Saturday, 26 October 2013 14:23

ከአሜሪካና አውሮፓ ታዋቂ የቀድሞ ተጨዋቾች ይመጣሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በአውሮፓ እና በአሜሪካ ነዋሪ በሆኑ ታዋቂ የቀድሞ እና የአሁን ዘመን ተጨዋቾች ቡድኖች በሚደረጉ የወዳጅነት ጨዋታዎች ገቢ ማሰባሰቢያ ልዩ የእግር ኳስ ፌስቲቫል መዘጋጀቱ ታወቀ፡፡ ነዋሪነታቸውን በቦስተን ያደረጉት እና በአዲስ አበባ የተጨዋቾችና ደጋፊዎች ማህበር የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ዳዊት ጌታቸው ለስፖርት አድማስ እንደገለፁት የእግር ኳስ ፌስቲቫሉ ጥር 11 ላይ በአዲስ አበባ ስታድዬም የሚካሄድ ይሆናል፡፡ ፌስቲቫሉ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ካሉት የእግር ኳስ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ማህበራት ጋር በትብብር በመስራት ተዘጋጅቷል፡፡ ለእግር ኳስ ፌስቲቫሉ ወደ አዲስ አበባ ከሚመጡት ታዋቂ የቀድሞ ተጨዋቾች መካከል እነ ካሳዬ አራጌ፤ አብዲ ሰኢድ፤ አቦነህ እና አብርሃም ብስራት ይገኙበታል፡፡ የእግር ኳስ ፌስቲቫሉ በችግር ላይ ያሉ እና የተጎዱ ተጨዋቾችን ለመርዳት፤ የታመሙትን ለማሳከም እና የእግር ኳስ ተጨዋቾች ስፖርቱን በጡረታ ከመለየታቸው በፊት የተሻለ ህይወት እንዲኖራቸው የማስተማር ዓላማዎችን በማነገብ እንደጠንቀሳቀስም ተገልጿል፡፡ ከእግር ኳስ ፌስቲቫሉ ጋር በተያያዘ በሚገኝ የስታድዬም ገቢ፣ ከተለያዩ ኩባንያዎች በሚገኝ የስፖንሰሺፕ ድጋፍ እንዲሁም ከማህበራቱ አባላት አመታዊ መዋጮ በሚገኝ አስተዋፅኦ የተጨዋቾች መረዳጃ ፋውንዴሽን ለመመስረት እንደታሰበም አቶ ዳዊት ጌታቸው ለስፖርት አድማስ ገልፀዋል፡፡
በአሜሪካ፤ በአውሮፓ እና በአዲስ አበባ ያሉት የእግር ኳስ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ማህበራት በሚያደርጓቸው ትብብሮች ባለፉት ጊዜያት ለቀድሞ ተጨዋቾች የገንዘብ እርዳታዎችን፤ የህክምና ድጋፎች እና ለተሻለ ህይወት የሚያበቁ እገዛዎች በማከናወን ሲሰራ መቆየቱን አቶ ዳዊት ጌታቸው ይናገራሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት በፊት ኬንያ ውስጥ በከፋ ችግር ላይ የነበረው የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ተጨዋች አብዱልከሪም ወደ አሜሪካ በመውሰድ በተሻለ ህይወት ቀሪ እድሜዉን እንዲያሳልፍ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች እና ምክትል አሰልጣኝ የነበረውን አስራት አዱኛ ከአውሮፓው ማህበር ጋር በመተባበር ወደ ስዊዘርላንድ ተወስዶ በተሻለ ኑሮ ውስጥ ገብቷል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ አንዳንድ ተጨዋቾች የህክምና ድጋፎች እና የገንዘብ ድግግሞሽ ተከናውነዋል፡፡ በተለይ የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ተጨዋች የነበረችው ብዙአየሁ ጀምበሩ አስቀድሞ ለክራንች ዳርጓት ከነበረውን ጉዳት በቂ ህክምና አግኝታ አገግማለች፡፡ በተመሳሳይ ሰለሞን አወቀ፣ ሰለሞን ገ/አማኑኤል እና ሲሳይ ተሰማ ለተባሉ የቀድሞ ተጨዋቾች ተመሳሳይ የህክምና ድጋፎችም መደረጉን አቶ ዳዊት ጌታቸው ገልፀዋል፡፡
አዲሱን የአዲስ አበባ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ማህበርን የቀድሞ የፖሊስ እና የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች የሆኑት ንጉሴ ገብሬ በፕሬዝዳትነት እየመሩት ናቸው፡፡ በዚሁ ማህበር የቀድሞ የምድር ጦር ክለብ አጥቂ መስመር ተሰላፊ በሃብቱ ገብረማርያም በምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዲሁም አቶ ተስፋዬ ከበደ በዋና ፀሃፊነት እየሰሩ ሲሆን የስራ አስፈፃሚ አባል በመሆን ቀድሞ የመድን ክለብ ተጨዋች የሆኑት ጌቱ መልካ እንዲሁም የአየር መንገድ ክለብ ተጨዋች የነበሩት አቶ ፍትሃነገስት በርሄ በህዝብ ግንኙነት ሃላፊነት ያገለግሉበታል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሜሪካ ያለው የእግር ኳስ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ማህበር በቅርቡ በአዲስ የስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ እንደተዋቀረ ታውቋል፡፡ አቶ ዳዊት አስመላሽ በአሜሪካው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በተሰጣቸው ሃላፊነት መሰረት ምርጫውን በአግባቡ እንዲከናወን ማድረጋቸውን የሚናገሩት አቶ ዳዊት ጌታቸው ናቸው፡፡ በአሜሪካ ያለው የእግር ኳስ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ማህበርን ለመምራት በተመረጠው አዲስ ኮሚቴ የቀድሞ የብሄራዊ ቡድንና የክለብ ተጨዋች አቶ አብዲ ሰኢድ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ፤ የእርሻ ሰብል ክለብ እና የብሄራዊ ቡድን ተጨዋች የሆኑት መንግስቱ ሁሴን በምክትል ፕሬዝዳንትነት፤ በቅዱስ ጊዮርጊስ ለረጅም ጊዜ በግብ ጠባቂነት የተጫወተው አቶ ታደሰ ተክለፃዲቅ በዋና ፀሃፊነት እየመሩት ናቸው፡፡

Read 3790 times