Saturday, 09 November 2013 12:00

የስፖርት ውርርድ በዳጉ ቤት በኢትዮጵያ ተጀመረ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

በ380ሺ ብር ካፒታል ፤ ከመቶሺ በላይ ተሳታፊና እስከ 10ሺ ብር ሽልማት

            በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአይነቱ ልዩ የሆነ አዲስ የስፖርት ውርርድ ጨዋታ እንደተጀመረ ዳጉ ቤት ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስተዋወቀ፡፡ ዳጉ ቤት ኢትዮጵያ በእንግሊዝና ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ አራት ኢትዮጵያዊያን የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን ለስራው በብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ሙሉ ፈቃድ አግኝቷል፡፡ የስፖርት ውርርዱ በውጭ ሀገር በሚካሄዱ የስፖርት ውድድሮች ላይ ተመስርቶ የተጀመረ ነው፡፡ በስፖርት የተለያዩ ሁኔታዎች በመወራረድ በህጋዊ መንገድ እየተዝናኑ መጫወት ይቻላል የሚለው ዳጉ ቤት፤ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት የገቢ ምንጭ በመፍጠር ለሀገር ጥቅም የሚያስገኝ ስራ እንደሚሆን ተስፋ ያደርጋል፡፡ የስፖርት ውርርዱን በህጋዊ መንገድ መጀመሩ በህብረተሰቡ ዘንድ ህገወጥ በሆነ መንገድ በመወራረድ የሚፈጠሩ አላስፈላጊ ችግሮች እንደሚከላከል የገለፀው ዳጉ ቤት ኢትዮጵያ ከስፖርት ውርርዱ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ሁኔታዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀስም አስታውቋል።

በዚህም በሀገራችን ለሚገኙ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የስፖርት ፌዴሬሽኖች እርዳታ በማድረግ ስፖርቱን ለማሳደግ እንደሚሰራ የገለፀው ድርጅቱ በተቋቋመበት የመጀመሪያው አመትም ከተጣራ ገቢው ሃያ በመቶውን ለቦሊንግ አሶሴሽን እርዳታ ለመስጠት መስማማቱንም አመልክቷል፡፡ የዳጉ ቤት ኢትዮጵያ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ንጋቱ የስፖርት ውርርዱ መሸነፍ እና ማሸነፍ ያለበት ጨዋታ መሆኑን ሲያስረዱ ተጨዋቾች እና ተሳታፊዎች የስፖርት ውድድሮችን በመመልከት ከሚኖራቸው መዝናናት ባሻገር በሚሰጡት ግምት ተሸላሚ የሚሆኑበትን እድል በመፍጠር እንዲሰራ እና አካሄዱም በህግና ስርዓት የተመራ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡ ዳጉ ቤት ኢትዮጵያን የጀመርነው እንደፓይለት ፕሮጀክት ነው የሚሉት አቶ አብርሃም ንጋቱ፤ የስፖርት ውርርዱን የጀመርነው በለጋሃር አካቢ በሚገኘው ሱቅ እና በድረገፅ በሚደረግ ግንኙነት ነው ብለው ማጫወት የጀመርነው በእግር ኳስ ቢሆንም ወደፊት የቅርጫት ኳስ እና የአትሌቲክስ ውድድሮችንም በማወራረድ ለማጫወት እናስባለን ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ወደፊት የውርርዱን መንገድ በአጭር የፅሁፍ መልዕክት እና በሚፋቁ የሎተሪ ካርዶች ለማድረግ እቅድ መኖሩን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንን በመወከል በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገኝተው የነበሩት የውድድሮች የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ተድላ ዘመናዊ ውርርድ በኢትዮጵያ ስፖርት መጀመሩ እንደሚያስደስት ገልፀው፤ ዳጉ ቤት ኢትዮጵያ ባለድረሻ አካላት ከሆኑት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንና የፌደራል ስፖርት ኮሚሽን ግልፅ በሆነ መንገድ ተግባብቶ መስራት እንደሚኖርበት መክረው አወራራጁ ድርጅቱ ስራውን ሲጀምር በውጭ ውድድሮች ላይ ከሚያተኩር ለአገር ውስጥ ውድድሮች ቅድሚያ ቢሰጥ የተሻለ ነበር ብለዋል፡፡ ለነገሩ ዳጉ ቤት ኢትዮጵያ የስፖርት ውርርዱን በውጭ አገር ውድድሮች መጀመሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውንና የስፖርት ጋዜጠኞችንም አላስደሰተም፡፡ የብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የስፖርት ውርርድ እጅግ አትራፊ ቢዝነስ መሆኑን ተናግረው ዳጉ ቤት ኢትዮጵያ የውርርድ ስርዓቱን በአገር ውስጥ ውድድሮች በተለይ የፕሪሚዬር ሊግ ክለቦችን በማሳተፍ ቢጀመር ምርጫዬ ነበር ካሉ በኋላ ‹‹ውርርድ ካለ የምመርጠው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ነበር፡፡

