Monday, 18 November 2013 10:30

“የኢትዮጵያ ህዝብ ለውጥ ፈልጓል፤ ግን ለውጡን የሚሸከምለት ፓርቲ ይፈልጋል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በቅርቡ
ከአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ጋር ውህደት፣ ከሌሎች 10 ፓርቲዎች ጋር ቅንጅት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ሲሆን ፓርቲው ከረጅም አመታት በኋላ
የፕሬዚዳንት ለውጥም አድርጓል፡፡
ከአዲሱ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሃሪ ጋር ፓርቲው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር እየፈጠረ ስላለው ውህደት እና ቅንጅት እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ በፓርቲው ጽ/ቤት ተገኝቶ አነጋግሯቸዋል፡፡

ከ“መድረክ” ጋር ያለው ጥያቄ “አንድነት” ሊፈታው የሚገባው ነው
ፓርቲያችን ግራ የተጋባ አይደለም
መኢአድ በሀገሪቱ ካሉ ፓርቲዎች ጠንካራው ነው
ህዝቡ እውነተኛውንና ውሸታሙን መለየት አለበት

ከ“አንድነት” ፓርቲ ጋር ውህደት ለመፈፀም የጀመራችሁት ውይይት ምን ላይ ደረሰ? ውህደቱንስ በዚህን ወቅት መፈፀሙ ለምን አስፈለገ?
ህዝባችንን ካለበት ችግርና የሰብአዊ መብት ጥሰት ነፃ ለማውጣት የጋራ አላማ ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድ ላይ መስራት ወሣኝነት አለው ብለን እናምናለን፡፡ ተለያይቶ ድምጽ ከመሻማት ይልቅ አንድ ላይ ሆኖ ሃብትንም ሆነ ሌላ ሌላውን አቀናጅቶ መንቀሳቀስ ጠቃሚ ነው፡፡ በህዝቡም ላይ በራስ መተማመንን ፈጥሮ ሃይል ያለው “ሊመራኝ የሚችል ፓርቲ አለኝ” ብሎ እንዲያምን አንድ መሆን ወሳኝ ነው ብለን እናምናለን፡፡ እኔ አሁን ባለው ደረጃ ማለት የምችለው፣ አንድነትና መኢአድ ለመዋሃድ ድርድር እያደረጉ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን መግለጫ ለመስጠት ያስቸግረኛል፡፡ ምክንያቱም ሂደቱ በራሱ ኮሚቴ የሚመራ ነው፡፡ ኮሚቴው ማንም ሰው በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ መስጠት አይችልም የሚል ፕሮቶኮል ፈርሟል፡፡ የየፓርቲዎቹ ባለስልጣናትም ሆኑ ተደራዳሪዎች መግለጫ መስጠት አይችሉም፡፡
ከአንድነት ጋር ውይይት ጀምረናል ብላችኋል፣ አንድነት ደግሞ የመድረክ ግንባር አባል ነው፣ እናንተ ደግሞ መድረክን እንደማትፈልጉት በተደጋጋሚ ገልፃችኋል፡፡ ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል?
መኢአድ በኢትዮጵያ አንድነት ጥላ ስር ለመሄድ ከማይፈልጉ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመንቀሳቀስ ይቸገራል፡፡ የመኢአድ አወቃቀሩም ሆነ አላማው ሁሉም ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ጥላ ስር መንቀሳቀስ አለባቸው የሚል ነው፡፡ በጐሣም ተደራጅተው በኢትዮጵያ ጥላ ስር ሆነን “አንዲት ሉአላዊት ኢትዮጵያ” በሚለው ስር አብረን እንሄዳለን ካሉ አብሮ ለመስራት ችግር የለውም፡፡
ስለዚህ አንድነት በመድረክ ስር ሆኖ እንዴት ይሆናል የሚለው የራሱ የአንድነት ጉዳይ ነው፤ የመኢአድ ጉዳይ አይደለም፡፡ መኢአድ እና አንድነት እየተደራደሩ ነው፤ ሁለቱም ተመሳሳይ ፕሮግራም፣ አላማ፣ ደንብ ያላቸው ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ከመድረክ ጋር ያለውን ጥያቄ አንድነት ሊፈታው የሚገባው ጥያቄ ነው እንጂ የመኢአድ አይደለም፡፡ ይሄ የድርድሩም አካል ነው፡፡
ውህደቱን ስትፈጽሙ አመራሩስ እንዴት ነው የሚደራጀው?
