Sunday, 24 November 2013 17:30

ቅቤ ተቀብቶ ዝምብ አይንካኝ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

ጥንት አንድ አዋቂ ሰው ነበር ይባላል፡፡ በመጪው ዓመት ምን እንደሚከተል ያውቃል አሉ፡፡ አንድ ቀን ንጉሡ የ አዋቂ መጥቶ መጪውን እንዲተነብይ ያስጠራውና ወደ ሸንጐ እየመጣ ሳለ፤ አንድ እባብ ያገኛል፡፡ “ንጉሡ ትንቢት ተናገር ብለውኛል፤ ምን ልበል?” አለና ጠየቀው፡፡ እባቡም፤
“መጪው ጊዜ ጦርነት ስለሆነ ፀልዩ! በላቸው” አለው፡፡
አዋቂው ሸንጐ ቀርቦ እባቡ እንዳለው፤ ለንጉሡ ተናገረ፡፡ “ያለው ዕውነት ነው” አሉና ንጉሡ ሸልመው ሸኙት፡፡ አዋቂው ወደቤቱ ሲመለስ ያን እባብ አገኘው፡፡ በጦሩ ወጋውና መንገዱን ቀጠለ፡፡
በሁለተኛው ዓመት እንደገና ንጉሡ አዋቂውን አስጠሩት፡፡ እዚያው ቦታ የቆሰለውን እባብ አገኘው፡፡
እባቡም፤ “ባለፈው ዓመት መጪው ጊዜ ምን እንደሚመስል ጠይቀኸኝ፤ ነግሬህ፣ ወግተኸኝ ሄድክ፡፡ ሆኖም አሁንም እነግርሃለሁ፡፡ ይህ ዓመት የበሽታ ዓመት ነውና ፀልዩ በላቸው” አለው፡፡
አዋቂው ወደ ሸንጐ ሄደና የበሽታ ዓመት እንደሚሆን ተናገረ፡፡ ንጉሡም “ባለፈው ዓመት የተናገረው ዕውነት ስለሆነ ዘንድሮም የተናገረው ዕውነት መሆን አለበት፡፡ በሉ፤ ሸልሙና ሸኙት” አሉ፡፡
አዋቂው ሲመለስ ያንን እባብ አገኘው፡፡ በድንጋይ መትቶ ወግሮ ወግሮ መንገዱን ቀጠለ፡፡
በሶስተኛው ዓመት እንዲሁ አዋቂው ሸንጐ ተጠራና ሄደ፡፡ መንገዱ ላይ እዛው ቦታ እባቡን አገኘው፡፡
“ዘንድሮስ ምን ብል ይሻለኛል?” አለው፡፡
“ባለፈው ዓመት መክሬህ፣ ተናግረህ፣ ተሸልመህ ስትመለስ በድንጋይ መትተኸኛል፡፡ ሆኖም አልተቀየምኩህም፡፡ በዚህ ዓመት የእሳት ዘመን ነውና ፀልዩ በላቸው” አለው፡፡
ወደንጉሱ ሄዶ “ዘንድሮ የእሳት ዘመን ነው” አላቸው፡፡
ንጉሡም፤ “ባለፉት ሁለት ዓመታት የተናገረው ዕውነት ስለሆነ፤ ዘንድሮም ያለው ዕውነት መሆን አለበት፡፡ ሸልሙትና ይሂድ” አሉ፡፡
አዋቂው ሲመለስ እባቡን አገኘው፡፡ አሁን ግን መምታት ሳይሆን በእባብ ሊያቃጥለው ሞከረና መንገዱን ቀጠለ፡፡
በቀጣዩ ዓመት ለአራተኛ ጊዜ ንጉሡ አስጠራው፡፡ አዋቂው መንገዱ ላይ እባቡን አገኘው፤
“ዘንድሮስ ምን ልበል?” አለው፡፡
እባቡም፤ “ዘንድሮ የጥጋብ ዘመን ስለሆነ ፈንድቁ! በላቸው” አለው፡፡
ንጉሡ የጥጋብ ዘመን መሆኑን ሲሰሙ “እስከዛሬ የተናገረው ምንም መሬት ጠብ የሚል ነገር አልነበረውም፡፡ ዘንድሮም ዕውነት ስለሚሆን በርከት አድርጋችሁ ሸልሙልኝ” አሉ፡፡
አዋቂው ወደቤቱ ሲመለስ እባቡን አገኘው፡፡ በዚህ ጊዜ ግን በሀር የተንቆጠቆጠ ካባ አለበሰው፡፡
እባቡም፤
“የመጀመሪያው ዓመት የፍልሚያ ዘመን ነበረና በጦር ወጋኸኝ፡፡
በሁለተኛው ዓመት የበሽታ ዘመን ነበረና በድንጋይ ወገርከኝ፡፡
በሦስተኛው ዓመት የእሳት ዘመን ነበረና በእሳት አቃጠልከኝ፡፡
በአራተኛው ዓመት ግን የጥጋብ ዘመን በመሆኑ ካባ አለበስከኝ፡፡ እነሆ ጥበቤን ሁሉ ሰጥቼሃለሁ፡፡ ያ ይበቃሃል፡፡ አሁን ካባህን መልሰህ ውሰድ፡፡ የሰጠሁህ ጥበብ ከምንም ነገር በላይ ነው፡፡ ጥበቤን ሁሉ ውሰድ፡፡ ራሴ የነገርኩህን የነገ ዕጣ - ፈንታ፤ ራሴውም መጋራት ስላለብኝ ነው ያልተበቀልኩህ! በምንም ቁሳቁስ ልትተካው አትሞክር”  
                                                        *   *   *
ዕጣ-ፈንታችንን አናመልጥም፡፡ የዕጣ-ፈንታችን አካል ነን፡፡ የምንለው፣ የምናቅደው፣ የምንራዕየው ሁሉ የእኛው አካል ነው፡፡ በተናገርነው እንነገርበታለን፡፡ በደነገግነው እንቀጣበታለን፡፡ በደሰኮርነው እናፍርበታለን ወይም እንኮራበታለን፡፡ በተለይ መንግስት ስንሆን ባወጣነው ህግ እከሌ ከእከሌ ሳንል፣ ወገናዊና ኢፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ መተዳደርና መቀጣት አለብን፡፡
