Print this page
Saturday, 26 October 2013 13:44

የ“ፖለቲካ ኳሳችን” የት እንደገባች አልታወቀም!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(12 votes)

ኢሕአዴግም ተቃዋሚም “ኳሷ እኛ ጋ የለችም” ብለዋል

ባለፈው ሰሞን ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ በፓርላማ የተቃዋሚ ተወካይ ለሆኑት የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ ጥያቄና አስተያየት የሰጡትን ምላሽ ሰምታችሁልኛል? (ካልሰማችሁ አመለጣችሁ!) የተከበሩ አቶ ግርማ እንዲህ አሉ፡- (ሃሳባቸውንበጥቅሉ አቀርባለሁ) “መንግስት ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ምክክር ካላደረገ የውጭ ኢንቨስተሮችን መሳብ አይሞከርም” የሚል ነው - ሃሳቡ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ሲመልሱም (ሌላውን ትተን አንኳሩን ብቻ) “እስካሁን የውጭ ኢንቨስተሮች ለመስራት ሲመጡ ሌላ ሌላውን እንጂ ከተቃዋሚዎች ጋር ትመካከራላችሁ ወይ? አላሉንም” ብለዋል (ጨዋታ ጨምረዋል ልበል!) 

እኔም ወግ ለመጀመር ያህል እቺን ካልኩኝ ወደ ቁምነገሩ ልግባ፡፡ እንግዲህ ዘመኑ የ “ልማት” ነውና የወጋችንም የመጀመርያ ማጠንጠኛ ልማት እንዲሆን ወድጄአለሁ፡፡ እርግጠኛ ነኝ … በዚህ “ቅዱስ” ሃሳቤ መቶ በመቶ ትስማማላችሁ፡፡ ምናልባት ቅሬታ ያለውም ካለ የአገሩን ተጨባጭ እውነታ የዘነጋ ነው ባይ ነኝ። እኔ ግን ቢያንስ መንግሥታችን “ልማታዊ መንግሥት” መሆኑን ላስታውሰው እወዳለሁ። በነገራችሁ ላይ ስለ ልማት ለማውራት የግድ “ልማታዊ ጋዜጠኛ” መሆን አያስፈልግም፡፡ (የሮኬት ሳይንስ እኮ አይደለም!)
እኔ የምለው ግን … አውራ ፓርቲያችን ኢህአዴግ “የልማት ዕቅድህ ካልተሳካ ህዝብ ይታዘብሃል” የሚል ሟርት በሰማ ቁጥር እኛ (ህዝብ ማለቴ ነው) ላይ መንጠልጠል አለበት እንዴ? (ጥያቄው ከጥላቻ ፖለቲካ የመነጨ አይደለም!)
ይሄውላችሁ … ሁለት አመት ቀርቶታል የተባለው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ እንደታሰበው ባይሳካ (አያድርገውና!) በምን ስሌት ነው የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የመንግስት መሆኑ ቀርቶ የህዝብ ዕቅድ የሚሆነው? ራሱ ኢህአዴግ አመንጭቶ ተግባራዊ ያደረገውን ዕቅድ እንዴት ለህዝብ ይሰጣል? (የኢህአዴግ ደግነት በዛብን!) ትንሽ ጥርጣሬ ግን አድሮብኛል - በደግነቱ ላይ፡፡ ለምን አትሉም? የራስን የልማትና ፖሊሲ ለህዝብ አሳልፎ የሚሰጥ አፍሪካዊ ፓርቲ አይተን አናውቅማ፡፡ አቦይ ስብሃት፤ “ከአፍሪካ ፓርቲዎች የተለየ ፓርቲ ነው” ያሉት ለነገሩ ገባኝ! የኢህአዴግም ባህል እኮ አይደለም፡፡ (ፓርቲው ባህሉን ለወጠ እንዴ?) ለምሳሌ ተከታታዩ የኢኮኖሚ ዕድገት የልማታዊ መንግስቱን ትክክለኛ አቅጣጫ የሚያመላክት ነው ሲባል እንጂ “የህዝቡ ውጤት ነው” ሲባል አልሰማንም (በስህተት እንኳን!) ታዲያ አሁን ምን ተገኘ? (“ልቤ ጠረጠረ” አለ፤ አንዱ የፌስቡክ ፀሐፊ)
በቅርቡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም በፓርላማ የተናገሩትን ስሰማ፤ ኢህአዴግ ስኬቱን በግሉ፣ ውድቀቱን ከህዝቡ ጋር ለመካፈል እንዳሰበ ጠርጥሬአለሁ፡፡ ቆይ በምን ተአምር ነው … የባቡሩ ፕሮጀክቱ እክል ቢገጥመው እኛ (ህዝቦች ማለቴ ነው) ተጠያቂ የምንሆነው? ከምሬ እኮ ነው…የልማት ፖሊሲው - የኢህአዴግ! እቅዱ - የኢህአዴግ! አተገባበሩ - የኢህአዴግ! በዚህ ውስጥ ታዲያ የእኛ ሚና የቱ ጋ ነው? ጠ/ሚኒስትሩ ግን “ልማቱ ባይሳካ … በህዝቡ ትፈተኑበታላችሁ” ለተባለው የአቶ ግርማ አስተያየት፤ “ልማቱ እኮ የህዝብ ነው፤ የሚሰራው ህዝቡ ነው፤ እኛ አስተባባሪ ነን” ሲሉ ከተጠያቂነት ለማምለጥ ሞክረዋል፡፡ እኔ የምለው… እኛ እኮ ኢህአዴግን የምንደግፈው በአስተባባሪነቱ አይደለም፤ በልማታዊ መንግስትነቱ እንጂ!! (ወዴት ሸርተት ሸርተት!) እናላችሁ … ልማቱና ትራንስፎርሜሽኑ እክል ሲገጥመው “የህዝቡ ነው” ምናምን አያዋጣም! በነገራችሁ ላይ … በ2002 አገራዊ ምርጫ ሌሊት ወጥተን ለአውራው ፓርቲ ድምፃችንን የሰጠነው እኮ ኢህአዴግ (ልማታዊ መንግስታችን ማለቴ ነው!) ይሄን ሃላፊነትና ተጠያቂነት መሸከሚያ በቂ ጫንቃ አለው ብለን ነው፡፡ ያለዚያማ ሌላ የተሻለ ትከሻ እናፈላልግ ነበር፡፡

