Saturday, 09 November 2013 10:27

በሌላ ሰው እጅ እሳት መንካት አያስፈራም! (የኦሮምኛ ተረት)

Written by 
Rate this item
(8 votes)

            ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንዲት አይጥ ወደ አያ ዝሆን ሄዳ ልጁን ለልጇ እንዲድርላት ጠየቀችው። አያ ዝሆንም፤ “እንዴት ባክሽ? እንዴት ብትደፍሪኝ ነው ልጄን ለልጅሽ የተመኘሻት?! እኔ ማን እንደሆንኩ አታውቂም ማለት ነው፡፡ ከእንስሳት ሁሉ ግዙፉና ጠንካራው እኔ ነኝ፡፡ ጥርሴ ልዩ ዋጋ ያለው አንጋፋ አባት ነኝ፡፡ የአንድ ሙሉ ጫካ ዛፍ ገለባብጬ ለመጣል እችላለሁ፡፡ እና ለአንድ አይጥ ለሚባል ጉድጓድ ውስጥ ለሚኖር ፍጡር፣ ለዚህ ደቃቃ ፍጡር ልጄን የምድር ይመስልሻል? ልጄንማ እንዲህ አድርጌ አላዋርዳትም!” አላት፡፡ አይጢትም፤ “ባለነጭ ጥርሱን ዝሆን ምንም ደቃቃ ብሆን የምጠቅመው ቀን ይመጣል” አለችው፡፡ አያ ዝሆንም በንቀት፤ “አንቺን ዓይነት ደቃቃ ለእኔ ዓይነት ግዙፍ እንስሳ ምን ሊያደርግ እንደሚችል አሁኑኑ ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡

አለበለዚያ ስለ ድፍረትሽ እግሬ ሥር አስገብቼ እደፈጥጥሻለሁ!” እያለ ወደሷ መምጣት ሲጀምር፤ በድንገት አዳኝ - ፈረሰኞች እየጋለቡ አቧራውን እያስጨሱ መጡ፡፡ አያ ዝሆን እነዚህ የአደን ሰዎች፤ ያንን የሚኩራራበትን ነጭ ጥርሱን ፍለጋ ሊገድሉት እንደሚችሉ በመገመት መደበቂያ ቦታ ይፈልግ ጀመር፡፡ ይሄኔ አይጢቱ፤ “ጌታ ዝሆን! አይዞህ አትፍራ፡፡ አሁን እየመሸ በመሆኑ ጠላቶችህ አያዩህም፡፡ እኔ ግን ችሎታዬን አሳይሃለሁ” አለችው፡፡ “እሺ” ብሎ ጥግ ይዞ ቆመ፡፡ ዕውነቱም ፈረሰኞቹ ስለመሸባቸው በአካባቢው ፈረሶቻቸውን አስረው ተኙ፡፡ ጨለማው ዐይን ሲይዝ አይጢት ሥራዋን ጀመረች፡፡

የኮርቻውን ቀበቶ፣ የድሃራይና ቀዳማይ ማንገቻ፣ የመቀመጫውን ግላሥ፣ የእርካቡን ገመድ፤ በጥርሷ ቀረጣጠፈችው፡፡ ፈረሰኞቹ፤ ጠዋት ፈረሳቸው ላይ ወጥተው አደናቸውን ሊቀጥሉ ሲጋልቡ ኮርቻና እርካባቸው ተበጣጥሶ እየተንሸራተቱ ወደቁ፡፡ እግርና እጃቸው ተሰብሮ አደናቸውን አቋረጡ፡፡ አያ ዝሆን ዛፉን ተደግፎ፣ በአይጢቱ ሥራ ተደንቆ፣ “ዕውነትሽን ነው እመት አይጥ፡፡ ከእኔ ጥርስ ያንቺ ጥርስ እንደሚሻል ገባኝ፡፡ ለትልቁ እንስሳ ትንሿ እንስሳ ልትጠቅመው እንደምትችል አስተዋልኩ፡፡ “በቃ ልጄን ለልጅሽ እድርለታለሁ” አላት፡፡

