Saturday, 19 October 2013 11:27

“ሶስት መቶ ስልሣ ዓይነት ዐይብ ያለውን ህዝብ ማስተዳደር ከባድ ነው” የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ደጐል

Written by 
Rate this item
(13 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ የሥነ - ከዋክብት ተመራማሪ በአንድ የገጠር ከተማ ይኖር ነበረ፡፡ የዚህ ሰው የሁልጊዜ ፈሊጥ ማታ ማታ ከቤቱ እየወጣ የሰማይ ላይ ከዋክብትን ማየትና የሰው ልጆችን ዕጣ -ፈንታና የተፈጥሮን አካሄድ መመርመር ነበር፡፡
ይህን ክህሎቱን ከጊዜ በኋላ የተረዱ የከተማይቱ ሰዎች ቀስ በቀስ ስለሱ አዋቂነት ማውራት ጀመሩ፡፡ ዋሉ አደሩና እየተከተሉት ዕጣ - ፈንታቸውን ይጠይቁት ያዙ፡፡
አንደኛው - “የሥነ - ከዋክብት አዋቂ ሆይ! የእኔ የወደፊት ዕጣ ምን ይሆን?” ሲል ጠየቀው፡፡
አዋቂ - “ያንተን የከዋክብት ፈለግ እንዳየሁት የመጨረሻ ዕልፈትህ ጠብ ውስጥ ገብተህ ነው፡፡ ያላሰብከው ሰው ነው የሚገድልህ” አለው፡፡
አንደኛው - “ታዲያ ምን ባደርግ ነው የሚሻለኝ?”
አዋቂ - “በምንም ዓይነት ጠብ አካባቢ አትገኝ”
ሌላ ተከታዩ ይመጣል፡፡
“አዋቂ ሆይ! የእኔስ ዕጣ ምን ይሆን?”
አዋቂ - “ኮከብህ የብልጽግና ነው፡፡ ነገር ግን ምቀኞች አሉብህ”
ተከታይ - “ታዲያ ምን ባደርግ ከእነዚህ ምቀኞች ተንኮል አመልጣለሁ?”
አዋቂ - “ደግ እየመሰሉ ከሚቀርቡህ ሰዎች ተጠንቀቅ”
እንዲህ እንዲህ እያለ በየጊዜው እየተከተሉ ዕጣ - ፈንታቸውን ለሚጠይቁት ሰዎች መልስ ሲሰጥና ሲመክር ሰነበተ፡፡
አንድ ማታ እንደተለመደው ከከተማው ዋና በር (ከተምበሪ) አልፎ ሄደ፡፡
ቀና ብሎ ዐይኖቹን ሰማዩ ላይ ተከላቸው፡፡ መመራመሩን፣ መጠበቡን፣ መፈላሰፉን ቀጠለ፡፡ ይህን የየከዋክብቱን አካሄድና እንቅስቃሴ እያየ፣ እንዳንጋጠጠ፣ መራመዱን ቀጠለ፡፡ ሳያስበው ከእግሩ ሥር ካለ አንድ ደረቅ ጉድጓድ ውስጥ ድንገት ጥልቅ አለ፡፡
እዚያ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ እንደወቀደ ያጓራና ያቃስት ገባ፡፡ አንድ ሰው በዚያ አቅራቢያ ሲያልፍ የዚያን የሚያስጓጉር አዋቂ ድምጽ ሰማ፡፡ ወደ ጉድጓዱ አፍ ቀረበና ቁልቁል ተመለከተ፡፡ ሁኔታውን ካስተዋለ በኋላ፤
“ምን ልታደርግ እዚያ ገባህ?”
“ወድቄ ነው”
“እንዴት ይሄን የሚያህል ጉድጓድ አላየህም?”
“ሰማዩ ላይ በጣም አተኩሬ ስለበረ ነው”
“አይ ወዳጄ!” እንደዛ ታላቅ አዋቂ ነህ ብለን የተቀበልንህ ሰው፤ ሰማይ ሰማይ ስታይ እግሮችህ ወዴት እንሚወስዱህ እንኳ ካላወቅህ፤ እኔ እንደሚሰማኝ፤ አሁን ያለህበት ቦተ ተገቢ ቦታህ ነው!” አለው፡፡
* * *
ሰማይ ሰማይ ስናይ እግራችን ሥር ያለውን ነገር አንዘንጋ፡፡ ሰማዩን አተኩረን ስናይ ቀልባችን ሙሉ በሙሉ እሱ ላይ ብቻ ካረፈ፤ ከሥር እግራችንን የሚመታንን እንቅፋትና የሚያሰምጠንን ጉድጓድ አናየውም፡፡ ወደኃያላን መንግሥታት ስናንጋጥጥ የራሳችንን ህዝብ እንረሳለን፡፡ አልፈን ተርፈንም የሰዎችን ዕጣ-ፈንታ ስንናገር የራሳችንን ዕጣ-ፈንታ ሳናቅ እንዳንቀር እንጠንቀቅ!
ኃያላን መንግሥታት ሲሻቸው የበኩር ልጅ፣ ሲሻቸው የእንጀራ ልጅ ማድረግን ይችሉበታል፡፡ ኃያላን መንግሥታት “ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ” ገንፎ መብላትን ያውቁበታል፡፡ መልዕክተኞቻቸውን ሲሻቸው በእርዳታ ሰጪ መልክ፣ ሲሻቸው በሚሲዮናውያንና በሃይማኖተኞች መልክ፣ ሲሻቸው በዲፕሎማት መልክ፤ ካልሆነም በቀጥታ ስለላ መልክተኞች - አሊያም በቱሪስት ወይም በፒስኮር መልክ ይልካሉ፡፡ ከከፋም የውስጥ ዐርበኛ ይቀጥራሉ፡፡ ላላ ያለ ካገኙም አገራቸው ድረስ ጋብዘው፣ አስተናግደው ሾመው፣ ሸልመው አንቱ ብለው ይቀባሉ፡፡
