Saturday, 30 November 2013 11:39

መፀዳጃ ቤት አልባዋ አዲስ አበባ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ከከተማዋ ነዋሪ ውስጥ ከአንድ ሚሊየን በላይ የሚሆነው ሜዳ ላይ ይፀዳዳል

ለ62 ዓመታት አዲስ አበባን ኖረውባታል፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት የሚያውቋት ይህቺው ከተማ በዘመን ብዛት እየዘመነች፣ እያደገችና እየተሻሻለች መሆኗን ባይክዱም በንጽህናዋ ረገድ ዕለት ተዕለት ቁልቁል መሄዷ ሁሌም ያስገርማቸዋል፡፡ በተለይ በተለይ ልጅነታቸውን ያሳለፉበትንና ወጣትነታቸውን ያጣጣሙበትን የከተማዋን እምብርት ፒያሣን ፈጽመው አይዘነጉትም፡፡
በዘመናቸው አራዳ እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት እኒህ አካባቢዎች፣ እንደሣቸው ባሉ ዘመነኞች እጅግ ይዘወተሩ ነበር፡፡ አካባቢዎቹ የመጠጥ እና የጭፈራ ቤቶች የሚበዙባቸው ሥፍራዎች ቢሆኑም ሁልጊዜም ንፁህና ለአይን ማራኪ እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ “አራዳው ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ዙሪያ የነበሩ የመናፈሻ ሥፍራዎች የስንቶቻችን መቀጣጠሪያና የእርቅ ሽምግልና መፈፀሚያ ቦታ ነበር መሰለሽ፤ ያኔ እንዲህ እንደዛሬው ቅጥ አንባሩ የጠፋበት ዘመን አልነበረም፡፡ ያኔ እንዲህ እንደአሁኑ በቤተክርስቲያን ደጃፍ እንደልብ መፀዳዳት ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነበር፡፡ በየጥጋጥጉና በየሜዳው የሚፀዳዱ ሰዎችን ይዘው የሚያስቀጡ ደመወዝተኛ የሚባሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ግን ህብረተሰቡም እራሱ ፈሪሃ እግዚአሃብሔር ያደረበት፣ ሜዳ ላይ መፀዳዳት የሚያሳፍረውና እርስበርሱ የሚከባበር ስለነበር ከተማዋ እንዲህ እንደዛሬው የህዝብ መፀዳጃ ቤት አትመስልም፡፡ አሁን አሁንማ አፍንጫው ሥር ሲፀዳዳ እፍረት የማይሰማውን የከተማ ነዋሪ ማዘጋጃ ቤቱ የሚያበረታታውና አይዞህ የሚለው ይመስላል። ማዘጋጃ ቤቱ እንኳንስ የከተማዋን ጽዳትና ውበት ሊጠብቅና ሊቆጣጠር ቀርቶ የራሱን ደጃፍ ከህዝብ መፀዳጃ ቦታነት ሊከለክልና ሊያስጥል አልቻለም። አላሙዲን የልጆቻችን ኳስ መጫወቻ የነበረውን ሰፊ ሜዳ ወስደው ሲያጥሩ እንዴት ያለ ሆቴልና መዝናኛ ቦታ ሠርተው አካባቢውን ሊያሣምሩልን ነው፡፡ ተመስገን አይናችን ጥሩ ነገር ሊያይ ነው ብለን ተደስተን ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው፡፡ ይኸው ሃያ ዓመት ሙሉ በአጥር ተከልሎ የመፀዳጃና የመዳሪያ ቦታ ሆኗል፡፡ እኔ የሚገርመኝ ማዘጋጃ ቤቱ እዚሁ ዓይኑ ሥር ያለውን የሠገራ ክምር ማጽዳት አቅቶት፣ የከተማ ጽዳት፣ የአካባቢ ጽዳት እያለ መለፍለፉ ነው፡፡ ለነገሩ የሰው አይን ላይ ያለች ጉድፍ እንደሚታይሽ በራስሽ ፊት ላይ ያለው ትልቅ ግንድ መች ይታይሻል።”
