Saturday, 07 December 2013 11:48

አውራ-ዶሮ ፈረስን ረግጦ፤ “እርግጫ ከኔ ተማር!” አለው የኦሮምኛ ተረት

Written by 
Rate this item
(40 votes)

አንድ የፈረንጆች ተረት አለ፡፡
ኮረዶች በማፍቀር ዕድሜ ላይ ያሉ ጐረምሶች፤ “የት ሄደን ነው ራት የምንገባበዘው?” ሲባባሉ፤ አንደኛው፤
“ኦሽን-ቪው ሆቴል እንሂድ” አለ
“ለምን?” ሲሉት፤
“እዚያ ቆንጆ ቆንጆ፣ የሚታዩ ኮረዶች አሉ!” አለ፡፡
ሁሉም ተስማሙና ሄደው በርቸስቸስ ሲሉና ሴት ሲያጫውቱ አመሹ፡፡
ይህ በሆነ ከአሥር ዓመት በኋላ እንደዚሁ ተገናኙ፡፡ “የት እናምሽ?” የሚል ጥያቄ ተነሳ!
“ኦሸን-ቪው ሆቴል” አለ አንዱ፡፡  
“ለምን?” አሉት፡፡
“ጥሩ ራትና ጥሩ መጠጥ አለ” አለ፡፡
ይህ በሆነ ከአሥር ዓመት በኋላ ዳግም ተገናኙ፡፡ አሁን ወደ ሰባ ዓመት ተጠግቷቸዋል እንግዲህ
“የት እንብላ ራት?” ተባለ፡፡
“ኦሺን ቪው ሆቴል” አለ አንደኛው፡፡
    *    *     *
“ለምን?” አሉት፡፡
“በጣም ፀጥ ያለ፣ የውቂያኖሱን ሰላምና ነፋሻ አየር የምናገኝበት ቦታ ነዋ!” አላቸው፡፡
ተያይዘው ነፋሻውንና ፀጥ ያለውን አየር ሲኮመኩሙ አመሹና ተለያዩ፡፡
ይሄ በሆነ ከአሥር ዓመት በኋላ እንደገና ተገናኙ፡፡ አሁን ጎብጠዋል፡፡ ከዘራ ይዘዋል፡፡ ባርኔጣ አድርገዋል፡፡ በጣም በዝግታ ነው የሚራመዱት፡፡ እየተደጋገፉ እየተቃቀፉ ነው የሚቆሙት፡፡
“ዛሬስ ለእራት የት እንሂድ?” አለ አንደኛው፡፡
“ኦሽን ቪው ሆቴል” አለ ሌላው፡፡
“ለምን?” ብለው ጠየቁ ሌሎቹ፡፡
ሰውዬውም፤
“እዛ ሆቴል ሄደን አናውቅማ!”
“ብራቮ! አዲስ ሆቴል ማየት በጣም ደስ ይላል” አለ አንዱ፡፡  
“ድንቅ ሀሳብ!”
“አስገራሚ ሀሳብ!”
“ጉደኛ ሀሳብ!” እየተባባሉ እየተጓተቱ፣ እየተገፋፉ፣ መሰሰሰስ እያሉ፤ ወደ ኦሽን ቪው ሆቴል አመሩ፡፡
*   *   *
የተፈጥሮን ሂደት ለማቆም አይቻልም፡፡ ይህን የተፈጥሮና የዕድሜ መሰላል፤ በየዕለቱ ከሚገጥመን አገራዊ ችግርና አፈታቱ ጋር ለማስተያየት ብንሞክር፤ አርጅተን ጃጅተን የሠራነውንና ያልሠራነውን፣ የሄድንበትንና ያልሄድንበትን ለመለየት የማንችልበት የመርሳት ዕድሜ እስከምንደርስ ንቅንቅ አልልም ብለን፤ በያዝነው ሥልጣንና ሹመት ሙጭጭ ካልን፤ በዚያውም ለተተኪው ትውልድ ቦታ ካልለቀቅን፤ የአገር- ለውጥ- ቀን እየራቀ ነው የሚሄደው፡፡ በእርግጥም ይሄ ቦታን በሰላም የመልቀቅ ባህል የዋዛ ነገር አይደለም፡፡ ፖለቲካዊ-ገፅ አለው፡፡ የኢኮኖሚ-ገፅ አለው፡፡ የግል ጥቅም-ገፅ አለው፡፡ ከፓርቲ ጋር፣ከራስ ጥቅም ጋር፣ ከራስ ህሊና ጋር መሟገትንና መታገልን ይፈልጋል፡፡ ይህን ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ የሆነ በማይገኝበት ዘመን የአገር ምጧ ብዙ ነው፡፡
ወጣቱ ላይ ዕምነት ይኑረን፡፡ ያለ ጥርጥር ወጣቱ አሸናፊ ነው፡፡ The New is invincible ይሉ ነበር የጥንት ፖለቲከኞች፡፡ ዛሬም ይሄ ዕውነታ አይሻርም፡፡ አዲስ ኃይል መፍጠር የአገር አቅም መፍጠር ነው። ይህ ማለት ግን የግድ በፖለቲካ የሚታቀፍ ወጣት ይኑረን ማለት አይደለም፡፡
