Print this page
Saturday, 30 November 2013 11:38

ከ“ፎርጅድ” ፖለቲከኞች፣ባለሥልጣናት፣ ፓርቲዎች፣ … ይጠብቀን!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(21 votes)

“የመለስን ራዕይ እናስፈጽማለን” እያሉ ተጐልቶ መዋል ምንድነው?
ሰሞኑን ፖሊስ በቁጥጥር ሥር የዋለውን የፎርጅድ “ስፔሻሊስት” ጉድ ሰምታችሁልኛል? የመቶ ምናምን መስሪያ ቤቶችን ማህተም፣ ቲተር፣ ወዘተ… በመቅረፅ ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ (ሳይማሩ ድግሪ እኮ ነው!)፣ መንጃ ፈቃድ፣ የጋብቻ ሰርተፊኬት፤ ውክልና፣ ሊብሬና ሌሎች ሰነዶችን “ሲያመርት” መክረሙን የሰማሁት ከኢቴቪ የፖሊስ ፕሮግራም ነው፡፡ (ፎርጅድ በፎርጅድ ሆነናላ!) ይሄኛውን የፎርጅድ “ስፔሻሊስት” ከቀድሞዎቹ ልዩ የሚያደርገው ምን መሰላችሁ? ያልደፈረው የመንግስት መስሪያ ቤትና የግል ተቋማት የለም፡፡ (አይዞህ ያለው ማነው?) የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ የፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የግል ክሊኒኮች፣ የመንግስትና የግል ዩኒቨርስቲዎች፣ ወዘተ (የማን ቀረ ታዲያ!) ማህተሞችን … ፎርጅድ እየሰራ የተለያዩ ማስረጃዎችን ያቀርባል ወይም ይቸበችባል፡፡ (ፎርጅድ ፈላጊው “በሽ” ነው ማለት እኮ ነው!)
የሚገርማችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማህተምና ቲተር እንኳን አልቀረም እኮ፡፡ የእነ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን ቲተርና የኦነግን (አደጋ አለው!) ማህተምም ሲያዘጋጅ እንደነበር ተገልጿል - የፎርጅዱ ስፔሻሊስት፡፡ እኔ የምለው ግን … በ“ፎርጅድ” ሙያ የሚያሰለጥን “ስውር ተቋም” አለ እንዴ? (ከሽብርተኝነት አይለይም እኮ!?) እዚህ አገር ታሪካዊቷን ጦቢያ “ፎርጅድ” የማድረግ አሻጥር (Sabotage) ተጠንስሷል ማለት ነው?
የፎርጅዱ ስፔሻሊስት ሲገርመኝ ሰሞኑን ደግሞ በዚያው የፖሊስ ፕሮግራም ላይ የመኪና ስርቆት የፈፀመች የአዲስ አበባ ኮረዳ ተመለከትኩና በግርምት ተሞላሁ፡፡ እንዴ… ማንን እንመን ታዲያ? (በፎርጅድ ኮረዶችም ተከበናል ማለት እኮ ነው!)
እኔ የምላችሁ … ይሄ የሌብነት ጉዳይ “ፕሮፌሽናል ቢዝነስ” መሰለ እኮ! (የሌቦች ማሰልጠኛ ተቋም ተከፈተ እንዴ?) በዚሁ ሰሞን 20 የሚደርሱ ከተለያዩ ሙያዎች የተውጣጡ ግለሰቦች በፎርጅድ ሰነዶች እየተጠቀሙ፣ የአፍሪካን መዲና ሲያጭበረብሩ እንደከረሙ ፖሊስ ተናግሯል፡፡ ይታያችሁ … ከመኪና አከራዮች ውሃ የመሰለች መኪና ይከራዩና ፎርጅድ ውክልና አሰርተው
ጆሮዋን ይሏታል፡፡ የድግስ ወንበሮችና ድስቶች እንዲሁም የግንባታ ማሽኖች እየተከራዩም  ቸብችበዋል፡፡ (8ኛው ሺ ገባ እንዴ?) የእነዚህ “ቁጭ በሉዎች” ሰለባ የሆነች አንዲት እመቤት ለፖሊስ ስትናገር፤ ሌቦቹ “ያሪስ” መኪና ይዘው ወደ ቢሮዋ እንደመጡ ገልፃለች፡፡ (ያሪሷም እኮ ፎርጅድ ናት!)
