Print this page
Monday, 18 November 2013 10:28

በማኔጅመንቱና በቦርዱ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ጃካራንዳ አክሲዮን ማህበር

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  መጋቢት 20 ቀን 2001 ዓ.ም በ950ሺ ብር ካፒታል ሥራ የጀመረው “ጃካራንዳ ኢንተግሬትድ አግሮ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር” የስራ አመራር ቦርድና ማኔጅመንቱ በውዝግብ ላይ ሲሆኑ ከሁለቱም ወገኖች የተለያዩ ቅሬታዎችና አስተያየቶች እየተደመጡ ነው፡፡ 
በመጀመሪያ የተነሳው ቅሬታ ከማህበሩ መስራችና ስራ አስኪያጅ ከነበሩት አቶ ደመላሽ ወጋየሁና ከሌሎች ሰዎችም ጭምር ሲሆን የስራ አመራር ቦርዱ በአመት ከተፈቀደለት 97ሺህ ብር በላይ በመጠቀምና ወደ 131 ሺህ ብር ከፍ በማድረግ ማህበሩን ለኪሳራ እየዳረጉ ስለመሆኑ፣ የቦርዱ ፀሐፊ አቶ ሙሉ ሸዋ ከስርዓትና ከደንብ ውጭ በየወሩ አምስት መቶ ብር ሊከፈለኝ ይገባል በሚል በፃፉት ደብዳቤ የ19 ወር 9500 ብር ያለ አላግባብ የተከፈላቸው ስለመሆኑ፣ አሁን እየሰራ ያለው ቦርድ መጋቢት 2 ቀን 2004 በተጠራ አስቸኳይ ስብሰባ ጊዜያዊ ቦርድ ሆኖ መመረጡንና ጥቅምት 9 ቀን 2005 ዓ.ም መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ ስልጣኑን ማፀደቅ ሲገባው አለማፅደቁን፣ በየአመቱ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት ሲገባው እስካሁን ስብሰባው አለመጠራቱን፣ ባለአክሲዮኖች የሚያውቁትንና የሚገናኙበትን ሁለት የስልክ መስመሮች ቀይረው በአዲስ ስለተኩት ባለአክሲዮኖች ግንኙነት መፍጠር አለመቻላቸውን፣ ቦርዱ የማህበሩን መተዳደሪያ ደንብ አላዘጋጀም፣ የ2006 አመት በጀትም የለውም፣ ቦርድ ሲመረጥ በንግድ ህግ ቁጥር 349 መሰረት በስራ ዘመኑ ላጠፋቸው ጥፋቶች ዋስትና ማስያዝ ቢኖርበትም በስራ ላይ ያለው ቦርድ ምንም አይነት ዋስትና አለማስያዙን፣ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተው ሳያስታውቁና ንግድ ሚኒስቴር ሳያውቅ ቢሮ መቀየራቸውንና መሰል ችግሮች በቦርዱ እየተከሰተ ስለመሆኑ አንዳንድ ባለአክሲዮኖችና መስራቹ አቶ ደምመላሽ ወጋየሁ ይናገራሉ፡፡
ይህንን በተመለከተም ለፀረ - ሙስና ኮሚሽን፣ ለገቢዎችና ጉምሩክ የህግ ማስከበር ዘርፍ ጽ/ቤት፣ ንግድ ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬትና ለሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ይናገራሉ፡፡
“ከ2500 በላይ ባለድርሻዎች ያሉትን ጃካራንዳ፤ ማህበርን በማመን አካል ጉዳተኞች፣ አቅመ ደካሞችና ዕድሮች ሳይቀሩ አክሲዮን ገዝተዋል ግን ብሩ በህገ - ወጦች እየተመዘበረ ነው ይህን በማጋለጤና ለምን በማለቴ ከስራና ከደሞዝ አግደውኛል” ይላሉ አቶ ደምመላሽ፡፡
ግለሰቡ አክለውም አክሲዮን ማህበሩ ስራውን በማስፋፋት፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን ባኮ ቲቤ ወረዳ፣ በ300 ሄክታር መሬት ላይ የእርሻ ስራ ልማት የጀመረ “ዩ ኤፍ ቢ ፋርም” የተባለ ድርጅት ለጃካራንዳ በሽያጭ ለማስተላለፍ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት፤ 2.5 ሚሊዮን ብር ያለ ደረሰኝ ከፈፀመ በኋላ ቀሪውን ግማሽ ሚሊዮን ብር ህጋዊ ደረሰኝ ሲያቀርቡ ለመክፈል ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የድርጅቱ ባለቤቶች ለተከፈላቸው 2.5 ሚሊዮን ብር ህጋዊ ደረሰኝ እንዲያመጡና ቀሪውን ግማሽ ሚሊዮን ብር እንዲወስዱ በቃልም በጽሑፍም ቢጠየቁም “ድርጅታችንን ዘግተናል፤ የምን ደረሰኝ ነው የምትጠይቁን” በሚል ማስቸገራቸውን የገለፁት አቶ ደመላሽ፤ ወደፊት እንዲከፈላቸው የተሰጣቸው ቼክ እንዲታደግ ማድረጋቸውን ጠቁመው አሁን በስራ ላይ ያለው ቦርድ ይህ ጉዳይ በሂደት ላይ መሆኑን እያወቀ እና ሪፖርት ተደርጐለት እያለ ከግለሰቦቹ ጋር በመመሳጠር እንዲሁም የመንግስትን ገቢና የድርጅቱን ጥቅም ለማሳጣት ቀሪ ገንዘባቸው እንዲከፈል ትዕዛዝ ለማኔጅመንቱ መስጠቱንና በዚህም አቶ ደመላሽ በግላቸው ቅራኔ ውስጥ መግባታቸውን ለኢፌድሪ ገቢዎችና ጉምሩክ የህግ ማስከበር ጽ/ቤት ለኢፌድሪ ፀረ ሙስና ኮሚሽን እና ለኢፌድሪ ንግድ ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት በፃፉት ደብዳቤ አሳውቀዋል። “ለተከፈላቸው ክፍያ ህጋዊ ደረሰኝ ሳያቀርቡ ለምን ቀሪ ክፍያ ይፈፀማል በሚል ቅሬታ በማሰማቴ ቦርዱ በህግ ለመጠየቅ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ጽፎልኛል” ያሉት አቶ ደመላሽ ነገር ግን ቦርዱ ለግለሰቦቹ ተባባሪ በመሆን እርሳቸውን ከስራና ከደሞዝ በማገድ ያለምንም ደረሰኝ 50ሺህ ብር የከፈላቸው መሆኑንና ይህም በህዝብ ንብረት ላይ መቀለድ መሆኑን በመግለጽ መቃወማቸውን ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የፃፉት ደብዳቤ ያሳያል። ይህን ጉዳይ የተመለከተው በንግድ ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ጥቅምት 21 ቀን 2006 ዓ.ም ለጃካራንዳ ኢንተግሬትድ አግሮ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር የስራ አመራር ቦርድ ሊቀመንበር “የአክሲዮን ማህበሩን አጠቃላይ አሰራር ዝርዝር የሚያሳዩ መግለጫዎች እንዲቀርቡ ስለመጠየቅ” በሚል ርዕስ ደብዳቤ የፃፈ ሲሆን፤ ጃካራንዳ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያገኙ ዘንድ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አክሲዮን በመግዛት ያቋቋሙት ማህበር ሲሆን ማህበሩ ለአባላት ጥቅም ከማስገኘት ይልቅ በርካታ አስተዳደራዊ ችግሮች ያሉበት ስለመሆኑ ከመስራች አባላት በጽሑፍና በቃል ቀርበው ለመ/ቤቱ ከሰጡት መረጃ መረዳቱን፣ በተጨማሪም የስራ አመራር ቦርዱ ወቅቱን ጠብቆ አባላትን ለስብሰባ በመጥራት በችግሮች ዙሪያ ማወያየትና መፍትሔ ማፈላለግ ሲገባው እስካሁን ስብሰባ ለመጥራት ፈቃደኛ አለመሆኑን በመግለጽ ጥቅምት 25 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ በስምንት ሰዓት በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ውይይት ለማድረግ በምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት እንዳገኙ ለቦርዱ ሰብሳቢ የፃፉት ደብዳቤ በዝግጅት ክፍላችን ይገኛል፡፡
