Saturday, 07 December 2013 12:56

“የወርቃማ ዘመን ትዝታዎቼ በስዕል ሥራዎቼ ላይ ጐልተዋል”

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(1 Vote)

ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ “ንግስ” በሚል ርዕስ በብሔራዊ ሙዚየም አዳራሽ ለእይታ ያቀረባቸው ስዕሎች ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ፤ ባለፈው ዐርብ ህዳር 20 ቀን 2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በኤግዚቢሽኑ ስላቀረባቸው ስዕሎችና በአሰራር ላይ ስለሚከተለው መንገድ ሰዓሊው በሰጠው ማብራሪያ ነበር ፕሮግራሙ የተጀመረው፡፡ “ንግስ” በሚል ርዕስ ለእይታ የቀረቡትን ስዕሎች የሰራኋቸው ከሕይወት ልምድ፣ ከንባብ፣ ከታሪክና ከሰማኋቸው ነገሮች በመነሳት ነው ያለው ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ፤ ሥራዎቹ ተሰርተው ለእይታ እንዲበቁ የሚያስተምርበት ዩኒቨርስቲ ለጥናትና ምርምር ጊዜ በመፍቀድ፤ ልጁ ጋብዛው ወደ ውጭ አገር በሄደበት አጋጣሚ በተለያዩ ኤግዚቢሽኖች ያያቸው ስዕሎችና የሥነ ጥበብ ታሪክ ተመራማሪው አቶ እሰዬ ገ/መድህን ያደረጉለት ትብብር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልፆ አመስግኗል፡፡ በመቀጠልም ሙያዊ የሆኑ ጉዳዮች ማብራራት ጀመረ፡፡ በማንኛውም ሙያ ውስጥ ተፈጥሮን የሚቃረኑ ሃሳቦች ተግባራዊ ሲሆኑ ይታያል፡፡ ተፈጥሮን መቀየር ስለማይቻል ለምን የበለጠ አናጐላውም የሚል እምነት አለኝ፡፡

በቀለም ቅብ ሥራ ውስጥ “አግዛፊዎች” አሉ፡፡ እነዚህ ከነበሩ ላይ ተነስተው ጉዳዩን ለማጉላት የሚጥሩ ናቸው፡፡ በተቃራኒው “ገዳፊዎች” አሉ፡፡ እነዚህ ቀለም ቅብ ሞቷል እንዲባል ምክንያት ይሆናሉ፡፡ የእኔ አስተሳሰብ የሚመነጨው ከዚህ መነሻ ነው፡፡ ስዕል የምስለው ከተፈጥሮ ጋር ያለኝን መስተጋብር ተመርኩዤ ሲሆን የቀለም ቅብ ሥራ ከባህላዊ አሰራር ተነስቶ “አግዛፊዎች” ዘመን ላይ መድረሱን አምናለሁ፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በሌሎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩና በቀለም ቅብ ሥራ ላይ ለውጥ ያመጡ ሰዓሊያን ነበሩ፡፡ ቀለም ቅብ ሁለት አውታረ መጠን ነው የሚሉ አሉ፡፡ በሦስት አውታረ መጠን መጠቀም ከባድ መሆኑን የሚልጹም አሉ፡፡ አንድ ነገር በማነሱ ምክንያት ሁለት ወይም ሦስት አውታረ መጠን ስለሚሆን “አይቻልም” ብሎ መከራከሩ ትክክል አይሆንም፡፡