እንግዲህ እንደነገርኩህ በዚህ ላይ መግለጫ ለመስጠት ያስቸግረኛል፡፡ ተደራዳሪዎች ስላሉ ይሄ ነው ብሎ ለማለት ፕሮቶኮሉ ያስረኛል፤ ነገር ግን ውህደት ከተካሄደ ውህደት የሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ ይፈፀማሉ ማለት ነው፡፡ ለዚህ ካለአመራሩ ይሄ ይሆናል ማለት አልችልም፡፡
መኢአድ ከሌሎች ፓርቲዎች የሚለየው በምንድነው?
ፓርቲያችን ተመሳሳይ ደንብ እና አላማ ካላቸው ፓርቲዎች የሚለይበት አንደኛ፣ ህብረ ብሔራዊ መሆኑ ነው፡፡ የመኢአድ እምነት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ፣ ጥላ ስር ሆኖ የእያንዳንዱ ዜጋ መብት ሲከበር፣ የሁሉም ዜጋ መብት ይከበራል ብሎ ያምናል እንጂ የአንድ ጐሣ መብት ሲከበር የጐሣው አባላት መብት ይከበራል ብሎ አያምንም። አሁን ለምሣሌ ገዢው ፓርቲ ውስጥ ያለው የብአዴን መብት ሲከበር፣ የእያንዳንዱ አማራ መብት ተከበረ ማለት አይደለም፡፡ የኦህዴድም በተመሳሳይ፤ ሌላው መኢአድ የሚመራው በሊበራል ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ነው፤ ይሄ ከሌላው የሚለየን ይመስለኛል። ሌላው የምንለይበት ፓርቲያችን ግዙፍ የሆነ አደረጃጀት ያለው ነው፡፡ በመላው ሃገሪቱ በሚገኘው እያንዳንዱ ቀበሌ መኢአድ አለ፡፡
በአራቱም ማዕዘናት ቢኬድ መኢአድ የሌለበት ቀበሌ የለም፡፡ እንዲሁም ፓርቲው የእያንዳንዱ ብሔር ጥንቅር ውጤት ነው፡፡
ምናልባት የብሔር ተዋጽኦው ሲነሣ እርስዎ ከሚሉት በተቃራኒ የአማራው ሚና የሚጐላበት እንዲያም ሲል አመራሩ እና ማዕከላዊ ኮሚቴው ለሰሜን ሸዋ አካባቢ ተወላጆች ብቻ የተሰጠ ነው የሚል ወቀሳ ይቀርብበታል…
እዚህ ላይ አሁን የመኢአድን አመራር ጥንቅር ያየህ እንደሆነ ከአማራው፣ ከጐፋው፣ ከወላይታው ያለበት ነው፡፡ ለምሣሌ የፓርቲውን ምክትል ተቀዳሚ ሊቀመንበር ብንወስድ ከጐፋ ነው፣ የመኢአድን የስራ አስፈፃሚ ብትወስድ ኦሮሞች አሉ፤ ለምሣሌ ብሩ ደሲሣ ከአሶሳ አለ፣ ገለቱ ኤጀርሣም አለ፡፡ ስለዚህ ይሄ የጠላት ወሬ ነው። መኢአድን ለማዳከም የሚነዛ አሉባልታ ነው። አማራው ከሌላው ብሔር የበለጠ በዚህ ፓርቲ ውስጥ ተሳትፎ የለውም፡፡ ለምሣሌ የአባላት ጥንቅርን የወሰድን እንደሆን በሰሜን ካለው አባል የበለጠ በደቡብ ነው ያለው፡፡ ከ39 በመቶ በላይ በደቡብ አካባቢ ያሉ ናቸው፡፡ ከሰሜን ሸዋ የመጡ ናቸው የሚባለው የሰሜን ሸዋ ህዝብ ወይም በዚያ የሚገኝ የአማራ ተወላጅ እንዳጋጣሚ ሆኖ አማራው ይገደል በነበረ ጊዜ ፕ/ር አስራት ፓርቲውን ይመሩ ነበር፡፡ ይህ ማለት ግን አመራሩ በጠቅላላ ከሰሜን ሸዋ ነበረ ለማለት አይቻልም። እሣቸው እንደ ፕሬዚዳንት ከሰሜን ሸዋ ይሁኑ እንጂ ከተለያዩ የአማራ ክፍሎች የተውጣጣ የስራ አስፈፃሚ መዋቅር