Saturday, 30 November 2013 10:41

የስልሳዎቹ ባለሥልጣናት አገዳደል

Written by  ሰሎሞን አበበ ቸኮል Saache43@yahoo.com/solouion.abebe395@facebbok.com
Rate this item
(3 votes)

ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም ነበር ያ የፍርሃት ግብታዊ እርምጃ የተወሰደው፡፡
በዚያች እለት ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ 13 ሚኒስትሮች (ምክትሎችን ጨምሮ)፣ 1 የዘውድ ም/ቤት ፕሬዚዳንት፤

ዘጠኝ የጠቅላይ ግዛት እንደራሴዎች፤ 2 የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት፣ 11 የተለያዩ የጦር ኃይሎች እና ፖሊስ

አዛዦች፣ 3 የአውራጃ አስተዳዳሪዎች፣ 7 በልዩ ልዩ ኃላፊነት ላይ የነበሩ (የኢት/ቀ መስቀል ኃላፊውን ጨምሮ) በድምሩ

52 የንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ባለሥልጣኖች በዚያች ዕለት ተረሸኑ፡፡
ከነዚሁ ጋር ሌ/ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም (የደርግ ሊ/መንበሩን) ጨምሮ የደርግ እና የንዑስ ደርግ አባላትም፣

በድምራቸው 8 የሆኑ፣ ከ፻ አለቃ እስከ ሻምበል የሚደርሱ መኮንኖች፣ አንድ ወታደር እና አንድ ሲኒየር ቴክኒሺያን

ተገደሉ፡፡ በድምራቸው 60ዎቹ እየተባሉ የሚጠሩት የደርግና የሌሎቹ ግድያ፣ የዚያ ትውልድ አብዮተኞች ጭካኔ

መጀመሪያ የሆነው አረመኔአዊ ተግባር ተፈፀመ - የዛሬ 39 አመት፡፡
ባለሥልጣናቱን የመግደሉን ሐሳብ ቀድሞውኑ የወጡኑት  ወደ አራት የሚያህሉ የደርግ አባላት ነበሩ። ከእነዚህም

መካከል የቻሉትን ያህል ተታኩሰውና ጥለው ለመሞት የበቁት ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም አንዱ ነበሩ፡፡ ሌሎቹ

ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ ኮማንደር ለማ ጉተማ እና ዶክተር በረከተ አብ ሃብተሥላሴ ነበሩ፡፡
ይህን የመግደል ምክር ሻለቃ መንግሥቱ ወደ ደርግ አባላት አቀረቡት፡፡ በደርግ አባላት ስብሰባ ላይ ሻለቃ ተስፋዬ

ገ/ኪዳን፣ ሻለቃ ብርሃኑ ባይህ፣ ሻለቃ አዲስ ተድላ እና ሌሎች ጥቂት የደርግ አባላት ተቃወሙት፡፡
ከፍ/ቤት ውጭ የሚደረግ ውሳኔ የመለዮ ለባሹን ድጋፍ ያሳጣናል በማለት ተከራከሩበት፡፡
ነገር ግን የአማን እና የመንግሥቱ ኃይለማርያም የሥልጣን ሽኩቻ የባለሥልጣናቱን ዕድሜ ቀጨው። አማን ሚካኤል

አንዶም ሲገደሉ ለርሳቸው ሞት ማጀቢያ በማድረግ የዚያኑ ዕለት እንዲፈፀም ተደረገ።
በእርግጥም  ጉዳዩ በአግባቡ ሊዳኝ መርማሪ ኮሚሽን የተባለ ኮሚቴ ተቋቁሞ መመልከት ጀምሮ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር

