Saturday, 30 November 2013 11:08

“የፖለቲካ ፍላጐት የለኝም፤ኖሮኝም አያውቅም”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

(የአዲስ አበባ 22ተኛ ከንቲባ)

መጋቢት በቀድሞው ሐረርጌ ክፍለ ሀገር ኤጀርሳ ጐሮ በተባለ ገጠራማ መንደር ነው የተወለዱት - በ1928 ዓ.ም፡፡

አባታቸው በአርበኝነት ከሞቱ በኋላ፣ መንግሥት የባለውለታ ልጆችን ሰብስቦ ሲያስተምር፣ ሐረር ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ

ትምህርት ቤት ገብተው የመማር ዕድል አገኙ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ፤ በ1945 ዓ.ም ተግባረ ዕድ

ኮሌጅ ገቡ፡፡ ሕንፃ ኮሌጅ ሲከፈት ከመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች አንዱ ሆነው ለአራት ዓመት የሚሰጠውን ትምህርት

የተከታተሉ ሲሆን ለተጨማሪ ትምህርትም ወደ ዩጐዝላቪያ ሄደዋል፡፡ ከትምህርት በኋላ በበርካታ መንግሥታዊ መሥሪያ

ቤቶች አገልግለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ 22ተኛ ከንቲባ ሆነውም ሠርተዋል፡፡ “የፖለቲካ ፍላጐት የለኝም፤ ኖሮኝም

አያውቅም” የሚሉት ኢንጂነር ዘውዴ ተክሉ፤ አሁን የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪዎች ፎረም ሰብሳቢ በመሆን ማህበራዊ

ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ጋዜጠኛ ብርሃኑ ሰሙ ስላሳለፉት ህይወትና የሥራ ዘመን አነጋግሯቸዋል፡፡


ዩጐዝላቪያ የሄዱበትን የትምህርት ዕድል እንዴት አገኙ?
የሕንፃ ኮሌጅ ትምህርታችንን ስናጠናቅቅ የማዕረግ ሁለተኛ ተሸላሚ ነበርኩ፡፡ ለምረቃ እየተዘጋጀን እያለ የትምህርት ቤቱ

አስተዳዳሪ፤ “የውጭ አገር ትምህርት ዕድል መጥቷል፤ መሄድ ትፈልጋለህ ወይ?” ሲሉኝ ተስማማሁ፡፡ ከእኛ ኮሌጅ

ሁለት፤ ከሌሎች ቦታ የተመረጡ አራት ልጆች ተጨምረው ወደ ዩጐዝላቪያ ሄድን፡፡ በወቅቱ ዩጐዝላቪያ የኢትዮጵያ

ትልቋ ወዳጅ አገር ነበረች፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቲቶም ብዙ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ይመጡ ነበር፡፡
በሕንፃ ኮሌጅ የተማርኩት ቢዩልዲንግ ቴክኖሎጂ ቢሆንም ተጨማሪ ትምህርትም ይሰጠን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ፣

ፖለቲካ ሳይንስና የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ተምረናል፡፡ በአገራችን ያለውን የሕንፃ አሰራር ጥበብን ለማየት የተለያዩ

አካባቢዎች እየሄድን እንጐብኝ ነበር፡፡ ጅማ፣ ሐረር፣ ጎንደር፣ ትግራይና ኤርትራ ወደመሳሰሉት ቦታዎች ሄደናል፡፡ እኔ

ለኪነ ህንፃ (አርክቴክቸር) ትምህርት ልዩ ፍላጎት ስለነበረኝ፣ ዩጐዝላቪያ ስሄድ አርክቴትር ፋኩልቲ ነው የገባሁት።

የትምህርት ጊዜ ለእረፍት ሲዘጋ የተለየዩ አገራትን እየዞርኩ እጎበኝ ነበር፡፡ ጀርመንን፣ ኦስትሪያን፣ ቡልጋሪያን፣ ሀንጋሪን

በዚያ አጋጣሚ ነበር ያየኋቸው። በ1961 ዓ.ም ትምህርቴን አጠናቅቄ መጣሁ፡፡
የት የት ሰርተዋል?
ከውጭ እንደመጣሁ ሥራ የጀመርኩት ሥራና ውሃ ሚኒስቴር በሚባል መሥርያ ቤት ነው - በሙያዩ ተመድቤ ምክትል