ነበር፡፡ ፕ/ር አስራት፤ የመላው አማራ ህዝብ ድርጅትን ሲያቋቁሙ የአማራው ወይም የአንድ ብሔር ፓርቲ አድርገው ለማቋቋም አልነበረም ፍላጐታቸው፤ ነገር ግን ይገደልና ይሰደድ የነበረውን አማራ ከጥቃቱ ለመከላከል ያህል ያቋቋሙት ነው፡፡ በወቅቱ ለጊዜው አማራው ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንከላከልና ኋላ ላይ ህብረ ብሔራዊ ሆኖ ሁሉንም ብሔሮች አሣትፎ ይቀጥል የሚል መርህ ነበራቸው፡፡ በዚህ መርህ አሁን ካለበት ደረጃ ደርሷል፡፡ አማራው በዚህ ውስጥ በምንም ሁኔታ የበላይነት የለውም፤ ይሄ የጠላት ወሬ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ከመድረክ ጋር አብረን አንሰራም ብላችሁ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ 10 ፓርቲዎች ያሉበት ቅንጅት በመኢአድ ጉልህ ሚና እየተፈጠረ ነው ያለው፡፡ ከዚህ ፓርቲዎች አብዛኞቹ የጐሳ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ከመድረክ ጋር አብሮ አያስጉዘንም ያላችሁበት አጀንዳን ወደ ጐን ትታችሁ አሁን እንዴት ከነዚህ ፓርቲዎች ጋር ለመቀናጀት መረጣችሁ?
ትክክል ነው እነዚህ ድርጅቶች የጐሳ ናቸው። ኢህአዴግ ኢትዮጵያን በጐሳ ሲሸነሽን እነዚህ ፓርቲዎች በጐሳቸው… ተደራጅተው ነው፤ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ፓርቲዎቹ የጐሣ ቢሆኑም በኢትዮጵያ ጥላ ስር ሆነን እንታገላለን ያሉ ናቸው። ስለዚህ ፓርቲዎቹ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር መሆንን የሚሹ ናቸው፡፡ የጐሣ/ብሔር/ ፖለቲካ እንደማያዋጣ አምናለሁ፤ በኢትዮጵያ ጥላ ስር ሆነን ከመኢአድ ጋር እንታገላለን ስላሉ ነው የተቀበልነው፡፡ እንግዲህ የነበሩት 33 ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ከ33ቱ አብዛኞቹ በጐሣችን ብቻ ነው የምንታገለው ስላሉ አማራጫቸውን ይዘው ሄደዋል፡፡ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ሆነን እንታገላለን ያሉት መኢአድ እንዲያታግላቸው ወደዚህ መጥተዋል፡፡ እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያለበት ከመጡት ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት የብሔር /ጐሣ/ ድርጅቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ህብረ ብሔራዊ ናቸው፡፡
ከመድረክ ስብስብ ጋር ያላችሁ መሠረታዊ ቅራኔ ምንድን ነው? ከስብስቡ ውስጥ በኢትዮጵያዊነት አያምኑም ብላችሁ የምትጠቅሷቸው ፓርቲዎች አሉ እንዴ?
በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ካለማመን ባሻገርም በአንዳንድ ፖሊሲያችንም እኮ እንለያያለን፡፡ ለምሣሌ በመሬት ጉዳይ፤ መኢአድ መሬት የህዝብ ነው፤ መንግስት ሊያዝበት አይችልም ብሎ ነው የሚያምነው፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጥሪት ሊኖረው ይገባል ብሎ ያምናል፡፡ ዜጐች መሬት ተከራይተው ሊኖሩ አይገባም፤ ይሄ የመኢአድ ፖሊሲ ነው፡፡ ነገር ግን የሌሎቹ የመድረክ አባላት ፕሮግራም በዚህ አያምንም፤ የኢህአዴግን ነው ይዘው የሚሄዱት፤ በነገራችን ላይ አንዳንዶቹ ኢህአዴግ ዲሞክራሲያዊ ስላልሆነ ነው እንጂ በፖሊሲ ደረጃ አንለይም ባይ ናቸው፡፡
መድረክ ውስጥ እንደዚያ የሚሉ ድርጅቶች አሉ?
አዎ! በሚገባ
የአስሩን ፓርቲዎች ፖሊሲና ፕሮግራም ካስቀመጡልን ነጥቦች አንፃር በሚገባ መርምራችኋል ማለት ነው?
መቶ በመቶ በሚገባ አጥርተን መርምረናል፣ ፕሮግራማቸውን አንብበን እና ተናበን ነው ይሄን ያደረግነው፡፡
በ1997 ስለተፈጠረው ቅንጅት አመሰራረትና ውድቀት ብዙ ተብሏል፡፡ የአሁኑን ቅንጅት ከፈረሰው ቅንጅት ምንድን ነው የሚለየው?
ቅንጅት ስንል ያው ቅንጅት ነው፡፡ አይለያይም። እያንዳንዱ ፓርቲ የራሱን ህልውና ጠብቆ ነገር ግን የሚመጣው ችግርና አደጋ በአንድ ላይ እንታገላለን ብሎ የሚያምን ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ላይ ተጨፍልቆ አንድ እንደመሆን አይታሰብም፡፡ በ1997ም እያንዳንዱ ፓርቲ በዚህ አይነት ሁኔታ ራሱን የቻለ ነበር፡፡
ግን በአንድ ፕሮግራምና በአንድ የመወዳደሪያ ምልክት ነበር ለምርጫው የቀረበው…
ይሄም ልዩነት አይኖረውም፤ እንደዚያው ነው። ነገር ግን የአሁኑ በየክልሉ ያሉት ፓርቲዎች ቢሮ ካላቸው እንደ ግንኙነት መድረክነት ያገለግላል፤ በየክልሉ በቀላሉ ተደራሽ መሆን ይቻላል፡፡ ከዚያ በተረፈ ከ97 ዓ.ም ቅንጅት ልዩነት የለውም፡፡
ወደ አንድነት ድርድሩ እንመለስና የ97 ቅንጅት ሲፈርስ መኢአድ ህልውናውን ጠብቆ ሲጓዝ “አንድነት” ደግሞ የመኢአድ አባላት የነበሩትን ጨምሮ በቅንጅቱ መፍረስ ቁጭት ባደረባቸው ፖለቲከኞች የተቋቋመ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ያን ጊዜ በአንድነት መጓዝ ያልቻላችሁ አካላት ዛሬ ምን ታይቷችሁ ነው አንድ ካልሆንን እያላችሁ ያለው?
