈጠረ” ብለን ብንነግረው፤ “የት ጋ ቆሞ? ከምንና እንዴት? ለምንስ ፈጠረን? እሱንስ ማን ፈጠረው?” ወዘተ…እያለ፤ እኛ አዋቂ ተብዬዎች በቸልታም በሉት በፍርሃት የማናነሳቸውን፣ ግን ሊነሱ የሚገባቸውን ጥያቄዎች ሁሉ ይጠይቃል፤ የሚመጣውን መልስም ሳይፈራና ለመልሱም ሳይጨነቅ ያን ድፍረት አብነት ውስጥ አውቀዋለሁ፡፡ ያን ድፍረት በመጋራቴም ብዙ ብዙ ተጠቅሜያለሁ፡፡ ይህንን መጽሐፉን ያነበበም ሰው ያን ጠቀሜታ እንደማያጣ እተማመናለሁ፡፡
በተማሪነት ዘመናችን ዘወትር እያነሳን ከምንወያይባቸው በርካታ የፍልስፍናም ሆነ ስነ - ፅሁፍ ነክ ርዕሰ ጉዳዮቻችን መካከል አስትሮሎጂ አንዱ እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ የኮከብ ትንተና ስለሰው ባህርይ ምን ያህል በትክክል ይነግረናል? መጠሪያ ስምስ ስለ ግለሰቡ ባህርይ ምን ይናገራል? የፊት ገጽታና የሰው ባህርይስ ምን ያህል ይዛመዳሉ? ሰውና አረማመዱ፤ አለባበሱ፣ ያሳደገው ውሻና የሚነዳው መኪናስ? የመዳፋችን አሻራስ ስለ እኛ ምን ይነግረናል? … ወዘተ እያልን፤ እናነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎችና መልስ ፍለጋ ይነበቡ የነበሩ መፃህፍትም አይዘነጉኝም፡፡ ከዛም አለፍ ብለን፤ ነፍስ ባላቸው ልቦለዶቻችን ውስጥ ባሉ ገፀ-ባህርያት ዙሪያም መሰል ትንታኔዎችን የማድረግ ፍላጎቱና ሙከራውም ነበር። አብነትን ልዩ የሚያደርገው ግን፤ ከብዙዎቻችን በተለየ-አምርሮ በጥያቄው የመግፋት ድፍረቱና አጀንዳ አድርጎ የያዘውን ጉዳይ ከስር መሰረቱ ለመፈልፈልና መርምሮ ለመረዳት ያለው ትጋት ነው። ዛሬ ይህን መፅሀፍ ሳነብም የታየኝ የአብነት ድፍረት፤ በሌሎችም ምናልባትም በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ ቢፅፍ የሚንፀባረቅ የአብነት መገለጫ፣ የማንነቱ አብነት ነው፡፡ ጠይቆ፣ ጠይቆ፣ ጠይቆ፣ መርምሮ፣ መርምሮ፣ መርምሮ፣ ያገኘውን መልስ፤ መልስ አልቦነቱንም ቢሆን፤ የደረሰበትን ትክክል ነው ብሎ ያመነበትን፤ ለመናገርም ሆነ ለመፃፍ ኢምንት የማይፈራ መሆኑም ነው የአብነት ሌላው መገለጫ። ቢፈራ እንኳን መፍራቱን አፉን ሞልቶ በድፍረት ይገልፀዋል፡፡
