Print this page
Saturday, 16 November 2013 14:53

“የጋዜጠኞች” ማህበራቱን ኢህአዴግ ራሱ ታዝቧቸዋል!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(11 votes)
  • “በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት ሙሉ በሙሉ ተከብሯል” - የጋዜጠኞች ማህበራት
  • “በኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ ለውጥና ማሻሻያ እናደርጋለን” መንግስት
  • ኢህአዴግ ሌሊት ሌሊት የምረጡኝ ቅስቀሳ እያጧጧፈ ነው!

እንደኔ አላጋጠማችሁ እንደሆነ አላውቅም እንጂ ኢህአዴግ ሌሊት ሌሊት የምርጫ ቅስቀሳ ጀምሯል (ህገ መንግስታዊ መብቱ እኮ ነው!) እኔን የገረመኝ ግን ቅስቀሳው ሳይሆን ቀኑን ትቶ ሌሊትን መምረጡ ነው፡፡ (ቀንማ “ቢዚ” ነው!) ባለፈው ሳምንት ነው፡፡ ሰኞ ወይም ማክሰኞ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሌሊት ላይ እንቅልፍ እምቢ አለኝና ኢቴቪን ከፍቼ ቁጭ አልኩኝ (ብቸኛ “አጫዋቼ” ነው አላልኳችሁም!) ምናልባት ከሌሊቱ 9 ሰዓት ወይም 10 ሰዓት ገደማ ይሆናል፡፡ ኢቴቪ የኢህአዴግ የሴቶች ሊግ አባላትን የልማት እንቅስቃሴ የሚያስቃኝ ፕሮግራም ማቅረብ ጀመረ፡፡ (“የሴቶች ሊግ” የተሰኘ አዲስ ፕሮግራም ሳይሆን አይቀርም!) በኋላ ሲገባኝ ግን የልማት ሳይሆን የምረጡኝ ቅስቀሳ ነገር ነው፡፡ እኔ የምለው … በህዝብ ንብረት ቅስቀሳ ይቻላል እንዴ? (ኢህአዴግም እኮ የህዝብ ንብረት ነው!) አንድ ጥያቄ ግን አለኝ፡፡ የ2007 ምርጫ ወደ 2006 ተዛወረ እንዴ? ለቀጣዩ ዓመት ምርጫ ዘንድሮ ቅስቀሳ አይጀምርም ብዬ እኮ ነው! እናላችሁ … በኮብልስቶንና በሌሎች “ደሃ-ተኮር” ስራዎች ላይ የተሰማሩ ሴቶች አስተያየት ሲሰጡ፣ እንደሌላው ጊዜ ስማቸው ወይም የሥራቸው ዓይነት አይደለም ቲቪ ስክሪኑ ላይ የተጠቀሰው፡፡

ለእያንዳንዱ ተናጋሪ “ሊግ አባል” የሚል መግለጫ (Caption) ነው የተሰጠው። (መቼ የተጀመረች ግልፅነት ትሆን?) አንደኛዋ የሊግ አባል፤ ኢህአዴግ ከጓዳ (ማጀት) አውጥቶ ለአደባባይ እንዳበቃት ገለፀች፡፡ እሷም ብትሆን በጥቃቅን ሳትደራጅ በፊት ነው የሊጉ አባል የሆነችው፡፡ (ባለውለታ ናት ማለት ነው!) ቀጠለች-ሴትየዋ፡፡ “ለሴቷ አማራጭ ያለው ፓርቲ ነው” ስትል አውራ ፓርቲውን በደንብ አሞካሸችው (በእሷ ዓይን “ሲያንሰው” እኮ ነው!) ትንሽ ቅር ያለኝ ግን ምን መሰላችሁ? አባል ለመሆን መዘግየቷ ነው። “በ2001 ዓ.ም ነው አባል የሆንኩት” ብላናለች፡፡ (ያን ሁሉ ዓመት የማን አባል ነበረች?) በነገራችሁ ላይ …ከሴቶች ሊግ አባላት ውስጥ 99 በመቶ ያህሉ በሥራ ላይ የተሰማሩ (employed ወይም self employed) ሲሆኑ በቅርቡ አንድም ሥራ አጥ (zero unemployment) የሊግ አባል እንደማትኖር የሊጉ ሊቀመንበር ተናግረዋል፡፡