የመንግሥትነታችን ትልቅ ቁም ነገር የህዝብን ደህንነትና የሀገርን ህልውና መታደግ ነው፡፡ ይህ ዋና ኃላፊነት ነው፡፡ ህዝብ እንዳይሸበር፣ እንዳይጠራጠር፣ ዕምነት እንዳያጣ ማድረግ፤ በአገሩ፣ በመንግሥቱና በኃላፊዎቹ ላይ የመተማመን ስሜት እንዲያድርበት ያደርገዋል፡፡  
“የመንግሥት መኖር ዓላማው የህብረተሰቡን የተለያዩ ፍላጐቶች ለማርካት፣ አገርን ለማጠንከር መሆን አለበት፡፡ መንግሥታዊ ህጐችና ተቋሞቹም ዘለዓለማዊ ሳይሆኑ ይህንኑ ማህበራዊ ፍላጐት ለማስገኘት ሲባል ከህብረተሰቡ ዕድገት ጋር አብረው የሚያድጉና የሚለወጡ መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ድህነት፣ ሰብአዊ ጉስቁልና፣ ሀዘንና ሰላም - የለሽነት ይቆራኘውና ለውድቀት ይዳረጋል” ይለናል የጥንቱ፣ የታህሣሥ 1953ቱ ንቅናቄ ተዋናይ፤ ግርማሜ ነዋይ (የታህሣሡ ግርግርና መዘዙ)
የህዝብን ችግር ቸል አንበል፡፡ የኋላ ኋላ ጣጣው ይመለከተናልና!
ለትናንሽ የኢኮኖሚ ችግሮች መፍትሔ ሳንሰጥ ወደ ውስብስብና ግዙፍ ችግርነት እንዲያድጉ ከፈቀድንና ቸልታችን ከበዛ፤ ያለ ጥርጥር ወደ ፖለቲካዊ ችግርነት ማደጋቸው አይቀሬ ነው፡፡
የወሎ ረሃብ እንደተነናቀ ወደ አብታዊ ማዕበልነት ተለወጠ፡፡ የሚሊተሪ ዲክታተራዊ አገዛዝ መናጠጥ፣ የቢሮክራሲያዊ በደል ማጠጥ፣ የሥልጣን መባለግና ያላግባብ መበልፀግ የአማጽያንን መፈልፈልና የተቃዋሚን ቁርጠኝነት መውለዱን ወለደ፡፡
ዛሬም የህዝብን ኑሮና የሀገርን ውስብስብ ችግሮች በወቅቱ የመፍታት ቅን ልቦና ከሌለ ዕጣ- ፈንታ ወዳዘዘው ውድቀት ማምራት ግድ ይሆናል፡፡ በዚህ ጉዳይ የመንግሥት ዋንኛ ትኩረት የአንበሳውን ድርሻ ይውሰድ እንጂ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራትና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጐች ወዘተ የነገዋ አገራችን ዕጣ-ፈንታ ይመለከተናል ማለት ኤጭ የማይባል ነገር መሆኑን ልብ ማለት ደግ ነው!
“የህዝብ ችግር እየተባባሰ በሄደ ቁጥር፤ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው እያወቀ እንዳላወቀ፣ እያየ እንዳላየ፣ በዝምታ መኖሩ ከባድ የህሊና ሸክምና ፈታኝ ጥያቄ ነው” ይላል ጄኔራል (መንግሥቱ ነዋይ፡፡)  
አቶ ብርሃኑ አስረስ “ማን ይናገር የነበረ…የታህሣሡ ግርግርና መዘዙ” በተባለው መጽሐፋቸው፤ ህዝብ ጭቆና ሲያንገፈግፈው ስለሚደርስበት ደረጃ ሲናገሩ፤
“የሕዝብን መነሳሳት ለማፍራት ብዙ ሙከራ ተደርጐ ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ቀፎው ተነክቶበት የተሸበረ ንብና ተስፋውን ጨርሶ የተነሳ ሕዝብ ተመሳሳይ በመሆኑ፤ የተፈፀመው ሙከራ ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ድሮው ተገዥነት ቦታው ለመመለስ አልቻለም…” ይሉናል፡፡
የአስተዳደር ብስለታችን፣ የዲፕሎማሲያችን ጥራት፣ ስለፓርቲና ስለ ሀገር ያለን ግንዛቤ፤ የምንመራውን ህዝብ አመኔታና ተቀባይነት የሚያስገኘው ቁልፍ ነገር መሆኑን መቼም ቢሆን መቼም እንወቅ፡፡ የህዝብን የልብ ትርታ፣ የሀገር ወዳዶችንና ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ድምጽ እንደገዝጋዡ ሳይሆን እንደ አጋዡ በማየት ማግባባት፣ ማስማማት፣ ማደራደር ከመሪዎቻችን የሚጠበቅ የብልህ እርምጃ ነው፡፡ ያለድካ

Read 5448 times