(ከተቃዋሚዎችም ቢሆን!) ባይሆን ጠ/ሚኒስትሩ የሰጡት ሌላኛው ሰበብ የተሻለ ነው፡፡ “እቅዶቹሰፋፊ ናቸው፤ የተለጠጡ ናቸው፤ ወገብ የሚያጐብጡ ናቸው” ብለዋል- ጠ/ሚኒስትሩ። ባይሳካልንም ለጥጠን ስላቀድን ችግር የለም እንደማለት፡፡ (አሪፍ ማምለጫ ይሏል ይሄ ነው!) እናላችሁ … ሥራችን ይለይ፤ የኢህአዴግና የእኛ! እሱ ተመራጭ፤ እኛ መራጭ ነን፤ እሱ አገልጋይ፤ እኛ ተገልጋይ፤ እሱ መንግስት፤እኛ ህዝብ ነን!! እሱ ተጠያቂ፤ እኛ ጠያቂ!! “ልማቱን የሚሰራው ህዝብ ነው!”
እስቲ ደሞ ለአፍታ ወደ አፍሪካይቱ ሌላ አገር እንሂድ፡፡ ሰሞኑን በቢቢሲ አፍሪካ የሰማሁት መረጃ፣ ትንሽ አፅናንቶኛል፡፡ (የሚያፅናና ነገር አይጥፋ አቦ!) መረጃው ምን መሰላችሁ? ናይጄሪያም እንደኛ በመብራት መጥፋት መሰቃየቷ እንደቀጠለ የሚገልፅ ነው፡፡ በርግጥ የናይጄሪያ መንግሥት (እንደማንኛውም አፍሪካዊ መንግሥት) ብዙ ሚሊዮን ዶላሮች በማውጣት ናይጄሪያውያንን በመብራት ሊያንበሸብሻቸው እንደሆነ አብስሯል። (ሥራው ሳይሆን ችሮታ- አይመስልም?) የሚያሳዝነው ግን ማንም ያመነው አለመኖሩ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ ለቢቢሲ አስተያየቱን የሰነዘረ አንድ ናይጄሪያዊ፤ የናይጄሪያ ባለስልጣናትን በከባዱ ወርፏቸዋል - “Big liars!` በማለት (ባለ ከባድ ሚዛን ውሸታሞች! ማለቱ ነው!) እናላችሁ… በመብራት መቆራረጥና መጥፋት መከራችንን የምንበላው እኛ የጦቢያ ልጆች ብቻ እንዳልሆንን ስገነዘብ ነው ትንሽም ቢሆን የተፅናናሁት - መከራችንን የሚጋሩን አፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች አገኘን ብዬ!
እኔ የምላችሁ… አፍሪካ ህብረት (“የአፍሪካ መሪዎች ማህበር” ቢባል ይሻላል!) በቅርቡ በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍ/ቤት (ICC) ላይ የጀመረውን ዘመቻ ሰምታችሁልኛል? ኧረ ከዘመቻም ያልፋል፡፡ አመፅ ወይም አድማ ነገር እኮ ነው የሚመስለው፡፡ (ለካስ መሪዎችም ያምፃሉ!)
ግን እኮ ለዘመቻም በሉት ለአመፃ ወይም ደግሞ ለአድማ መተባበር ይፈልጋል፡፡ ለአንድ ዓላማ በአንድ ልብ መቆም! …የአፍሪካ መሪዎች ያለመደባቸውን ትብብር ዘንድሮ ከየት እንዳመጡት ግርም ብሎኛል፡፡
አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ግን ትብብሩ የተፈጠረው “ነግ በእኔ” ከሚል የስጋት ስሜት ነው ብለዋል። አያችሁ … ዓለምአቀፍ ፍ/ቤቱ በተገኙበት ተይዘው እንዲመጡለት ማዘዣ የቆረጠባቸው የሱዳንና የኬንያ ፕሬዚዳንቶች ጉዳይ በ“አድማ” እልባት ካላገኘ እንደለመደው ነገ ወደ ማን ሊዞር እንደሚችል መገመት ከባድ ነው፡፡ (“ምን ያለበት ዝላይ አይችልም” አሉ!) እናም ዓለም አቀፉ ፍ/ቤት ኢ-ፍትሃዊ ነው፤ አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ ልትፈታ ይገባል” በሚል እየተሟገቱ ወደፊት በአፍሪካ ህብረት ስለሚቋቋመው የአፍሪካውያን ፍ/ቤት ማለም ጀምረዋል፡፡ (ሶማሊያ የሚመደብ አፍሪካዊ ሰላም አስከባሪ ኃይል ጠፍቶ እንደነበር ልብ ይሏል!)