መስፍን ወ/ማርያም፣ ዶክተር በረከተአብ ኃብተሥላሴ፣ ዶክተር ደሃድ አበቋያ፣ ዶ/ር መኮንን ወ/አማኑኤል፣ አቶ አሰፋ

ሊበን፣ አቶ ዘነበ ኃይሌ፣ አቶ ሁሴን እስማኤል፣ አቶ ጌታቸው ደስታ፣ ኮማንደር ለማ ጉተማ፣ ኮ/ል ነጋሽ ወ/ማካኤል፣

ሻለቃ ዓለማየሁ ሥዩም፣ ሻለቃ አድማሱ ነጋሽ፣ ሻምበል ምትኩ ደምሴ፣ ሻምበል ሰላም ህሩይ፣ እና አቶ መዋዕለ መብራቴ

የነበሩበት ኮሚቴ ነበር በአዋጅ የተቋቋመው። ከኮማንደር ለማ ጉተማ ጀምሮ ያሉት የደርግ አባላት ነበሩ፡፡ ከዚህም ሌላ

ይህንኑ ጉዳይ የሚመለከት የወረዳና የጠ/ፍ/ቤቶች ልዩ የጦር ፍ/ቤት ተቋቁሞ ነበር፡፡ የጦር ፍ/ቤቱ ዳኞች በመሆን

የተሾሙት ኮ/ል ንጉሤ ወ/ሚካኤል፣ ኮማንደር ተስፋዬ ብርሃኑ፣ ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ ሻለቃ ይልቃል ክንዴ፣

ሻምበል ሰሙ ንጉሥ ሥዩም፣ ሻምበል ቀማቸው ገብሬ ሲኾኑ ዐቃቤ ሕግ በመኾን ደግሞ ኮ/ል ጐሹ ወልዴ ተሰየሙ፡፡

በኋላ ግን በሻለቃ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ፊርማ በአንድ ደብዳቤ ችሎቱ በኢኮኖሚ አሻጥር ላይ ብቻ እንዲያተኩር የሚል

ትእዛዝ ወጣ። መርማሪ ኮሚሽኑም የያዘው ምርመራ እንዲቀዘቅዝ ተደረገ፡፡
ደርግ የንጉሠ ነገሥቱን ባለሥልጣናት ከሐምሌ 1966 ጀምሮ ቀስ በቀስ እየለቀመ በማስገባት ንጉሡን ብቻቸውን

አስቀራቸው፡፡ በመጨረሻ በመስከረም 1967 እሳቸውንም ወደ ማረፊያቸው አወረዳቸው። ከዚያ ጊዜያዊ ወታደራዊ

መንግሥትን ዐወጀ፡፡ የሚያስገርመው በዚህ ዓዋጅ ዐልጋ ወራሹ ካልሆኑም የንጉሡ የልጅ ልጅ ከላይ ንጉሥ ኾነው

እንደሚሾሙም ተገልፆ ነበር፡፡
የመንግሥቱ ኃይለማርያምና የአማን ሚካኤል አንዶም ቅራኔ በዚህ ዓዋጅ ተጀመረ፡፡ ጄኔራሉ ከሕዝብም እንዲካተት

ፈላጊ ነበሩ፡፡ በእነሚካኤል እምሩ ተጠንቶ የቀረበውም የመድኅን መንግሥትም ይህን ያካትት ነበር፡፡
አማን ሚካኤል አንዶም በኤርትራ ጠቅላይ ግዛት የተወለዱ፣ ጣሊያን የኢትዮጵያን ግዛት አስፍቶ በመያዝ የቅኝ ገዢ

መንግሥትን ባቆመ ጊዜ ከሀገር ተሰድደው በሱዳን ስለ ኢትዮጵያ ነፃነት የታገሉ ኢትዮጵያዊ ነበሩ። ንጉሠ ነገሥቱ ከሱዳን

በኦሜድላ ሀገራቸው በገቡ ጊዜ አብረው ከነበሩ ወታደሮች አንዱ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አባል በመኾን

እስከ ከፍተኛ መኮንንነት ደረጃ በመድረስ፣ በተለይ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ባደረገችው ውጊያ ጀግንነታቻውን

ያስመሰከሩ እና የተከበሩ ጄኔራል ነበሩ፡፡ ደርግ ሲነሳ በጄኔራል ማዕረግ በወታደሩና በባለሥልጣናቱ ዘንድ የታወቁና

የተከበሩ የጦር መሪ ሆኑ፡፡ በአገርና በውጭ መኮንንነት ከፍተኛ ትምሕርቶችን የተማሩ ሲኾኑ በመከላከያ ሠራዊት

በተለያዩ ኃላፊነት ተመድበው አገልግለዋል፡፡ በአመራራቸው እና በውትድርናቸው የተደነቁም ነበሩ፡፡ የቃኘው ሻለቃ

የኮሪያ ዘማቹ አዛዥ በምድር ጦርም በተለያዩ የአዛዥነት ቦታ ተመድበው ሠርተዋል፡፡
መስከረም 2 ቀን1967 የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ሀገሪቱን እንደሚመራ፣ ሲታወጅ ልዑል አልጋ ወራሽ፣ እሳቸውም