“ያለ ደረሰኝ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮኑን ብር ለግለሰቦቹ እንዴት ልትሰጡ ቻላችሁ በሚል ለአቶ ደመላሽ ላነሳነው ጥያቄ “አሁን ካለው ቦርድ በፊት ስራ ላይ የነበረው ቦርድ ባስተላለፈው ትዕዛዝ መሰረት ክፍያ ፈጽመናል” ሲሉ መልሰዋል፡፡
የቦርድ አመራሮች ራሳቸው ቼክ ፈራሚ ራሳቸው ፈቃድና ወሳጅ በአጠቃላይ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው የሚሰሩበት አካሄድ ፈጽሞ ከህግ ውጭ በመሆኑ አሁንም ተቃውሟቸውን እንደሚቀጥሉ የተናገሩት አቶ ደመላሽ በአሁኑ ሰዓት እኔን ተክተው የሚሰሩት አቶ ፍቅረማርያም ሃ/ጊዮርጊስ የቁጥጥር ኮሚቴ ሆነው በሚሰሩበት ጊዜ ከላይ በቦርዱ ላይ ባነሳናቸው ቅሬታዎች ዙሪያ አብረው ይሰሩ እንደነበር ጠቁመው የቁጥጥር ኮሚቴ ሆነው ሳለ ስራ አስኪያጅ ሆነው መሾማቸው ከህግ አሰራር ውጭ ነው በማለት ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። “እስካሁን ከላይ የገለጽኳቸውን 11 ነጥቦች ለንግድ ሚኒስቴር፣ ለድርጅቱ የውጭ ኦዲተር እና ለሚመለከታቸው አቅርቤያለሁ” ያሉት የቀድሞው የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ እና አደራጅ አሁንም ችግሮች ባለመቀረፋቸው የህዝብ ንብረትና ገንዘብ አደጋ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የእኔነት ስሜት ተሰምቷቸው የሚሰሩ ሰራተኞች በደሞዝ ማነስ ስለመሰናበታቸው በቦርዱ የተባረሩ ሠራተኞች ስለመኖራቸው እና በመሰል ጉዳዮች ስለተነሱት ቅሬታዎች በአስቸኳይ ምላሽ ካልተገኘ የድርጅቱ ህልውና አደጋ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የማህበሩ ባለድርሻና የቀድሞው የማህበሩ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ የነበሩት አቶ ጌታቸው ገብረየስ በበኩላቸው በአዲስ አበባ በሃላፊነት በሚሰሩበት ወቅት 12.5 ሚሊዮን ብር መሰብሰባቸውን ገልፀው “እኛን አምነው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ አክሲዮን ገዝተው ጥቅም ሲጠብቁ ኩባንያው አሁን ያለበት ችግር ላይ መገኘቱ አንገት ያስደፋል” ይላሉ፡፡ ለድርጅቱ መቋቋም ደም የመስጠት ያህል መስዋዕትነት እንደከፈሉ የሚናገሩት አቶ ጌታቸው በዚህም ለጤና እክል ተጋልጠው በፈቃዳቸው ስራቸውን መልቀቃቸውን፣ ነገር ግን አሁን ያለው የቦርዱ አሰራርም ሆነ ኩባንያው ያለበት ሁኔታ ስጋት እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡
“አሁን ሥራ ላይ ካለው ቦርድ በፊት የነበሩት ሁለት ጊዜ የተመረጡ የቦርድ አመራሮች በድርጅቱ ላይ ባደረሱት ጥፋት በጠቅላላ ጉባኤ ተሽረው አሁን ያለው ቢመረጥም ጥፋት እንጂ ልማት አላመጣም” ያሉት አቶ ጌታቸው፣ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ቦርዶች ላይ መንግስት እርምጃ ቢወስድ ኖሮ ሶስተኛው ለእንዲህ አይነት ስህተት አይነሳሳም ነበር ሲሉ አማረዋል፡፡
“ይህንን በመቃወም እንቅስቃሴ እያደረገ ያለው አቶ ደመላሽ ከመስከረም ስድስት 2006 እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ ከስራም ከደሞዝም መታገዱ የቦርዱን ችግር ያሳያል” ብለዋል፡፡
ከላይ የተቀሱትን ቅሬታዎች መነሻ በማድረግ የቦርዱ አባልና ፀሐፊ የሆኑትን አቶ ሙሉ ሸዋ ከበደን ያነጋገርን ሲሆን ቦርዱ በአስቸኳይ ስብሰባ የተመረጠ እንደመሆኑ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ ስልጣኑን ለምን አላፀደቀም የሚለውን ጥያቄ አስቀድመናል የቦርዱ ፀሐፊው መጋቢት 2 ቀን 2004 ዓ.ም በተጠራ ጠቅላላ ጉባኤ የቀድሞ የቦርድ አባላት ያጠፉት ጥፋት ተገልፆና የሚባረሩት ተባረው በተደረገ ምርጫ አሁን ስራ ላይ ያለው ቦርድ ሃላፊነት መረከቡን ገልፀው ይሁን እንጂ ይህ ቦርድ ሀላፊነት ሲረከብ ኩባንያው በብዙ ምስቅልቅል ችግሮች ውስጥ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ በተለይም የድርጅቱ መስራች እና ስራ አስኪያጅ የነበረው አቶ ደመላሽ ወጋየሁ ተናኜ የተባለው ግለሰብ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በሀላፊነት እየተንቀሳቀሰ እንደነበርና መጋቢት ሁለት በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ መሳተፉን፣ ከዚያም በጉባኤው ምርጫ መሰረት አሁን 18 ወራት በመስራት ያስቆጠረው ቦርድ የመጀመሪያው ስራ ርክክብ ማድረግ እንደነበር ገልፀው የቀድሞው ቦርድ ጋር ርክክብ ከማድረግ ይልቅ ህጋዊ ቦርድ አይደላችሁም በሚል ወደ ፍርድ ቤት ሄደው ከፍተኛ ክርክር እንደነበርና ጉዳዩ በፍትህ አካል ታይቶ “ጉባኤው የመረጠውን አካል ህጋዊ አይደለህም ማለት አይቻልም” ሲባል ተፈርዶባቸው 36ሺህ ብርም እንደተቀጡ የቦርዱ ፀሀፊ ይናገራሉ፡፡
“ከዛን ጊዜ ጀምሮ የኩባንያውን ውስብስብ ችግሮች በመፍታት ረገድ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ከማድረግ አልቦዘንም” የሚሉት ፀሀፊው አቶ ደመላሽም የቦርዱን ችግሮች ለመፍታት አብሮ ከቦርዱ ጋር ሲሰራ እንደነበረም አስታውሰዋል፡፡ ጉባኤው የቀድሞውን የድሬክተሮች ቦርድ ሲያሰናብት አቶ ደመላሽ በስራ አስኪያጅነት እንዲቀጥል ስምምነት ላይ መደረሱን የሚገልፁት አቶ ሙሉ ሸዋ፣ “አቶ ደመላሽ አልፀደቁም ህጋዊ አይደሉም ለሚለው እኛ ለሶስተኛ ጊዜ የተመረጥን እንጂ ለኩባንያው አዲስ አይደለንም” ካሉ በኋላ ግለሰቡ ከስራ የተሰናበተው ለአክሲዮን ማህበሩ አባላትም ሆነ ለሌሎች አካላት ውዥንብር የመንዛት እንቅስቃሴ ላይ በመሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አቶ ደመላሽ “በኩርፊያ በገዛ ፈቃዱ ጳጉሜ አንድ ቀን 2005 የኩባንያውን ስራ ለቆ የተለያዩ ለማህበሩ ጐጂ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሆነ ደርሰንበታል” ይላሉ አቶ ሙሉ ሸዋ፡፡
