Saturday, 16 November 2013 14:13

የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በውሀ ችግር ሰልፍ አካሄዱ

Written by  ማህሌት ፋሲል
Rate this item
(2 votes)

ዩኒቨርስቲዎች የውሃ እጥረት ለማቃለል እየጣርን ነው ብለዋል

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በውሃ እጦት ረቡዕ እለት ሰልፍ ከወጡ በኋላ በርካታ ተማሪዎች የታሰሩ ሲሆን፤ ለሦስት ሳምንት ውሃ መቋረጡን በመቃወም የተሰበሰቡ የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የግቢው ጥበቃ እንደበተናቸው ተገለፀ፡፡ በአቃቂ የሚገኘው የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም በውሀ እጦት መቸገራቸውንና ሰሚ ማጣታቸውን ተናግረዋል። የዩኒቨርሲቲዎቹ አስተዳደሮች በበኩላቸው፤ ውሃ ጨርሶ ጠፍቷል መባሉ የተጋነነ አባባል ነው በማለት፣ የውሃ እጥረት ለማቃለል እየጣሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በውሃ እጦት የተነሳ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳካሄዱ የተናገሩ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ረቡዕ ማታ የከተማዋ ፖሊስ የዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ በመግባት በርካታ ተማሪዎችን እንዳሰረ ገልፀዋል፡፡ በማግስቱ የተወሰኑ ተማሪዎች ከእስር መለቀቃቸውንና ግቢው መረጋጋቱም ተነግሯል፡፡

ውሃ ካጣን ሦስት ሳምንት ሆኖናል የሚሉት የአዳማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በበኩላቸው፤ የዩኒቨርስቲ አስተዳደር መፍትሔ ሊሰጠን አልሞከረም ብለዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች ተሰባስበው ሁለት ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሲሞክሩ በግቢው ፖሊሶች እንደተበተኑ ተማሪዎቹ ጠቅሰው፤ አንድ ጄሪካን ውሃ ለመቅዳት ከሶስት ሰዓት በላይ ለወረፋ እንቆማለን ብለዋል፡፡ በሁለት ቀን አንዴ ውሃ ታገኛላችሁ ተብለን በዩኒቨርስቲው አስተዳደር ፕሮግራም ቢለጠፍም፤ በተባለው ቀን ውሃ አግኝተን አናውቅም ያሉት ተማሪዎቹ፤ ለንጽህና ቀርቶ የመጠጥ ውሃ የምናገኘው በግዢ ነው ብለዋል።

የዩኒቨርስቲው የአለም አቀፍና የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተር አቶ ታጉ ዘርጋው፤ የውሃ ችግር የተከሰተው በዩኒቨርስቲው ውስጥ ብቻ ሳይሆን በከተማው ሁሉ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ዩኒቨርስቲው ለሃያ ሺ ተማሪዎች ውሃ የሚያቀርበው የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር ጭምር ነው ብለዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ውሃ የለም መባሉ ግነት ነው ያሉት አቶ ታጉ፣ ያለውን ውሃ አብቃቅተን ለማዳረስ ብንሞክርም በተለያዩ ምክንያቶች እጥረት ተከስቷል ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የአቃቂ ግቢ ተማሪዎችም የውሀ ችግር እየተባባሰ መሆኑን ገልፀው፤ በአቃቂ አካባቢ ውሀ እያለ ግቢ ውስጥ ግን በሦስት ቀንም እንደልብ አይገኝም ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታረቀኝ ታደሰ፣ የውሀ ችግር መኖሩን ጠቅሰው፣ ውሃ ለበርካታ ቀናት ይቋረጣል መባሉ የተሳሳተ መረጃ ነው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለሰአታትም ሲሆን ውሀ መቋረጥ እንደሌለበት ዩኒቨርስቲው ያምናል ያሉት ዶ/ር ታረቀኝ፤ ውሀ ሁሌ እንዲኖረን ማድረግ የሚችሉት የውሀና ፍሳሽ ተቋማት ናቸው፤ በበኩላችን ችግሩን ለመቅረፍ አመቺ ቦታ መርጠን፤ ለቦታው ካሳ ከፍለን የውሀ ማከማቻ ታንከር በማስቀመጥ ውሃ እንዳይቋረጥ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የውሃ ጉድጓድ ለመጠቀም ሶስት የውሃ መሳቢያ ሞተሮች አስመጥተናል ብለዋል፡፡

Read 2013 times