 ገዳም ሰፈር ተወልደው ላደጉትና የከተማዋ ጽዳት በእጅጉ ለሚያሳስባቸው አቶ አሰፋ ታዬ፤ የከተማዋ አስተዳደር የከተማዋን ንጽህናና ጽዳት በመጠበቁ ረገድ ምን እየሠራ እንደሆኑ ፈጽሞ አይገባቸውም። በከተማዋ ዋና ዋና ጐዳናዎች ላይ ተከምረው ሃላፊ አግዳሚውን የሚያሰቅቁ የቆሻሻ ክምሮች ማንን እየጠበቁ እንደሆነም ግራ ይገባቸዋል። “የድሮዎቹ ደመወዝተኞች የአካባቢውን ንጽህና ለመጠበቅና ህብረተሰቡ በተገቢው ቦታ መፀዳዳት እንዳለበት በማስተማሩ ረገድ ሰፊ ሥራን ይሰሩ ነበር። የዛሬዎቹ ደንብ አስከባሪዎች ግን ከሱቅ በደረቴዎች ጋር ሌባና ፖሊስ ሲጫወቱ ነው የሚውሉት፡፡ ‘መሽናት ክልክል ነው’ ብሎ በመፃፍና በመለጠፍ ብቻ ምንም ለውጥ ማምጣት አይቻልም። የግንዛቤ ለውጥ ለማምጣት መስራት አለበት፡፡ እንደውም እኮ ሰው የሚፀዳዳው “መሽናት ክልክል ነው” የሚሉ ጽሑፎች በተለጠፋባቸው ቦታዎች ላይ ነው፡፡
እናም ባለስልጣናቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ቢያስቡበት ጥሩ ነው፡፡ ፎቅና መንገድ መሥራት ብቻ አንድን ከተማ ሊያሣድጋት አይችልም፡፡ ንጽህናዋም ወሳኝ ነው፡፡ የከተማዋ አስተዳደር በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ካልሰራ በስተቀር አሁን እንዲህ ከፍተኛ ወጪ እየወጣበት የሚሰራውና ብዙ የተባለለት አዲሱ የባቡር ሐዲድ መፀዳጃ ላለመሆኑ ማረጋገጫ የለንም፡፡” የአቶ አሰፋን ትዝብትና ሥጋት የሚጋሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ቁጥር በርከት ያለ ነው፡፡ ከተማዋ ያለ ፕላን የተሰሩ መንገዶችና ቤቶች የሚበዙባት፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎች በአግባቡ ያልተሰራባትና አሮጌ መንደሮች የተበራከቱባት እንደመሆኗ በቂ የመፀዳጃ ቤቶች የሏትም፡፡ አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ የሚፀዳዳው በየመንገዱና በየጥጋጥጉ ላይ ነው፡፡
የህብረቱ መቀመጫ፣ የአፍሪካ መዲና፣ የታላላቅ አለምአቀፋዊ ድርጅቶችና ሆቴሎች መናኸሪያ እየተባለች የምትሞካሻው ከተማችን አዲስ አበባ፤ እጅግ ደካማ የንጽህና አጠባበቅ እንዳላትና በሚሊዮን የሚቆጠረው ነዋሪ ህዝቧ ዛሬም በሜዳ ላይ እንደሚፀዳዳ አንድ መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይፋ ያደረገው ይኸው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በከተማዋ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖር ሲሆን ከዚህ ቁጥር ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወይንም 25 ከመቶ የሚበልጠው የከተማዋ ነዋሪ የመፀዳጃ ቤት የለውም፡፡ ይኸው መፀዳጃ ቤት አልባ የከተማዋ ነዋሪ በየመንገዱ ላይ እና በየቤቶቹ ጥጋጥግ ይፀዳዳል፡፡
የመኖሪያ ቤቶች ተጠጋግተው በተሰሩባቸውና እጅግ በርካታ ህዝብ በሚኖርባቸው አካባቢዎች፣ ነዋሪዎቹ በአብዛኛው የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት ለማግኘት አለመቻላቸውን መረጃው አመልክቶ ሜዳ ላይ የመፀዳዳት ሂደቱም በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ጐልቶ እንደሚታይ ጠቁሟል፡፡