አብነት በመፅሐፉ፣ አስትሮሎጂ “ሳይንስ ነው” ብሎ አስረግጦ ሲነግረን፤ ፍፁም ማመንታት ሳይታይበት ነው፡፡ አስትሮሎጂን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ማህበራዊ ሳይንሶች ከሚከተሉት የአጠናን ዘዴ ጋር በተያያዙ ውዝግቦች እንደ ሳይንስ ላለመቀበል ያለውን ክርክርም አጥቶት አይደለም በመፅሐፉ ውስጥ የሚለውን ያለን። እራሱ አንብቦ፣ መርምሮና ፈትኖ ሳይንስነቱን ቢያምን እንጂ። “አስትሮሎጂ ይሰራል፣ የሰዎችን ባህርይ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል” ሲለንም፤ በሙሉ ድፍረት ነው፡፡ ማወቅ ባስገኘለት ድፍረት፡፡ በኋላ ብመለስበትም፤ እንደ ወራት ሁሉ ዘመናትም ሀገራትም ኮከብ እንዳላቸው የሚያብራራበት መንገድም ድፍረትን አያጣም፡፡ የልቦለዱን ገፀ-ባህርይ የ“ፍቅር እስከ መቃብሩ”ን ጉዱ ካሳ፤ በአስትሮሎጂ ማዕቀፍ ውስጥ ሲተነትነውም ቢሆን … ለኔ የሚያምር ድፍረት ጎልቶ ይታየኛል፡፡ አብነት በድፍረትና በእርግጠኝነት ስለ አስትሮሎጂ ምንነትና ፋይዳ አስረግጦ የሚነግረን ለምን እንደሆነ ለማሳየት፣ በመፅሀፏ ገፅ አራት ላይ ያነሳትን እንደ ምሳሌ ላንሳና ወደሚቀጥሉት ነጥቦቼ ልሻገር፡፡ የአስትሮሎጂ አዋቂና አድናቂ የነበረው ኒውተን፤ አስትሮሎጂን አጣጥሎ በፊቱ ለተናገረ የስራ ባልደረባው የሰጠውን መልስ ደራሲው ይጠቅሳል፡- “ወዳጄ ሆይ፤ አንተ አስትሮሎጂን አላጠናህም፤ እውቀቱም የለህም። እኔ ግን አጥንቼዋለሁ፤ አውቀውማለሁ፡፡” ነበረ የኒውተን ምላሽ፡፡ አብነትም፤ ይሄ መልስ ውስጡ ያለውን፣ የልቡን ሀሳብ ስለወከለለት ሆን ብሎ የጠቀሰው ይመስለኛል። ሀሳቤን ይደግፉልኛል፣ ያጠናክሩልኛል ብሎ “እከሌ እንዳለው”ን መደጋገም ቀርቶ አንዴ እንኳን ማለቱን የማይመርጠው አብነት፤ ይህን ጥቅስ ሲጠቀመው ለሀሳቡ ትልቅነት በሰጠውን ዋጋ ምክንያት ይመስለኛል። በመፅሀፉ ውስጥ ዘርፉ ላይ  ያደረገውን ሰፊ ንባብና ምርምር ያህል በድፍረት የሚነግረንን እምነቱን ታላላቅ አንደበቶችን  በመጥቀስ (ወይም በመዘርዘር ልበለው) ተቀባይነትን ሲሻ አይታይም፡፡ ነጥቡን አስረግጦ ነግሮህ ውሳኔውን ላንተው ይተዋል እንጂ።
አስትሮሎጂ የሚያቀርበው ትንታኔ እውነት እንደሆነ የሚያረጋግጡ ጥቂት የማይባሉ የፍተሻ ጥናቶችን በተወሰኑ ምሳሌዎች ብቻ አመላክቶን ያልፋል፤ በመፅሀፉ ውስጥ፡፡ የአስትሮሎጂን ሀሳብ ውድቅ ለማድረግ ተነስቶ የሃያ ሺህ ሰዎች የልደት ሰንጠረዥ ላይ ቅኝት ያደረገው ታዋቂው የፈረንሳይ የስነ-ልቦና ባለሙያ ሚቸል ጎክሊን፤ በተገላቢጦሹ የአስትሮሎጂ ትንታኔ፤ ዘመናዊ የስነ-ልቦና ትንታኔ ከሚያስቀምጠው የሰው ልጆች የባህርይ ክፍፍል ጋር የተገጣጠመ መሆኑን ማረጋገጡንም፤ አብነት በመፅሀፉ (ገፅ 11) ላይ ይጠቅስልናል፡፡ ይህንን መሰል ብዙ ብዙ ማስረገጫዎችን አብነት እንደሚያውቅ አውቃለሁ፡፡ ሁሉን ግን አልፃፈልንም፤ አላሻውምና! ወይም ሌላው ዝርዝር የእሱ መገለጫ የሆነው ቁጥብነቱ ገድቦታልና፡፡ “በመላው ኮስሞስ ውስጥ መንፈሳዊና ቁሳዊ ጥምረት አለ” ሲል የፃፈውን በዩኒክ ዩኒቨርስቲ የትወራዊ ፊዚክስ ፕሮፌሰር የሆነው ሩዶልፍ ቶማስ ቼክን ሲጠቅስልንም፤ አብነት እራሱም በከዋክብቱ፣ ፕላኔቶቹና በእኛ፣ በሀገራችን፣ በዘመናችን፣ በጤናችን፣ በመካከላችን፣ በህልምና በእውናችን … በዘርፈ ብዙ የህይወት አላባዎቻችን መካከል አንድ አይነት መጣመር እንዳለ ማመኑን እየነገረን ይመስለኛል፡፡
ጥልቀት
ከነአባሪዎቹ ከ142 ገፆች ባልበለጠው በዚህ “ትንሽ” መፅሀፍ፤ በአስትሮሎጂ ማዕቀፍ ውስጥ ፀሃፊው ያነሳቸው ዘርፈ ብዙና ጥልቅ ሀሳቦችን በስሱ እንኳን ለመዳሰስ፤ እኔ አስር እጥፍ የሚበልጥ ዳጎስ ያለ መፅሀፍም ቢፃፍ ይበቃ አይመስለኝም፡፡ ተቆርጠው የቀሩ የሚመስሉና ተነካክተው የተተው ትልልቅ ጉዳዮችን እንኳን ትቼ፤ ዋና ዋና ነጥቦችን በወፍ በረር ብቃኝ፣ አብነት በመፅሀፉ ስለሚያነሳው ጉዳይ ምን ያህል በስፋትና በጥልቀት አብጠርጥሮ እንደፃፈልን ያሳያል ብዬ እገምታለሁ፡፡
የአኳሪየስ ኮከብ ዘመን በመግባቱ፤ አኳሪየስ ኮከብ ባላት አገራችን ላይ ያለውንና የሚኖረውን አንደምታ፤ በአስትሮሎጂ ማዕቀፍ ውስጥ መተንተንን ዋና የትኩረት ነጥቡ ባደረገው በዚህ መፅሀፍ፤ አዘጋጁ አስትሮሎጂን አስመልክቶ ያቀረበልን ማብራሪያ ስፋትና ጥልቀት ያለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በሚያጠግብና ሁሉም አጣጥሞ ሊያነበው በሚገባ ሁኔታ፡፡
ለዋናው ትንታኔ ዳራ ለመስጠት ሲል፣ ስለ አስትሮሎጂ ታሪካዊ አመጣጥና አሰራር በአስር  ገፆች ብቻ ያቀረበልን መረጃ እንኳን፣ እንደኔ-እንደኔ እራሱን የቻለ በርዕሱ ላይ የተፃፈ ዳጎስ ያለ መፅሀፍ ተነቦም የማይገኝ ጭብጥ ነው፡፡ ይህን ጥንታዊ የሆነ ጥበብ፤ ተጀመረ ተብሎ ከሚታሰብበት ከዛሬ ስድስት ሺህ አመታት ገደማ ጀምሮ ያለውን እድገቱን፤ እንደ ኃጢአት፣ አጉል እምነትና ወንጀል ተቆጥሮ አንቀላፍቶ ስለነበረበት ረዥም የጨለማ ጉዞ ጨምሮ ዳግም ልደቱንም አብነት ሲያወጋን፤ ከሰፊ ንባብ በተገኘና እጥር ምጥን ብሎ በቀረበ ገለፃ ነው፡፡ አይጠገቤው ሸጋ አቀራረቡ በዛ ላይ ተጨምሮበት፡፡