ለነገሩ የዚህ የፎርጂድ ነገር በሌቦች ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በመንግስትም በተቃዋሚዎችም በምሁሩም በባለሙያውም … በሁሉም ዘንድ እየታየ ነው፡፡ ሰሞኑን አንዲት የስራ ባልደረባዬ መታወቂያዋን ለማሳደስ ወደ ቀበሌ ጐራ ብሎ የገጠማትን አጫወተችኝ፡፡ የቀበሌው ሠራተኞች ወደው ይሁን ተገደው (እነሱም አያውቁት!) የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ምስልና “የመለስን ራዕይ እናስፈፅማለን” የሚል መፈክር የተፃፈበት ቲ-ሸርት ለብሰው ተደርድረዋል-ቢሮአቸው ውስጥ፡፡ ችግሩ ግን ምን መሰላችሁ? ቲ-ሸርቱ ለስራ ሊነሽጣቸው (Inspire ሊያደርጋቸው) አልቻለም፡፡ እንደውም መልበሳቸውንም ሳይዘነጉት አልቀሩም፡፡ ለነገሩ የራሱ ራዕይ የሌለው ሰው “የታላቁን መሪ” ራዕይ ላስፈፅም ቢል እንዴት ይሆናል? (“የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር” አሉ!) እናም ባልደረባዬን በቅጡ ሊያስተናግዷት አልቻሉም፡፡ (መታወቂያ ማደስ እኮ ነው!) እሷ ተገትራ እነሱ ወሬያቸውን እያደሱ ነበር፡፡ የማታ ማታ ዱላ ቀረሽ ሙግት ገጥማ ነው መታወቂያዋን ያደሱላት፡፡ (የፎርጅዱ “ስፔሻሊስት” በቀን ስንት የቀበሌ መታወቂያ ያመርት ይሆን?)
በነገራችሁ ላይ አንድ ፖሊስ ኦሪጂናሉንና ፎርጅዱን የቀበሌ መታወቂያ አነፃፅረው ሲናገሩ “ፎርጅድ የሚመስለው የቀበሌው ነው” ብለዋል፡፡ (የፎርጅዱን ስፔሻሊስት ወደ ህጋዊ መስመር ማምጣት አይቻልም እንዴ?) በእርግጥ መጀመሪያ ቅጣቱን መቀበል አለበት፡፡ እናላችሁ … “የመለስን ራዕይ እናስፈፅማለን” የሚል ቲሸርት ለብሰው ወሬና ሃሜት ሲያነክቱ የሚውሉ የቀበሌና የወረዳ ሰራተኞች ሁሉ “ፎርጅድ ኢህአዴጐች” ናቸው፡፡ (ኢህአዴግም ፎርጂድ አለው እንዴ?)   
ይሄውላችሁ … በቲቪ መስኮት “ኪራይ ሰብሳቢ… ፀረ ሰላም ሃይላት፣ የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝ” እያሉ የሚያደነቁሩን ስንቶቹ ካድሬዎችና ባለስልጣናት ሙሰኞች ሆነው እንደተያዙ በዓይናችን በብሌኑ ዓይተናል፤ሰምተናልም፡፡ አሁን እነዚህ ምን ይባላሉ? “ፎርጂድ ባለሥልጣናት!”  (“made in” የት ይሆኑ?) አንዳንዴ ሳስበው የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ፎርጅድ ሰነዶች ብቻ ሳይሆን ፎርጅድ ተቃዋሚዎችን የሚሰሩም ሳይኖሩ አይቀሩም፡፡ ጊዜ ፊቱን ያዞረባቸው ቀን ግን ቅሌት ቀለባቸው ይሆናል፡፡ (“የህዝብ ነኝ” እያሉ ህዝብን ማታለል አደጋ አለው!)
በየጊዜው የአገሪቱ የትምህርት ጥራት “ወድቋል” ሲባል እንሰማለን አይደል?! አንድም ቀን ግን ተጠያቂው “እገሌ ነው” ብለን ደፍረን አናውቅም (እኛም ራሳችን ፎርጅድ ሳንሆን አንቀርም!) እርግጥ ነው ኢህአዴግ መራሹን መንግስት የሚወነጅሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይሄ ግን “ክሊሼ” ነው - የተሰለቸ፤ የታከተ ሰበብ! ነገርዬውን ጠልቃችሁ ስትመረምሩ ግን ዋንኞቹ ተጠያቂዎች “ፎርጅድ መምህራን” እንደሆኑ ትገነዘባላችሁ፡፡ እንዴ … ሴት ተማሪዎችን “እራት ልጋብዝሽና ስለ ግሬድሽ እንመካከር”፣ “250 ብር አምጣና ማርክ ልጨምርልህ” የሚሉ መምህራኖች እኮ በርክተዋል፡፡ እናም የትምህርት ጥራት እንጦሮጦስ የወረደው በእነዚህም “ፎርጅድ የቀለም ሰዎች” ምክንያት ነው፡፡ (መንግስትም ግን ከተጠያቂነት አያመልጥም-ጠያቂ ካለ!) የሰው ፈጠራ ወይም የጥበብ ሥራ አሊያም ሃሳብ፣ ወዘተ … መንትፈው የራሳቸው በማስመሰል እነሆ በረከት የሚሉን “ከያኒያን”ም እኮ “ፎርጂድ አርቲስቶች” ናቸው-የጦቢያ የጥበብ ቆሌ የተጣላቻቸው!
