Saturday, 12 October 2013 13:04

ዘላለማዊ መንግስትና ዘላለማዊ ሰልፍ የለም!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(14 votes)

          እኔ የምላችሁ… ሰሞኑን ምርጫ “በሽ” ሆነ አይደል! በአንድ ሳምንት ውስጥ እኮ ሦስት “ታላላቅ ምርጫዎች” ተደርገዋል፡፡ የሰሞኑን ምርጫዎች ደረጃ እንስጣቸው ከተባለ በቅድምያ የሚመጣው በፓርላማ የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ነው፡፡ (ግን ምርጫ ነው ሹመት?) የአዲሱን ፕሬዚዳንት ንግግር በኢቴቪ የተከታተለ ወዳጄ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው “ያቀረቡት ሪፖርት የቱርክ ነው እንዴ?” አባባሉ ገርሞኝ “እንዴት የቱርክ አልክ?” አልኩት “የቱርክ አምባሳደር አልነበሩ!” አለኝ ኮስተር ብሎ፡፡ በኋላማ እንደዚያ ያለበት ምክንያት ገባኝ፡፡ በተመረጡበት ቀን ያንን ሁሉ ሪፖርት ማቅረባቸው እንግዳ ሆኖበት ነው (የኢህአዴግ “ባህል” አልገባውም ማለት ነው!)
የሰሞኑ ሌላ ምርጫ ደግሞ ከትላንት በስቲያ በሸራተን አዲስ የተካሄደው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የአመራሮች ምርጫ ነበር፡፡ (ፊፋን ማለቴ አይደለም!) ያ እንኳን “የዓመቱን ታላቅ ቅሌት” የፈፀመውን አገር በቀል ፌዴሬሽን ማለቴ እኮ ነው (“የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም” አሉ!) ሦስተኛውስ ምርጫ? ሦስተኛው የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ምርጫ ነው፡፡ ይሄም ማህበር ባለፈው ቅዳሜ ለስምንት ዓመት የመሩትን አመራሮች በምርጫ አውርዷል (“የጀመርኩትን ልማት ሳልጨርስ” ማለት አያዋጣም)፡፡

በነገራችሁ ላይ ያለፈው የደራስያን ማህበር አመራር፣ ደራስያንን ሳይሸልም አትሌቶችን ለመሸለም ባዝኗል እየተባለ ሲታማ ሰምቼአለሁ (“አካሄድ ጥራት” ይጐድለዋል ማለት እኮ ነው!) በነገራችሁ ላይ አመራሩ በ97 ዓ.ም ሃላፊነት ሲቀበል የተረከበውን 30ሺ ብር ካፒታል 2.7 ሚ. ብር አድርሷል ተብሏል (አድናቂው ነኝ!) አሁን ዕዳው የአዲሱ አመራር ነው (“ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናግር” አሉ) እኔ በበኩሌ አዲሱ አመራር የኢትዮጵያ ደራሲያንን ከድህነት አረንቋ እንደሚያወጣ ትልቅ እምነት አለኝ፡፡ (የህዝብ አደራ መሆኑ ይታወቅልኝ!) ይሄን እውን ለማድረግ ደግሞ “ልማታዊ ደራስያን ማህበር” መፍጠር የግድ ይላል፡፡ የኢትዮጵያ የደራስያንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት (ደራስያን) ተርታ የሚያሰልፍ ማህበር ያስፈልጋል፡፡

(ከገዢው ፓርቲ የተቀዳ ራዕይ ነው!)