(ልብ አድርጉ! “አንድም የሊግ አባል” ነው የተባለው!) በነገራችሁ ላይ … ሊጉ የሚመራው “ሰጥቶ መቀበል” (ፈረንጆቹ Give and take ይሉታል) በሚለው መርህ ነው፡፡ በአበሽኛ “እከክልኝ ልከክልህ” የሚባለው መሰለኝ፡፡ እናላችሁ … የሊጉ አባላት በ2002 እና በአካባቢና ማሟያ ምርጫዎች ኢህአዴግን በመምረጥ ብቻ ሳይሆን እንዲመረጥ በመቀስቀስም ለፓርቲያቸው ያላቸውን የማይናወጥ “ታማኝነት” አሳይተዋል ብላለች - የሴቶች ሊግ ሊቀመንበሯ፡፡ (ካላሳዩማ አለቀላቸው!) እኔ የምለው … የሊግ አባል የመሆን ዕድል ላላገኙ የጦቢያ ሴቶች የሥራ ዕድልና ብድር የሚሰጣቸው ማነው? (ጥያቄ እኮ ነው!) እንደው ለጨዋታ ያህል ነው እንጂ… በኢቴቪ በውድቅት ሌሊት የተላለፈው የሴቶች ሊግ የምርጫ ቅስቀሳ ምንም ክፋት የለውም (አሳቻ ሰዓት ከመቅረቡ በቀር!) የሊጉን ቅስቀሳ ኮምኩሜ ልተኛ ስል ግን አንድ ሃሳብ መጣልኝ። “Drink Responsibly” ወይም “በሃላፊነት ስሜት ተጐንጩ” የሚለውን የቢራ ማስታወቂያ ታውቁታላችሁ አይደል? ኢህአዴግን ጨምሮ ሁሉም የጦቢያ ፓርቲዎች ራሳቸውን ሲያስተዋውቁና ሲቀሰቅሱ “Support Responsibly” ወይም “በሃላፊነት ስሜት ይደግፉ!” የሚል ማስታወቂያ ቢያክሉበት አልኩ-ለራሴ፡፡

(እንዴ … የፖለቲካ የአልኮል መጠን እኮ ከቢራ የአልኮል መጠን በብዙ እጅ ይልቃል፡፡) እኔ የምለው … ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ህብረት የተካሄደውን የአፍሪካ ሚዲያ መሪዎች ፎረም እንዴት አያችሁት? የአፍሪካ ነገር ሁሌ ችግሯን ሁሉ በፈረንጆቹ ላይ ማላከኳ አናደደኝ እንጂ ጋዜጠኞቹ መወያየታቸውና መወቃቀሳቸው የሚበረታታ ነው። አንድ ቀን ከምዕራባውያን ላይ ወርደው ራሳቸውን መቻላቸው አይቀርማ! የእኔን ትኩረት የበለጠ የሳበው ግን ጉባኤው እንዳይመስላችሁ! በፎረሙ መጠናቀቂያ ላይ ሦስት የጦቢያዋ “የጋዜጠኞች ማህበራት” ያወጡት “ድንቅ” የአቋም መግለጫ ነው። (ሦስቱ ማህበራት ለኢትዮጵያ ብቻ ነው ወይስ ለሶማሊያም?) እናላችሁ … የማህበራቱ መግለጫ የጋዜጠኞች ሳይሆን የ“አብዮታዊ መንግስት” ወይም “ድርጅት” ነበር የሚመስለው፡፡ ከአቋም መግለጫቸው መካከል አንደኛው ደግሞ ከኢህአዴግ ቃል በቃል የተኮረጀ ነው (ኮማ ሳይቀር!) ልዩነቱ ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ በተደጋጋሚ “በኢትዮጵያ ውስጥ ከሙያቸው ጋር በተያያዘ የታሰሩ ጋዜጠኞች የሉም” የሚል ምላሽ ሲሰጥ ደንፍቶ አያውቅም። እነሱ ግን ቀላል ቀወጡት! አገር ይያዝልን እኮ ነው ያሉት፡፡ ቦታው ስላልተመቻቸው ነው እንጂ ሽለላና ቀረርቶ ሁሉ ዳድቷቸው ነበር፡፡

(ኢህአዴግ ራሱ እኮ ሳይታዘባቸው አይቀርም!) እኔማ ምነው በገመገመልኝ ብዬ ነበር፡፡ ለካስ የኢህአዴግ አባል አይደሉም (ናቸው እንዴ?) የጋዜጠኞች ማህበራቱ ሁለተኛው የአቋም መግለጫ ደግሞ “በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት ከየትኛውም የአፍሪካ አገራት የበለጠ ተከብሯል” የሚል ነው፡፡ ይሄኛውም በድንፋታና በጩኸት የታጀበ ነበር፡፡ ይሄን የሰሙ የአፍሪካ ጋዜጠኞችና የሚዲያ መሪዎች አገራቸው እስከሚገቡ እንዴት እንደሚቸኩሉ አልታያችሁም? (ለመሳቅ እኮ ነው!) እንኳን እነሱ ኢህአዴግም ይሄኔ በመግለጫው ፍርስ ብሏል (አይነግረንም እንጂ!) እውነቴን እኮ ነው … መንግስት ራሱ “በአገራችን የፕሬስ ነፃነት ሙሉ በሙሉ ተከብሯል” ብሎ አያውቅም፡፡ (ከየት አመጡት ታዲያ?) በነገራችሁ ላይ … የአፍሪካ ሚዲያ መሪዎች ፎረም መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ … መንግስታቸው፤ በኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ ለውጥና ማሻሻያ እንደሚያደርግ ተናገሩ እንጂ “የፕሬስ ነፃነታችን እንከን የለሽ ነው!” ብለው አልተመፃደቁም፡፡ “ዲሞክራሲውም … ነፃ ፕሬሱም … የሰብአዊ መብት አያያዙም ወደፊት ከልማቱ ጋር እየተሻሻለ ይሄዳል” ነው - የኢህአዴግ አቋም፡፡ (“ከጳጳሱ በላይ አማኝ” አሉ!) የጋዜጠኞች ማህበራቱ ጉዳይ በዚሁ ቢያልቅ “ተመስገን” ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት ምሽት ደግሞ “የነፃ ጋዜጠኞች ማህበር” ፕሬዚዳንትና ጋዜጠኛ ሳምሶን ማሞ ይሄንኑ ጉዳይ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያብራሩ ተጋብዘው ነበር - በኢቴቪ፡፡

