Saturday, 14 December 2013 10:58

የ“ኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” ሊቋቋም ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

“የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” የተሰኘ ማህበር ለመመስረት ጋዜጠኞች እንቅስቃሴ መጀመራቸውን የመድረኩ ጊዜያዊ መስራች ኮሚቴ አስታወቀ፡፡ ከትላንት በስቲያ በኢትዮጵያ ሆቴል ኮሚቴው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የማህበሩ መቋቋም ዋናው አላማ፤ ጋዜጠኞች በስራቸው ለአደጋ የተጋለጡ እንደመሆናቸው፣ ችግር በሚያጋጥማቸው ጊዜ ለመረዳዳት የሚያስችል ተቋምም ሆነ ማህበር ባለመኖሩ፣ እርስ በእርስ ለመተጋገዝና ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በሀገራችን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ቢረጋገጥም፣ የመገናኛ ብዙሀን ሙያ ከመጐልበት ይልቅ እያደር መጫጫቱ እንደሚያሳስበው የገለፀው ጊዜያዊ መስራች ኮሚቴው፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሙያው ባለቤት የሆኑት ጋዜጠኞች ለተለያዩ ጥቃቶች ሲጋለጡ መቆየታቸውንና እየተጋለጡም መሆናቸውን ጠቁሞ፤ ከጥቃቶቹም ውስጥ ያለ አግባብ መታሰር፣ ማስፈራሪያና ዛቻ ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ጠቁሟል፡፡ “ጋዜጠኞች ለሌሎች መብት የሚታገሉትን ያህል በራሳቸውና በሙያው ላይ የተጋረጡ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት አልታደሉም” ያለው ኮሚቴው፤ ከዚህ እውነታ በመነሳት ነፃና ገለልተኛ የሆነ፣ ለጋዜጠኝነት ሙያና ለጋዜጠኞች መብት የሚቆም ማህበር ማቋቋም ጊዜ የማይሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሆነ በመግለጫው አብራርቷል፡፡

በቅርቡ በስራ ባልደረቦቹ ላይ የተመሰረተውን ክስ ለመከታተል ወደ ሀዋሳ ተጉዞ ከባድ የትራፊክ አደጋ የደረሰበት የ“ኢትዮ ምህዳር” ጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጅ የጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ጉዳይ ለማህበሩ መቋቋም ምክንያት እንደሆነ የገለፀው ኮሚቴው፤ በአደጋው ወቅት ጋዜጠኛውን ለመታደግ፣ ለጋዜጠኝነትና ለጋዜጠኞች የሚቆረቆሩ ተቋማት አለመኖራቸው እንደተረጋገጡ ጠቁሟል፡፡ በጋዜጠኞች ላይ ለሚደርሱ አይነተ ብዙ ችግሮች ፈጥኖ የሚደርስ “የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” የተሰኘ ማህበር ለመመስረት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የገለፀው ኮሚቴው፤ ለሙያው ፍቅርና ክብር ያላቸው ጋዜጠኞች በአባልነት እንዲሳተፉ ጥሪ አስተላልፏል።

ኮሚቴው ማህበሩ ከተቋቋመ በኋላ ያከናውናቸዋል ያላቸውን ዋና ዋና ተግባራት ይፋ ያደረገ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 29 መሰረት የተፈቀደውን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ለማስከበር፣ የጋዜጠኞችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ፣ በተከታታይ ትምህርትና ስልጠና ሙያዊ ብቃት ለማስጠበቅ፣ በጋዜጠኞች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የገንዘብ፣ የቁሳቁስና የህግ አገልግሎት ድጋፍ ለማድረግና በዘርፉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ጋዜጠኞች እውቅና ለመስጠት የሚሉት ይገኙበታል፡፡ መድረኩ በዋናነት በአባልነት የሚያቅፋቸው በጋዜጠኝነት ሙያ በማንኛውም መገናኛ ብዙሀን መስክ በማገልገል ላይ የሚገኙትን ሲሆን በሙያው ላይ ለመሰማራት በሂደት ላይ የሚገኙትንና ከሙያው ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያላቸውን ግለሰቦች በተባባሪ አባልነት ያስተናግዳልም ተብሏል፡፡ ጋዜጠኞች በምስረታው ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉና በቅርቡ በሚጠራው ጠቅላላ ጉባኤ በመገኘት የማህበሩ አመራሮች ምርጫ ላይ እንዲሳተፉ ኮሚቴው ጋብዟል፡፡

Read 1674 times