Print this page
Saturday, 26 October 2013 14:26

1ኛው ኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶን

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ሃዋሣ ከተማ ላይ የተካሄደው 1ኛው ኃይሌ ገ/ስላሴ ስኬታማ አጀማር እንደነበረው ተገለፀ፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት በሃዋሣ የግማሽ ማራቶንና የጎዳና ላይ ሩጫዎችን ያካሄደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የማራቶኑን በአስደናቂ ዝግጅት በማካሄድ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የአትሌቲክስ ውድድሮች አዘጋጅ ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ከሚያካሂዳቸው የሞሃ ማራቶን እና የአበበ ቢቂላ ማራቶን ነበሩ፡፡ በግል ተቋም በታሪክ የመጀመርያው የማራቶን ውድድር አንደኛው የኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶን” ነው፡፡ ማራቶኑ በሌሎች የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድሮች ታጅቦ የተካሄደ ሲሆን የህፃናት የ2ኪ.ሜ የጐዳና ውድድር፣ የ5 ኪ.ሜ ህዝብ አሳታፊ ሩጫ እና የግማሽ ማራቶን ውድድሮች ናቸው፡፡ የኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን በሃዋሣ ከተማ አውራ ጐዳናዎች የተደረገው በተገቢው የማራቶን ርቀት ሲሆን በአይ. ኤ. ኤ. ኤ ፍ ባለሙያ ሂውጅ ጆንስ በሰራው ልኬት ማረጋገጫ እና ዕውቅና አግኝቶ ነው፡፡
ማራቶኑን በማዘጋጀት በተለይ ሶስት አካላት በአጋርነት ሰርተዋል፡፡ በማርኬቲንግ እና በፕሮሞሽን እንቅስቃሴዎች በባለቤትነት የመራው የአሜሪካው ሞራይ ማውንተን ስፖርትስ ነው፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የውድድሩን ዝግጅት እና ኦፕሬሽን አከናውኗል፡፡ አዋዜ ቱርስ ደግሞ ከውድድሩ ጋር በተያያዘ በተለይ የውጭ አገር ተሳታፊዎች በማቀላጠፍ ተሳትፏል፡፡ ኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶንን የማዘጋጀት ሃሳብን የተወጠነው በአሜሪካው የአትሌቲክስ ውድድሮች አዘጋጅነት በሚታወቀው ሞራይ ማውንቴን ስፖርትስ ነበር፡፡ የሮክን ሮል ማራቶን እና ታዋቂውን የግራንድ ፕሪ ውድድር ካርልስባድ የማዘጋጀት ልምድ አለው
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አየለ እንደገለፀው ሞራይ ማውንቴን ስፖርትስ ሃሳቡን ያመነጨው በአሜሪካ እና በአውሮፓ ከሚካሄዱ ውድድሮች የተለየ ማራቶን መዘጋጀት አለበት በሚል ነው፡፡ ስለዚህም ታላላቅ የረጅም ርቀት ሯጮችን በማፍራት ወደ የሚታወቁት ሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ኬንያና ኢትዮጵያ ተተኮረባቸው። ከኃይሌ ገብረስላሴ ጋር በነበራቸው ትውውቅ ኢትዮጵያ ተመረጠች፡፡
ሞራይ ማውንቴን ስፖርትስ ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዝግጅት ክፍያ በመፈፀም ፤ለውድድሩ የሚያስፈልገውን ወጭን በመበጀት፤ ስፖንሰሮችና ባለ ድርሻ አካላትን በማስተባበር፤ የውጭ ተሳታፊዎችን በመማረክ እና አጠቃላይ የማስተዋወቅ እና የፕሮሞሽን ተግባራትን በዋና አጋርነት ሰርቷል፡፡ አቶ ኤርሚያስ አየለ እንደገለፀው የኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶንን ለማሰናዳት በውድድሩ ዙርያ የተሰባሰቡ አጋሮች ለአንድ አመት ሰርተዋል፡፡ ሞራይ ማውንቴን ስፖርትስ አማካኝነት ስለየኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶንን በታላላቆቹ የኒውዮርክ፤ ቺካጎ እና የበርሊን ማራቶኖች በክፍያ በሚገኝ ቦታ ቢልቦርዶችን በመስቀል ማስተዋወቅ ተደርጓል፡፡ ሞራይ ማውንቴን ስፖርትስ የዚህን ውድድር አጠቃላይ ወጪ የሸፈነ ሲሆን እስከ 2 ሚሊዮን ብር ወጭ አድርጓል፡፡ ይህንኑ ማራቶንን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ እንቅስቃሴ 200ሺ ዶላር ማግኘት ተችሏል፡፡ ይህ የገንዘብ ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ በሞራይ ስፖርትስ አማካኝነት የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ከልብ ጋር በተያያዘ የጤና ችግር ድጋፍ ለሚሹ እና ለተቸገሩ ህፃናት እርዳታ ለሚሰጠው ለእንጦጦ ፋውንዴሽን የተበረከተ ነው። የሃዋሳው ውድድር የዓለም ማራቶን ሪከርድ ለሁለት ጊዜያት በሰበረው ታላቁ የማራቶን ሯጭ ኃይሌ ገ/ስላሴ በመሰየሙ በርካታ የውጭ አገር ስፖርተኞች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ውድድሩ ላይ እንዲሳተፉ ምክንያት ነበር፡፡ ለማራቶኑ ድረገፅ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ትኩረትም የጠቀመ አሰያየምም ነው፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላለፉት 4 ዓመታት በሃዋሣ ከተማ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫዎች የግማሽ ማራቶን ውድድሮችን ሲያዘጋጅ ቆይቷል፡፡ ይህ ልምዱ በኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶን ዝግጅት የተቀላጠፉ ስራዎች እንዲከናወኑ አግዟል፡፡ በሐዋሳ ከተማ ለውድድሩ የተመረጡት አውራ ጎዳናዎች ሜዳማ መሆናቸውና አቀበትና ቁልቁለት ስላልበዛባቸው ለአትሌቶች የተመቹ ነበሩ፡፡ የአየሩ ሁኔታ ግን በሙቀት ሳቢያ ትንሽ አስቸጋሪ ስለነበር የውድድሩ አዘጋጆች ማራቶኑ በማለዳ እንዲካሄድ አድርገዋል፡፡ የማራቶን ውድድሩ በተሳካ ሁኔታ ተዘጋጅቶ፣ በአማረ ሁኔታ ተስተናግዶ እና በሰለማዊና በአስደናቂ የውድድር መንፈስ ታጅቦ መጠናቀቁን አቶ ኤርምያስ አየለ ይገልፃል፡፡ ስኬታማ አጀማመር እንዳደረግን ያረጋገጥነው ሐዋሣ ከተማ ለማራቶን የምትመች መሆኗን ስላመለከትን በርካታ ተሳታፊዎች ከውጭ መጥተው በመወዳደራቸው፤ ሁሉም ተሳታፊዎች በማራቶኑ የተሰማቸውን እርካታ በ99 በመቶ በመግለፃቸው፤ የማራቶን ርቀቱን በ7 ሰዓት ጨርሶ የገባ ተወዳዳሪ እንኳን ሩጫውን በከፍተኛ ሁኔታ እንደተደሰተበት ማሳወቁ እንዲሁም በአጠቃላይ ክንውኑ ስፖርትና ቱሪዝምን በማስተሳሰር በታየበት ውጤት እንደነበርም አብራርቷል፡፡
በኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶን እና በ5ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው እና በግማሽ ማራቶን ውድድር ለመሳተፍ ከውጭ አገር የመጡ ስፖርተኞች ብዛት እስከ 150 መድረሳቸው መሆኑ ለውድድሩ ጥሩ አጀማመር መገለጫ የሚሆን ነው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አየለ፤ ከእነዚህ የውጭ አገር ተሳታፊዎች 50ዎቹ በማራቶን እንዲሁም 32 ያህል በግማሽ ማራቶን በመወዳደር ደስተኞች ናቸው ብሏል። የማራቶን ውድድሩ ከተዘጋጀባቸው አላማዎች ዋንኛው ለአገር ውስጥ አትሌቶች የውድድር እድል ለመፍጠር ነው፤ በውድድሩ ላይ ከ40 በላይ ክለቦች አትሌቶቻቸውን አሳትፈዋል፤ የግል ተወዳዳሪዎች ምቹ መስፈርት በማውጣት እንዲካፈሉ ተደረጓል ማራኪ የገንዘብ ሽልማት በማቅረብም ለውድድሩ ትኩረት ተፈጥራል፡፡ በውድድሩ ለሚሳተፉ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች በሽልማት እና በስጦታ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር መሰጠቱን