Saturday, 09 November 2013 11:52

በዓለም ታላላቅ ማራቶኖች ሊግ እንደፀጋዬ ነጥብ የሰበሰበ የለም

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

         ኢትዮጵያዊው ማራቶኒስት ፀጋዬ ከበደ በዓለም ታላላቅ ማራቶኖች ሊግ (World Marathon Majors) ባለፉት 5 የውድድር ዘመናት 186 ነጥብ በመሰብሰብ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበ አትሌት ተባለ፡፡ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው 43ኛው የኒውዮርክ ማራቶን በመሳተፍ በሁለተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ፀጋዬ ከበደ 60ሺ ዶላር ከማግኘቱም በላይ በ2012 /13 የውድድር ዘመን የዓለም ታላላቅ ማራቶኖች ሊግን በአንደኛ ደረጃ በመጨረስ የ500ሺ ዶላር ተሸላሚ ሆኗል፡፡ የ26 ዓመቱ አትሌት ፀጋዬ ከበደ የማራቶን ሊጉን ያሸነፈው በ2012 እኤአ በለንደን ማራቶን በ3ኛ ደረጃ 10 ነጥብ፤ በ2012 እኤአ በቺካጎ ማራቶን በአንደኛ ደረጃ 25 ነጥብ፤ በ2013 በቺካጎ ማራቶን በአንደኛ ደረጃ 25 ነጥብ እንዲሁም ባለፈው ሳምንት በኒውዮርክ ማራቶን በሁለተኛ ደረጃ 15 ነጥብ አስመዝግቦ በአጠቃላይ ድምር 75 ነጥብ በማግኘቱ ነበር፡፡

አትሌት ፀጋዬ ከበደ በዓለም ታላላቅ ማራቶኖች ሊግ ከ1 እስከ 3 ባለው ደረጃ ለ10 ጊዜያት በመግባት ብቸኛው ማራቶኒስት ሲሆን ባለፉት አራት የውድድር ዘመናት በ2008 /09 በ35 ነጥብ አምስተኛ፤ በ2009 /10 በ65 ነጥብ ሁለተኛ፤ በ2010 /11 በ51 ነጥብ አራተኛ እንዲሁም በ2011 /12 በ46 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ በማግኘት ሲፎካከር የቆየ ነበር፡፡ ስለ ፀጋዬ ምርቃት - በ14 ትልልቅ የማራቶን ውድድሮች ከ2 ሰዓት ከ10 ደቂቃዎች በታች በመግባት ከዓለማችን ምርጥ ማራቶኒስቶች ተጠቃሽ ነው፡፡ - ምርጥ ሰዓቱ በ2012 እኤአ ላይ በቺካጎ ማራቶን ሲያሸንፍ ርቀቱን በ2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ38 ሰኮንዶች የሸፈነበት ነው፡፡ - በኦልአትሌቲክስ ድረገፅ መረጃ መሰረት በዓለም የማራቶን አትሌቶች የምንጊዜም ውጤታማነት ደረጃ በ1333 ነጥብ 4ኛ ነው፡፡

- በ2007 እኤአ ላይ ከፍተኛ አልቲትዩድ ባላት አዲስ አበባ የመጀመርያ የማራቶን ውድድሩን የአበበ ቢቂላ ማራቶንን በ2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ53 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ አሸንፎ ነበር። ከ2007 ጀምሮ በትልልቅ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች መሳተፍ ጁምሯል፡፡ በ2008 እኤአ የፓሪስ ማራቶንን ፤ በ2008 እኤአ እና በ2009 እኤአ በጃፓኑ የፉካካ ማራቶን፤ በ2010 እና በ2013 እኤአ የለንደን ማራቶንን፤ በ2012 እኤአ ደግሞ የቺካጎ ማራቶንን አሸንፏል፡፡ በ2008 እኤአ በቤጂንግ ኦሎምፒክ፤ በ2009 እኤአ ላይ በበርሊን የዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም በ2012 እኤአ ላይ በለንደን ኦሎምፒክ በማራቶን ሶስት የነሐስ ሜዳልያዎችን ነው የሰበሰበው አትሌቱ በ2013 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አራተኛ ደረጃ ነበረው፡፡

Read 2166 times