መቼም አንድ ላይ ስትሠራ ትጋጫለህ ትኮራረፋለህ፣ የሃሣብ ልዩነት ይፈጠራል። እያንዳንዱ አመራር ልዩነት ይኖረዋል፡፡ ይሄ እንግዲህ ያለ ነው፡፡ ችግራችን ምንድነው ልዩነት ሲመጣ የግለሰቦች ፀብ ነው ነጥሮ የወጣው፤ ነገር ግን ይሄ መሆን የለበትም፡፡ ግለሰቡን ሣይሆን ከተቃወምንም ሃሳቡን ነው መቃወም ያለብን። ኢትዮጵያውያን የሚጐደለን ይሄ ይመስለኛል። ስለዚህ እንዳልከው አንድነትን የመሠረቱት ብዙዎቹ ሰዎች ከዚህ አኩርፈው የሄዱ ናቸው። ያኔ በተለያዩ ምክንያቶች ሄደዋል፡፡ አሁን ግን ከስህተቶቻችን ተምረን አብረን ጠንክረንና ተባብረን እንሠራለን። አንድ ጊዜ ተጣልተናልና መልሰን አብረን መስራት አንችልም የሚል እምነት አይኖረንም፡፡ እየተጋጨንም ዞረን ደግሞ ስህተታችንን አምነንና ተማምነን መስራት ምንም ማለት አይደለም፡፡ ለወደፊትም አለመግባባቶች ቢኖሩ በዚህ መልኩ እየተማመኑና እየተወያዩ መሄዱ ይቀጥላል የሚል እምነት ነው ያለኝ እና ከዚህ አንፃር ቢታይ መልካም ነው፡፡
በየጊዜው ፓርቲዎች መድረክ፣ ትብብር፣ ህብረት፣ ቅንጅት እያሉ በጋራ እየተሰባሰቡ ሲወድቁ ሲነሱ የኢትዮጵያ ህዝብ ታዝቧል፡፡ መኢአድም የዚህ ሂደት አንዱ አካል ነው፡፡ ለወደፊትስ ፓርቲያችሁ በዚህ ሁኔታ እስከየት ድረስ ነው ሊጓዝ የሚችለው?
እንግዲህ ባለፉት 22 አመታት የፓርቲዎች ስብስብ አንድ ሲሆን ሲለው ደግሞ ሲፈርስ ኖሯል፡፡ እንደ እኔ አመለካከት ይሄ የሆነው ሁሉም ነገር በግለሰቦች ፍላጐት ላይ የተመሠረተ ስለነበረ ነው፡፡ ይሄ ኢትዮጵያንም ሆነ ዜጐቿን የጐዳ ትልቁ በደል ነው፡፡ አንዳንዱ የፓርቲ አመራር ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ቆሜያለሁ ካለ፣ ራሱን ለዚያ አላማ መሸጥ አለበት፡፡ ግቡ ወይም የሩቅ አላማው ኢትዮጵያውያንን ነፃ ማውጣት ወይም በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ሠፍኖ ማየት መሆን አለበት። ግን በዚህች ሀገር እስካሁን ሲደረግ የቆየው እኔ ሊቀመንበር ካልሆንኩ፣ የኔ ፓርቲ የበላይ ካልሆነ ሲባል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አሁንም ቢሆን መኢአድ ሊያደርግ የሚችለው የጋራ ትግል አስፈላጊነትን ያምናል፤ ስለዚህ እስከቻለው ድረስ ከአላማው ጋር ከሚስማሙት ጋር አብሮ ይሠራል፡፡ ይህ መሆኑ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ አንደኛ ድምጽ አይሻሙም፤ በሁለተኛ ደረጃ በህዝቡ ላይ በራስ የመተማመን ስሜትን መፍጠር ይቻላል። አለኝታ የሚሆን ፓርቲ አለኝ ብሎ እንዲያምን ይገደዳል፡፡ ደካማና የተነጣጠለ ፓርቲ ሆነው ካያቸው ግን ህዝቡ እምነት ሊጥልባቸው ይቸገራል እና መኢአድ አሁንም| ተመሳሳይ ፕሮግራም ካላቸው ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት ቁርጠኛ ነው፤ ግን ይሄ የሚሆነው በቅንነት፣ በእውነተኛነት ኢትዮጵያን እያሰበ ከሚመጣ አካል ጋር ነው፡፡ ሸር ይዞ ከሚመጣ ጋር ግን ለመስራት ይቸገራል፡፡