አንድ ሰው እንቅስቃሴ ላይ ሲሆን በአራት አውታረ መጠን ላይ እንዳለ ነው የሚታመነው። ውሻችንን በሰንሰለት አስረን በመንገድ ስንሄድ የሰንሰለቱ እርግብግቢት ወይም መሽከርከር ምን ይመስላል? የውሻው፣ የጌታው የኮቴና የእግር እንቅስቃሴስ? ሁለትና ሦስት አውታረ መጠንን ለማሳየት የውጭ አገር ሰዓሊያን ብዙ ማሳያ አቅርበዋል፡፡ እኔ የማልቀበላቸው አሉ፡፡ ከአገር ውስጥ በደብረብርሃን ሥላሴ ቤተክርስቲያን፣ በአባ ዘወልደማርያም ማሞ የተሳለውንና ከውጭ አገር ደግሞ የሚካኤል አንጀሎንና የመሳሰሉትን የተለያዩ ማሳያዎች በምስል አስደግፎ በማቅረብ ማብራራቱን የቀጠለው ሰዓሊው፤ “የምናየው ነገር በትልቅና በትንንሽ መስመሮች የተወሰነ ነው፡፡ አንድ ቀለም ቅብ እኛ ማየት በቻልነው መጠን ነው የሚገለፀው፤ በአጉሊ መነጽር ማየትና በነፃ ዓይን ማየት የተለያየ ነው” ብሏል፡፡ አውሮፓውያን ‘ህዳሴያችን’ በሚሉት ዘመን ስዕል የሚገለፀው አንድ ሰው አንድን ነገር በመስኮት እንደሚያይ ተደርጐ ነበር ያለው ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ፤ በመስኮት ማየቱን ትቶ፣ ከቤት ወጥቶ ማየት አይቻልም ወይ? በሚል ያነሳሁት ጥያቄ በ “ንግስ” ኤግዚቢሽን ያቀረብኳቸውን ስዕሎች ለመስራት አስችሎኛል ብሏል፡፡

ስዕሎቹ በልጅነት ትዝታዎቼ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ የአለቶቹ ትልቅነት በዚያ ዘመን እይታዬ በውስጤ የተቀረፁ ናቸው፡፡ ዛሬ ሄጄ ሳያቸው ያን ያህል አይገዝፉም፡፡ ጥልቀትን ወደ ውስጣችን ለማምጣት፤ ሁሉም ሰው ከፍታ ቦታዎችን መውደዱን፤ የከሰል፣ የችቦ፣ የኤርታሌ…ግለትን ለማሳየት የሳልኳቸው ናቸው፡፡ አለቱን ወይም የምስላቸውን ነገሮች ከፍሬም ውጭ አድርጌ የመጠቀሜ ዋነኛ ምክንያትና መነሻ በጥንታዊ የአገራችን ስዕሎች ያየሁት አሳሳል ነው፡፡ በኤግዚቢሽኑ ካቀረብኳቸው ስዕሎች መካከል “ንግስ” ከሌሎቹ ጋር የሚያያዝ ነገር የለውም። በወጣትነቴ ትልቅ ሥራ እሰራለሁ የሚል ሕልም ስለነበረኝ ያንን ምኞቴን ያሳካሁበት ሥራ ነው፡፡ “ንግስ”ን ለመሳል 3 ዓመታት ጠይቆኛል፡፡ የሰዎቹና የአልባሳቱ ብዛት ብዙ ጊዜ ከወሰዱብኝ ምክንያቶች ዋናው ነው ብሏል፡፡ ሰዓሊ መዝገቡ፤ የውይይት መነሻ ሀሳቡን አቅርቦ ሲያጠቃልል፤ የጥያቄ፣ የሙገሳና የአስተያየት መስጫ ሞቅ ያለ መድረክ ተከፈተ፡፡ ከእነሱም መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት፡- ከጣሊያን ወረራ በኋላ የመጡ ኢትዮጵያዊ ሰዓሊያን ዘመናዊነትን አገራዊ ለማድረግ ሞክረዋል። የኢትዮጵያውያኑን ሥራ ከምሥራቁም ሆነ ከምዕራቡ ሰዓሊያን ሥራዎች ጋር ብናወዳደር ጫና እንዳላረፈባቸው እናስተውላለን፡፡ የመዝገቡ ተሰማ ሥራዎችን ስንመለከት ደግሞ በአገራዊ መሠረት ላይ የመጨረሻውን ማህተም አኑሮልናል፡፡ በ1920ዎቹ የጀመረው ኢትዮጵያኢዝም ከሌሎች ተነጥሎ ወጥቶ በራሱ ማደግ መቀጠሉን የመዝገቡ ሥራዎች ያረጋግጣሉ፡፡ በሰለጠነው ዓለም ከሌሎች ጋር በእኩል ሁኔታ መሰለፍ እንደሚችል አረጋግጧል።