ዋና አርክቴክት ሆንኩ፡፡ በ1965 ዓ.ም ወደ አስመራ ተቀይሬ ሄድኩ፡፡ አብዮቱ የፈነዳው እዚያ እያለሁ ነበር፡፡ ከአብዮቱ

በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሼ ቀድሞ በነበረኝ ኃላፊነት ተመድቤ መሥራት ቀጠልኩ፡፡ ከዚያ በኋላ በተለያዩ መሥሪያ

ቤቶች እየተመደብኩ ሠርቻለሁ፡፡ የዚያ ዘመን አንዱ ችግር ሙያህም ባይሆን “ተመድበሀል። ገብተህ ሥራ፡፡ ሁላችንም

ተመድበን እየሰራን ነው ያለነው” ይባል ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት በሙያዬ ብቻ ሳይሆን እየተመደብኩም በተለያዩ ቦታዎች

ሠርቻለሁ፡፡ በብሔራዊ ሀብት ልማት ሚኒስቴር በመምሪያ ኃላፊነት፤ በከተማ መሬት አስተዳደር በሥራ አስኪያጅነት፤

በኪራይ ቤቶች አስተዳደር ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅነት፤ በከተማ ፕላን በዋና ኃላፊነት፤ በምርት ዘመቻና ማዕከላዊ

ፕላን በቡድን መሪነት … በተለያዩ ቦታዎችና ኃላፊነቶች ሠርቻለሁ።
በከንቲባነት ሊመረጡ የቻሉት እንዴት ነበር?
ለከተማ ፕላንና አስተዳደር ጥናት ተሰርቶ አዋጅ እንዲወጣ ሲታሰብ የቴክኒክ ሪፖርቱን ያቀረብኩት እኔ ነበርኩ፡፡

ከተሞች እንዴት እንደሚለሙና እንደሚደራጁ ነበር ያጠናነው፡፡ በዚያ አጋጣሚ ለከንቲባነት እንድወዳደር መታሰቡን

ሰምቻለሁ፡፡ የከተማ አስተዳደር ምርጫ ሲደረግ ግባና ተወዳደር ተባልኩ፡፡ በሙያዬ ብሰራ ይሻለኛል ብዬ ተቃውሜ

የነበረ ቢሆንም “ያው ነው፤ ምርጫውን አሸንፈህ የምትገባ ከሆነ እዚያም የምትሰራው ተመሳሳይ ነው” ተባልኩ፡፡
የምርጫው ሂደት ምን ይመስል ነበር?
አዲስ አበባ ከጃንሆይ ጊዜ ጀምሮ በቻርተር ነው የምትተዳደረው፡፡ በዘመኑ የምርጫ ውድድሩ የሚጀምረው ከቀበሌ

ነው፡፡ ያንን ያሸነፉ በከፍተኛ ደረጃ ይወዳደራሉ፡፡ ከከፍተኞቹ ቀጥሎ ዞን ቢኖርም ዞኖቹ ምርጫውን የማስተባባር ሥራ

ነበር የሚሰሩት። በዚህ መልኩ ተወዳድሬ ነው ከንቲባ ለመሆን የቻልኩት፡፡  
የአዲስ አበባ ስንተኛው ከንቲባ ነዎት?
22ተኛው ነኝ፡፡ በዚህ ኃላፊነት ከ1973 እስከ 1981 ዓ.ም ድረስ ነው የሠራሁት፡፡ ሥራ ስንጀምር ቀደም ብሎ ታቅዶ፤

ጠረጴዛ ላይ ካገኘነው ሥራ አንዱ የሌኒን ሐውልት ግንባታን የሚመለከት ነበር፡፡ እቅዱ ሞዴል የተሰራለትና ብዙ ደረጃ

የተጓዘ ነበር፡፡ ሞዴሉ ሁለት ሐውልቶችን ይዟል፡፡ አንዱ የሌኒን ሐውልት ሲሆን ሁለተኛው 30 ሜትር ርዝመት

የሚኖረውና ከሌኒን ሐውልት በስተጀርባ የሚቆም የአክሱም ሐውልት አምሳያ እንደሚኖር ያሳያል፡፡ ለዚህ ሥራ ደግሞ

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት 30 የተለያዩ አገራት መሪዎች የተከሏቸው ባህር ዛፎች ሙሉ ለሙሉ ይመነጠራሉ

ይላል፡፡ በሐውልቶቹ ዙሪያ ፏፏቴ እንደሚኖርም ተመልክቷል፡፡
እኛ ሥራ ስንጀምር በእቅዱና በሞዴሉ ዙሪያ አስተያየችሁን አቅርቡ ተባልን፡፡ የአክሱም ሐውልት የአርክቴክት ሚስጢሩ