መኢአድ ራሱ አንዴ ሲቀናጅ፣ ሲዋሃድ፣ ሲተባበር ሲያሻው ደግሞ ቅንጅቱና ውህደቱን ሲያፈርስ የኖረ ፓርቲ ነው፤ አሁንም በዚህ አዙሪት ውስጥ መሆኑን ያዩ ወገኖች ፓርቲው ግራ የተጋባ ነው ሲሉም ይደመጣል…
ፓርቲያችን ግራ የተጋባ አይደለም፡፡ ግልጽ አላማ ግልጽ የሆነ ፕሮግራምና ደንብ ያለው ፓርቲ ነው። ፓርቲው ህብረ ብሔራዊ፣ ብዙ አባላትና ደጋፊዎች በውጭም በሀገር ውስጥም ያለው በመልካም አመራር የሚመራ ፓርቲ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን አምነው ከሚመጡ ፓርቲዎች ጋር ለመስራት መኢአድ ዝግጁ ነው፤ ነገር ግን የሚመጡትን ፓርቲዎች ለመምራት የሚሞክር ሳይሆን አብሮ የሚሰራ ነው፡፡
በየክልሉ ያሉ ቢሮዎቻችሁ እየተዘጉባችሁ እንደሆነ ስትገልፁ ከርማችኋል፡፡ ከነዚህ ክልላዊ እና ጐሣዊ ፓርቲዎች ጋር ለመቀናጀት የወሰናችሁበት ሚስጥር ምናልባት ዳግም ለመጠናከር አስባችሁ ይሆን?
ይሄም ዝም ብሎ ግምታዊ አስተያየት ነው እንጂ ፓርቲው አሁን በየትም ቦታ ብትሄድ ቢሮ አለው ወይም መዋቅር አለው፡፡ እንደተባለው በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት በተለይ የወረዳዎቹ ቢሮዎች ተዘግተው ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ መኢአድን ብቻ ሣይሆን ሌሎችንም ጐድቷቸዋል፡፡ ስለዚህ አሁን መኢአድ በሃገሪቱ ካሉ ፓርቲዎች ጠንካራው ነው ብል ስህተት አይደለም። በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ ደጋፊዎቻችን ለፓርቲው መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው። እዚህ ያለው አመራርም የተዘጉ ቢሮዎችን ለማስከፈት ጥረት እያደረገ ነው። እስከ 2007 ድረስ ሙሉ ለሙሉ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ቢሮ ይኖረናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ይህን ካልኹ፣ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ፤ “አንድ ላይ ካልተባበራችሁ፣ ካልሠራችሁ ለትግሉ አስቸጋሪ ነው” በሚል ህብረት እንድንፈጥር እየጠየቀ ነው፡፡ ስለዚህ መኢአድ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደ አንድ መጥቶ፣ ጠንካራ ፖለቲካ ፓርቲ ተፈጥሮ፣ መወዳደር አለባቸው እንጂ መቶ ደካማ ፓርቲዎች ዝም ብለው መጮህ የለባቸውም የሚል እምነት አለው፡፡ ከዚህ አንፃር ነው እንጂ እኛ ድክመት ኖሮብን በእነሱ ለመሸፈን አይደለም፡፡ እነሱ ብዙም ይዘው የሚመጡት ነገር የለም፡፡
መኢአድ ከሌላው የተሻለ ሰፊ ህዝባዊ መሠረት ካለውና አደረጃጀቱም ጠንካራ ከሆነ በምርጫ ወቅት ለምን ተፎካካሪ ሊሆን አልቻለም?