እናንተ … ሳላስበው እኮ ሌላ ዝርዝር ውስጥ ገባሁ! እንጂማ አነሳሴ ሰሞኑን “ምርጫ አልበዛም ወይ?” ለማለት ነው፡፡ እርግጥ ነው ይሄ የሚያሳየው “ዲሞክራሲያዊ ሂደቱ መሳካቱን” ነው - እንደ ሰላማዊ ሰልፉ!! ትንሽ ያሰጋኝ ምን መሰላችሁ? ሁሉም እየተነሳ ምርጫ ላካሂድ ካለ “መሰላቸት” ይመጣል (ሥራም እኮ ያስፈታል!) ምርጫ ማድረግ ልክ እንደ ሰላማዊ ሰልፍ ሁሉ ህገመንግስታዊ መብት ቢሆንም ልማቱን ማደናቀፍ ግን ቀዩን መስመር ማለፍ ነው፡፡ (ዘላለም ምርጫ የሚካሄድበት አገር እኮ የለም!!)
በነገራችሁ ላይ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ተቃዋሚዎች የሚያደርጉትን ሰላማዊ ሰልፍ በተመለከተ የሰጡት ምላሽ ተስማምቶኛል። “ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ችሮታ ሳይሆን ህገመንግስታዊ መብታቸው ነው” ብለዋል፡፡ (ከሰማይ የወረደ ዕፁብ ድንቅ አባባል እኮ ነው!) እሳቸው ትንሽ የደበራቸው ምን መሰላችሁ? ልማት ማደናቀፉ ነው! (“ሥራ ያስፈታል” አይደል ያሉት?) ይታያችሁ… 99 ፓርቲዎች (የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶችንም ይጨምራል እንዴ?) ለ99 እሁዶች ሰልፍ ሲወጡ ጥበቃ ማድረግ ያስፈልጋል (ይሰለቻል እኮ!) “ሆኖም ዲሞክራሲ ስለሆነ እንታገሳለን” ብለዋል፡፡ እኔማ “ሥራችን ነው!” እንዲሉ ነበር የጠበቅሁት። ቢሆንም የኢዮብን ትዕግስት ከሰጣቸው እዛ ጋ እንደርሳለን አንድ ቀን!!
እሳቸውን ብቻ ሳይሆን እኔንም ጭምር የደበረኝ ግን ምን መሰላችሁ? ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ሃሳቡ የራሳቸው የተቃዋሚዎች ሳይሆን የውጭ ሃይሎች ነው መባሉ ነው (ብቻ የኒዮሊበራሎች እንዳይሆን?) በእርግጥ ይሄን ጉዳይ ራሳቸው ተቃዋሚዎች በአንደበታቸው አላረጋገጡልንም። እውነት ከሆነ ግን በጣም ነው የምታዘባቸው። እንዴ… “አገር በቀል” ተቃዋሚ ፓርቲ እንኳን ላይኖረን ነው እንዴ! (ኢህአዴግማ ገዢ ፓርቲ እኮ ነው!) እናላችሁ … ተመሳሳይ ጥያቄ እየያዙ በየእሁዱ ተቃውሞ ሰልፍ የመውጣቱን ነገር በተመለከተ መቀጠል እንደማይችል ሲገልፁ፤ “ሰልፍ ለዘላለም የሚካሄድበት አገር የለም!” ብለዋል፡፡ እኔም እውነት ነው ብያለሁ፡፡ ለምን አትሉኝም? “ዘላለማዊ መንግስት የለማ!” (ለነገሩ ዘላለማዊ ተቃውሞውም እኮ የለም!) በእርግጥ ዘላለማዊ ህይወት አለ ይባላል። እዚህ ሳይሆን በሰማያዊው ዓለም! (ሰማያዊ ፓርቲ አልወጣኝም) አንድ አባት ስለተቃዋሚዎች ሰልፍ ምን እንዳሉኝ ታውቃላችሁ? “ያደለውማ እሁድ እሁድ ተቃውሞ ሳይሆን ፀሎት ያደርጋል፡፡” (ሥልጣን እንጂ መጽደቅ ማን ፈለገ?)