ይህን ለማሳካት ትኩረት ሰጥታችሁ መስራት አለባችሁ፡፡ እግር ኳሱ በተነቃቃ መንፈስ እንዲቀጥል፤ በወጣቶች ላይ በስፋት እንዲሰራ እና ክለቦች የገቢ ምንጮቻቸውን እንዲያሰፉ በሚያደርግ አሰራር ብትንቀሳቀሱ ጥሩ ነው፡፡ ከእነ አርሰናል አስቀድመን ለኢትዮጵያ ክለቦች ማሰብ ይገባል፡፡ የክለቦች መጠናከር ለብሄራዊ ቡድን ድጋፍ እንደሚሆን መታወቅ አለበት፡፡ በማለት ሃሳባቸውን አስረድተዋል። ከጋዜጠኞች መካከልም የዳጉ ቤት ኢትዮጵያ የስፖርት ውርርድ በውጭ አገር ውድድሮች መጀመሩ የአገር ውስጥ ውድድሮች የሚያስፈልጋቸውን ትኩረት ሊያሳጣ አይችልም ወይ በሚል ስጋት የቀረበ ጥያቄም ነበር፡፡ የዳጉ ቤት ኢትዮጵያ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ንጋቱ በእነዚህ ሃሳቦች ላይ በሰጡት ምላሽ የስፖርት ውርርዱን በአገር ውስጥ ውድድሮች ለመጀመር የቅርብ ጊዜ እቅድ አለመኖሩን ሲገልፁ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ የእግር ኳስ ውድድሮች ባላቸው የፉክክር ደረጃ እና ሂደት ለውርርድ በሚያመች ሁኔታ ላይ አለመገኘታቸውን በመጥቀስ የጨዋታዎችን ውጤት በህገወጥ ሁኔታ ለመቀየር የሚያስገድዱ ጥፋቶች በዚህ ምክንያት ሊያጋጥሙ መቻላቸው ሌሎች ችግሮችን ሊያመጣ መቻሉን አስበን የተውነው ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የእግር ኳስ ውድድሮች ለስፖርት ውርርድ አመቺ ሊሆኑ እስከሚችሉበት አስተማማኝ የእድገት ደረጃ ግን ድጋፍ በማድረግ አብረን እየሰራን እንቀጥላለን በማለትም ምክትል ስራ አስኪያጁ ቃል ገብተዋል፡፡

በጋዜጣዊው መግለጫ ላይ ተገኝተው የነበሩት የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ተወካይ የስፖርት ውርርድን ለማካሄድ የሚያስችል መመርያ በኢትዮጵያ መንግስት የፀደቀው ባለፈው ዓመት መሆኑን ሲገልፁ ፍቃድ የሚያገኙ ድርጅቶች በህግ ማዕቀፍ ሆነው ውርርዱን እንዲያጫውቱ እንደሚደረግና የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር አፈፃፀሙን በመከታታል በመቆጣጠር አብሮ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ የስፖርት ውርርድ በህጋዊ መንገድ ማከናወን ሊያጋጥሙ የሚችሉ ማህበራዊ ቀውሶችን ለመከላከል አስተዋፅኦ እንዳለው ያስገነዘቡት የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ተወካይ ፤ ውርርዱን ለሚያደርግ ተቋም ፈቃድ የምንሰጠው ባለን መመርያ መሰረት ድርጅቱ ከሚያገኘው አጠቃላይ ገቢ የመንግስት 50 በመቶ ድርሻን እንዲከፍል፤ ለማህበራዊ ግልጋሎት ቢያንስ 20 በመቶ ያህል እንዲያበረክት እንዲሁም ውርርዱን ያለምንም ቅሬታዎች እና ችግሮች በትክክል እንዲያከናውን በማሳሰብ ነው ብለዋል፡፡ የትኛውም ድርጅት፤ ተቋም ወይም ግለሰብ ለስፖርት ውርርድ ህጋዊ ፈቃድን ማግኘት እንደሚችል ያስረዱት የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ተወካይ ፤ የሚሰጠው ፍቃድ በየዓመቱ የሚታደስ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የስፖርት ውርርድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተስፋፋ ሲሆን ገበያው 70 በመቶ የሚያተኩረው በእግር ኳስ ስፖርት ላይ ነው፡፡ በመላው ዓለም የሚደረጉ የስፖርት አወራራጅ እና አቋማሪ ኩባንያዎችን በመገምገም በየዓመቱ ከ55ሺ በላይ የስፖርት ግጥሚያዎችን የሚከታተለው ስፖርት ራዳር የተባለ ተቋም ይፋ ባደረገው መረጃ ኢንዱስትሪው በየዓመቱ ከ700 ቢሊዮን ዶላር እንደሚንቀሳቀስበት አመልክቷል፡፡