ያለ፣ የነበረ ወደፊትም የሚኖር ዘዴያቸው ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ካልተሳካ የቁርጡ ቀን መጣ ማለት ነውና እንደ ኢራቅ የጦር ዘመቻ ያካሂዳሉ፡፡ እንደግሎባላይዜሽን አበጋዞች ሳይሆን እንደጥንቶቹ ቅኝ ገዢዎች- በግልጽ ወረራ ያካሂዳሉ፡፡
ከሁሉም ይሰውረን፡፡ ሲያወድሱ ሰማይ፣ ሲጥሉ እንጦር አውርደው ከትቢያ ይደባልቃሉ፡፡ የሁልጊዜ መሳሪያቸው ነው፡፡ እስካመቸናቸው እስካልቆረቆርናቸው ድረስ ያለእኛ በትክክለኛው የዕድገት መስመር ላይ ያለ አገር አይገኝም፡፡ “እንዲህ እያልሽ ውቴልሺን ሽጪ” እንዳለው ወሎ፤ የሚነግራቸው ጠፍቶ ነው፡፡ ለእነሱ የከፋን ለታ ግን ያለእኛ ኋላቀር፣ ያለእኛ ደንቆሮ፣ ያለእኛ ጦርነት ናፋቂ፣ ያለእኛ ረሃብተኛ፣ ያለእኛ መናጢ ደሃ የለም፡፡ ”እፀድቅ ብዬ ባዝላት ተንጠልጥላ ቀረች” ይሉናል፡፡
ከበረታን፤ “አላህንም አትክዳ፣ ሐረጓንም አትልቀቅ” እንዳሉት ጠቢብ ማሰብ አለብን፡፡
የኃያላኑን የቢዝነስ ኮሙኒቲ አይተን እኛ ምን እንሥራ ማለታችን ደግ ነገር ሆኖ፤ ከእዚህ ሁሉ በስተጀርባ ምን አለ? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ ምን ያህል ከልባቸው ነው? እነሱ፤ ለህዝባችን ይበጃል ያሉትን ማንኛውንም እኩይ ተግባር ከመፀፈም ወደኋላ ብለው ያውቃሉን? ብለን እንጠይቅ፡፡ ሁሉንም በትጋት በጉጉት - ዐይን እናስተውል፡፡
የፖለቲካ ፀሐፍት እንደሚነግሩን፤ “ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የሚወድቁት ስህተት ስለሚሰሩ ሳይሆን ስህተታቸውን እንዴት እንደሚያርሙ ስለማያውቁ ነው፡፡ ይሄ የእኛም ችግር ነው፡፡ ሁለት ተጠቃሽ ባህሪዎቻችን፡- “ካፈርኩ አይመልሰኝ (Rigidity)”፣ እና “የአብዬን እከክ ወደእምዬ ልክክ (Blame shifting)” ናቸው፡፡ የሠራሁት ነገር ስህተት እንዳለበት ቢነገረኝም አልለቀውም፡፡ አንዴ አድርጌያለሁ ብያለሁ፡፡ ብያለሁ፡፡ ኃያላኑም ተናግረዋል፤ ማለት አይበጅም፡፡ በተቻለ መጠን በኃያላን ውዳሴ አለመማለል ብልህነት ነው! “ቅጥ - ያጣ መረጃ” ይዘን ነው እስካሁን የሄድነው ተብሏል፡፡ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮቻችን፣ የሚጨበጡትንና የማይጨበጡትን ጨምሮ፤ ስፍር - ቁጥር የላቸውም፡፡ በአንድ የድህነት ባኮ ከትተን ልንገላገላቸው መንገድ ከጀመርን ከራርመናል፡፡ አሁንም ግን በመጨለምና በንጨላጨል መካከል ነን፡፡
በሬዲዮ ጥያቄና መልስ ፕሮግራም “የሱዳን ዋና ከተማ ማን ትባላለች” ሲባል “አማርኛ ይሁንልኝ” …“የቆጡን አወርድ ብላ…” ጨርሰው ሲባል “ስፖርት ይሁንልኝ”፤ ዓይነት መልስ የሚመልስ ህብረተሰብ ይዘን እየዳከርን ነው፡፡ አገራችን፤ ላዩም ታቹም ይሄን መሳይ ነው!
በጭካኔ ፍትሕን ማምጣት (Brutal justice) እና የኢኮኖሚ አምባገነንነት (Economic Dictatorship) ቦታ ቦታ አላቸው፡፡ ጊዜ ጊዜም አላቸው፡፡ ለመተግበር ፍፁም ጥንቃቄን ይጠይቃሉ። ውጤታቸው ጠላት ማብዛት፣ ዜጋን ማስኮረፍ፣ ሕዝብን መሬት ውስጥ መክተት ሊሆን ይችላል፡፡ ሆደ - ሠፊና ለጋሥ አምባገነን መሆን (Benevolent Dictator) የዋዛ ነገር አይደለም፡፡ ህብረተሰብን በቅጡ ማሳመን ይሻል፡፡ በተለይም የተለያየ ሃይማኖት፣ ባህልና ብሔረሰብ ባለበት አገር እጅግ ከባድ አስተዳደራዊ ምሉዕነትን ይጠይቃል፡፡ የፈረንሳዩ መሪ ደጐል “ሶስት መቶ ስልሳ ዓይነት ዐይብ ያለውን ህዝብ ማስተዳደር ከባድ ነው” የሚለን ለዚህ ነው!

Read 3330 times