በዲጂታል ካሜራዎች ብቻ ሊቀረፁ የሚችሉ ምስሎችን በስዕል ሸራው ላይ መሳል የቻለው መዝገቡ፤ በ100 ዓመት የሥነ ጥበብ ታሪካችን ውስጥ አዲስ መንገድ ፈጥሯል፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያዊ ስዕልና አሳሳልን የሚመራው ማነው? የሚለው ጥያቄ የሚያጓጓ ቢሆንም መልሱን ለጊዜ እንተወው፡፡ እንደ መዝገቡ ተሰማ በድንቅ ሥራዎቻችን ምሳሌ መሆን ከቻልንና ለሥነ ጥበብ ጥናት ሰፊ ጊዜ ከሰጠን በመስኩ ፈጣን ዕድገት ይመዘገባል፡፡ በእኛ ሙያ ውስጥ አቅጣጫዎች አሉ ከተባለ አንዱ አቅጣጫ የመዝገቡ ተሰማ ነው፡፡ ግርማ ይፍራሸዋ በፒያና ሙዚቃ፣ መዝገቡ ተሰማ በቀለም ቅብ ሥራዎቻቸው ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝተዋል። በጥረትና ትጋት እዚህ የደረሰ ወጣት ሰዓሊ ነው፡፡ ብዙዎቻችን ተመኝተን አቅቶናል፡፡ በሌሎች አገራት ሰዓሊያን ማዕረግና ስልጣን አላቸው፡፡ በእኛ አገር ሰዓሊ ከትምህርት ቤት ከተመረቀበት እስከሚሞትበት ዕለት ድረስ ሰዓሊ ተብሎ ነው የሚታወቀው፡፡ አፈወርቅ ተክሌ በአገራቸው መዝኖ የሚያከብራቸው ስላጡ ፈረንሳይ ሄደው ራሳቸውን ስላስተዋወቁ “ሎሬት” ተባሉ፡፡ ትርጉሙ ክብር የሚገባው ማለት ነው፡፡ መዝገቡ ተሰማም ክብር የሚገባው መባል አለበት። ዓይን ያለኝ ይመስለኝ ነበር፡፡

ዓይኔን የከፈተልኝ መዝገቡ ተሰማ ነው፡፡ ክብር መስጠትን በተመለከተ የተሰጠ አስተያየት አለ፡፡ በቀድሞ ዘመን ለኪነ ጥበብ ሰዎች የሚሰጥ ሊቅ፣ ሊቀ ጠበብት፣ ሊቀ ሊቃውንት … የሚባሉ ማዕረጎች ነበሩ፡፡ ያ በጎ ጅምር ስላልቀጠለ ነው አንዱን ባለሙያ ከሌላኛው መለያ ያጣነው፡፡ በስዕሎቻቸው ብዥታን ለማጥፋት ብዙ የለፉ ሰዓሊያን አሉ፡፡ በብዥታ ውስጥ መንፈሳዊ ርዕሰ ጉዳዮችን ልታያቸው ያልሞከርከው ለምንድነው? ስዕሎቹ እንደማይሸጡ ገልፀሀል፡፡ ዕጣ ፈንታቸው ምንድነው የሚሆነው? ለአገር ውስጥ ከሆነ ስዕሎችህን በቅናሽ እንደምትሸጥ አውቃለሁ፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲገዛህ ብታደርግ … አገራቸውን በለምለምነቷ፣ በሰቆቃዋ … የሚገልጿት አሉ፡፡ በዚህ ኤግዚቢሽን ላቀረብካቸው ሥራዎች መነሻህ ምንድነው? ድንጋይና አለቶቹ የኢትዮጵያን ታላቅነት ለማሳየት ይሆን? እንስሳቱን በቋጥኝና በድንጋያማ ቦታዎች ያኖርካቸው ምን ልትነግረን ፈልገህ ነው? ስዕሎችህ ላይ የበዛ ፀጥታ መስፈኑ ይታያል፡፡ ሰዎችም፣ እንስሳት ላይም ፀጥታ ጎልቷል፡፡

