Saturday, 16 November 2013 14:04

“ዋልያዎቹን ከናይጄሪያ በክብር አንቀበላቸው” - ቴዲ አፍሮ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾችን (ዋልያዎቹን) ለመደገፍ ባለፈው ረቡዕ ከባለቤቱ አምለሰት ሙጬ ጋር ወደ ካላባር ናይጄርያ የተጓዘው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን፤ ከጨዋታ መልስ የጀግና አቀባበል ይገባቸዋል አለ፡፡ ከሳምንት በፊት “መሬት ሲመታ” የተሰኘውን ሙዚቃ ቪድዮ ለዋልያዎቹ በመስጠት ለአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው መፅሃፍት ያበረከተው ቴዲ አፍሮ፤ ሙዚቃውን የሰራው አድናቆቱን ለመግለጽና ለማበረታታት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ የሙዚቃው ግጥምና ዜማ የቴዲ አፍሮ ፈጠራ ሲሆኑ፣ የሙዚቃ ቪዲዮውን ያዘጋጀችው ባለቤቱ አምለሰት እንደሆነች ይታወቃል፡፡

ቴዲ አፍሮ ከዋሊያዎቹ ጋር ሲገናኝ የሰሞኑ ጉብኝት የመጀመሪያው እንዳልሆነ የገለፁት የድምፃዊው ተወካይ ጌታቸው ማንጉዳይ፤ አምኖ ዋልያዎቹ የቴዲ አፍሮ ተጋባዥ እንግዶች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ ብሔራዊው ቡድን ከ31 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በመጨረሻው ጨዋታ ዋዜማ ቴዲ አፍሮ በጊዮን ሆቴል ባዘጋጀው ኮንሰርት “ብታሸንፉም ባታሸንፉም የክብር እንግዶቼ ናችሁ” ብሎ ዋልያዎቹን ጋብዟቸው ኮንሰርቱን ታድመዋል።

በዋሊያዎቹ ስኬት መደነቁንና መመሰጡን ቴዲ አፍሮ ገልፆ፤ ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ በተሳተፉበት ወቅት ኮንሰርት እንዳቀረበና ከዛምቢያ ጋር ያደረጉትን የመክፈቻ ጨዋታ ስታድዬም ገብቶ እንደተመለከተ ይናገራል። ከ5 ወር በፊትም በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባካሄዱት የባህልና ስፖርት ፌስቲቫል ላይ ኮንሰርት ሲያቀርብና ከሙዚቃ ከባንዱ ጋር የዋሊያዎችን ማልያ ለብሶ ለስኬታቸው አድናቆቱን አሳይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከፍ ብሎ በታየበት የስፖርት መድረክ ሁሉ ልዩ ክብርና ኩራት ይሰማኛል ያለው ቴዲ አፍሮ፤ “ዋልያዎቹ በዓለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያንን አንድ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ አዲስ ተስፋም ፈጥረዋል። በማንኛውም ውጤት ወደ አገራቸው ሲመለሱ የጀግና አቀባበል ይገባቸዋል ብሏል - ቴዲ አፍሮ ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ በኮካ ኮላ ኩባንያ ለቀጣዩ የፊፋ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ከሚያሰሩ ይፋዊ ዘፈኖች መካከል የአፍሪካውን ድርሻ እንዲሰራ መመረጡ መመረጡ የሚታወቅ ሲሆን፤ የዘፈኑ ቀረፃ በኬንያ ተከናውኖ ሲሆን በቅርቡ በመላው ዓለም ለአድማጮች እንደሚቀርብ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በካላባር ከተማ ለሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ባለፈው ረቡዕ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቻርተር አይሮፕላን ከተጓዙት 215 ኢትዮጵየውያን መካከል፤ 60 ያህሉ የዋልያ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ ለአውሮፕላን ትኬት 28ሺ ብር የከፈሉት ደጋፊዎች፣ በናይጄሪያ ቆይታቸው ወደ 40ሺ ብር ገደማ ወጪ እንደሚያደርጉ ተገልጿል፡፡

Read 2154 times