የሚገርመው ታዲያ የምሽቱ አጀንዳ “በኢትዮጵያ የታሰሩ ጋዜጠኞች አሉ የሉም” ወይም “የፕሬስ ነፃነት ተከብሯል አልተከበረም” የሚለው አልነበረም። የአገር ሉዓላዊነት ማስከበር፣ አንድነትና ነፃነትን ማስጠበቅ ወዘተ … ሆነና አረፈው (የአቋም መግለጫ በማውጣት “አርበኝነት” የለም እኮ!) የኢቴቪ ጋዜጠኛው (ጋባዡ ማለት ነው) ታደሰ ሚዛን፤ ለጋዜጠኞች ማህበሩ ፕሬዚዳንት አስገራሚ ጥያቄ አቀረበ (ሃሳቡን እንጂ ቃል በቃል አይደለም!) “በቀጣይ እንደ CPJ ያሉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ነን ባዮች ‘በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ታስረዋል፣ የፕሬስ ነፃነት ታፍኗል’ እያሉ የሚያወጡትን መግለጫ እንዴት መከላከል ይቻላል?” ፕሬዚዳንቱም አስገራሚ ምላሽ ሰጠ፡፡ “ፅናትና መስዋዕትነት ይጠይቃል” በማለት፡፡ የምን ፅናት ነው? የምንስ መስዋዕትነት? እውነቱን መናገር እኮ በቂ ነው - እንደ ኢህአዴግ፡፡ (እውነት አንፃራዊ መሆኗ እንዳይረሳ!) ሁለቱን ጋዜጠኞች ወይም የ “ነፃ ጋዜጠኞች” ተወካዮች በኢቴቪ የጋበዘው ጋዜጠኛ፤ አንድ ነገር ግን ሳይሸወድ አልቀረም፡፡ (“አውቆ በድፍረት ሳያውቅ በስህተት” ሊሆን ይችላል!) ምን መሰላችሁ? የጋዜጠኞች ማህበራት ያወጡትን መግለጫ፣ የአገርን አንድነት (ዳር ድንበር) እንደማስከበር ነው የቆጠረው፡፡

(በአቋም መግለጫ “አንድነት” ተከብሮ አያውቅም እኮ!) እናም … ማህበራቱ ወደፊትም ተመሳሳይ መግለጫ በማውጣት የአገሪቱን አንድነት ለማስጠበቅ ይጥሩ እንደሆነ ጠየቀ - ወደ ውይይቱ መጠናቀቂያ ላይ፡፡ (ወይ ፍሬን መበጠስ!) መልሱም “ፍሬን የበጠሰ” ስለሆነ ትቼዋለሁ፡፡ አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ሦስቱ የጋዜጠኞች ማህበራት ዓላማ ምንድን ነው? (የጋዜጠኞችን መብት ማስከበር እንዳይሉኝ ብቻ!) “ኢህአዴግ ማረኝ” ማለት ይሄኔ ነው፡፡ (“የባሰ አለና አገርህን አትልቀቅ” አሉ!) እናንተ … እኔም ፖለቲካዊ ወጌን በአቋም መግለጫ ልቋጨው ዳድቶኝ ነበር፡፡ (አንድዬ እኮ ነው ያዳነኝ!) በሉ ሰሞኑን በቴክስት የደረሰኝን “ቧልት” ላካፍላችሁና ልሰናበት፡- “ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ዕቅድ ጉባኤ ላይ የተሳተፈችና የቡራዩን የስነ ተዋልዶ ጤና ኤክስቴንሽን የጐበኘች አንዲት አሜሪካዊት፣ በተለይ ለኢቴቪ በሰጠችው ቃለ ምልልስ፤ ‘ምነው እኔም ኢትዮጵያ ውስጥ በወለድኩ’ ስትል አድናቆቷን ገለፀች” (ማንም ምንም ቢል የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ እንደሆነ መሳካቱ አይቀርም!!) ድል ለዋልያዎቹ!!

Read 4293 times