ብዙዎች የአስትሮሎጂ መፃህፍት፤ የአስትሮሎጂን ታሪክና አመጣጥ፣ ከግብፃውያን፣ ከከለዳውያን፣ ከሱሜራውያንና ሌሎች መሰል ጥንታዊ ስልጣኔዎች ጋር ብቻ አያይዘው መፃፋቸውንና ኢትዮጵያን አለመጥቀሳቸውን ቁጭት በተመላበት ድምፀት የሚገልፅልን ፀሃፊው፤ የኢትዮጵያችንን ከአስትሮሎጂ ጥበብ ጀማሪ አገሮች ተርታ ተሰላፊነት አስረግጦ ይነግረናል-ከጥንቃቄ ጋር፡፡ ምክንያቱም የነበሩንና ያሉንን እውቀቶች መርምሮ፣ ቆፍሮ አውጥቶ፣ በመረጃ አስደግፎ ለብርሃን ማብቃቱ ገና ብዙ ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ ያውቃልና፡፡ (ከእንግዲህ እሱም አርፎ እንደማይተኛና ለዚሁ ስራ እንደሚተጋም አምናለሁ፡፡ የመፅሃፉ ዋና ትኩረት ባለመሆኑ ለጊዜው ነካክቶ ተወት ያድርገው እንጂ ነገ በሙሉ ልቡና አቅሙ እንደሚመለስበት በእምነትና በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡)
አልበርት ፓይክ በ1871 አሜሪካ ውስጥ አዘጋጅቶ ባሳተመው “ስነ-ምግባርና ቀኖና ለፍሪሜዚነሪዎች” በተሰኘ፤ ለዘመናት ምስጢራዊነቱን ጠብቆ ለዘለቀው ምስጢራዊ ድርጅት አባላት በሚሰጥ መፅሀፍ ውስጥ፤ የኢትዮጵያን ሀያል ሀገርነትና በስልጣኔም ከግብፅ ቀዳሚነት፤ ብሎም የብዙ ሚስጢራዊ ጥበቦች ባለቤት እንደነበረች የፃፈውን በዚህ መፅሀፉ ቀንጭቦ ያስነበበን አብነት፤ ሌሎችም ምሁራን የፃፏቸው መሰል ዘገባዎች እንዳሉ ያውቃል፤ ለጊዜው ዝርዝር ውስጥ አልገባም ብሎ ይለፈው እንጂ፡፡ ይህም ቁጥብነት ብዬ በርዕሴ ያመላከትኩት የአብነት ሌላኛው መገለጫ ነው፡፡
አብነት ስለ አስትሮሎጂ ታሪክና አመጣጥ ብቻ ሳይሆን ስለምንነቱና አሰራሩም፤ አጠር አድርጎ ነገር ግን አግዝፎ ባቀረበልን ገለፃ፤ በብዙዎች ዘንድ ስለ አስትሮሎጂ ያለውን የላይ ላዩን ግርድፍ ግንዛቤ ከፍ ባለ ደረጃ የሚያሳድግ ይመስለኛል፡፡ ፀሐይ፣ ጨረቃና ስምንቱ ፕላኔቶች በአስትሮሎጂ ትንታኔ ያላቸውን ፋይዳ ሲያስረዳን ብትንትን አድርጎ ነው፤ አብጠርጥሮና አሳምሮ፡፡ እነዚህ አካላት በህይወታችን ዙሪያ ያላቸውን ተፅእኖ በሳይንሳዊ መንገድ ለማብራራት የሚያደርገው ሙከራም ሳይዘነጋ፡፡ እንደ ምናልባትም በምሳሌ መልክ ብዙ ጊዜ ሰምተነው ሊሆን የሚችለውን፤ በብዙ አገሮች በተመዘገበ የስታትስቲክስ መረጃ፤ ጨረቃ ሙሉ በሆነች ጊዜ የወንጀል ቁጥር ተበራክቶ የመታየቱን ሁኔታና ሌሎችም አመልካች አብነቶች በመፅሃፉ ውስጥ ጠቀስ ጠቀስ ማድረጉም አልቀረም፡፡