በተቃውሞ ሰልፍ ዙርያ በኢህአዴግና በተቃዋሚዎች መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት ምን አሰብኩ መሰላችሁ? (ማንም ወክዬ ሳይሆን “እንደዜጋ” ማለቴ ነው) ኢህአዴግን ጨምሮ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሰልፍ ሲወጣ፣ በወጣው ህዝብ መጠን “ታክስ” ማስከፈል! አያችሁ… ግብር ሲጣል ድንገት እየተነሱ ሰላማዊ ሰልፍ አደርጋለሁ ማለት ይቀራል፡፡ መንግስትም ዝም ብሎ አይከለክልም፡፡ (መብትና ግዴታ ፈጠርኩለት ማለት ነው) በነገራችሁ ላይ መንግስት ከሰልፉ የሚገኘውን ግብር ለጥበቃ ነው የሚያውለው (ማትጊያ በሉት!)
ሌላው ደግሞ የሰላማዊ ሰልፍ ቦታዎችን የሚመለከት ነው፡፡ በየጊዜው “መስቀል አደባባይ ካልሆነ፣ የለም ጃንሜዳ ነው” የሚል ውዝግብ ከምንሰማ “ለምን በኪራይ አይሆንም?” ብያለሁ (ልክ እንደኮንሰርት!) ያኔ … “ቦታው እየለማ ነው” ምናምን የሚሉ ሰበቦች ይቀራሉ (ፖለቲካ ሳይሆን ቢዝነስ ነዋ!) እናላችሁ … የሰላማዊ ሰልፍ ማድረጊያ ቦታዎች የተለያዩ ታሪፎች ይወጣላቸዋል፡፡ በግሌ ባካሄድኩት የገበያ ጥናት መሰረት፣ መስቀል አደባባይ ከፍተኛውን ክፍያ የሚያስከፍል ቦታ ሲሆን ዝቅተኛው ዋጋ ደግሞ ጃንሜዳ ነው (ተመራጭነቱ ዝቅተኛ ስለሆነ እኮ ነው!) እርግጠኛ ነኝ… ይሄን ፕሮፖዛል ኢህአዴግ ሳያቅማማ ይቀበለዋል፡፡ በሁለት ምክንያቶች! አንደኛው ሰላማዊ ሰልፍ የወቅቱ “ፋሽን” (ወረት ማለቴ ግን አይደለም!) ስለሆነ አዋጭ ነው - ብዙ ገቢ ይታፈስበታል (በግብርም በኪራይም!) እንደምታውቁት ኢህአዴግ ደግሞ ገንዘብ በብዛት ይፈልጋል (ልማታዊ መንግስት ነዋ!)
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ምን መሰላችሁ? ለ99 ፓርቲዎች 99 እሁድ ጥበቃ ከማድረግ ይገላገላል፡፡ እንዴት ብትሉ … ብዙዎቹ ተቃዋሚዎች በፋይናንስ በኩል “ቺስታ” ስለሆኑ ሰልፉን በግል ሳይሆን ተጣምረው ለማድረግ ይገደዳሉ። (ለተቃዋሚዎች “ኢንዶውመንት” አይፈቀድም እንዴ?) እናላችሁ … ኢህአዴግ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ህገመንግስታዊ መብትን ሳይጥስ ወይም አዲስ የ “ጥሰት” አዋጅ መደንገግ ሳያስፈልገው ችግሩ ተፈታ ማለት ነው፡፡ (የኢህአዴግ አላማ እኮ “የልማት ሠራዊት” መገንባት እንጂ “የሰልፍ ሰራዊት” መገንባት አይደለም!)
በነገራችሁ ላይ ጥናቱ ስላልተጠናቀቀ ነው እንጂ ለሰላማዊ ሰልፍ የጥበቃ ድጋፍ የሚገኝበትን መንገድ እየመረመርኩ ነው፡፡ ቻይናን ከመሰሉ ኮሙኒስት ወዳጅ አገራት ፀጥታ አስከባሪ በድጋፍ ከተገኘም እኮ ሌላ አማራጭ ይሆናል፡፡ የእኛ ፖሊሶች በየእሁዱ ጥበቃ በማድረግ ሲወጠሩ የቻይና ፖሊሶች ዘና ብለው እንደሚውሉ መረጃ አለኝ (ቻይና የተቃውም ሰልፍ የለማ!)