ያልታወቀ፤ የኢትዮጵያና የዓለምም ትልቅ ቅርስ ነው፡፡ ሌኒን የወዛደር መሪ ነው፡፡ ሁለቱን ነገሮች የሚያገናኝና

የሚያመሳስል ምንም ነገር የለም፡፡ ሐውልቶችን ማዳቀልም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት የሌለውና የተከለከለ ነው።

ከዚህም ባሻገር የ30 አገራት መሪዎችን ሥም የያዘ ዛፍ አጥፍቶ፣ ሌላ ታሪክ መሥራት አሳማኝ አይደለም ብለን

አስተያየታችንን አቀረብን፡፡
ሪፖርቱን ያቀረብነው ለከተማው ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ነበር፡፡ አስተያየታችንን ለሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም

እንድናቀርብ ታዘዝን፡፡ ቀጠሮ ተይዞልን ሄደን ሀሳባችንን ስንነግራቸው “እነዚህ ሰዎች የሚሉት ትክክል ነው፡፡ እኛ

በጊዜው እንደዚህ አላሰብንበትም ነበር፡፡ የሶቪየት መሪ ሲመጡ ለሌኒን ሐውልት መሥሪያ ቦታ አዘጋጁ ሲባል ነው

ቦታው ተመርጦ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት …” ስላሉ ሐውልቶቹን ማዳቀሉ ቀርቶ፤ ታሪካዊ ዛፎች ሳይቆረጡ

የሌኒን ሐውልት ተሰራ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ 100ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓልም የተከበረው በእናንተ የስልጣን ዘመን ነው፡፡ ዝግጅቱ ምን ይመስል

ነበር?  
የከተማዋን 100ኛ ዓመት የማክበር እቅድም እኛ ከመምጣታችን በፊት የታቀደ ነበር፡፡ ሊከበር የታሰበው ግን በ1976

ዓ.ም የነበረ ቢሆንም እኛ ከመጣን በኋላ ተክለፃዲቅ መኩሪያን የመሳሰሉ የታሪክ ምሁራንን በመጠየቅ ማስተካከያ

ተደርጐ በዓሉን በ1979 ዓ.ም አክብረናል፡፡ አዲስ አበባ ከአፄ ምኒልክና ከእቴጌ ጣይቱ ጋር የተያያዘው ታሪኳ የቅርብ

ቢሆንም ከአብርሐ አጽብሃና ከንጉሥ ዳዊት ጋር የሚያያዝ ጥንታዊ ታሪክ እንዳላትም ይታወቃል፡፡ ከተማዋ

የተመሠረተችበትን 25ተኛ፣ 50ኛና 75ተኛ ኢዮቤልዩ ስለማክበሯ የሚገልጽ መረጃ አላገኘንም ነበር፡፡ 100ኛው ኢዮቤልዮ

የመጀመሪያ ነበር፡፡
ለበዓሉ ምን አቀዳችሁ? ምን ተሳካ? ያልተሳካውስ?
ለበዓሉ ብሔራዊ ኮሚቴ እንዲዋቀር ስንጠይቅ፣ ከእናንተ ውጭ ማንም አይመጣም፤ ሥራችሁን ቀጥሉ ተባልን፡፡ የአዲስ

አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራው ባለቤት ሆኖ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትንና ባለሙያዎችን እያሳተፍን መሥራት

ጀመርን፡፡ እንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያንን ስንጐበኝ በዕቃ ማስቀመጫ ክፍል ውስጥ ብዙ ታሪካዊ ቅርሶችን ስላየን፣

ከባህል ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንጦጦ ላይ ሙዚየም አሰርተን ቅርሶቹ እዚያ እንዲቀመጡ አደረግን፡፡
መስቀል አደባባይ በራስ ብሩ ቤት ለተመሳሳይ አገልግሎት የሚውል ሙዚየም አደራጀን፡፡ ከቤተመንግሥት በውሰት

ያመጣናቸው ቅርሶችንና ከግለሰቦች የተበረከቱልንን ይዘን ነው ሙዚየሙን ያቋቋምነው፡፡ ከሽሮ ሜዳ እስከ እንጦጦ

ያለውን መንገድ በአፋልት ያሰራነው የመቶኛ ዓመቱን በዓል ምክንያት በማድረግ ነው፡፡ ከራጉኤል እስከ ጐጃም በር

ፍተሻ ጣቢያ ያለውን ጥርጊያ መንገድንም አስፋልት ለማድረግ አቅደን የነበረ ቢሆንም በገንዘብ እጥረት ምክንያት

አልተሳካም፡፡
ሌላው ያልተሳካልን እቅድ እንጦጦ ራጉኤል ቤተክርስቲያን አጠገብ፣ አዲስ አበባንና በዙሪያዋ ያሉ አካባቢዎችን

የሚያሳይ ማማ ሬስቶራንት መስራት አለመቻላችን ነው፡፡ 50 ሜትር ከፍታ ያለውን ሕንፃ ለመሥራት ከማሰብም በላይ

የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦለት ነበር፡፡ ቦታውን የመረጥንበት ምክንያት አፄ ምኒልክ ከባለስልጣኖቻቸውና ከአገር