ካልፈለጉም ልጃቸው ልዑል ዘርዓ ያዕቆብ እንደሚነግሡ ቢገለጽም፣ ንጉሠ ነገሥቱን ከሥልጣን ካወረዱ በኋላ ሀገሪቱን

እንዲመሩ የተደረጉት እኚኹ ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም ነበሩ፡፡
ጄኔራሉ ግን የደርግ አባላቱ በተለይም ዋነኛው ተዋናይ መንግሥቱ ኃይለማርያምን አልወደዷቸውም። ከደርግ አባላት

መካከል አጥናፉ አባተ፣ ብርሃኑ ባይህ፣ ሲሳይ ሃብቴ፣ ሞገስ ወልደሚካኤል፣ ዓለማየሁ ኃይሌና በዕውቀቱ ካሣ የተባሉት

የራሳቸው ቡድን በመፍጠር፣ ከደርግ ውጭ ተመካክረው የወሰኑትን የመንግሥቱ ኃይለማርያምን አንደበተ ርቱዕነት

በመጠቀም ያስፈጽሙ ነበር፡፡
ከጄኔራል አማን ሚካኤል ጋርም የሐሳብ ልዩነት መጣ፡፡ “መንግሥቱ ኃ/ማርያም ጄኔራሉ ናቁን የሚል መንፈስ ያደረበት

ይመስለኛል፣” በማለት ጀኔራል ውብሸት ደሴ ይናገራሉ፡፡ ጄኔራል ውብሸት በጊዜው ከኤርትራው ኃይል ተወክለው

የደርግ አባል የነበሩትና ከአማን ሚካኤል አንዶም ጋር ወደ ኤርትራ በመጓዝ የነበረውን የእርስበርስ ጦርነት ሁኔታ

እንዲያጠኑ፣ ሕዝቡንና ጦሩንም አማክረው መፍትሔውን እንዲያቀርቡ ተልከው ከነበሩት አንዱ ናቸው፡፡ (ምስክርነት፣

ተስፋዬ ርስቴ፣ ግንቦት 2001፣ ገጽ 52)
የኤርትራው ጉብኝት የተደረገው በጥቅምት ወር 1967 ዓ.ም ነበር፡፡ በዚያ የሥራ ጉብኝት ጄኔራል አማን አንዶም

ሚካኤል “ሕዝቡን በየሰፈሩ፣ ጦሩን በየጦር መደቡ ገብተው አነጋግረዋል፡፡” (ዝ.ከ. ገጽ 52)
የእርስ በርስ ጦርነቱ በውይይት ተፈትቶ ሰላም እንዲወርድ መንገድ መጥረግ እንደጀመሩ የመሰከሩት ጄ/ል ውብሸት ደሴ፤

በሥራ ጉብኝቱ ፍጻሜ ላይ ሕዝቡን በአሥመራ ሣባ ስታዲየም ሰብስበው በትግርኛ፣ በአማርኛና በዐረብኛ የሰላም

መልእክተኛ መሆናቸውን እንደገለጹም ጠቅሰዋል። “የሕዝቡን ስሜት የሚፈነቅል ንግግር” ብለው የጠቀሱላቸው እንዲህ

ይላል:- “ሰላም ይዤላችሁ መጥቻለሁ፤ እኔ የሰላም ምልክት፣ ለሰላም የቆምኩ ነኝ፡፡ አማን ማለት ሰላም ማለት ነው፡፡”
አማን ሚካኤል አንዶም በኤርትራ ጉዳይ ላይ ፌዴሬሽኑ መመለስ እንዳለበት ያምኑ ነበር፡፡ አማን በኤርትራ ጠ/ግዛት

ነዋሪ ዘንድ የተወደዱ ሆኑ፡፡ በእነመንግሥቱ ግን ተጠመዱ፡፡
ከጥቅምቱ የአማን ኤርትራን መጐብኘት ተከትሎ፣ ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ ወደ ኤርትራ በመሔድ የተለየ ዘገባ ይዘው