                                                       * * *

ትልቅ ነን የምንል ሹሞች፤ ባለሥልጣናት ወይም የበላይ አካላት፤ ትናንሾች ናቸው ብላችሁ የምታስቧቸውን የበታች አካላት አትናቁ! ትንሹም አቅም አለውና፡፡ አበሻ ጋን በጠጠር ይደገፋል ይላል! ጋን በክብ መቀመጫው ለመቆም ምን ያህል እንደሚቸገር መረዕየት (Visualize የማድረግ) አቅም ብቻ ነው የሚጠይቀው፡፡ በፓርቲ ሰውነት፤ በመንግሥት ሹመኛነት፣ በትምህርት “ማዕረግ”፣ በውትድርና የበላይነት፣ በሊቀመንበርነት ነጭ ጥርስ ያለን ግዙፍ አካል ነን ለማለትና ለመገበዝ መሞከር፤ ክፉ ቀን ሲመጣ የት ልደበቅ ማለት ምን ያህል እንደሚያሸብር የትልቁ ዝሆን ታሪክ ሁነኛ ነገር ነው፡፡ ላፎንቴን ገጣሚው፤ “ድርጭትና ተራራው” በሚለው ግጥሙ - “ይህ ኩራትና ግብዝነት፣ መቼም የትም አያደርስህ እንዳንተ ትልቅ ባልሆንም፤ እንደኔ ትንሽ አደለህ!” የሚለው ይሄንኑ ዕውነታ ለማፀህየት ነው፡፡ ተፎካካሪዎችን መናቅ፣ ተቃዋሚዎችን መናቅ ከግዝፈት እሳቤ የመጣ ከሆነ ራስን ያለማየት ችግር እንዳለ ነው የሚያስገነዝበን፡፡ ወጣት ልጆቻችን የትምህርት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አጠያያቂ አይደለም፡፡

ትምህርት ተማሩ የሚባለው የሚማሩበት ከባቢ አየር ጤናማ ሲሆን ነው፡፡ የትምህርቱ ጥራትና ክብደት፣ መምህሩ፣ የጽዳት ሠራተኞቹ፣ የትምህርት መሣሪያዎቹ፣ የመጫወቻ ሜዳዎቹ እና የመጫወቻ ክፍለ ጊዜያቱ፣ የማጠናከሪያ ትምህርቱ፣ የወላጅ መምህርና ተማሪ ስለስተ ጥምረቱ፡፡ ዛሬ ጥያቄ ውስጥ ነው፡፡ አንዱ ሲሳካ ሌላው እያነከሰ ወላጆችን እያስጨነቀ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ሸፍተው የሚውሉባቸው ቦታዎች እጅግ ዘግናኝ ገጽታ ነው ያላቸው፡፡ ያለዕድሜያቸው በሱስ ይጠመዳሉ፡፡ ያለ ዕድሜያቸው ያልተፈለገ እርግዝና ሰለባ ይሆናሉ።

ት/ቤቱም ወላጁም የዚህ ዕውቀት የለው አይመስሉም፡፡ ስለተረካቢ ትውልድ የምናስብ ከሆነ ይህን አሰቃቂ ዕውነታ ተቀብለን አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ አለብን! ዛሬ የማይናገር አፍ፣ ራስ - አቀብ (Self –censored) አፍ፣ የፈራ አፍ እንዳለ ሁሉ፤ ቀን አመቸኝ ብሎ የሚቀላምድ አፍ፤ የባለቤቱ ልጅ ነኝ ብሎ ዘራፍ የሚል አፍ፣ እኔ ብቻ ነኝ የተማርኩ የግድህን ስማኝ የሚል አፍ፤ የሚሰማውና የሚታዘበው አድማጭ ያለ የማይመስለው ዋልጌ አፍ ብዙ አፍ አለ፡፡ ህገመንግስት በዘፈቀደ የሚተረጐም ከሆነ፤ ቅጡን ያጣና አፍራሹና ፈራሹ የማይታወቅበት ሥርዓተ አልበኝነት እንዳይፈጠር ሥራዬ ብሎ ማጤን ተገቢ ነው፡፡ ህገ -መንግሥት አላዋቂ የሚጭበረበርበት፤ ጮሌ እንዳሻው እኔን ብቻ ስሙ የሚልበት መሆን የለበትም፡፡

የመመሪያዎች ግልጽነት ህብረተሰብን ከመወናበድ እንደሚያድን አንድ ሁለት የለውም። ወቅታዊ መግለጫዎች ራስ - አድን በመሆናቸው ይበረታታሉ፡፡ መንገድ እንደሚዘጋ ያወቀ አሽከርካሪ ካልሆነ ወጪና የጊዜ ኪሣራ ይድናል፡፡ ሚዲያዎቻችን ወቅታዊ መረጃ ማቅረብ ግዴታቸው ሆኖ ሳለ በሌሎች ዜናዎችና ዘገባዎች ከተጠመዱ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” እንዳይሆኑ ሥጋት አለ፡፡ ሁኔታዎች ተባብሰው የማይቀለበሱበት ደረጃ እስኪደርሱ መጠበቅ ቢያንስ የዋህነት ነው አንተ ነህ አንተ ነህ በሚል ሰበብ መሸጋገር የአፍታ ጠቀሜታ ብቻ ነው ያለው፡፡ ጥቅም ያለው ነገር ሲሆን ራስን ማጨት፤ የከፋ ነገር ሲመጣ ሌላውን መመደብ፤ ቢያንስ ጊዜ ያለፈበት ታክቲክ እንደሆነ እንረዳ፡፡ “በሌላ ሰው እጅ እሳት መንካት አያስፈራም!” የሚለውን ተረት የአዘቦቱ ሰውም ይረዳዋል፡፡

Read 4695 times