Monday, 25 November 2013 11:19

አትጩኹ! ጩኸት ለማንም አይበጅም

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

በመላው ዓለም የመስማት ችግር ያለባችሁ ሰዎች ምን ያህል እንደሆኑ ያውቃሉ? እጅግ በርካታ ቁጥር እንደምትጠሩ እገምታለሁ፡፡ ሚሊዮን ያህል ናቸው። በአገራችን፣ ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ በትክክል ባይታወቅም በአሜሪካ ግን 50 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የመስማት ችግር አለባቸው፡፡
ከእነዚህ ሰዎች ጋር መግባባት በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ Shouting won’t help የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ ካትሪን ቡቶን ትናገራለች፡፡ ምክንያቱንም ስታስረዳ “መጮህ (shouting) ምንም አይጠቅምም፡፡ ለምን ብትሉ? እኔና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የመስማት ችግር ያለባቸው ሰዎች ብትጮኹም አንሰማችሁም” በማለት መስማት ከተሳናቸው ሰዎች ጋር በምናወራበት ወቅት ጮሆ መናገር ጥቅም እንደሌለው አስረድታለች፡፡
ካትሪን ቡቶን፣ የግራ ጆሮዋ መስማት ያቆመው ወጣት ሳለች በ30 ዓመቷ ሲሆን የቀኙ ደግሞ 50 ዓመት ሲሞላት እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ከሰዎች ጋር ለመግባባት ከፍተኛ ችግር ሆኖባት ነበር፡፡ ነገር ግን የተፈጠረውን ችግር አምና ከመቀበል በስተቀር አማራጭ አልነበራትም፡፡ በዚህ የተነሳ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከሥራ ባልደረባ፣ ጋር እንዴት መግባባት እንደሚችሉ ጥናት ማካሄድ ጀምራ ዘዴውንም አገኘችና መጽሐፍ አሳተመች፡፡ ከጓደኞቿና ከቤተሰቦቿ ጋር ሲወያዩ እንዴት ማውራት እንዳለባቸው፣ እንዴት እንደምትረዳቸው ካስተማረቻቸው በኋላ፣ ሕይወት (ነገሮች) ቀላል እንደሆኑላት ትናገራለች፡፡ ለመሆኑ መስማት ከተሳናቸው ሰዎች ጋር ስንወያይ መግባባት የምንችልባቸው ነጥቦች ምንድናቸው? Reader’s digest ከቡቶን መጽሐፍ ውስጥ ቀንጭቦ የጠቀሳቸውን አምስት ዘዴዎች እነሆ፡፡
አትጩኹ - የመስማት ችግር ካለበት ሰው ጋር ሲወያዩ ወይም ሲጫወቱ፣ እየጮኹ መናገር፣ ሰውዬው እንዲሰማዎት አይረዳውም፡፡ ማድረግ ያለብዎት፣ በተቻለዎት መጠን፣ መካከለኛ በሆነ ድምጽ፣ መግለጽ የፈለጉትን ዓ. ነገር፣ ቃላት ጥርት አድርገው ይናገሩ፡፡ ነገር ግን ቀድሞውኑ ድምጽዎ በተፈጥሮው ዝቅተኛ ወይም የማይሰማ ከሆነ፣ ድምጽዎን ከፍ ወይም ጐላ አድርገው ይናገሩ፡፡
ወደማይሰማው ሰው ጆሮ አታጋድሉ - የመስማት ችግር ያለባቸው ሰዎች ሁሉም ማለት ይቻላል፤ ተናጋሪው የሚለውን የሚረዱት፣ የተናጋሪውን ከንፈር በማንበብ ነው፡፡ ስለዚህ መስማት ወደተሳነው ሰው ጆሮ ዞሮ መናገር ምንም አይጠቅምም፡፡ ምክንያቱም እንደዚያ በሚያደርጉበት ጊዜ መስማት የተሳነው ሰው፣ የተናጋሪውን ሰው ከንፈር ማየትና ማንበብ ስለማይችል ነው፡፡
ጫጫታ አስወግዱ - አብዛኞቹ የመስማት ችግር ያለባቸው ሰዎች፣ የሚንጫጫ ድምጽ ካለ፣ የተናጋሪውን መልዕክት መረዳት አይችሉም፡፡ ለምሳሌ፣ ውሃ ከቧንቧ ሲቀዳ፣ ሲጢጢጢ የሚል ወይም የጉምጉም ድምጽ ሲኖር፣ ንግግር ለመለየት በጣም ይቸገራሉ፡፡ ስለዚህ፣ ቲቪው ወይም ራዲዮኑ ከፍ ባለ ደምፅ ሲያወራ ለመናገር አትሞክሩ፡፡
ሁላችሁም አንድ ላይ አትናገሩ - ስምንት ወይም 10 ሰዎች በሚገናኙበት ስብሰባ ወይም የእራት ግብዣ ላይ ስትሆኑ፣ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ካሉ፣ ከሚደራረቡ ርዕሶች ይልቅ አንድ ዋነኛ ርዕስ መርጣችሁ በተራ አውሩ ወይም ተናገሩ። ምክንያቱም፣ እዚህ ጠረጴዛ ላይ አንድ ርዕስ፣ እዚያኛው ላይ ሌላ ርዕስ፣… ተነስቶ ሲወራ፣ የመስማት ችግር ያለበት ሰው በአንድ ጊዜ፣ በተለያየ ጠረጴዛ ላይ የሚናገሩትን ሰዎች ከንፈር ማንበብ ስለማይችል ነው፡፡
“ምንም አይደለም/ችግር የለውም” አትበሉ
መስማት የተሳነው ሰው፣ ሁለትና ሦስት ጊዜ ነግራችሁት ካልገባው ወይም ካልተረዳችሁ፣ ደጋግማችሁ ሞክሩ እንጂ ተስፋ ቆርጣችሁ ወይም “ተረድቶኛል” ብላችሁ አትተውት፡፡ ምክንያቱም መስማት ለተሳነው ሰው፣ ሁሉም ነገር ችግር ስለሆነበት ነው፡፡  

Read 2834 times