Saturday, 26 November 2011 09:13

ከ40 ዓመት በፊት የታተመው መፅሃፍ “የባሕርይ አወራረስ”

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

“አንዲት ጥቁር ሲካካ ከአንድ ነጭ አውራ ዶሮ የፈለፈለች እንደሆነ፤ ልጆችዋ በሙሉ ገብስማ ይሆናሉ፡፡ ጫጩቶች ወይ አባታቸውን ወይም እናታቸውን አይመስሉም፡፡ መልካቸው በሁለቱ ወላጆቻቸው መሐከል ነው የሚሆነው፡፡ እነዚህ ጫጩቶች አድገው እርስ በእርሳቸው ቢዋለዱ ልጆቻቸው ሦስት መልክ ይዘው ይመጣሉ፡፡ ጥቂቶቹ የወንድ አያታቸውን (ነጭ) ሲመስሉ፤ ጥቂቶቹ ደግሞ የሴት አያታቸውን (ጥቁር) መስለው ይወጣሉ፡፡ ብዙዎች ግን እንደ ወላጆቻቸው ገብስማ ነው የሚሆኑት፡፡”

መሳ ለመሳ የባሕርይ አወራረስ ምን ውጤት እንዳለው ከላይ የቀረበውን ሀሳብ አስፍሮ የሚያስነብበው “የባሕርይ አወራረስ” በሚል ርዕስ በፍሥሐ ኃይለመስቀል ተዘጋጅቶ በ1960 ዓ.ም የታተመው መጽሐፍ ነው፡፡ ዛሬ በአገራችን በቀዳሚነት በመመሥረታቸው፣ በጥሩ አገልግሎት ሰጪነታቸው፣ ለአገርና ሕዝብ ጠቃሚ በመሆናቸው … ምክንያት “ታላቅ” ተብለው ለመወደስ የበቁ ተቋማት አሉ፡፡ የታላቅነታቸው መነሻ ምን ነበር? ለአጀማመሩ እነማን፣ የት፣ መቼ፣ ምን … ዋጋ ከፍለውላቸዋል? ቀዳሚውን ዋጋ የከፈሉ አካላትስ እንደሚገባው እየታወሱ ነው? በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከሚገኙ ማዕከላት አንዱ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ሲሆን ተቋሙ በዚህ ስያሜ ከመጠራቱ በፊት በመጠሪያ፣ በዓላማና በተግባር ያለፈባቸው የተለያዩ ሂደቶች ነበሩት፡፡ በ1964 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቋቋም “ብሄራዊ የአማርኛ መርሃ ልሳን ድርጅት” ነበር የሚባለው፡፡ ለአማርኛ ቋንቋ ዕድገት እንዲያገለግል ታስቦ የተመሠረተው “ድርጅት”፤ ከመቋቋሙ ከአራት ዓመት በፊት ስለ ጉዳዩ አስፈላጊነት ካሳሰቡት ምሁራን አንዱ “የባሕርይ አወራረስ” መጽሐፍን ያዘጋጁት ደራሲ ፍስሐ ኃይለመስቀል ሲሆኑ ምክንያታቸውን ሲገልፁም፤ “ተፈላጊውን አሳብ የሚገልጹ ቀልጠፍ ያሉ የአማርኛ ቃላት ባለማግኘቴ አንዳንድ የፈረንጅ ቃላት መዋስ ግድ ሆኖብኛል፡፡ አማርኛችን እንዲዳብር የሚጥሩ ይህን ሲያስተውሉ ቅር እንደሚሰኙ አምናለሁ፡፡ እኔ እንደማስበው፣ ስለ ቃላት አወሳሰን አንድ ድርጅት እስኪቆም ድረስ የቃላት መምረጥ ጉዳይ የግል አስተያየት ነው” ብለው ነበር፡፡ ከዚያም በመቀጠል “ለቋንቋ ዕድገት የሚሰራ አካዳሚ እንዲቋቋም አደራ” ብለዋል፡፡ 
መጽሐፉ በተለይ ለአገራችን ከዘመኑ ቀድሞ የታተመ ታላቅ ሥራ ይመስላል፡፡ በቅሎ የማትወልደው ሰማይን በርግጫ መትታ ወደ ላይ ስለገፋችው እግዚአብሔር ረግሟት ነው፤ ላሊበላዎች በሌሊት ተነስተው ካልዘመሩ ይቆመጣሉ፤ ወር የገባ ዕለት ቡና ተፈልቶ አድባሩ ቅቤ ካልተቀባ በሽታ ይከሰታል … የሚሉ አስተሳሰቦች ከንቱ እምነትና ባዶ ፍርሀት ናቸው የሚሉት ደራሲዎች፤ መጽሐፉን ያቀረቡት ሳይንሳዊ ትንታኔዎችን በስዕልና በፎቶግራፍ በማስደገፍ ጭምር ነው፡፡
በባሕርይ አወራረስ ላይ ሳይንሳዊ ጥናት ማድረግ መቼ እንደተጀመረና መጽሐፉ እስኪታተመበት ዘመን ድረስ ያለውን ወቅታዊ መረጃ ለአንባቢያን ያቀረበው መጽሐፉ፤ ዋነኛ ምንጭ አድርጎ የተጠቀመው በዘርፉ ዋናውን ጥናት ያደረጉት የኦስትሪያዊ መነኩሴ አባ ሜንድልን የምርምር ውጤት ነው፡፡ መነኩሴው በዘርፉ ያደረጉትን ጥናት በ1866 እ.ኤ.አ በመጽሐፍ አዘጋጅተው ማቅረባቸውንም ደራሲ ፍሥሐ ኃይለመስቀል ጠቁመዋል፡፡