ሽማግሌዎች ጋር ተቀምጠው የሚመክሩበት መስክ መሆኑን ስለተነገረን ነበር፡፡
ቦታው ላይ ለሕፃናት መዝናኛ አምባ የመሥራት ዕቅድም ነበረን፡፡ ይህም አልተሳካም፡፡ ከተሳኩልን ሥራዎች ሌላኛው

ለከተማዋ ስድስት አዳዲስ ፓርኮችን አዘጋጅተን ማስመረቅ መቻላችን ነው፡፡ ሐምሌ 19፣ ፒኮክ፣ የካ ማካኤል፣ መርካቶ

ራጉኤል፣ ጐላ ሚካኤል መናፈሻ ቦታዎች የዚያ ዘመን ውጤት ናቸው፡፡ አራቱ የመናፈ ቦታዎች አሁንም አገልግሎት

በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአዲስ አበባ ታሪክ ዙሪያ ምሁራን የሚወያዩበት ሲምፖዚየምም ተካሂዷል፡፡ ታስበው

ያልተሳኩ ነገሮች ቢኖሩም የከተማዋ 100ኛ ዓመት ኢዮቤልዮ በደመቀና በተሳካ ሁኔታ ነበር የተከበረው፡፡
በ1981 ዓ.ም የከንቲባነት ዘመንዎ ሲያበቃ የት ገቡ?
ቀድሞ ወደነበርኩበት ማዕከላዊ ፕላን ተመልሼ፣ በኮሚሽነርነት የአንድ መምሪያ ኃላፊ ሆኜ መሥራት ቀጠልኩ፡፡ እዚያ

እያለሁ ነው የስርዓት ለውጥ የተካሄደው፡፡ ከደርግ ባለስልጣናት  አንዱ ስለነበርኩ ‘ትፈልጋላችሁ’ ተብለው ከታሰሩት

አንዱ ሆኜ በሰንደፋ ፖሊስ ማሰልጠኛ ለተወሰነ ጊዜ ታስሬያለሁ። በኋላ በነፃ ተሰናበትኩ፡፡ ከዚያ በኋላ በግልም በጋራም

የራሴን ሥራ ሞክሬያለሁ፡፡ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ ያስደስተኛል፡፡
አሁን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ፎረም ሰብሳቢ ነዎት፡፡ እንዴት ወደዚህ ኃላፊነት መምጣት ቻሉ?
መንግሥት ወይም የአገር መሪ የሚኮነው በሦስት መንገድ ነው፡፡ አንዱ ከንጉሳዊያን ቤተሰብ መወለድ ነው፡፡ ሌላኛው

በምርጫ ተወዳድሮ መመረጥ ሲሆን ሦስተኛው አንዱ ሌላውን ታግሎ በማሸነፍ ነው፡፡ ኢሕአዴግም ከእነዚህ በአንዱ

መንግሥት ሆኗል፡፡ እኔ አንድ መሠረታዊ የሆነ የግል እምነት አለኝ፡፡ የአካባቢዬ የስልጣን አካል ሲጠራኝ መሄድ አለብኝ

ብዬ አምናለሁ፡፡ ቀበሌ ማለት መንግሥት ነው፡፡ ከቀበሌው ጋር ያልተገናኘ ከላይኛው አካል ጋር እንዴት ሊገናኝ

ይችላል? በዚህ እምነትና አቋሜ ምክንያት በተጠራሁባቸው መድረኮች እየተገኘሁ የተሰማኝን አስተያየት አቀርባለሁ፡፡ ይህ

ደግሞ የምጋበዝባቸውን መድረኮች ቁጥር አበራከተው፡፡
መሠረታዊ የሆነው የሕዝብ አደረጃጀት የሚፈጠረው በጉርብትና ነው፡፡ በጉርብትና ለመገናኘት ደግሞ መሠረታዊ የሆነ