ፓርቲው እየታገለ ያለው እሱ ብቻ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን ነው፡፡ እንደተባለው ፓርቲው ጠንካራ መሠረት ያለው ቢሆንም ከገዢው ፓርቲ የሚደርስበት ጫናም በዚያው ልክ የሰፋ ነው። አባላቱ ንብረታቸውን ይነጠቃሉ፣ ይታሰራሉ፣ ይደበደባሉ፤ ሰዎች የፓርቲው አባል ስለሆኑ ብቻ የተለየ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ እንደነዚህ አይነት ተጽእኖዎች ደግሞ ሊያራምዱ አይችሉም፡፡ በሌላ መንገድ ገዥው ፓርቲ የራሱን የደህንነት አባላት እና ካድሬዎች በየፓርቲዎቹ ውስጥ ሰግስጐ ያስገባል፡፡ በዚህም በፓርቲ ውስጥ መናወጥ ይፈጥርና የፓርቲውን አመራር ያዳክማል፡፡ ይሄ በማዕከል ብቻ ሳይሆን በዞንና በወረዳም ጭምር የሚደረግ ነው፡፡ እንደነዚህ አይነት ተጽእኖዎች ናቸው ከፍተኛ ችግር የፈጠሩት፡፡ ህዝቡም መወጣት ያለበትን ሃላፊነት መወጣት አለበት፡፡ እውነተኛውንና ውሸታሙን መለየት መቻል አለበት፤ ዳር ሆኖ መመልከቱ አይጠቅምም፡፡
ተቃዋሚዎች ለመዳከማቸው ገዢውን ፓርቲ ተጠያቂ ያደርጋሉ፤ ገዥው ፓርቲ ደግሞ ጠንካራ ተቃዋሚዎች ባለመኖራቸው ሸክሜ በዝቷል እያለ ነው…
እዚህ ላይ ሁለት ነገር ነው የሚታየኝ፡፡ አንደኛ አቶ መለስም በህይወት በነበሩ ጊዜ የተናገሩት ነው፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ቢመጣ ሩቅ መንገድ ሄደን እንቀበለዋለን ተብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ቅንጅት ተፈጥሮ ጠንካራ ፓርቲ ሲመጣ በጥይት ግንባሩን ነው ያሉት። ይሄ አባባል እንግዲህ ፖለቲከኞቻችን ለይስሙላ የሚጠቀሙት መሆኑን አረጋጋጭ ነው፡፡ “እንዳይበላ ግፋው እንዳያማህ ጥራው” አይነት ነገር ነው፡፡ አሁንም አቶ ኃይለማርያም የተናገሩትን ሰምቸዋለሁ “ሌሎቹ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሃላፊነትን መሸከም ስላልቻሉ የሃገሪቱ ሸክም ሁሉ ኢህአዴግ ላይ ወድቋል። ተበራቱ” የሚል ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ኢህአዴግ ምንም አይነት ሃላፊነት ሊሸከም የሚችል ፓርቲ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ለምን? የኢትዮጵያን ህዝብ ሰብአዊ መብት እየጣሰ ያለ ፓርቲ፣ ሃላፊነት እሸከማለሁ ቢል አይታመንም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የኢትዮጵያን ህዝብ አዎንታ የተቀበለ ፓርቲ አይደለም፡፡ በሃይል፣ በመሳሪያ ስልጣን የያዘ ፓርቲ ነው፡፡ እኔ የማዝነው አቶ ኃይለ ማርያም በጣም ክርስቲያን ናቸው ይባላል፤ ግን በእዚህ አይነት ጉዳይ ላይ የሚናገሩት ነገር ከእምነታቸው ይቃረንብኛል፡፡ እነሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ያቁሙና ከዚያ በኋላ ጠንካራ ተቃዋሚ ካጡ ይሄን ነገር ሊናገሩ ይችላሉ፡፡
መኢአድን ጨምሮ ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በግለሰብ አውራዎች ላይ የተመሠረቱ ሆነው ይታያሉ። ከፕሮግራምና አላማቸው ይልቅ ፕሬዚዳንቶቻቸው ጐልተው ይወጣሉ፡፡ የሚሆነው ለምን ይመስልዎታል?