መጡ፡፡ “በአስቸኳይ ጦር ካልተላከ ኤርትራ አለቀላት፣” አሉ፡፡ (ዝ.ከ.53) የአማን “በውይይት ሰላም ይውረድ”፣ ማለት

ቀርቶ የተስፋዬ ወ/ሥላሴ “ጦር ይላክ” በደርጉ ተወሰነ። ፊት ለፊት የታዩ ልዩነቶች አስቀድሞም ነበሩ። ልዩነቱ በዚህ

ላይም ታየ፡፡ አማን ተጠረጠሩ፡፡ ጦሩ በደርግ ላይ እንዲነሳ ቅስቀሳ ጀመሩ ተባሉ፡፡ አማን በኢትዮጵያ አንድነት ላይ

የመጠርጠራቸው ነገር አበሳጫቸው፡፡ ጦር ወደ ሰሜን እንዲላክ ተወስኖ የትኛው ጦር ይሒድ በሚለው ላይም አማን

ሚካኤል አንዶም የተለየ አቋም ያዙ፡፡ ለዚህ ውሳኔ የተደረገውን ስብሰባም ጥለው ወጡ፡፡
ይኽ ኹሉ እየተጨማመረ በሥልጣን ፈላጊዎቹ የደርግ አባላት ዘንድ የአማን ሚካኤል አንዶም ጉዳይ እያበቃቃ መጣ፡፡

እርሳቸውም በግልጽ ይወርፉ ጀመሩ፡፡ “በመሀይማን ጫጫታ አገር አይመራም፣” ይሉ ነበር፡፡
ረቡዕ፣ ኅዳር 7 ቀን 1967 ላይ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጄኔራሉ የማያውቁት ጉብኝት አደረጉ፡፡ የጦር ሠራዊት አባላትን

ሰብስበው ስለ “ኢትዮጵያ ትቅደም” መግለጫ አደረጉ፡፡ ጎፋ ሰፈር በነበረው የታንከኛ ክፍል በመገኘት ይኽን መግለጫ

መስጠታቸው ጄኔራሉን ሥልጣናቸው የይስሙላ ኾኖ እንዲሰማቸው ግድ አለ። “ካልተፈለግሁ፣ ለምልክትነት

አልቀመጥም” አሉ፡፡
በዚኹ ከሥራ ገበታቸው በመቅረት ከቤታቸው ይውሉ ጀመሩ፡፡ በዚህ ርምጃቸው ሥጋት የገባው ደርግ፤ ወደ ጀኔራሉ

መልእክተኞችን መላክ ጀመረ። ይህን ያደረጉት ያኔ ሻለቃ የነበሩት መንግሥቱ ኃ/ማርያም ነበሩ፡፡ በመጀመሪያ ጀኔራል

ግዛው በላይነህና ሻ/ብርሃኑ ባይህን መሪ ያደረገ ልዑክ፣ ቀጥሎ የመረጃ ቢሮ ኃላፊው የነበሩበት ቡድን፣ በኹለቱ ሳይሳካ

ሲቀር ራሳቸው ሻ/መንግሥቱ የሚመሩት ቡድን ቤታቸው ድረስ ሔዶ አነጋገሯቸው፡፡
ከመጨረሻው ቡድን ጋር ስምምነት ላይ ተደርሶ ወደ ኃላፊነታቸው ለመመለስ ቻሉ፡፡ በስምምነቱ ውስጥ ኅዳር 7 ቀን 67

መንግሥቱ ያለ ጄኔራሉ ዕውቅና ያደረጉት ጉብኝት በመገናኛ ብዙኃን እንዳይገለጽም ተብሎ ነበር፡፡ የኾነው ግን

በተቃራኒው ነበር፡፡ መንግሥቱ ያደረጉት ጉብኝትና የሰጡት መግለጫ እሑድ ዕለት ኅዳር 11 ቀን 1967 በጦር ኃይሎች

ፕሮግራም ተላለፈ፡፡
ጄኔራሉ በዕለቱ ዘውዲቱ ሆስፒታል ውስጥ ለሚያደርጉት ጉብኝት ተነሥተው ሣለ ፣ በሬዲዮ ያ ጉብኝት ሲተላለፍ ሰሙ፡፡

ጉብኝቱን ሰርዘው ተመለሱ፡፡ ከሥራ ገበታቸው በመቅረት እንደገና ቤት መዋል ጀመሩ፡፡ እቤታቸው ኾነው ወደ ተለያዩ

ጦር አዛዦችና መኮንኖች እየደዋወሉ እንዲነሱ ማስተባበሩን ቀጠሉበት፡፡ ይኽ የስልክ ቅስቀሳቸው ግን በደርግ ተጠልፎ

አንድ በአንድ ይያዝ ነበር። በተለይ ከጄኔራል ግዛው በላይነህ ጋር ያደረጉት የስልክ ምልልስ በደርግ ዘንድ ፍርሃትና

ሥጋት ከመፍጠሩም በተጨማሪ የራሳቸው የጄኔራሉን ሕይወትም እንዲቀጭ አደረገ፡፡
“… ግዛው አገራችን በእነዚህ ቂጣቸውን ባልጠረጉ ጨምላቆች ተመርታ ወደ ጥፋት መሔድ የለባትም፡፡ አንተም

