Saturday, 07 December 2013 12:16

ዋልያዎቹ ከአፍሪካ ምርጥ ቡድኖች አንዱ ሆነዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ ሶስት ብሄራዊ ቡድኖች አንዱ መሆኑን አስታወቀ፡፡ አስቀድሞ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በዓመታዊ የኮከብ ተጨዋቾች ምርጫው በሁለት ዘርፎች 3 ኢትዮጵያውያን በእጩነት እንደጠቀሳቸው ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ ስኬት በማግኘት በአገሪቱ እግር ኳስ ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሯል። የዋልያዎቹ ስብስብ በ2013 የአፍሪካ ምርጥ ቡድኖች የመጨረሻ እጩ ሆኖ የቀረበው ከምእራብ አፍሪካዎቹ ቡድኖች ናይጄርያ እና ቡርኪናፋሶ ጋር ነው፡፡ ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፍ በ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ የበቃው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ20ኛው ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻው ጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ በ2014 እኤአ በደቡብ አፍሪካ በሚስተናገደው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ እንደሚሳተፍም ይታወቃል፡፡ በካፍ ዓመታዊ ኮከብ እግር ኳስ ተጨዋች ምርጫ በመላው ዓለም ከሚጫወቱ አፍሪካዊ ፕሮፌሽናሎች በእጩነት ከቀረቡት 25 ተጨዋቾች ሳላዲን ሰኢድ ሲጲጁ በሌላው በአፍሪካ ብቻ በሚጫወቱ ከቀረቡት 23 እጩዎች ደግሞ አዳነ ግርማና ጌታነህ ከበደ ተካትተዋል፡፡ የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋቾች ምርጫ ላይ በተለያዩ ዘርፎች ያሸነፉት የሚሸለሙት ከወር በኋላ በናይጄርያ ሌጎስ በሚካሄድ ስነስርዓት ይሸልማሉ፡፡ በተያያዘ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በወጣቶች ላይ በማተኮር ጠንክረን ከሰራን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዕድገት በጣም ተጠናክሮ ይቀጥላል በማለት ለፊፋ ድረገፅ በሰጡት ምላሽ ተናግረዋል፡፡ ፊፋ በድረገፁ በሰውነት ቢሻው ላይ ያተኮረ ዘገባውን ሲሰራ ዋና አሰልጣኙን ቀድሞ የባይሎጂ መምህር እና የእግር ኳስ ተማሪ መሆናቸውን ጠቅሶ ነበር፡፡ ‹‹መምህርነት እና የእግር ኳስ አሰልጣኝነት ተመሳሳይ ሙያ መሆናቸው እጅግ በጣም ጠቅሞኛል፡፡ አስተማሪነቴን ካቆምኩ በኋላ በመጀመርያ በአገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የእግር ኳስ ስልጠና ኮርሶችን ወስድኩ ፡፡ ከዚያም የካፍ እና የፊፋ ኮርሶችንም ተከታትያለሁ፡፡ በውጭ አገርም የትምህርት ኮርሶችን አግኝቻለሁ፡፡ አሁን ሙያዬ መምህርነት አይደለም የማስተምረው እግር ኳስን ሆኗል ›› በማለት አሰልጣኝ ሰውነት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ኢንተርናሽናል ውድድሮችን የጀመርነው ለአፍሪካ ዋንጫ እና ለዓለም ዋንጫ የማለፍ ግቦችን በማቀድ ነበር፡፡ ግቦቻችን ለማሳካት በጣም ጠንክረን መስራት እንዳለብንም በመገንዘብ ቀን ከሌሊት ልምምድ አድርገናል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ መሻሻልን ለመረዳት ብዙ እንደማያስቸግር ለፊፋ ድረገፅ ዘገባ ያስረዱት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ‹‹ዋናው ምስጥር በርትቶ መስራት እና ሁሉም ተጨዋቾች በአንድ አይነት አስተሳሰብ እንዲሰሩ ማስቻል ነው፡፡ የቡድናችን ጥንካሬ ያለው አንድነት እና ትስስር ነው፡፡›› ብለዋል የኢትዮጵያን እግር ኳስ ቀጣይ እድገት ብሩህ ለመናድረግ መሰራት ስላለበት ሲናገሩ‹‹ በወጣቶች ደረጃ ወርደን በመስራት የኳስ ተሰጥኦ ያላቸውን ልጆች ማሳደግ አለብን፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት እና ሶስት አመታት በርካታ ምርጥ ችሎታ ያላቸውን ተጨዋቾች ማሰባሰባችን አይቀርም፡፡ በእነሱ ላይ አተኩረን ከሰራን የብሄራዊ ቡድናችን ጥንካሬ ይቀጥላል፡፡›› ብለዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የ2013 የዓለም ኮከብ እግር ኳስ ተጨዋቾች ምርጫ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ከሮናልዶ ወይም ከሜሲ የቱ ያሸንፋል በሚል የተፈጠረው ክርክር ትኩረት እንደሳበ ነው፡፡ አንዳንድ ዘገባዎች ፉክክሩ በክርስትያኖ ሮናልዶ፤ ሊዮኔል ሜሲ እና ፍራንክ ሪበሪ መካከል እንደሚሆን እየገለፁ ናቸው፡፡ እንደውም በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ኤጀንሲያ ኒውስ የተባለ ታዋቂ የስፔን ሚዲያ አሸናፊውን ደርሸበታለሁ ብለው ዘግቧል፡፡ እንደኤጀንሲያ ኒውስ መረጃ ሜሲ ለአምስትኛ ጊዜ የዓለም ኮከብ ተጨዋች ሆኖ የወርቅ ኳሱን እንደሚሸለም ተገልፆ፤ ክርስትያኖ ሮናልዶ፤ ፍራንክ ሪበሪ ፤ አንድሬስ ኢንዬስታ እና ዝላታን ኢብራሞቪች እስከ አምስተኛ ደረጃ እንዳገኙ ታውጇል፡፡ ከግብ ጠባቂዎች በምርጥ 11 ቡድኑ ለመካተት የቀረቡ 5 የመጨረሻ እጩዎች ከሳምንት በፊት ይፋ ሲደረጉ ጣሊያናዊው የጁቬንትስ ግብ ጠባቂ ጂያንሉጂ ቡፎን፤ ስፔናዊው የማድሪድ ግብ ጠባቂ ኤከር ካስያስ፤ ቼካዊው የቼልሲ ግብ ጠባቂ ፒተር ቼክ፤ ጀርመናዊው የባየር ሙኒክ ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኑዌር እንዲሁም ስፔናዊው የባርሴሎና ግብ ጠባቂ ቪክቶር ቫልዴዝ ናቸው፡፡ ለዓመቱ ምርጥ ጎል ለሚሸለመው የፑሽካሽ አዋርድ 10 ተጨዋቾች በአስር ምርጥ ጎሎቻቸው በእጩነት ሲቀረቡ የኔይማር እና የኢብራሞቪች ጎሎች ይገኙበታል፡፡ በፊፋ ድረገፅ የተሰጡ ድምፆች ከተሰበሰቡ በኋላ ለመጨረሻ ፉክክር የሚበቁ ሶስት የዓመቱ ምርጥ ጎሎች የሚታወቁት ሰኞ ነው፡፡ በዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ ምርጫ ለመፎካከር የቀረቡ አስር እጩዎች ካርሎ አንቸሎቲ፤ ራፋ ቤኒቴዝ፤ አንቶኒዮ ኮንቴ፤ ቪሰንቴ ዴልቦስኬ፤ አሌክስ ፈርጉሰን፤ ጁፕ ሄንየስ፤ የርገን ክሎን፤ ጆሴ ሞውሪንሆ፤ ሊውስ ፊሊፕ ስኮላሬ እና አርሰን ቬንገር ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ተጨዋች ሆኖ ለማሸነፍ የበቃው አይቮሪኮስታዊው ያያ ቱሬ ነው፡፡ የማንችስተር ሲቲ ወሳኝ አማካይ ተጨዋች የሆነው ቱሬ በቢሲሲ የዓመቱ አፍሪካዊ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ ከመመረጡ ባሻገር ለፊፋ የወርቅ ኳስ ሽልማት የታጨ ብቸኛው አፍሪካዊ ነው። ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ በተካሄደው የቢቢሲ የዓመቱ ኮከብ ተጨዋች ምርጫ ላይ በመጨረሻ እጩነት ከቀረቡት ተጨዋቾች ናይጄሪያውያኑ ጆን ኦቢ ሚኬል እና ቪክቶር ሞሰስ እንዲሁም የዛምቢያው ጆናታን ፕሪቶፕያ ይገኙበት ነበር፡፡

Read 1395 times