በእርግጥ ይሄ ነገር መሆን የሌለበት ነው፡፡ አመራር ብቻ አይደለም፤ አባላትም በሁሉም ነገር ላይ ተሣትፎአቸው መጠየቅ አለበት፡፡ የእነሱ ተሣትፎ ከሌለበት የኔ ነው የሚሉት ነገር ሊኖር አይችልም። በመጀመሪያ ደረጃ አባላቱ የኔ ነው ሊሉ የሚችሉት ፓርቲው አሣታፊ ሲሆን ነው፤ ስለዚህ እንደነዚህ አይነት ነገሮች በቀጣይ ሊታረሙ የሚገቡ ናቸው፡፡ አመራሩና አባላቱ የውስጥ እኩል ተሣትፎ ሊኖራቸው ይገባል። አንድ ሰው አንድ ፓርቲ ሊሆን አይገባም። የእከሌ ፓርቲ ሊባል አይገባም፡፡ መኢአድ ያንን ለማድረግ እየሰራ ነው፡፡ በአደረጃጀቱም ትልቁን ስልጣን የሚሰጠው ከታች ላለው ነው፡፡ የፓርቲ አመራሮች ራሳቸውን ለአባላቱ ተገዢ ካላደረጉ፣ ነገ ለሚመሩት የኢትዮጵያ ህዝብ ተገዢ ሊሆኑ አይችሉም።
የ2007 ምርጫ እየተቃረበ ነው፡፡ መኢአድ ከምርጫው ምንድን ነው የሚጠብቀው?
እኛ ስራችንን እየሰራን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አዎንታውን ከሰጠን ስልጣን ለመያዝ ከመጓዝ የሚያግደን ነገር የለም፣ ነገር ግን የመጫወቻ ሜዳው በትክክለኛው መንገድ ካልሄደ የኢትዮጵያን ህዝብ ልናማው አንችልም፡፡
እኛንም ህዝቡ ሊያማን አይገባም፤ ማማት ያለበት ገዢውን ፓርቲ ነው፡፡ በጥይት በዱላ እየደበደበ አባላቶች እንዳይሳተፉ የሚያደርግ ከሆነ፣ በምርጫ ወቅት ካርድ እየሰረዘ አሽነፍኩ የሚል ከሆነ፣ በምርጫ ወቅት ታዛቢዎቻችንን እየደበደበ፣ በመድሃኒት እያሠከረ እያስተኛ የሚዘርፍ ከሆነ መታማት ያለበት ገዢው ፓርቲ ነው፡፡ መኢአድ በ2007፤ መቶ በመቶ አሸንፋለሁ ብሎ እየተራመደ ነው ያለው፤ ይሄን ደግሞ እርግጠኞች ነን። ለምን ካልን አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ለውጥ ፈልጓል፤ ግን ለውጡን የሚሸከምለት ፓርቲ ይፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬ በብዙ መልኩ መብቱ ተጥሷል። የሃገሪቱን የኢኮኖሚ ትሩፋት መጠቀም ተስኖታል፡፡ የቀን ሠራተኛው፣ ብሎኬት ሠራተኛው፣ ዶሮ አርቢው ሣይቀር ከውጭ እየመጣ ነው፡፡ የሀገሪቱ ዜጋ መጠቀም አልቻለም፡፡

Read 3232 times Last modified on Monday, 18 November 2013 12:29