ሠራዊትህን አዘጋጅና ይልቅ ተነሣ” ማለታቸው ምስክርነት በተባለው መጽሐፍ ተጠቅሷል (ገጽ 56)
ይህ ቃላቸው ተጠልፎ እንዳለ ለሻለቃ መንግሥቱ ደረሰ፡፡ ሻለቃው ሦስተኛውን ክፍለ ጦር ጠሩ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ

ዙሪያ የነበሩ የፖሊስ ሠራዊትና ልዩ ልዩ ክፍሎችን፣ የንዑስ ደርግ አባላትን ኹሉ ወደ ደርግ ጽ/ቤት በአስቸኳይ ጠሩ፡፡
እንዲህ እያደረጉ ሳለም ጄኔራሉን እንዲይዙአቸው ከክብር ዘብ ሠራዊት 6ኛ ብርጌድ ለተውጣጣ ወታደሮች ትእዛዝ ደርሶ

ነበር፡፡ “እንዴት ብለን በአማን ላይ መሣሪያ እናነሳለን?” አሉና ትዕዛዙን ሳይቀበሉ ቀሩ፡፡ ወደ ሌሎች መለዮ ለባሾች

ትዕዛዙ ዞረ፡፡ እነዚያም እንደዚያው ብለው ሳይቀበሉት ቀሩ። ይህ የጄኔራሉ መወደድና መከበር፣ ይህን ያህል የኾኑት

ጄኔራልም ከደርግ ማፈንገጥ የደርጉን ውድቀት ያመላከተ ኾኖ እስከ መታየት ደረሰ፡፡ ከዚህም የተነሣ በርሳቸው ላይ

የጭካኔ እርምጃ በአፋጣኝና በጠነከረ ኹኔታ እንዲፈጸም እነ መንግሥቱን አሳሰበ፡፡
ፍርሃቱ ግን ጄኔራሉን ብቻ ሳይኾን፣ ታሥረው የነበሩትን የዘውድ አገዛዙ አባላትንና ሌሎችንም ጭምር የሚያኝክበት

ጥርስ እስከማብቀል ደረሰ፡፡ ደርግ መውደቁ ካልቀረ ይጠሏቸው የነበሩትን የንጉሠ ነገሥቱን ባለሥልጣናት ረሚም

አድርጐ እንዲወድቅም ነበር የታሰበው፡፡
መንግሥቱ ኃ/ማርያም ከደብረ ብርሃን አካባቢ ያመጧቸው በዳንኤል የሚመራው ቅልብ ኃይል ወደአማን ተልኮ በተኩስ

ልውውጥ ጄዴኔራሉ ሞቱ፡፡
ይህን የጄኔራሉን ጉዳይ ለመወሰን መንግሥቱ ስብሰባ እየመሩ ሣለ፣ ዳንኤል መጥቶ የጄኔራሉን መገደል ሲነግራቸው፣

“እንግዲህ እምቢ ካሉ በኃይል እጃቸውን እንዲሰጡ ይደረግ” ሲሉ ጮክ ብለው ተሰብሳቢው እንዲሰማው አድርገው

ተናገሩ፡፡
ከዚህ በኋላ በንጉሠ ነገሥቱ ባለሥልጣናት ላይ የግድያ ውሳኔ በድምጽ እንዲወሰን ተደረገ፡፡ “እከሌ” ተብሎ ይጠራል፡፡

“ይገደል” ተብሎ እጅ ይወጣል። ያኔ ማንም “አይገደል” ለማለት አይችልም፡፡ ይገደሉ የተባሉት ከ52ቱ በላይ ነበሩ፡፡

እንደነልዕልት ተናኘወርቅ፣ እንደነንቡረዕድ ኤርምያስ ከበደ፣ እንደነሊቀ ሥልጣናት ኃብተማርያም ያሉ ሌሎችም

ነበሩበት፡፡ የተገደሉት ግን 52ቱ ብቻ ነበሩ፡፡ ቀሪዎቹ 8ቱ የራሱ የደርግና የንዑስ ደርግ አባላት ነበሩ፡፡  

Read 7174 times