ይህንን ችግር ለማስወገድ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር መተባበርና በሜዳ ላይ መፀዳዳት እጅግ አሣፋሪ ተግባር እንደሆነ ተገንዝቦ፣ ከድርጊቱ መቆጠብ ይገባዋል ሲልም መረጃው አመላክቷል። ለነዋሪው ህብረተሰብ በቂ የመፀዳጃ ቤት ሊገነባ እንደሚገባም አስገንዝቧል፡፡
ሰሞኑን በ(Wash Ethiopia movement) አስተባባሪነት በአዳማ ከተማ ውስጥ በተከበረው አምስተኛው አገር አቀፍ የሃይጂንና የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ፌስቲቫልና አለም አቀፍ የመፀዳጃ ቤት ቀን በዓል ላይ እንደተገለፀው፤ በአገሪቱ ከ60-80 በመቶ የሚሆነው የጤና ችግር ተላላፊ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ደግሞ 75 በመቶ የሚሆነው በንፁህ የመጠጥ ውሃ እጥረትና በአካባቢ ንፅህና ጉድለት ሣቢያ የሚከሰት ነው፡፡ በአገራችን የህፃናት ገዳይ በሽታዎች ከሆኑ የጤና ችግሮች መካከል ግንባር ቀደም የሆነው የተቅማጥ በሽታም ከንፅህና ጉድለት ጋር ተያይዞ የሚከሰት እንደሆነ ተጠቁሞ፤ በአፍሪካ ከንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረትና ከግልና ከአካባቢ ንፅህና ችግር ጋር በተያያዙ የጤና ችግሮች በየሰዓቱ 115 ሰዎች እንደሚሞቱ በዚሁ ፌስቲቫል ላይ ተገልጿል፡፡
የአገሪቱ ርዕሰ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ፤ በዚህ መልኩ ሜዳ ላይ የሚፀዳዳ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህዝብ እንዳለባት ስሰማ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ የምትገኘው የዶርዜ ሃይዞና የሸበዲኖ ወረዳ ነዋሪዎች ይህንን ሲሰሙ ምን እንደሚሉ ማሰቡ አቃተኝ፡፡ በእነዚህ ወረዳዎች እጅግ አሣፋሪው ተግባር ሜዳ ላይ መፀዳዳት ነው፡፡ እነዚህ ቦታዎች “ሜዳ ላይ ከመፀዳዳት የነፃ” (Open deification Free) ተብለው በተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ሜዳ ላይ መፀዳዳት እጅግ አሣፋሪ ተግባር መሆኑን ያምናሉ፡፡ ይህንን አሣፋሪ ተግባር ላለመፈፀም በእጅጉ ይጠናቀቃሉ፡፡ ይህንን እምነታቸውን ጥሶ መንገድ ላይ የሚፀዳዳ ሲያዩ በዝምታ አያልፉትም፡፡ ነዋሪዎቹ እንዲህ አይነት “አደጋ” በአካባቢያቸው ሲፈፀም የሚጠራሩበት የራሣቸው የሆነ የኮድ መጠራሪያ ድምፅ አላቸው። ይህንን ጥሪ የሰማ የአካባቢው ነዋሪ ሁሉ ጥሪው ወደተደረገበት ቦታ በፍጥነት ይሄዳል፡፡ ሰውየው (ሴትየዋ) መፀዳዳታቸውን እስኪጨርሱ ድረስ ይጠብቁና ሠገራውን በፕላስቲክ ከረጢት ውስጥ እንዲከት ያስገድዱታል፡፡ በሠገራው ላይ የሰውየው ሙሉ ስም ይፃፍበትና በዋናው መንገድ ላይ ይንጠለጠላል፡፡ “የእከሌ ሰገራ ነው” የሚለውን ፅሁፍ የሚያነበው የአካባቢው ነዋሪ ህዝብ ለሰውየው የሚሰጠው ግምት እጅግ ያነሰና የወረደ ይሆናል፡፡ ይህም ድርጊቱን በፈፀመው ሰው ሞራልና ስብህዕና ላይ ከፍተኛ ውድቀትና በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድም መገለልን ያስከትልበታል፡፡ ማንም ሰው ይህ እንዳይደርስበት  ሜዳ ላይ ከመፀዳዳት ይቆጠባል፡፡ አዲስ አበቤዎች ከዚህ ምን ይማሩ ይሆን?  

Read 4885 times