Saturday, 14 December 2013 10:54

የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን የሰጠው ማስተባበያ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን የተቋቋመበት ዋና ዓላማ በአዲስ አበባ ከተማ ሊደርሱ የሚችሉትን እሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎችን ነዋሪውንና ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ፣ አደጋን አስቀድሞ ለመከላከልና ከተከሰተም ፈጥኖ በመቆጣጠርና በማረጋጋት የነዋሪውን ደህንነት (Safety) እንዲጠበቅ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህ ተልዕኮው መሰረት ህዳር 25 ቀን 2006፣ ከቀኑ 9፡15 ገደማ፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታው ጆንያ ተራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የገበያ ማዕከል የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ፣ የእሳት አደጋው ከተከሰተው በላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉ ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ የእለቱን አደጋ አስመልክቶ ጋዜጣችሁ ባለፈው ቅዳሜ ህዳር 28 ቀን 2006 እትሙ ላይ “ከንቲባ ድሪባ የእሳት ቃጠሎ ተጐጂዎችን አቤቱታ አጣራዋለሁ አሉ” በሚል ርዕስ፣ የተቋማችንን ተልዕኮ በሚያሳንስና ገጽታችንን በሚያበላሽ እንደዚሁም ተቋማችንን ከህዝብ ጋር በሚያጋጭ መልኩ፣ መልካም እይታና ሚዛናዊነት የጐደለው ስሜትን ብቻ ያስተናገደ ዘገባ ማቅረባችሁ መስሪያ ቤታችንን አሳዝኗል፡፡ በዘገባችሁ ላይ አንዳንድ ነጋዴዎች፤ “የእሳት አደጋ ሰራተኞች ከበላይ አካል መመሪያ አልተላለፈልንም በሚል ሰበብ ቆመው ሲያዩ ነበር” ለተባለውኧ በማናቸውም እሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎችን ምክንያት መተኪያ የሌለውን የሰውን ህይወትና ንብረት ማዳን ሰብአዊ አገልግሎት ጭምር ከመሆኑም ባሻገር፣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተቋቋመበት ዋናው አላማ ነው፡፡

ማናቸውንም አደጋ ፈጥኖ ለመቆጣጠር ባለሙያዎችም ሆኑ በየደረጃው የሚገኙ የመስሪያ ቤቱ የስራ ሃላፊዎች፤ በአደጋው ስፍራ የሚገኙ በመሆኑና ስራው ላይም በቀጥታ የሚሳተፉበት አሰራር እንጂ የሰው ህይወትና ንብረት ለማዳን የማንም አካል ትዕዛዝ ወይም ፈቃድ ተጠይቆ አያውቅም፤ ወደፊትም አይጠየቅም፡፡ አንዳንድ የመስሪያ ቤታችን ሰራተኞች ጉቦ ጠይቀዋል ለተባለውም፣ እንደዚህ አይነት አሉባልታ ቀደም ሲልም ሆነ አሁን በግለሰቦች የሚነገር ሲሆን ይህንኑ ለማጣራት በሚደረገው ሂደትም የጋዜጣ ዝግጅት ክፍላችሁን ጨምሮ “ሲሉ ሰማን” ከማለት ውጪ ተጨባጭ መረጃ አልቀረበም፡፡ ይሁን እንጂ ስራችን በህዝብ ፊት የሚሰራ በመሆኑ፣ ተጨባጭ መረጃዎች ካሉ ከህግ አካላት ጋር ተባብረን የምንሰራ መሆኑን ማረጋገጥም እንወዳለን፡፡ ሌላው አደጋዎች ሰፋ ሲሉ ሌሎች ተባባሪ ተቋማትንና የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያጋብዙ በሆነ ጊዜ ሁሉ በትብብር ስንሰራ ቆይተናል፡፡ በዚህ የእሳት አደጋም የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ፤ ኤርፖርቶች ድርጅት እንዲሁም የፀጥታ ኃይሎችና የአካባቢውን ህብረተሰብ በማሳተፍ፣ በሁሉም ቅርንጫፍ ጣቢያዎቻችን የሚገኙ የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪዎችንና አምቡላንሶችን ከበቂ ባለሙያዎች ጋር በማሰማራትና ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ አደጋው የከፋ እንዳይሆን ማድረግ ተችሏል፡፡

ጋዜጣችሁ ባቀረበው ዘገባ ግን የአደጋ መቆጣጠር ሰራተኞቻችንም ጭምር የአደጋው ሰለባ በመሆን አደጋውን ለመቆጣጠር ያደረጉትን ጥረት ለማየት አልፈለገም፡፡ ስለዚህም የላክነውን ይሄን ጽሑፍ በጋዜጣችሁ ላይ በማስተናገድ ላቀረባችሁት ዘገባ ማስተካከያ እርምጃ እንድትወስዱ እያሳሰብን፣ ይህ ሳይሆን ቢቀር የህግ አግባቦችን ለመጠቀም የምንገደድ መሆኑን እንገልፃለን፡፡ አማኑኤል ረዳ ኃይሉ (ኮ/ር) ም/ዋና ዳይሬክተር ከአዘጋጁ፡- ባለፈው ቅዳሜ የጋዜጣችን ዕትም፤ “ከንቲባ ድሪባ የእሳት ቃጠሎ ተጐጂዎችን አቤቱታ አጣራዋለሁ አሉ” በሚል ርእስ የወጣው ዘገባ፣ ጋዜጠኞቻችን አደጋው በደረሰበት ስፍራ ተገኝተው ተጐጂዎች ለከንቲባው ያቀረቡትን አቤቱታ በመስማት፣ ተጐጂዎችን በማነጋገርና ፎቶግራፍ በማንሳት የተጠናቀረ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን ደውለን የሚመለከተውን ኃላፊ በማነጋገር፣ በጉዳዩ ላይ የሰጡትን ምላሽ አካተን ማውጣታችንን ይታወሳል፡፡

Read 2574 times