የቁመት መመሳሰልና መለያየት፣ የመልክ አንድነትና ልዩነት … ያላቸው ሰዎች፣ እንስሳት፣ እጽዋት ሲዋለዱ የሚገኘው ውጤት ምክንያት ምን እንደሆነ፤ እንዲሁም ረጃጅሞች አጭር፣ አጫጭሮች ረጅም ሊወልዱ የሚችሉበትን ሳይንሳዊ ትንታኔ የያዘው “የባሕርይ አወራረስ” የተሰኘ መጽሐፍ፤ እግረ መንገዱን ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር የተያያዘ ብዙ ጉዳዮችን ያነሳል፡፡
ማዳቀል ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ በዘር ብዙ የማይለያዩ እንስሳትን በማዳቀል የተሻለ ፍጡር ማግኘት እንደሚቻል በማሳያነት የቀረበችው በቅሎ ናት፡፡ “በቅሎ የፈረስና የአህያ ባህርያት ስለተዛነቁባት ነው ጠንካራ የሸክም ከብት የሆነችው፡፡” ይላሉ ደራሲው፡፡
የጾታ አወሳሰን፣ የመንትያነት ሚስጢር፣ የሰለጠኑና ያልሰለጠኑ በሚባሉ ሕዝቦች መሐል የተፈጠረው የልዩነት ምክንያትና ስለመሳሰሉት ተያያዥ ጉዳዮች ሰፋ ያለ መረጃ ለመስጠት የሚሞክረው መጽሐፉ፤ የሰው ልጆች በጋብቻ ከመጣመራቸው በፊት የደም ዓይነታቸውን ተመርምረው ቢያውቁ በተለምዶ ሾተላይ የሚባለውን (RH) ችግር ይከላከላሉ ይላል፡፡
“የደም ዓይነት” የሚለው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ ከቀረቡት ሦስት ጥያቄዎች አንዱ አቶ በቀለና ወ/ሮ ብሪቱ ስለሚባሉ ሁለት ባልና ሚስት የጋብቻ ታሪክ ያመላክታል፡፡ ወ/ሮ ብሪቱ ከመጀመሪያ ባላቸው ከአቶ በቀለ ስድስት ጊዜ አርግዘው የመጀመሪያ ልጃቸው ብቻ ደህና ሲያድግ የቀሩት ግማሾቹ ሞተው ተወለዱ፡ግማሾቹ ደግሞ ወዲያው እንደተወለዱ ሞቱ፡፡ በዚህ ምክንያት ጋብቻቸው ፈረሰ፡፡
ወ/ሮ ብሪቱ ለሁለተኛ ጊዜ በመሠረቱት ትዳር የወለዷቸው ልጆች ሁሉም ደህና ሆኑ፡፡ አቶ በቀለም ዳግም በመሠረቱት ትዳር ያፈሯቸው ልጆች ሁሉም ጤነኞች ሆኑ፡፡ በአቶ በቀለና በወ/ሮ ብሪቱ የመጀመሪያ ጋብቻ የተፈጠረው ችግር ከደም ዓይነታቸው ጋር የተያያዘ ነበር የሚለው መጽሐፉ፤ በዚህ መልኩ ባለትዳሮች ከጋብቻ በፊት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይመክራል፡፡
የማንኛውም ፍጡር ባሕርይ ከወላጆች የሚገኝ እንደሆነ በማውሳትም፤ በተፈጥሮ የሚገኝ ባሕርይን ሊለውጡ የሚችሉ እንደ አካባቢ፣ የኑሮ ደረጃ፣ የምግብ ዓይነትና የአየር ፀባይ የመሳሰሉት ለለውጥ መከሰት አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉት ሁሉ የሰካራም ልጅ ሰካራም፣ የነጋዴ ልጅ ነጋዴ ሲሆኑ የምናየው ከተፈጥሮ የባሕርይ አወራረስ ጋር በተያያዘ ሳይሆን አካባቢ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ምክንያት እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎችን እያቀረበ ያብራራል፡፡
የደራሲ ፍሥሐ ኃይለመስቀል “የባሕርይ አወራረስ” ለታተመበት 1960 ዓ.ም ብቻ ሳይሆን ዛሬም ቢሆን ሊነበብ የሚችል መጽሐፍ ነው፡፡ ከ40 ዓመት በፊት የታተመው ይሄ መፅሃፍ፤ እንዲህ የፋና ወጊነት ተግባር ቢያከናውኑም የሚያስታውሳቸው ያጡ በየሙያ ዘርፉ ብዙ ሰዎች እንደነበሩ የሚያመለክት ነው፡፡
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የታተመው መፅሃፉ 96 ገፆች ያሉት ሲሆን የተዘጋጀበት ዋነኛ ዓላማ የሰው፣ የእንስሳትና የእፅዋት ባሕርይና ተፈጥሮ ከአንዱ ወደ ሌላው እንዴት እንደሚተላለፍ ለማሳየት ነው፡፡
በ14 ምዕራፎች የቀረበው መጽሐፍ፤ ለእያንዳንዱ ምዕራፍ ለአንባቢያን የቀረቡ የመወያያ ጥያቄዎችም አሉት፡፡ አልፎ አልፎ በየገጹ የግርጌ ማስታወሻና መጨረሻ ላይ ቃላት መፍቻም አካትቷል፡፡ በመፅሃፉ መግቢያና መቅድም መጽሐፉ ከተዘጋጀበት ዓላማ ወጣ ያሉ ታሪካዊ መረጃዎች ሰፍረዋል፡፡

 

Read 3540 times Last modified on Saturday, 26 November 2011 09:20