በርካቶች ስለ አስትሮሎጂ ሲነሳ፤ እንደ ብቸኛው አጀንዳ አድርገው የሚመለከቱት የሚመስለኝ፤ “የእከሌ ኮከብ ሊዮ ነው፤ እከሊት ኮከቧ ሊብራ ነው” ሲባል ታሳቢ የሚደረገው የፀሐይ ምልክት (በተወለድንበት ወር ፀሐይ የገባችበት ከአስራ ሁለቱ የዘዲያክ ምልክቶች አንዱ የሆነው ዋና ኮከባችን) ከሃምሳ እስከ ሰባ በመቶ የሚሆነውን ባህርያችንን ብቻ የሚገልፅ መሆኑንና እንዲያውም እስከ 1930፣ በአስትሮሎጂ ጥናትና ልምምድ ይህ የፀሐይ ምልክት የሚባለው ነገር እንዳልነበረና የአንድን ሰው ኮከብም በዚህ መልኩ መስራት ከሙያ ውጭ እንደሆነ በማስረዳት፣ የተሟላ የባህርያችንን ትንታኔ ለማወቅ የልደት ሰንጠረዥን የመስራትን አስፈላጊነትና አሰራሩንም፤ ለዚህም የተወለድንበትን ዓመተ ምህረት፣ ወር፣ ቀንና ሰዓት እንዲሁም የተወለድንበትን አገርና ቦታ በማካተት፣ አንድ ሰው እንዴት የራሱ ብቻ የሆነ የኮከብ ትንታኔ እንደሚኖረው ይገልፅልናል፡፡ እንደ ፀሐይ ሁሉ ጨረቃና ሌሎቹ ፕላኔቶቹ በወቅቱ የነበሩበትን ሁኔታ ተመርኩዞ ስላለው የኮከብ ትንታኔ ግልፅልፅ አርጎ ያስረዳናል፡፡ ዝርዝሩን እኔ ባልነካካው እመርጣለሁ፡፡ በደፈናው ግን፤ አንድ ነገር ማለት የምችል ይመስለኛል፡፡ የአንባቢውን ግንዛቤ አስፍቶ፣ ስለ አስትሮሎጂም መሰረታዊ ዕውቀትን አስጨብጦ፣ ፋይዳና ጥቅሙንም ፍትፍት አድርጎ ማቅረቡ ለፀሃፊው የተሳካለት ይመስለኛል፡፡
የመፅሃፉ ዋና ክፍል የሆኑትን የአኳሪያስ ዘመን ትንታኔ (ስምንተኛው ሺህ በመባል የሚገለፀው)፣ ስለ ሀገራት ኮከብና የኢትዮጵያ ኮከብ አኳሪያስ መሆን ስላለው አንድምታ፤ ባማረ ሁኔታ ተከሽኖ የቀረበውን፤ አንባቢ እራሱ አንብቦ፣ አጣጥሞ እንዲደመምበት፣ እንዲማርበትና እራሱንም እንዲመለከተበት ከመተው ውጪ፤ በዚህች አጭር ፅሁፍ ልነካካውና አድበስብሼው ላልፍ አልመርጥም። ስለ ዘመናትና ስለ ሀገራት ኮከብ፣ ስለ አስትሮሎጂ ጥቅምና ምክሮቹ ቁልጭ አድርጎ የሚያቀርበው ትንታኔ፤ ለእኔ መፅሃፉን በማንበብ ብቻ የሚገኝ ነው፡፡

ቁጥብነት