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በዓለም አቀፍ አቋማሪ እና አወራራጅ ድርጅቶች ተመራጭ መሆኑን የሚገልፁ መረጃዎች ክለቦች ከ19 የተለያዩ ኩባንያዎች ጋር በአጋርነት በመስራት በዓመት በአማካይ እስከ 6 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያገኙ ነው፡፡ በ80 የብሮድካስት ኩባንያዎች ዓለም አቀፍ የስርጭት ሽፋን ያለው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከሚሰሩ አቋማሪ እና አወራራጅ ድርጅቶች በአርሰናል ፓዲ ፓወር፤ በቼልሲና በማንችስተር ሲቲ 188ቤት እንዲሁም በማንችስተር ዩናይትድ ቢዊን በአጋርነት መስራታቸው ይጠቀሳል፡፡ ዳጉ ቤት ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የማጫወቻ ሱቅ ለገሃር ኮሜርስ አካባቢ ከኖክ ማደያ አጠገብ መክፈቱን የገለፁት አቶ አብርሃም ንጋቱ ፤ ዳጉ ቤት ዶት ኮም (www.DagooBet.com) ዌብ ሳይት ኦን ላይን በመጠቀም መጫወት እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡ ውርርዱ የሚካሄድባቸው መንገዶች - አሸናፊውን ቡድን በመገመት መወራረድ - ትክክለኛ ውጤት በመገመት መወራረድ - የጨዋታውን የመጀመሪያ አጋማሸ ውጤት በመገመት መወራረድ - ቀድሞ ጐል የሚያስቆጥረውን ክለብና ተጫዋች በመገመት መወራረድ - የማስጠንቀቂያ ካርድ የሚመለከቱ ተጫዋቾችን በመገመት መወራረድ - እንዲሁም በሌሎች መጫወት ይቻላል ህግጋት እና መመሪያዎች - በ90 ደቂቃ የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድር ውጤት መወራረድ ይችላሉ፡፡

- ነገር ግን ውርርዱ የተጨማሪ ሰዓት (30 ደቂቃ) እና የመለያያ ምትን አያጠቃልልም፡፡ - ሁሉም ውርርድ የሚካሄደው ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ይሆናል - 1,X,2 እነዚህ ለውርርዱ የምንጠቀምባቸው ኮዶች ሲሆኑ የሚወክሉልን ጨዋታው ይዞት ሊመጣ የሚችለውን ሦስት አይነት ውጤት ነው፡፡ - 1 ባለሜዳው ያሸንፋል X ቡድኖቹ አቻ ይወጣሉ 2 ከሜዳው ውጪ የሚጫወተው ያሸንፋል፡፡ ስለዚህ በውርርዱ ላይ መሳተፍ የሚፈልግ አንድ ሰው ቢያንስ 3 ጨዋታዎች ቢበዛ ደግሞ 10 ጨዋታዎች ላይ መወራረድ ይችላል፡፡ ለምሳሌ 1 X 2 አርሰናል vs ከማንችስተር 2፡10 3.30 2.90 ሳውዝሃፕተን vs ከፉልሃም 1.80 4.05 3.90 ቶትንሃም vs ኒውካስትል 3.60 3.10 2.75 እርስዎ የመረጡት ከመጀመሪያው ጨዋታ አርሰናል ያሸንፋል ከሆነ ኮድ 1 ሲሆን ያለውም ዋጋ 2.10 ይሆናል በሁለተኛው ጨዋታ ሳውዝሃፕተን ያሸንፋል ብለው መወራረድ ከፈለጉ ኮዱ 2 ሲሆን ያለውም ዋጋ 2.90 ይሆናል ሦስተኛው ጨዋታ በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል በለው መወራረድ ከፈለጉ የውርርድ ኮዱ X ሲሆን የውርርድ ዋጋውም 3.10 ይሆናል፡፡ እንበልና ከላይ የመረጡት ሶስቱንም የጨዋታ ውርርድ አሸነፉ፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው እያንዳንዱ ውረርድ የራሱ የሆነ ዋጋ አለው ስለዚህ በሶስቱም አሸናፊ ስለሆኑ የሶስቱንም ዋጋ እናበዛለን ይኸውም 2.10 X2.90 X3.10 = 18.87፡፡ መጀመሪያ ላይ ለውረርድ ያስያዙት 10 ብር ቢሆን ከላይ የተመለከተውን የሶስት ጨዋታዎች ዋጋ ብዜትን ማለትም 18.87 ባስያዙት ገንዘብ (10 ብር) በማባዛት የ188.70 አሸናፊ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን ይህ የጨዋታውን ግብር አያጠቃልልም፡፡ ማሳሰቢያ ከተወራረዱ በኋላ የሚሰጥዎትን ደረሰኝ በጥንቃቄ ይያዙ፡፡ አሸናፊ ከሆኑ ደረሰኙን ይዘው በቀረቡ ጊዜ ያሸነፉት ገንዘብ ይከፈልዎታል፡፡

Read 10250 times