Saturday, 14 December 2013 10:51

አንድነት የኔልሰን ማንዴላን ህልፈት የተመለከተ ፕሮግራም አካሄደ

Written by 
Rate this item
(4 votes)
  • የፓርቲው አመራሮች በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ሀዘናቸውን ገልፀዋል

የታላቁን የነፃነት ታጋይ የኔልሰን ማንዴላን ህልፈት ተከትሎ፣ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ከትላንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ የሀዘን መግለጫ ፕሮግራም በጽ/ቤቱ ያካሄደ ሲሆን በፕሮግራሙ ላይም ስለኔልሰን ማንዴላ የነፃነት ትግል፣ ከኢትዮጵያ ጋር ስለነበራቸው ቁርኝትና ከማንዴላ ምን ትምህርት ይወሰድ በሚሉት ዙርያ ንግግር ተደርጓል፡፡ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከፕሮግራሙ ቀደም ባሉት ቀናት ደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ በመሄድ፣ በኔልሰን ማንዴላ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን መግለፃቸውን የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲው ወር በገባ በሶስተኛው ቀን በሽብርተኝነት ወንጀል ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙትን እነ አንዷለም አራጌን እንደሚያስብ የጠቆሙት የፓርቲው ዋና ፀሃፊ አቶ አስራት ጣሴ፤ የኔልሰን ማንዴላን የሀዘን መግለጫ ታህሳስ ሶስት ቀን ያደረገው ማንዴላ በነፃነት ትግል፣ በእነ አንዷለም ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳረፉ መሆናቸውን ለመጠቆም እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

“ማንዴላን ደቡብ አፍሪካ ወልዳ ብታሳድገውም ኢትዮጵያ ደግሞ አስተምራና ከሞት አትርፋ ለደቡብ አፍሪካ አበርክታዋለች” ብለዋል-ፀሃፊው፡፡ ማንዴላ ኢትዮጵያ ውስጥ በትምህርት ላይ እያሉ የደቡብ አፍሪካ ነጭ መሪዎች ለግል ጠባቂው ጉታ ዲንቃ፣ ጉቦ ከፍለው ሊያስገድሏቸው እንደነበር ያስታወሱት አቶ አስራት፤ ሆኖም ጉታ ዲንቃ ምስጢሩን ለማንዴላ አስተማሪ በመንገራቸው ከሞት መትረፋቸውን ጠቅሰው፣ ይህ ምስጢር ወጥቶ ከሞት ባይተርፉ ኖሮ ኢትዮጵያም፣ አፍሪካም ሆነ ዓለም ማንዴላ ስለሚባል ሰው አያውቅም ነበር ብለዋል፡፡ በ25 አመታቸው አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስን (ANC)ን ተቀላቅለው፣ በ46 ዓመታቸው ለእስር የተዳረጉ የነፃነት ታጋይና የመቻቻል ተምሳሌት ኔልሰን ማንዴላ፤ በሮቢን ደሴት ለ27 ዓመት በእስር ተሰቃይተው ከወጡና አፓርታይድ ከወደቀ በኋላ እ.ኤ.አ በ1994 የመጀመሪያው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡

ማንዴላ፤ “ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን እንዳስተማሩና ያሰሯቸው ሰዎች ላይ የቂም በቀል እርምጃ ከመውሰድ እርቅና መግባባትን በመምረጣቸው አለም በአንድ ድምፅ ተስማምቶ “ተምሳሌት” ብሏቸዋል ያሉት አቶ አስራት፤ ከ1ሺ በላይ ሽልማቶችና የማዕረግ ስሞች፣ 85 የክብር ድግሪዎች፣ የ45 የአለም ከተሞች የክብር ነዋሪነት፣ እንዲሁም ማንዴላ የተወለዱበት የልደት ቀናቸው ጁላይ 18 በተባበሩት መንግስታት ውሳኔ “የማንዴላ ቀን” ተብሎ ተሰይሞላቸዋል፤ ይህ ሁሉ የተገኘው ለነፃነት በተከፈለ መስዋዕትነት ነው ብለዋል አቶ አስራት ጣሴ፡፡

“እነአንዷለም ሽብርተኞች ተብለው ታስረዋል፤ ግን ሽብርተኞች አይደሉም፤ የነፃነት ትግል ቄስና ደብተራ ናቸው” ያሉት አቶ አስራት፤ ኔልሰን ማንዴላም በእንግሊዞች “አሸባሪ” ተብለው እንደነበር አስታውሰው፤ እነ አንዷለምም በቅርቡ የነፃነት ታጋይነታቸውን አለም እንደሚያውቀው ተናግረዋል፡፡ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሊቀመንበር አቶ አበባው መሀሪ ያደረጉት ንግግር ደግሞ በኔልሰን ማንዴላና በአፄ ሚኒልክ ላይ ያተኮረ ሲሆን ልክ እንደ ኔልሰን ማንዴላ ሁሉ አፄ ምኒልክም በኢትዮጵያ ውስጥ የመቻቻልና የአንድነት መንፈስ እንዲኖር ያበረከቱትን አስተዋፅኦ አስታውሰው፤ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የጥላቻና የጐሪጥ መተያየት ፖለቲካ አውግዘዋል። አቶ አበባው አክለውም፤ በምኒልክ ዘመን መቻቻልና አንድነት በመኖሩ የውጭ ጠላትን ማሸነፍ መቻሉን የገለፁ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ማንዴላ ይቅር ባይነትና መቻቻል ካልመጣ፣ ለአገሪቱም ሆነ ለህዝቧ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

Read 1435 times