Saturday, 16 November 2013 15:28

ኢትዮጵያ እጆቿን ለዓለም ዋንጫ ዘርግታለች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

           ብራዚል የምታዘጋጀው 20ኛው የዓለም ዋንጫ የቀረው 7 ወራት አካባቢ ነው፡፡ እስከዛሬ ማለፋቸውን ያረጋገጡት አዘጋጇን ብራዚል ጨምሮ 21 ብሔራዊ ቡድኖች ናቸው፡፡ አፍሪካን በመወከል ወደ ብራዚል የሚጓዙት 5 ብሔራዊ ቡድኖች የሚታወቁት ደግሞ ዛሬ ፤ነገ እና ማክሰኞ በሚደረጉ 5 የመልስ ጨዋታዎች ናቸው፡፡ አፍሪካን የሚወክለው የመጀመርያ ብሄራዊ ቡድን የሚታወቀው ነገ 12 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ላይ ዋልያዎቹ ከናይጀሪያ አቻቸው ጋር በካላባር በሚገናኙበት ወሳኝ ፍልሚያ ነው፡፡ ሌላው የዛሬ ጨዋታ ሴኔጋል በሜዳዋ አይቬሪኮስትን የምታስተናግድበት ይሆናል፡፡ ነገ ካሜሮን ከቱኒዚያ ሲጫወቱ ማክሰኞ እለት ግብፅ ከጋና እንዲሁም አልጄርያ ከቡርኪናፋሶ የመጨረሻዎቹ ሁለት የመልስ ጨዋታዎች ያደርጋሉ፡፡ ረቡዕ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ዋና አሰልጣኝ ሰዉነት ቢሻዉ መግለጫ በሰጡበት ወቅት‹‹ የዓለም ዋንጫ ጉዳይ ከዛሬ በኋላ ያበቃለታል፡፡ በመደጋጋፍ ተጫውተን ናይጄርያን በማሸነፍ ታሪክ ለመስራት ተዘጋጅተናል፡፡ ለወደፊቱ እንደ እርሳስ የሾለ ብሄራዊ ቡድን እንዲኖረን ከስር መሰረቱ መስራት ያስፈልገናል፡፡

በማለት ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል አዲሱ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ አዲስ አበባ ስታዲየም በመገኘት ከናይጀሪያ ጋር ለሚጠበቀው ወሳኝ ጨዋታ በልምምድ ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በማበረታት ያላቸውን አድናቆት ነገረዋቸዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ‹‹ ከናይጄሪያ ጋር ካላባር ላይ የምታደርጉትን የ90 ደቂቃ ወሳኝ ፍልሚያ እመለከታለሁ እንደምታሸንፉ እምነቴ ነው ፤ጎል ስታስቆጥሩ እያጨበጨብኩ ደስታዩን እገልፃለሁ …በድል እንንደምትመለሱ እምነቴ ነው›› ብለዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻህ ደግሞ ‹‹ ስትመለሱ የጀግና አቀባበል በማዘጋጀት ባለፉት አንድ አመታት ላደረጋችሁት አስተዋፅኦ ምላሽ የሚሆን ማበረታቻ እንሰጣለን ›› ሲሉ ለእያንዳንዳቸው የመኪና ሽልማት እንደሚሰጥም በአቶ አብነት ገብረመስቀል ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ በቀረቡ የቦነስ ክፍያዎች ለግብፅ ተጨዋቾች በነፍስ ወከፍ 25ሺ ዶላር፤ ለአይቬሪኮስት 18 ሺ ዶላር፤ ለጋና 15ሺ ዶላር፤ ለናይጄርያ ደግሞ 5ሺ ዶላር እንደሚበረከትላቸው ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡ ቋሚ አሰላለፉ እና የግብ እድሉ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 30 ተጫዋቾች ወደ ካላባር ተጉዘዋል፡፡ ሁሉንም ተጨዋቾች ለመውሰድ የተወሰነው ከመልሱ ጨዋታ ለሴካፋ ውድድር እና ለቻን በቂ ተመክሮ እና ልምድ እንዲያገኙ ተብሎ ነው፡፡