ሌላው ቢቀር በ“ንግስ” ስዕል ላይ አንዲት ሕፃን ስታጨበጭብ ከምትታየው በስተቀር ፀጥ ያለና ያልተለመደ የሚመስል ሥነ ስርዓት ነው። ምክንያትህ ምንድነው? ለመዝገቡ ከቀረቡት ጥያቄዎች ለአንድ ሁለቱ እኔ ምላሽ አለኝ፡፡ ሰዓሊው ሀሳቡን በሸራዎቹ ላይ ዘርግፏል፡፡ በስዕሎቹ ላይ የሚታየው ሰላምና ፀጥታ በመዝገቡ ውስጥ ያለውን እርጋታ አመልካች ነው። ታሪካችን በጦርነት የተሞላ ቢሆንም ለመዝገቡ ሰላምና ፀጥታው በዝቶ ታይቶታል፡፡ እነዚህን መሰል ጥያቄዎች አስተያየትና ሙገሳዎች ከቀረቡ በኋላ ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ የማጠቃለያ ሀሳቡን አቅርቧል፡፡ የዓለማችን ብዙ ሰዓሊዎች ማዕረግ የላቸውም ያለው መዝገቡ፤ ባለ ማዕረግ ባለመሆኔ ችግር የለውም ብሏል። ከመንፈሳዊ ጉዳይ ጋር ለተነሳው ጥያቄም በሁለቱም አቅጣጫ ድብቅ አለሞች እንዳሉ፤ የሰው ልጅ የማየትና የመረዳት አቅሙም ውስን መሆኑን ገልጿል፡፡ ተፈጥሯችን ከሰጠን በላይና በታች አናይም፤ ጆሯችን ከሚችለው በላይ ሙዚቃ አናዳምጥም። የእይታ አቅማችንን ለማጉላት ሳይንቲፊክ ማይክሮስኮፕ እንደምንጠቀመው ሁሉ አንዳንድ ሰዓሊያንም ሥራዎቻቸውን በአብስትራክት የሚያወሳስቡት ስሜትና ሀሳባቸው ለመግለጽ ከመጨነቅና ከመጓጓት ነው፡፡

የስዕሎቹ የነገ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን እኔም አላውቅም፡፡ የሚያግዘኝ ካገኘሁ በተለያዩ ቦታዎች ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት ለሕዝብ ባሳይ ደስ ይለኛል። እያንዳንዱ ስዕል የራሱ የሆነ ዕድል አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ “ሰቆቃውን ዘመን እኔም አልፌበታለሁ። ሁላችንም በዕድሜ ዘመናችን በተለየ የምናስታውሰው ወርቃማ ጊዜ አለን፡፡ የእኔ ወርቃማ ዘመን እስከ 16 ዓመቴ በትውልድ ቀየዬ የቆየሁባቸው ጊዜያት ነበሩ። በኋላ በግልም፣ በጋራም፣ በቤተሰብ ደረጃም … ብዙ ችግር አሳልፌያለሁ፡፡ ካሳለፍኩት ችግር ይበልጥ የወርቃማ ዘመን ትዝታዎቼ በስዕል ሥራዎቼ ላይ ጎልተው ወጥተዋል፡፡ ከመናገር ይልቅ ዝምታ የተሻለ ዋጋ የሚኖረው ጊዜ አለ፡፡ በ “ንግስ” ስዕል ላይም ፀጥታ ሰፍኖ የሚታየው ያችን የፀጥታ ቅጽበት ጠብቄ ስለሳልኩት ነው፤” በማለት የማጠቃለያ ሃሳቡን ቋጭቷል፡፡

Read 2011 times