በዚህ አጋጣሚ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከውጭ የጥበቃ ድጋፍ በማፈላለግ በግሌ የጀመርኩትን “አገራዊ ጥረት” እንዲያግዙኝ ጥሪ አቀርባለሁ። (ይሄን መፍትሔ ያፈለቅሁት “የግጭት አፈታት ዘዴ” በሚል በወሰድኩት ስልጠና ኢንስፓየርድ ሆኜ ነው!)
በተረፈ አንድ ገና በሃሳብ ደረጃ የወጠንኩት ፕሮፖዛል እንዳለኝ ልገልፅላችሁ እፈልጋለሁ፡፡

(በሰላማዊ ሰልፎች ዙሪያ) ግን ዳጐስ ያለ ፋይናንስ የሚያስፈልገው ነው፡፡ ሃሳቡ ምን መሰላችሁ? የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሰላማዊ ሰልፎች “ልማታዊ” እንዲሆኑ የመቃኘት ስራ ነው፡፡ “ለልማታዊ መንግስት ልማታዊ ተቃውሞ” እንዲሉ፡፡ አያችሁ ለእንደኛ ዓይነቱ አገር የሚያስፈልገው ልማታዊ ተቃዋሚ ነው፡፡ እኔ የምለው … ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በ11ኛው ሰዓት ለተቃዋሚዎች የለገሱትን ምክር ሰምታችሁልኛል? (“የዘገየ ምክር” ብለውታል አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች!) ምክሩ ግን ምን መሰላችሁ? ተቃዋሚዎች በብሄራዊ ጥቅሞች ላይ የጋራ አቋም በመያዝ የታማኝ ተቃዋሚነት ዲሞክራሲያዊ ባህልን እንዲገነቡ የሚመክር ነው (“ታማኝ ተቃዋሚ” ሲሉ “ልማታዊ ተቃዋሚ” ማለታቸው መሰለኝ!)
እኔ የምላችሁ… የዛሬው ፖለቲካዊ ወግ በሰላማዊ ሰልፎች አጀንዳ ተሞላ አይደል? (እኔ ራሴ የፃፍኩ ሳይሆን ተቃውሞ ሰልፍ ያደረግሁ ነው የመሰለኝ!) በነገራችሁ ላይ የሰኞ ዕለቱን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ (ይቅርታ “ሹመት” ማለቴ ነው!) ብዙዎች በ “Surprise” የተሞላ ነበር ብለውታል፡፡ በከፊል እስማማለሁ፡፡ እንዴት ቢባል…ኢህአዴግ እስከመጨረሻው ቀን ድረስ ድምፁን አጥፍቶ ቆይቶ፣ ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን በብቸኛ እጩነት “እነሆ” ብሎናላ (አንድ ሰው “እጩ” ይሆናል እንዴ?) ይሄ የኢህአዴግ “Surprise” ሲሆን በፓርላማ ብቸኛው የተቃዋሚ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ደግሞ ኢህአዴግ ላቀረበው “እጩ” ሙሉ ድጋፋቸውን በመስጠት እኛን ብቻ ሳይሆን ም/ቤቱንም ጭምር “ሰርፕራይዝ” አድርገዋል፡፡
(“Surprise” ሳይሆን “ሽወዳ” ነው!!) እኔ ግን አዲስ “የትግል ስትራቴጂ” ብዬዋለሁ፡፡ (እየደገፉ መቃወም ማለት እኮ ነው!) በመጨረሻ ለብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድናችን ድልን እመኛለሁ!! ሰናይ ሰንበት!!

Read 3595 times