በውጭ አገር የነበሩትን ዩሱፍ ሳላህ እና ሆነ ፉአድ ኢብራሂምን አልጠራሁዋቸዉም ያሉት አሰልጣኝ ሰዉነት ፤ ከቡድኑ ጋር አብረው ልምምድ ለመስራት በጠየቁት መሰረት እድሉን እንደሰጧቸው በማስረዳት እነ ጌታነህና ሳላሀዲንን የሚያስቀምጥ አቋም እንደሌላቸዉም ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት እንዳረጋገጡት አዲስ አበባ ላይ በተደረገው የመጀመርያ ጨዋታ ላይ በጉዳት ያልተሰለፈው ወሳኙ የአጥቂ መስመር ተጨዋች ጌታነህ ሙሉ ለሙሉ ተሽሎታል፤ ስለዚህም በዛሬው ጨዋታ መሰለፉ የማይቀር ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ዝግጅቱ ብሄራዊ ቡድኑ ከጥቅምት 11 ቀን ጀምሮ ሰርቷል። በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በውጪ የሚጫወቱትን ሳላዲን ሰዒድ፤አዲስ ህንፃ፤ጌታነህ ከበደ፤ፉአድ ኢብራሂም ፤የሱፍ ሳላህን ጨምሮ ሁሉም ተጨዋቾች ተሟልተው እስከ ረቡዕ በአዲስ አበባ ልምምዳቸውን ሰርተዋል፡፡ በሞቃታማው ካላባር ለሚደረግ ጨዋታ በራሳችን አየር ሰርተን አንድ ቀን ሲቀረው ብንሄድ ይሻላል በሚል ተመካክረው ነው፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ካላባር ከገባ በኋላ ከፍተኛ ባረፈበት የቻናል ቪው ሆቴል ጥበቃ እየተደረገለት ልምምዱን በ5 ደቂቃ ርቀት በሚገኝ ሜዳ ላይ ላለፉት ሁለት ቀናት ሰርቷል፡፡

ለዛሬው ወሳኝ የመልስ ጨዋታ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚከተሉትን አጨዋወት በተመለከተ ሲናገሩ አጥቅቶ መጫወትን እንደሚያተኩሩበት ቢያመለክቱም ግብ እንዳይገባብን ከፍተኛ ጥንቃቄ እናደርጋለንም ብለዋል፡፡ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት በዋልያዎቹ አሰላለፍ 4-4-2 ወይንም 4-3-3 ፎርሜሽን ሊጠቀሙ ይችላሉ እየተባለ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ የማጣርያ ጉዞ ከዋልያዎቹ አባላት በተለይ አንዳንዶቹ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡ በሁሉም ዘጠኝ ጨዋታዎች በመሰለፍ 799 ደቂቃዎች የተጫወተው አበባው ቡጣቆ በከፍተኛው ግልጋሎቱ የሚጠቀስ ተጨዋች ነው፡፡ አምበሉ ደጉ ደበበ በ7 ጨዋታዎች ለ630 ደቂቃዎች፤ ስዩም ተስፋዬ በ8 ጨዋታዎች ለ655 ደቂቃዎች፤ አይናለም ኃይሉ በ6 ጨዋታዎች 540 ደቂቃዎች እንዲሁም አዳነ ግርማ በ7 ጨዋታዎች 417 ደቂቃዎች በመጫወት አስተዋፅኦ ነበራቸው። በዛሬው ጨዋታም እነዚህ ተጨዋቾች ወሳኝ አገልግሎት መስጠታቸው ይጠበቃል፡፡ የዋልያዎቹ ግምታዊ አሰላለፍ ግብ ጠባቂ ሲሳይ ባንጫ ተከላካዮች - አበባው ቡጣቆ፤ ደጉ ደበበ፤ አሉላ ግርማ፤ አይናለም ሃይሉ አማካዮች - አስራት መገርሳ፤ ሽመልስ በቀለ፤ ምንያህል ተሾመ፤ አዳነ ግርማ አጥቂዎች - ሳላዲን ሰኢድ፤ ጌታነህ ከበደ ዛሬ በካላባር በሚደረገው ጨዋታ ትልቁ እና አስፈላጊው ሚና ከዋልያዎቹ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎችም ይጠበቃል፡፡