ባነሰቸው አንኳር ነጥቦች ዙሪያ ሁሉ ቆርጦ ያስቀረብን፤ ከዛም ይበልጥ የሚያውቀውና ያተወው  ብዙ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ይህም የአብነት ሌላው መገለጫ ነው። ቁጥብነቱን ያሳስበኛልና ስለዛ ጥቂት ልበል፡፡ ቁጥብነት የፀሃፊው መገለጫ ነው ስል፣ ሁለት አበይት ባህርያቱን ልጠቅስ ፈልጌ ነው፡- አብነት ላይ የማውቃቸውንና በ “ኢትዮጵያ ኮከብ” መፅሀፍ ላይም ያስተዋልኳቸው ናቸው፡፡
ደራሲውን ሳውቀው ጀምሮ ሲናገርም ሆነ ሲፅፍ፤ የቱንም ያህል ግዙፍና ውስብስብ፣ ረቂቅና ሰፊ በሚባል ሀሳብ ላይ ቢሆን፤ ቅልብጭና ጥርት አድርጎ ነው፡፡ ገና ብዙ ይላል ብለህ ስትጠብቀው፤ እሱ ግን የሚለውን ብሎ ጨርሷል፡፡ አብነት ግጥም ነው ብል (ያውም የሚጥም ቅኔ) ያጋነንኩ አይመስለኝም። የሚለው ነገር ኖሮ ያንን ሳይለው ቀርቶ ሳይሆን ሌሎቻችን ብዙ ብዙ ብለን የምንገልፀውን ሀሳብ፣ እሱ በአጭሩ አስውቦ ሊለው በመቻሉ ይመስለኛል። ምናልባትም ባለው ላቅ ያለ የቋንቋ ክህሎት እና ፈጣሪ በቸረው ፀጋ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
አብነት በመፅሀፉ መደምደሚያ ስለ ብሔራችን ኮከባችን ከፃፈው ጥቂት አቅርቤ ቅኝቴን ልቋጭ፡፡

ስለ ብሔራዊ ኮከባችን
አሁን የዘመን ዓይነጥላችን ተገፏል፡፡ ስለዚህ በደስታ መደናበርና በሐሴት መጨፈር ሳይሆን መንገዳችንን አጥርተን በመመልከት፣ በልዕልና ጎዳና ላይ በእርጋታና በልበ ሙሉነት መጓዝ ነው የሚጠበቅብን፡፡
አሁን እውቀትን እናክብራት፤ ጥበብንም እናንግሣት። ከስደትም እንመልሳት፡፡
አሁን ባጭር ታጥቀን እንሥራ፡፡ የዘመናት መከራን የቻለ ጫንቃችን ብልፅግናን መሸከም አይሳነውም፡፡
አሁን የድህነትን ድሪቶ አውልቀን የብልፅግናን ፅዱ አልባሳት እንጎናፀፍ፡፡ ድሪቷችን ሲወልቅ ይበርደናል፡፡ ያ ግን ሃላፊ ነው፡፡
አሁን ለፅልመት የለኮስነውን ኩራዝ አጥፍተን በሙላት የፀሐይ ብርሃን እንጓዝ፡፡ በጭለማ ያዘገምን ህዝቦች፤ በብርሃን መራመድ አይሳነንም፡፡
አሁን የድህነትን፣ የማይምነትንና የበታችነትን ሬሳ ታቅፈን አንቀመጥ፡፡ እሱን አልቅሰን እንቅበረው። እርማችንን እናውጣና አዲስ ህይወት እንጀምር፡፡ ስላለፈው የጽልመት ዘመን ማላዘናችንን በዚሁ እናብቃ፡፡
አሁን ፀሐይ ወጥታለች፡፡ ጽልመት ነው ብለን ለዘመናት የከደንነውን ዓይን በድፍረት መግለጥ አለብን፡፡ የድንጋሬ ህመም ይኖራል፡፡ ግን ሃላፊ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኮከብ ለዘላለም ያብራ!! አሜን!

Read 6825 times