የገለፀው አቶ ኤርሚያስ፤ በወንዶች የማራቶን ርቀቱን ከ2 ሰዓት 12 ደቂቃ በታች ለሚገባ 100ሺ ብር እንዲሁም በሴቶች 2 ሰዓት ከ30 ደቂቃ በታች ለምትገባ 100ሺ ብር የቦነስ ሽልማት ቀርቦ ነበር ብሏል፡፡ በውድድሩ ላይ ያሸነፉ አትሌቶች አዘጋጆቹ ምርጥ ሰዓት ያላቸውን አትሌቶች አብዝተው ቢያሳትፉ እና አሯሯጮችን ቢመድቡ የተሻለ ነበር በማለት ለስፖርት አድማስ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በሌላው የዓለም ክፍል አትሌቶችን ለተሳትፎ በመክፈል እና የሚከፈላቸውን አሯሯጮች በመቅጠር ይሰራል። በኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን በዚህ መንገድ የመስራት እቅድ ያልበረን ኢትዮጵያ የሯጮች አገር እንደመሆኗ ጥሩ ተወዳዳሪ ማግኘት ስለማንቸገር ነው ያለው አቶ ኤርሚያስ፤ በዚህ ውድድር ላይ ተሳትፈው እስከ 30ኛ ደረጃ የሚያገኙ አትሌቶች በሌላው አለም ጥሩ የማራቶን ተወዳዳሪ ሊሆኑ መቻላቸውን መታሰብ እንዳለበት ያስገነዝባል፡፡
የመጀመርያው አሸናፊ መሆኔ ትልቅ ታሪክ ነው
አትሌት ጉዲሳ ሸንተማ
ባለፈው ሰሞን አንደኛውን የኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን ከማሸነፉ በፊት አትሌት ጉዲሣ ሸንተማ በትልልቅ የማራቶን ውድድሮች ሰፊ ዓለም አቀፍ ልምድም ነበረው፡፡ በ2006 እ.ኤአ በበርሊን ማራቶን ኃይሌለ ተከትሎ በመግባት በ2ኛ ደረጃ ሲያጠናቅቅ ርቀቱን በ2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ47 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ በመሸፈን ነበር፡፡ በ2008 እ.ኤ.አ ላይ ደግሞ በፓሪስ ማራቶንና፣ በዱባይ ማራቶን ተወዳድሮ በተመሳሳይ 4ኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡ ማራቶኑን በጥሩ ሁኔታ በመቆጣጠር ተወዳድርያለሁ ብሎ ለስፖርት አድማስ የተናገረው አትሌት ጉዲሣ ሸንተማ የኃይሌ ገ/ስለሴ ማራቶንን የመጀመርያው አሸናፊ መሆኔ ትልቅ ታሪክ ነው ሲል ተሳትፎውን ለሽልማት በመጓተት ሳይሆን፣ በኃይሌ መሰየሙንና እንደተምሳሌት ስለሚመለከተው በከፍተኛ ደስታ ተቀብሎታል፡፡ የመሮጫ ጐዳናው ዳገትና ቁልቁለት ያልበዛበት በመሆኑ ምቹ ነበር የሚለው አትሌት ጉዲሣ ፣ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ካደረግኳቸው የማራቶን ውድድሮች ጋር ሲነፃፀር ለየት የሚለው እና አስቸጋሪነቱ ከተማዋ ሞቃታማ በመሆኑ ብቻ ነው ብሏል፡፡ አሯሯጮች ቢኖሩ የተሻለ ሰዓት ማስመዝገብ ይቻል ነበር ያለው አትሌት ጉዲሣ ሸንተማ በቀጣይ እንዲስተካከል እጠብቃለሁ ብሏል፡፡ በኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን ሳሸንፍ ያስመዘገብኩት ሰዓት በሌሎች የዓለም አገራት ከሚካሄዱ ትልልቅ ማራቶኖች በአንዱ ቢሆን 2 ሰዓት 06 በታች እንደገባሁ የሚቆጠር ነውም ብሏል፡፡
በአገሬ ህዝብ ፊት ባደረግኩት ውድድር ተደስቻለሁ አትሌት አልማዝ ነገደ
በሴቶች ምድብ የመጀመርያው የኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን አሸናፊ ለመሆን የበቃችው አትሌት አልማዝ ነገደ ናት፡፡ ርቀቱን በ2 ሰዓት ከ39 ደቂቃ ከ50 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ለመሸፈን ነው፡፡ በአገሬ ህዝብ ፊት ያደረግኩት ውድድር ነው ብላ ተደስታለች፡፡ አልማዝ ማራቶንን ለመጀመሪያ ጊዜ አምና የቡካሬስት ማራቶን በመሳተፍ ሲሆን አሸናፊ ነበረች፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በአሜሪካ በተካሄዱ የግማሽ ማራቶን እና የጐዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች ምርጥ ሰዓቶችን በማስመዝገብ ተሳክቶላታል፡፡
የኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን አሸናፊነት ትልቅ መነቃቃት እንደፈጠረላት የተናገረችው አልማዝ፤ መሮጫው ጎዳና ሜዳማ እና አስፋልት መሆኑ ውድድሩን ደስ የሚል ውድድር አድርጐታል ብላለች ጥሩ ሰዓት ያላቸው አትሌቶች በብዛት አለመሳተፋቸውና አሯሯጭ አለመኖሩ የተሻለ ሰዓት ለማስመዝገብ ለነበራት ፍላጎት ተፅእኖ የፈጠረ ነበር፡፡ ማራቶኑ በአገር ውስጥ መዘጋጀቱ ውድድር ለሚፈልጉ አትሌቶች ጥሩ እድል መሆኑን የገለፀችው አትሌት አልማዝ ነገደ፤ ተመሳሳይ የማራቶን ውድድሮች በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች በብዛት መካሄዳቸው ለተተኪ አትሌቶች ሰፊ የውድድር እድል ስለሚጠቅሙ ያስፈልጋሉ ብላለች፡፡ በሃዋሣው የኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን ተሳትፌ ያገኘሁት ውጤት በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለመሳተፍ ይጠቅመኛልም ብላለች፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ወደ ሌላ የእድገት ምዕራፍ አሸጋግሯል ሪቻርድ ኔሩካር
ታዋቂው እንግሊዛዊ አትሌት እና የአትሌቲክስ ባለሙያ ሪቻርድ ኔሩካር የኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ወደ ሌላ የእድገት ምዕራፍ አሸጋግሯል ይላል፡፡ ከዓመታት በፊት በታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅነት የሠራ ነው እና አሁን ተቀማጭነቱን በእንግሊዝ አድርጎ ከተቋሙ ጋር መስራቱን የቀጠለው በኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን ስኬታማነት ታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያ በልምዱ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሚና ነበረው፡፡ በማራቶን ውድድሩ 82 ተወዳዳሪዎች ከ16 የተለያዩ አገራት ለመምጣታቸው የአሜሪካው ሞራይ ማውንቴን ስፖርትስ ያደረገው እንቅስቃሴ ወሳኝ እንደነበር ሪቻርድ ኔሩካር፤ ተናግሯል፡፡ በማራቶን ውድድር በመሳተፍ የሚዝናኑ ስፖርተኞችን ከውጭ አገራት በማሰባሰብ የመጀመርያው ኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን ስኬታማ ነበር ያለው ሪቻርድ፣ የውድድሩ ድባብ ጥሩ እንደነበር፣ የትራፊክ ፖሊስ፣ የፖሊስ አባላትና የከተማው ህዝብ ለውድድሩ የተቃና ሂደት የሰጡት ትብብር የሚመሰገን ብሏል፡፡ ውድድሩን በቀጣይነት ለማዘጋጀት ከፍተኛ ልምድ ተገኝቷል፡፡ የኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን በማዘጋጀት ቱሪዝምንና ስፖርትን በማስተሳሰር ውጤታማ ለመሆን እንደሚቻል ተረጋግጧል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለ ድርጅት ትልቁን የማራቶን ውድድር በማዘጋጀት የሚከብድ ነበር ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የጎዳና ላይ ውድድሮችን በማዘጋጀት ያለውን የ13 ዓመታት ልምድ በመጠቀም ሰርቶ አቅሙን በመፈተሹ ወደፊትም በመላው ዓለም ከሚገኙ በአትሌቲክስ ውድድር አዘጋጅነት ከሚሰሩ ተቋማት እና ድርጅቶች ጋር በመተባበር ውድድሩን በየዓመቱ ለማካሄድ የሚያስችል አጀማመር ነው በማለት ለስፖርት አድማስ አስተያየት ሰጥቷል፡፡ ሃዋሣ የማራቶን ውድድር ለማዘጋጀት ከኢትዮጵያ ምናልባትም ብቸኛዋ ምቹ እና ተመራጭጥ ከተማ ናት ያለው ሪቻርድ ኔሩካር ወደፊት ምናልባትም ከ5 ዓመታት በኋላ በአዲስ አበባ ሌላ የማራቶን ውድድር ለማዘጋጀት ይሞከራል ብሏል፡፡

Read 5426 times
Administrator

Latest from Administrator