“የድሬክተሮች ቦርድ በወር አንድ ጊዜ እየተገናኘ ማኔጅመንቱን ይቆጣጠራል እንጂ ዝቅ ብሎ ኦፕሬሽናል ስራአይሰራም” የሚሉት የቦርዱ ፀሀፊ፣ “እኛ ስራውን ስንረከብ ከገጠሙን ፈተናዎች ውስጥ የ2002፣ የ2003 እና የ2004 ዓ.ም ሂሳብ አለመመርመሩ ነው” የሚሉት አቶ ሙሉ ሸዋ ከዚያም ቦርዱ በያዘው አቋም የ2003 እና የ2004 ዓ.ም ሂሳብ በውጭ ኦዲተር መመርመሩን ይናገራሉ። የውጭ ኦዲተሩም የማህበሩ አባላት የሰየሙት በመሆኑ በሂሳብ አያያዙም ላይ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት አስተያየት ሰጥቷል ብለዋል፡፡ “ለረጅም ጊዜ ስራ አስኪያጅ ሆኖ እንደመስራቱ የውጭ ኦዲተሩ ችግሮች ብሎ በሰጣቸው አስተያየቶች ላይ ለጠቅላላ ጉባኤ ስራ አስኪያጁ ምላሽ እንዲሰጥ በማለት የስብሰባ ፈቃድ አውጥተን፣ የአዳራሽ ኪራይ ተነጋግረን ጨርሰን እያለ ጉዳዩ ወደ ውጥረት ሲገባ ጳጉሜ 1 ቀን 2005 ዓ.ም ከስራ እንድናሰናብተው ጠየቀን” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
“አንድ አክሲዮን ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ ሲጠራ ዋናውን እና አባለት መስማት የሚፈልጉት የፋይናንስ ሪፖርት ነው” ያሉት የቦርዱ ፀሀፊ፣ የፋይናንስ ሪፖርት በምናዘጋጅበት ጊዜ እንቅፋቶችን የፈጠረብን ያለው አቶ ደመላሽ ነው” ብለዋል። ፀሀፊው አክለውም ብዙ የአክሲዮኑ ባለ ድርሻዎች አዲሱን ቦርድ የአቶ ደመላሽ አሸርጋጅ አድርገው በመውሰድ “ሰውየው አጭበርባሪ ነው ለምን አትሰሙንም” በሚል ተቃውሞ ሲያሰሙ ነበር ይላሉ፡፡ ጳጉሜ አንድ ቀን ስራውን ሽባ አድርጐ ሲጠፋ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ የፋይናንስ ሪፖርት ተደርጐ ጉባኤው የሚወሰነውን ሰምተህ መሰናበት አለብህ በሚል ደብዳቤ መፃፋቸውን እና የፃፉትን ደብዳቤ ኮፒ ሰጥተውናል፡፡
የቦርዱን አመታዊ በጀት በተመለከተ ከ97ሺህ ብር እንዴት 131ሺህ ብር አደገ ለሚለው ጥያቄ አቶ ሙሉ ሸዋ ሲመልሱ ቦርዱ እንደማንኛውም የአክሲዮን ማህበር ቦርድነቱ በንግድ ህጉና በአክሲዮን ማህበር መተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ወርሀዊ አበልና የስብሰባ አበል እንዳለው ገልፀው፣ ወርሀዊ እና የስብሰባ አበሉን የሚከፍለውም አቶ ደመላሽ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡
“ማህበሩ በትክክለኛ በጀት የሚንቀሰቀስ አልነበረም ትክክለኛ በጀት በ2004 ዓ.ም የሰራነው እኛ ነን” የሚሉት አቶ ሙሉ ሸዋ ከመጠን በላይ ተከፈለ የሚባለው ሊሆን አይችልም ምክንያቱም በወር የሚከፈለው እና በስብሰባ የሚከፈለው አባል የታወቀ ነው ብለዋል፡፡ “ምናልባት ከፍ ብሏል ብሎ አቶ ደመላሽ የገለፀው በማህበሩ የተለያዩ ችግሮች ሳቢያ በርካታ ስብሰባዎች ይካሄዱ እንደነበር፣ በድርጅቱ ላይ የተመሰረቱ በርካታ ክሶች እንደነበሩ፣ አቶ ደመላሽን በየሳይቱ ለስራ በላክነው ቁጥር “ሰዎች ሊገድሉኝ እየተከታተሉኝ ነው” ሲል እሱን ለማዳን ወደ አዋሽ እንደሚሄዱ፣ ባኮቲቤ ላይም ሽፍቶች ሊገድሉኝ ነው ሲል ተነስተው እሱን ለማዳን እንደሚሄዱ ገልፀው ይህ ሁሉ ወጪ ሲወጣ ያውቃል ግን በደብቅና ለቦርዱ አባላት ጥቅም ተብሎ የባከነ ሳይሆን እርሱ ለፈጠራቸው ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት ነው ይላሉ፡፡ “ከዚህ በተረፈ ላጠፋው ጥፋት ሽፋን ለመፍጠር በቦርዱ ላይ ስም የማጥፋት ዘመቻ ቢከፍትም ማንም ከህግ የሚያመልጥ ስለ ሌለ እኛም ካጠፋን እሱም ካጠፋ በህግ እንጠየቃለን” ብለዋል አቶ ሙሉ ሸዋ፡፡
“ጥቅምት ሰባት ቀን በስድስት ገፅ ደብዳቤ ቦርድ ደንቆሮ ነው በሚል ዘለፋ አካሂዷል” ሲሉም ተናግረዋል የቦርዱ ፀሀፊ፡፡
ቦርዱ እስካሁን ጠቅላላ ጉባኤ ለምን አልጠራም በሚል ላነሳነውም ጥያቄ ስራ ላይ ያለው ቦርድ መጋቢት ወር 2004 መመረጡን ፀሀፊው አስታውሰው፣ በንግድ ህጉ መሰረት የበጀት አመቱ ባለቀ በሶስት ወር ስብሰባ መጥራት ግድ መሆኑንና የበጀት አመቱ ባለቀ በሶስት ወር ስብሰባ ለማካሄድ የ2004 የበጀት ሪፖርት መጠየቃቸውን ሆኖም እንኳን የ2004 የ2002 እና የ2003 ሪፖርት እንደሌለ እንደደረሱበት ይህ ሁሉ ሪፖርት ሳይስተካከል ጠቅላላ ጉባኤ መጠራት እንደማይቻልና ይህን ሲያስተካክሉ ስብሰባውን እንዳልጠሩ ተናግረዋል። ከአቶ ደመላሽ ጋር የጠባቸውም መነሻ ይሄው እንደሆነ ያብራራሉ፡፡
“የ2003 የሂሳብ ሪፖርት አቅርብ ሲባል ሂሳብ ያዧ ዘግታበት ሄዳለች በሚል ማስመርመር አልቻልኩም አለ” የሚሉት ፀሀፊው ቦርዱ ለቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስና ለፌደራል የመጀመሪያ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንተ አመልክቶ ፖሊስና የፍትህ አካላት ባሉበት ሳጥኑ መከፈቱን፣ የ2003 እና የ2004 ዓ.ም በብዙ ውጣ ውረድ እንዲዘጋ ማድረጋቸውን ገልፀዋል። ጉባኤው ለሾመው የውጭ ኦዲተር እንዲመረመርም ተደርጓል ይላሉ፡፡
“ይሁን እንጂ የ2005ን ጠቅላላ ጉባኤ እንዳንጠራም አቶ ደመላሽ እንቅፋት ሆኖብልና” ይላሉ ምክንያቱንም ሲያስረዱ፣ ሂሳቦችን በማሳከርና ውዥንብር በመፍጠር እንዲሁም የ2005ን የፋይናንስ ሪፖርት ሀርድና ሶትፍ ኮፒ ወስዷል ከዚያም ኮምፒዩተሩ ውስጥ ቫይረስ በመክተት ድራሹን አጥፍቶታል ይላሉ። ተጠባባቂ ስራ አስኪያጁ አቶ ፍቅረማሪያም ሃ/ጊዮርጊስ ሲጠይቁትም ለማቅረብ ፈቃደኛ አልሆነም ይላሉ፡፡ ይህ ባለበት ሁኔታ ከ 2500 በላይ አባላትን ጠርቶ ምን ይነገራል” ሱሉ ጠይቀዋል የቦርዱ ፀሀፊ።
“ቦርዱ በትክክል የሰራው 13 ወር ነው ከዚያ በፊት ያሉትን ስምንት ክሶች ስናስተካክል ነበር” ያሉት አቶ ሙሉ ሸዋ ከነዚህ ክሶች ውስጥ አንዱ ገንዘብ ያዧ ሊደፍረኝ ነበር ያለ አግባብ ከስራ ተባርሬያለሁ” የሚል እንደነበር ያብራራሉ፡፡