በዓለም ዋንጫው 9 የማጣሪያ ግጥሚያዎች ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸውን 14 ጐሎችን አምስት ተጨዋቾች አስመዝግበዋል፡፡ በ7 ጨዋታዎች 617 ደቂቃዎችን በመጫወት 4 ጐል ያስቆጠረው ሳላሃዲን ሰኢድ ሲሆን ጌታነህ ከበደም በተሰለፋቸው 5 ጨዋታዎች 317 ደቂቃዎችን በመጫወት እኩል 4 ጐሎች አስመዝግቧል፡፡ በ7 ጨዋታዎች 508 ደቂቃዎችን የተጫወተው ሽመልስ በቀለ ሁለት ጐሎችን አስቆጥሯል፡፡ በ4 ጨዋታዎች 192 ደቂቃ የተሰለፈውና ኡመድ ኡክሪ 581 ደቂቃዎችን የተጫወተው ምን ያህል ተሾመ በ5 ጨዋታ 204 ደቂቃዎች ያገለገለው ቀሪዎቹን ሦስት ጐሎች በነፍስ ወከፍ አስቆጥረዋል፡፡ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል? የናይጄርያን ብሄራዊ ቡድን በካላባር በሚገኘው የዩኤስ ኡስዋኔ ስታድዬም በቅርብ ጊዜ ተሸንፎ አያውቅም፡፡ ለማሸነፍ ከጫፍ ደርሶ አንድ እኩል አቻ የወጣው የሃራምቤ ኮከቦች የተባለው የኬንያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫው የምድብ ማጣርያ ነበር። በ1994፤ በ1998፤ በ2002 እና በ2010 እኤአ ላይ አራት ዓለም ዋንጫዎችን የተሳተፈችው ናይጄርያ ዛሬ ኢትዮጵያን ካሸነፈች አምስተኛው ተሳትፎዋን ስታረጋግጥ ኢትዮጵያ ደግሞ የመጀመርያ ታሪካዊ ስኬቷ ይሆናል፡፡ የቀድሞው የግብፅ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሃሰን ሺሃታ ለዓለም ዋንጫ የማለፍ እድል አላቸው ብለው በልበሙሉነት ግምት የሰጡት ለአይቬሪኮስት፤ ለአልጄርያ እና ለናይጄርያ ነው። ናይጄርያ ኢትዮጵያን ጥላ የምታልፈው በሁለቱ ቡድኖች ያለው ልምድ ከፍተኛ ልዩነት ስለሚፈጥር ነው ብለው ሃሰን ሺሃታ ተናግረዋል፡፡

የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ሮይ ሆጅሰን በበኩላቸው 20ኛው የዓለም ዋንጫን የማሸነፍ እድል የሚኖረው ከአውሮፓ አገሮች ይልቅ ለአፍሪካ ተወካዮች ነው ብለው ተናግረዋል፡፡ የብራዚል አየር ንብረት የሚስማማው ለአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች መሆኑን የጠቀሱት ሆጅሰን የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች በአውሮፓ የክለብ እግር ኳስ ያላቸው ልምድንም እንደ ከፍተኛ አቅም ተጠቅመው ዓለም ዋንጫን ሊያሸንፉት ይችላሉ ብለዋል፡፡ነገ ዋልያዎቹ ከንስሮቹ ጋር በሚያደርጉት ትንቅንቅ ጨዋታው ስንት ለስንት ይጠናቀቃል? ቀድሞ ማን ጎል ያሰቆጥራል? ለዋልያዎቹ እነማን ያገባሉ? የሚሉት ጥያቄዎች በተለይ ባለፉት ሶስት እና አራት ቀናት በከፍተኛ ደረጃ መላው ኢትዮጵያዊን እያነጋገሩ ነበር፡፡ በዛሬው ጨዋታ ኢትዮጵያ 2ለ0 ወይም 3ለ2 ማሸነፍ ከቻለች በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ማለፏን ታረጋግጣለች፡፡ በሜዳዋ የምትጫወተው ናይጀሪያ በጨዋታው አቻ ውጤትና በማንኛውም ውጤት ማሸነፍ፤ በ1 ጎል ልዩነት መሸነፍ እንዲሁም 0ለ0 ፣ 1ለ1 እና 3ለ3 አቻ መለያየት ይበቃታል፡፡ ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ዛሬ ካላባር ላይ በሚያደርጉት የመልስ ጨዋታ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል ? በሚል ጥያቄ ኢትዮፉትቦል በድረገፁ አንባቢዎቹን አሳትፎ ነበር፡፡ 331 አንባቢዎች ድምፅ በመስጠት ተሳትፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ያሉት 67.07 በመቶ ሲሆኑ ናይጄሪያ እንደምታሸንፍ የገመቱት 29.31 በመቶ ናቸው።