ይኼውላችሁ… የአፍሪካውያን ፍ/ቤት መቋቋሙ ላይ ተቃውሞ የለኝም፡፡ እንደውም “እስከዛሬ የት ነበሩ?” ባይ ነኝ፡፡ እዚህ ጋ ግን (በኢህአዴግ ቋንቋ መናገር ይፈቀድልኝ) በቅርቡ ዘመቻ የከፈቱት የአፍሪካ መሪዎች ወይም ህብረቱ ማጥራት ያለባቸው አንኳር ጉዳዮች ያሉ ይመስለኛል፡፡ እኔም በግሌ (በአፍሪካዊነቴ ማለቴ ነው!) እርማቸውን በጋራ ለቆሙት የአፍሪካ መሪዎች የምወረውራቸው አንዳንድ ያልገቡኝ ጥያቄዎች አሉ፡፡ (ይቅርታ አድርጉልኝና… የአፍሪካ መሪዎች የማይፈቱ እንቆቅልሾች ይመስሉኛል!) እስቲ እነ ኢዲ አሚንን፣ እነ ሞቡቱን፣ እነ ጋዳፊን፣ እነ ሙባረክን፣ እነ ሙጋቤን እና ሌሎቹን የለየላቸው አምባገነን መሪዎች አስቧቸው! (ልማታዊ መንግስታትን አይመለከትም!) ቆይ… ምናቸው ይገባል? አንዳንዴ ሳስበውማ … የአፍሪካ ህዝቦች ፈጣሪያቸውን ክፉኛ በድለውት ለቅጣት የተላኩ ይመስሉኛል - አምባገነኖቹ የአፍሪካ መሪዎች!! (ግን ፈጣሪ እንዴት ቢጨክንብን ነው?!) አያችሁልኝ… የእኔ ነገር! የአምባገነኖችን ጉዳይ እያመነዠኩ ጥያቄዎቹን ዘነጋኋቸው፡፡ እናላችሁ… አፍሪካ ህብረትም ሆነ መሪዎቹ በሁለቱ ፕሬዚዳንቶች ጉዳይ አቋማቸው ምንድነው? (ስለተረሳሳ እኮ ነው!) ዓለም አቀፉ ፍ/ቤት የሚያቀርብባቸውን ውንጀላ አልፈፀሙም ነው? ወይስ “ጉዳዩ እሱን አይመለከተውም፤ ለእኛ ለአፍሪካውያን ይተውልን” ተብሎ ነው? አልታያችሁም … የአፍሪካ ፍ/ቤት አፍሪካውያን መሪዎች ላይ ሲፈርድ? በነገራችሁ ላይ ጠ/ሚኒስትራችንና የአፍሪካ ህብረት ሊ/መንበር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ “ጨፍጫፊዎችና ወንጀል የፈፀሙ የአፍሪካ መሪዎች አይከሰሱ” የሚል አቋም እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ (ትንሽ ያፅናናል ልበል?)
ወጋችንን በአገራዊ ፖለቲካ ብንቋጨውስ? እንደኔ ታዝባችሁ ከሆነ … ብዙ ጊዜ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች “ኳሷ በኢህአዴግ ወይም በመንግስት እግር ስር ናት!” እያሉ ሲናገሩ እንሰማ ነበር፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ “ኳሷ በተቃዋሚዎች እግር ስር ናት!” ሲሉ ሰማሁ፡፡ ኳሷ ተሰውራለች ማለት እኮ ነው! አያችሁ … የፖለቲካ ኳሷ ጠፍታለች፤ የት እንዳለች ተቃዋሚም ሆነ ኢህአዴግ አያውቁም፡፡ ስለዚህ ኳስ አገኘን ብለው እግር ለእግር ሲማቱ የከረሙት ለዚህ እኮ ነው መቆሳሰልና ስብራት የበዛው፡፡ እናም ቀዳሚው ስራችን የፖለቲካ ኳሷን ፈልጐ ማግኘት ነው፡፡ ኢህአዴግና ተቃዋሚ ኳስ በሌለበት ሜዳ ላይ ተፋጥጠዋል፡፡ እቺን ኳስ አፈላላጊ ኮሚቴ በአፋጣኝ ማቋቋም አለብን (አንድዬ ይርዳና!)

Read 3214 times