“ያፈረሰ ቄስ ተመልሶ አይቀድስ፣ የሸሸ ንጉሥ ተመልሶ አይነግሥ” በሚባልበት አገር የማይሻሩና በልብ ፅላት ላይ የተፃፉ ህግጋት አሉ፡፡ እነዚህ በባህልና በማህበራዊ ልምድ የዳበሩና የታመኑ ናቸው! አገር ያወቃቸውና ያመነባቸው የወል ህግጋት እንዳሉ ሁሉ፤ ሰው በግሉ በራሱ ላይ የሚወስንባቸው ግለ-ደንቦችም አሉ፡፡ እንዲህ ያሉት ህገ-ደንቦች ሲበራከቱ ስደት ልጓም ያጣል፡፡ ስደተኛው የትየለሌ ቢሆን የማይገርመው ለዚህ ነው! ውጤቱን እንደ ዛሬው በአስከፊ መልኩ ባንቀምሰውም በውሱን መልኩ የምናውቀው ስደትና አስከፊ ውጤት ነበር፡፡ “የራሱን ጭራ ሳያይ ውሻ ፍየልን ጭራሽን ዝቅ አድርጊ” ይላል የሚል ኦሮምኛ ተረት አለ፡፡ የራሳችን ነውር ሳይታየን ስለ ሌላው አስነዋሪ ነገር መናገር ክፉ እርግማን ነው! የሌሎቹን አገሮች፤ ፓርቲዎች፣ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ስንተች እኛስ? የእኛስ? ብለን መጠየቅን አንርሳ! ልማዶቻችንን፣ በዓሎቻችንን ስብሰባዎቻችንን እንገምግም፣ እንመርምር፣ እናሻሽል፡፡ በዓላት በራሳቸው ግቦች አይደሉም፡፡ ወደፊት መራመጃ እንጂ!  
ከፖለቲካ ባህላችን ውስጥ እጅግ ሚዛን የሚደፋ አንድ ባህል አለ፡፡ ብዙ ሊጤን ይገባል! የይቅር መባባል ባህል!  ቂም፣ የወንጀለኝነት-ስሜት፣ ብድር-የመመለስ ፍላጎት፤ አጥፊ ናቸው፡፡ ዴቪድ ሀውኪንስ እንዲህ ይለናል፡፡ “የ2ኛው የዓለም ጦርነት አንጋፋ ተሳታፊዎች አሰቃቂውንና አንገፍጋውፊን ጦርነት ከተወጡ በኋላ አብዛኞቹ የጠላት ተፋላሚዎች በፍጥነት ይቅርታ ተደራረጉ፣ ይቅር ተባባሉ፡፡ ሰላምታ ተሰጣጡ፡፡ የፍልሚያውን ፍፃሜም በዓል አከበሩ፡፡ በአዲስ የመተሳሰብ መንፈስ ተጨባበጡ፡፡ አሜሪካኖች አቶሚክ ቦምብ የጣሉና በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎችን የቀጠፉ ነበሩ፡፡ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ግን “በቃ ጦርነትኮ ይሄው ነው” ተባለ! የትላንት ተፋላሚዎች የዛሬ ጓደኛ ሆኑና ይጠያየቁ ጀመር፡፡ ይሄው እስካሁንም የተረፉት ታላቁን የጦርነት ቀን ያከብራሉ”
በአያሌ ሰዎች በተግባር እንደተረጋገጠው፤ አሉታዊ አመለካከትና የወንጀለኛነት ስሜት ፤በአዎንታዊ የመረዳት ስሜት፣ በመረዳዳትና በትውስታ ስሜት፤ ሊተካ ይችላል፡፡ … በዚህ ስሜት ሲታይ ከዚህ ቀደም ይጠሉ የነበሩ ሰዎች ይቅርታን ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ያስፈሩ የነበሩ ሰዎችም አሁን ሰላማዊ ሆነው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ዋናው ራስን ለማየትና ጥፋትን ለመቀበል ዝግጁ የመሆን ጉዳይ ነው። እርግጥ እንደኛ በፊውዳሊዝም ለተተበተበ፣ ባልለየለት ካፒታሊዝም ለታጠረና ሁሉን ጥፋት በሌሎች ላይ መላከክን ሥራዬ ብሎ ለያዘ ህብረተሰብ ፤ ከአባዜው በቀላሉ ለመገላገል አይቻልም! ሆኖም ይቻላል ብለን አዕምሮአችንንና ልቡናችንን ክፍት እናድርግ፡፡ ለዚህ ቁልፉ ነገር፤ አንዱ ከሌላው መማሩ ነው፡፡ ችግሩ ግን ያልተማረው የተማረውን ካላስተማርኩ፣ አላዋቂው አዋቂው ካላዳመጠኝ የሚልበት፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአዕምሮም በአካልም ያልዳበረው ሰው፤ ልምድ ያለውንና የዳበረውን ሰው፤ ዘራፍ ሲልበት፣ ሲፎክርበት፣ ከእኔ ወዲያ ላሣር ሲለው የታየበት አገር መሆኑ ነው! “አውራ ዶሮ ፈረሱን ረግጦ፤ ‘እርግጫ ከእኔ ተማር!’” አለው፤ የሚለው የኦሮምኛ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው!!

Read 18384 times