3.63 በመቶ ደግሞ አቻ ውጤት ተንብየዋል። በሌላ በኩል ታዋቂው ጐል ስፖርት ድረገጽ አንባቢዎችን በማሳተፍ በሠራው የውጤት ትንበያ በቀረቡ 3 የውጤት ግምቶች ሙሉ ለሙሉ አሸናፊነቱ የተሰጠው ለናይጀሪያ ነው፡፡ 12.46 % 2ለ0፣ 10.38 % 3ለ1 እንዲሁም 18.69 % ያህሉ 3ለ0 በሆነ ውጤት ናይጀሪያ በሜዳዋ ኢትዮጵያ እንደምታሸንፍ ገምተዋል፡፡ ሶከርዌይ በሰራው ትንበያ ደግሞ ናይጄርያ 73.4 በመቶ እንዲሁም ኢትዮጵያ 23.8 በመቶ የማሸነፍ እድል ሲኖራቸው አቻ የሚወጡበት ግምት ደግሞ 8 በመቶ ነው፡፡ በሶከርዌይ ድረገፅ ናይጄርያ 0 ኢትዮጵያ 2 ብለው የገመቱ 24.9 በመቶ፤ ናይጄርያ 3 ኢትዮጵያ 0 ብለው የገመቱ 20.97 በመቶ ናይጄርያ 2 ኢትዮጵያ 0 ብለው የገመቱ 12.9 በመቶ ናቸው፡፡ አስራት መገርሳ የሱፐር ሱፕርት ዘጋቢ አስራት መገርሳን ተወዳጁ የዋልያ ተጨዋች ብሎታል፡፡ አዲስ አበባ ላይ በተደረገው የመጀመሪያው ጨዋታ ላይ የነበረው ምርጥ ብቃት የናይጀሪያ ምክትል አሰልጣኝ ዳንኤል አሞካቺን አሳስቦት ነበር የሚለው ዘገባው በወቅቱ ንስሮቹ በከፍተኛ ሞገስ የመሃል ሜዳውን በተቆጣጠረው አስራት በኩል መጫወታቸውን ትተው በክንፍ እንዲንቀሳቀሱ ሲጮሆባቸው ነበር ብሏል፡፡ ስቴፈን ኬሺም በናይጀሪያ ቋንቋ “ቾይ” ወይም ዋው ብሎ አስራት መገርሳን አደንቆታል።

=======================

አበባው ቡጣቆ የዋልያዎቹ ወሳኝ የግራ መስመር ተመላሽ ተጨዋች የሆነውና በሁሉም የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበረው አበባው ቡጣቆ በበኩሉ ለሱፐር ስፖርት በሰጠው አስተያየት “እግዚአብሔር ከኛ ጋር ነው” ብሏል፡፡ ፀሎት ያደረግነው በካላባር ለኩራት የሚያበቃን ገድል ለመፈፀም ነው” ያለው አበባው ‹‹ለናይጀሪያውያን የማይቻል የመሰለውን ነገር ችለን እናሳያቸዋለን›› ሲልም ተናግሯል፡፡ እንደ ሱፐር ስፖርት ገለፃ አበባው ቡጣቆ በቅርብ ጊዜ በቱርክ ክለቦች ዓላማ ውስጥ መግባቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

=======================

ደጉ ደበበ የኢትዮጵያ ተከላካይ መስመር ምሰሶ ተብሎ በሱፐር ስፖርት የተሞካሸው አምበሉ ደጉ ደበበ ነው፡፡ “በካላባር ግዙፍ ተራራ መውጣት አለብን፡፡ እንደማንኛውም የእግር ኳስ ተጨዋች ውጤቱ በ90 ደቂቃዎች ይወሰናል ብለን ተስፋ አድርገናል፡፡ ናይጀሪያውን ጥንካሬያቸው ፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው ስለሆነ ይህን በትኩረት እንከላከላለን” በማለት ደጉ ደበበ ለሱፐር ስፖርት በሰጠው አስተያየት ተናግሯል፡፡

=======================

አዲስ ህንፃ ያለውን ምርጥ የኳስ ችሎታ ሱፐር ስፖርት ያደነቀለት ሌላው የዋልያዎቹ ወሳኝ ተጨዋች አዲስ ህንፃ ነው፡፡ “የአፍሪካ ሻምፒዮን መሆናቸውን ብናከብርም በምንም ሁኔታ ዝቅተኛ ግምት ሊሰጡን አይችሉም” ብሎ ለሱፐር ስፖርት የተናገረው አዲስ ህንፃ፣ “ስለ ዓለም ዋንጫ የምናልመው ሁልጊዜ ነው፡፡ በሜዳችን ባደረግነው የመጀመያ ጨዋታ ህልሞችን መና የቀረ መስሎ ነበር፡፡ ግን ፍጻሜው ገና አልለየለትም” ብሏል።

Read 3662 times