የጋራ ነገር ያስፈልጋል፡፡ መሠረታዊው ነገር በቦታ፣ በጊዜና በአገልግሎት ይገለፃል፡፡ እያንዳንዳችን በየዕለቱ ሦስት

ተግባራትን በተደጋጋሚ እንፈጽማለን፡፡ 8 ሰዓት በሥራ፣ 8 ሰዓት በእንቅልፍና 8 ሰዓት ደግሞ በእረፍት ወይም

በመዝናናት እናሳልፋለን፡፡
በአንድ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች እርስ በእርስ ካልተገናኙ፣ ካልተወያዩና በጋራ ካልተዝናኑ ከተማ ነው አይባልም፡፡

የከተማ ሕዝብ አደረጃጀት ፍልስፍና መሠረቱም አብሮነትን የሚያጐላ ነው። ይህንን አመለካከትና ፍልስፍና

ስለማምንበት ባለፉት 12 ዓመታት ለሊዝ ፖሊስ የማሻሻያ ውይይት ሲደረግ፣ የአዲስ አበባ ተሐድሶ ኮንፈረንስ ሲጠራና

በመሳሰሉት መድረኮች እየተጋበዝኩ ተሳትፌያለሁ፡፡ በእነዚህ መድረኮች ተገኝቼ ሃሳቤን መግለጽ በመቻሌ ደስተኛ ነኝ፡፡
ይህንን ተሳትፎ የማደርገው በጡረታ ዕድሜዬ ነው፡፡ ልማት የጋራ ነው፡፡ ብንወድም ብንጠላም እየሰራን ነው

ልዩነታችንን ወደ አንድ ለማምጣት መጣር ያለብን፡፡ ሥራና ልማትን ትቶ መሟገትና መጨቃጨቁ የሚያስገኘው ጥቅም

የለም፡፡ በአሰራሮች ላይ ችግሮች እንዳሉ አያለሁ፡፡ ለምሳሌ ለልማት እንዲነሱ የሚደረጉ ሰዎች የሚከፈለው ካሳ

የገበያውን ዋጋ መሠረት ያደረገ አለመሆኑ ትክክል አይደለም፡፡
የከተማ መሬት በመንግሥት መያዙ ብዙ ጥቅም እንዳለው አምናለሁ፡፡ በደርግ ዘመንም መሬት የመንግስት ነበር፡፡

በከተሞች መሬት በነፃ እናድል ነበር፡፡ ኢሕአዴግ በሊዝ አለ፡፡ ይህ ደግሞ ገንዘብ በማስገኘት ብቻ ሳይሆን መንግሥት

ለከተማው ፕላን መሥራት እንዲችልም አድርጎታል፡፡ ነገር ግን ለሕዝብ አገልግሎት፡- ትምህርት ቤት፣ ገበያ፣ መዝናኛ፣

ጤና ጣቢያ ሊሰራባቸው የተከለሉ ቦታዎች ላይ ማስተር ፕላኑ ባስቀመጠው መሠረት ለምን እንዳልተሰሩ

የሚመለከታቸው አካላትን በሕግ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ለምን እንዳልተሰሩ ይህን መሰል ሀሳብና አስተያየቼን በየመድረኩ

እየተገኘሁ መግለፄ በሂደት የከተማ ነዋሪዎች ፎረም ሰብሳቢ ሆኜ እንድመረጥ ምክንያት ሆኗል፡፡
ተቃውሞ አልገጠመዎትም?
ከ1997 እስከ 1999 ዓ.ም መንግሥት ከአዲስ አበባ ሕዝብ ጋር ቅሬታ ላይ በነበረበት ጊዜ እንዴት አብረህ ትሰራለህ?

የሚሉኝ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ይህንን መሰል ጥያቄ የሚያቀርብልኝ የለም፡፡ የሚጠይቀኝ ከመጣም ‘አገሬ አይደለም ወይ?

ለምንድነው በልማት ሥራ የማልሳተፈው?’ ብዬ መልሼ መጠየቄ አይቀርም፡፡ ይህንን ተሳትፎ በነፃና በፍላጐቴ ነው

የማከናውነው፡፡ የፖለቲካ ፍላጐት የለኝም፤ ኖርኝም አያውቅም፡፡
ቤተሰባዊ ሕይወትዎ ምን ይመስላል?
የማከብራት ባለቤትና ሦስት ሴት ልጆች አሉኝ፡፡ ቤተሰቤ የተባረከ ነው፡፡ እኔም ሰላምና እርጋታ ያለኝ ሰው ነኝ፡፡

በደስታና በሰላም ነው የምንኖረው፡፡  


Read 4348 times