በንግድ ሚኒስቴር የምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ለቦርዱ የፃፈውን ደብዳቤ በተመለከተም ቦርዱ ለሚኒስቴሩ ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ምላሽ የሰጠበትን ደብዳቤ ከቦርዱ ፀሀፊ አግኝተናል፡፡ ደብዳቤው ለምን ስብሰባ እንዳልጠራ አቶ ወጋየሁ ፈፀሙ ያለውን ስህተትና እየተካሄዱ ያሉ ጉዳዮችን ለዳይሬክቶሬቱ ፅፏል፡፡
“አቶ ደመላሽ ወጣትና የሀሳቡ አመንጪ ነው በሚል እምነትና ሀላፊነት ጥለንበት ነበር” የሚሉት ፀሀፊው አሁን ጥሎ ሲሄድ የስድስት ወር የቤት ኪራይ፣ የሶስት ወር የሰራተኞች ደሞዝ፣ የስድስት ወር የቢሮ ስልክ ሂሳብ፣ ቀጥተኛ መስመር ያለው የተንቀሳቃሽ የሶስት ወር ሳይከፍል እጅግ በርካታ ኪሳራዎችን አድርሶ እንደሆነ ይናገራሉ። ገንዘቡን ለመክፈል ባደረግነው ጥረት ከዚህ በፊት ከቦርዱ እውቅና ውጭ በዱቤ 160 ከብቶችን ሸጦ በፍ/ቤት ግለሰቦቹን አሳስረው አክሲዮን ማህበሩን ሂሳብ በመሰብሰብ እየተንቀሳቀሱና እዳዎችን እየከፈሉ እንደሚገኙ ፀሀፊው ተናግረዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ቲኬ ህንፃ ላይ የተከራየው ቢሮ ከማህበሩ አቅም በላይ 40ሺህ ብር በወር እንደነበረ፣ ከዚያም ቦርዱ ወደ 20ሺህ ዝቅ የሚል ቢሮ መከራየቱን፣ አሁን ደግሞ የነገው ሰው ት/ቤት ፊት ለፊት ባለ 12ሺህ ብር ቢሮ በመከራየት ኩባንያውን ከወጪ እየታደጉ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ሰራተኞችን ቦርዱ እያባረረ ነው የሚባለውን በተመለከተ በየሳይቱ ያሉ ፕሮፌሽናል ሰራተኞችን እያባረረ የነበረው አቶ ደመላሽ መሆኑንና የቦርዱ አባላት ግን አግባብተው መመለሳቸውን ከነዚህም ውስጥ አንድ ሳይንቲስት እና አግሮኖሚስት እንደሚገኙበት ፀሀፊው ገልፀዋል፡፡
ሁለት የስልክ መስመሮችን መቀየር አስመልክቶም ፀሀፊው መስመሮቹ መቀየራቸውን አምነው እሱ ደውሎ በርካታ ገንዘብ በመቁጠሩ ቴሌ ሄደው ማዘጋታቸውን ሌላ አዲስ መስመር ቦርዱ ማውጣቱንና ለአባላት ማሳወቁን ገልፀዋል፡፡
ማህበሩ የመተዳደሪያ ደንብ የለውም የተባለውን በተመለከተ እርሱ ከስራ የለቀቀው ከሁለት ወር በፊት ነው ይህን ጥያቄ እስከ ዛሬ ለምን አላነሳም ሲሉ ጠይቀው ማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ያለው መሆኑን እንዲሁም የ2006 በጀት የለውም መባሉንም አስተባብለዋል፡፡
ያነጋገርናቸው አንድ ከፍተኛ አክሲዮን ያላቸውና ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ ግለሰብ በሁለቱ ወገኖች ውዝግብ በህዝብ ንብረትና ገንዘብ ላይ ኪሳራ እንዳይደርስ መንግስት በአፋጣኝ ጣልቃ ገብቶ እልባት እንዲያገኝ አሳስበዋል፡፡
ጉዳዩን ንግድ ሚኒስቴር እየተከታተለው እንደሆነ በደረሰን ጥቆማ መሰረት ንግድ ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ከመደወል ባሻገር ሀላፊው በሰጡን ቀጠሮ ቢሯቸው ድረስ ብንሄድም አስቸኳይ ስብሰባ እንደገቡ የነገሩን በመሆኑ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡


Read 2721 times