እንግዲህ ፎርጅድ ያልገባበት የህይወት ዘርፍ የለም፡፡ ለምሳሌ እዚህቹ መዲናችን ላይ የፍቅር ፎርጅድ የሚሰሩ እኮ በሽበሽ ናቸው - ከወንዱም ከሴቱም፡፡ መጀመርያ ላይ “እመቤቴ፣ ንግስቴ፤ ማሬ ወለላዬ …” እያለ የፍቅረኛውን እግር ለማጠብ የሚዳዳው የጦቢያ ወንድ፤ አግብቶ “ንብረቱ” ካደረጋት በኋላ ግን ውጭ ውጭውን ያያል፤ ኮረዳ ያማርጣል፡፡ ይሄንን እኔ “ፎርጅድ ባል” ብየዋለሁ፡፡ “ፎርጅድ ሚስቶችም” “በሽ” ናቸው!! (ዘመኑ እኮ ነው!)
ቁጥራቸው ባይበዛም መታወቂያቸው ወይም ፓስፖርታቸው ላይ “ፎርጅድ ኢትዮጵያዊ” በሚል መገለፅ ያለባቸው አንዳንድ በ “ሃሰት” የተሰሩ ዜጐችም አሉ - እዚህችው ጦቢያችን ምድር ላይ፡፡ ባለፈው ጊዜ የአገልግሎት ቀኑ (expiration date) ያለፈበት የታሸገ ምግብ ከውጭ አስመጥተው በሱፐርማርኬት ስለሚሸጡ ስግብግቦች አልሰማችሁም? እስቲ አስቡት … የተበላሹ የህፃናት ምግብና ወተት ለወገን እየሸጡ ትርፍ ማጋበስ … ምን ይባላል? እውነቴን ነው … እነዚህ ከሽብርተኞች በምንም አይለዩም፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን ህሊናቸውን ለገንዘብ የሸጡ ግለሰቦች “ሆዳም” ወይም “ስግብግብ”፤ በሚል ለመግለፅ መሞከር ዝም ብሎ ቃላት ማባከን ነው፡፡ ትክክለኛው መጠሪያቸው “ፎርጅድ ኢትዮጵያውያን” ነው-ተመሳስለው የተሰሩ! (“ሃሰተኛ” ኢትዮጵያውያን እንደማለት!) በዜጐቻቸው ሰቆቃ የከበሩ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችም እንዲሁ ከዚህ የተሻለ ስም ሊሰጣቸው አይችልም፡፡ እነሱም “ፎርጅድ ኢትዮጵያውያን” ናቸው (እንደ ፎርጅድ ብር ቁጠሯቸው!) ጥፋት እንጂ ልማት የላቸውም፡፡  
እንዴ … ሰሞኑን በመከራና በችግር ተጠብሰው ከሳኡዲ እየተመለሱ ያሉት ዜጐች ለዚህ ጦስ የተዳረጉት እኮ በእነሱ ነው፡፡ እህቶቹን ሲኦል እየወረወረ በሚያጋብሰው ገንዘብ እንቅልፉን ለጥጦ የሚያድር ሰው ኢትዮጵያዊ ሊባል አይችልም … “ፎርጅድ ኢትዮጵያዊ” እንጂ!
ደሞ አሉላችሁ … እንደ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ያሉ “እንቁ ኢትዮጵያውያን”! የውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ የስደተኛ ዜጐች እንግልት እንዴት እንዳንሰፈሰፋቸው አላያችሁም? በየመድረኩ በመቆርቆር ስሜት የሚያንፀባርቋቸው ንግግሮች በቂ ምስክሮች ናቸው፡፡ “ለካ ኢህአዴግ እንዲህም ያሉ ሰዎች አሉት!” (ደሞ እንዳይሰማኝ!) ከባለስልጣንነታቸው ይልቅ ሰዋዊነታቸው የሚልቅ፤ ከኢህአዴግነታቸው የበለጠ ኢትዮጵያዊነታቸው የሚጐላ ምርጥ የጦቢያ ልጅ! ከዚህ በላይ እንዳላደንቃቸው ግን “አደጋ አለው!” (ኢህአዴግ ፓርቲው እንጂ ግለሰቦች ሲሞሉ አይወድም!) ፓርቲው እኮ የተገነባው በግለሰቦች ስብስብ ነው፡፡ (ረስቶት ይሆናላ?!)

Read 6105 times