Saturday, 12 October 2013 12:46

ፊቱን ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንግዲህ ልጆቹ እዚህ ደርሰዋል፡፡ ምስጋና ይግባቸው፡፡ ነገ አንድዬ ከእነሱ ጋር ይሁንማ! በኳሷ እንኳን ትንሽ ‘ቸስ’ እንበል! ታዲያ… ውጤቱ ምንም ይሁን ምንም፣ ሁሉም ነገር ‘በልክ’ ቢሆን አሪፍ ነው፡፡
በ‘ልክ’ የመሆንን ነገር ካነሳን…አለ አይደል…ዘንድሮ ብዙ ነገር የሚበላሸው ‘በልክ’ አልሆን እያለ አይመስላችሁም! ልክ ነዋ…ምንም እንኳን ስለ ውሀ ልክና ‘ሞራሌ’ ምናምን የሚባሉ የግንባታ ነገሮች ባናውቅም… አንድ ከተማ እንዲህ እንዳለ ፍርስርሷ ይወጣል እንዴ! አሀ…የፈለገው ሥራ ይሠራ… ህይወት እኮ መቀጠል አለባት!
እናላችሁ…ዘንድሮ ብዙ፣ በጣም ብዙ፣ እጅግ በጣም ብዙ ሰው በየቦታው ባለው ቁፋሮ የተነሳ በተለያየ መልኩ እየተቸገረ ይገኛል፡፡ የሚገርመው እኮ…ምናለ እግረኛ እንዲተላለፍ ብቻ የሚተው ቦታዎች ላይ እንደው መርገጫ ድንጋይ ምናምን ማስቀመጥ ይህን ያህል ትልቅ ነገር ነው! ሰዉ…ሱሪውንና ቀሚሱን እየሰበሰበ፣ ጫማው በ‘ጭቃ ባህር’ ውስጥ እየጠለቀ፡ ከአሁን አሁን “በእንትኔ ዘጭ አልኩ!” እያለ እየተሳቀቀ ለምን ይቸገራል! በአካባቢው ባለ ግንባታው የተነሳ “እግረኞች በዚህ እለፉ…” ከተባለ ቢያንስ፣ ቢያንስ ሳይደናቀፍ፣ ሳይንገዳገድ፣ ደግፈኝ/ደግፊኝ ሳይባባል እንዲተላለፍ በዶማና በአካፋ ቢጤ ነካ፣ ነካ ማድረግ የሩብ ሰዓት ሥራስ ይጠይቃል!
ነው…ወይስ ወደላይ ‘ከፍ’ እያሉ ሲኬድ ታቹ አይታይም! ይሄን ያህል ‘ደቃቆች’ ሆነናልሳ! አለበላዛ…መቼም አማሪካን ‘ወዳጃችን’ አይደለች… የ‘ናሳ’ ጠፈር ተመራማሪዎች ማርስን የሚሰልሉበትን መነጽር ያውሱልንና ‘ላይ ቤቶች’ ጉዳችንን ይዩልንማ!
የምር ግን…የተሻለ ‘ነገ’ የሚታሰበው እኮ ዛሬም እየተኖረ ነው፡፡ አለበለዛ አባቶቻችን…
ጊዜ ከዘገየ ከመሸ በኋላ
ገና ጥርስ አውጥቼ እንጀራ ልበላ፣
ያሉት ነገር ነው የሚሆነው፡፡
እናላችሁ…‘ልክ አልሆን’ ያሉ ነገሮች በየቦታው መከራችን እያበዙብን ነው፡፡ አንዱ ጋ ልኩን ያልፋል፣ አንዱ ጋ ልኩ ግማሸ ላይ እንኳን አይደረስም፡፡
እናማ…ለምሳሌ በዚች ‘ተለጣጭ ወንበር’ የምትባል ነገር ስንመጣ…የሚቀመጡባት ሰዎች ወይ ከ‘ጭንቅሌ አለመዳበር’፣ ወይ ከተራ የወንዝ ልጅ ሰብሳቢነት፣ ወይ ከለየለት ‘ፕሪሚቲቭ’ እብሪት…‘ልካቸውን አላውቅ’ እያሉ ነገርዬው “ምን እንዳታመጣ” አይነት የመንደር ጠብ ያለሽ በዳቦ እየመሰለ ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በተለይ ይሄ ‘ዘመዳ ዘመድ እየሰበሰቡ በዙሪያ የማደራጀት’ ነገር…አለ አይደል…ይቺን አገር ወዴት እየወሰዳት እንደሆነ አያሳስባችሁም! ዘንድሮ መቼም “የተማረ ይግደለኝ…” ምናምን የሚባለው ተረት ‘ላልተወሰነ ጊዜ ከአገልግሎት ውጪ’ ሆኖላችሁ…“አወቀ” የሚባለውም፣ “እውቀት ይጎድለዋል” የሚባለውም…እየተጠራራ፣ ምን አለፋችሁ ‘የእንትን ድርጅት’፣ ‘የእንትን ኩባንያ’ የሚባሉት ነገሮች የበር ላይ ጽሁፎች ሆነው የቀሩ እየመሰለ ነው፡፡ ልክ ነዋ… ውስጥ ስትገቡ “የእንትን አውራጃ መረዳጃ እድር” የሚመስሉ ነገሮች ታያላችኋ!
በበፊቱ ዘመን እንዲህ እንደ ዘንድሮ ዘመድ ለዘመድ እየተፈላለገ ሲጠራራ…ባዶ ሜዳ ላይ የቀረ ምስኪን የተቀኛት የምትስመስል ቅኔ ነገር ምን ትል መሰላችሁ…
ጠምጄ ነበረ ልዘራ ዳጉሳ
ለካስ ረስቼው ዘር የለኝምሳ፡
አሪፍ አይደለች…ይቺን ቅኔ መሪ ቃል ያደረገ ማህበር ይቋቋምልንማ! (እንትና…በዛ ሰሞን “ብፈልግ፣ ብፈልግ ‘ግንዴን’ ማግኘት አልቻልኩም…” ያልከው…ምናልባት የአንተው – አውላላ ሜዳ ላይ እንደቀረነው ምስኪኖች– ግንድ ሳይሆን ቁጥቋጦ ነገር ሆኖ እንደሁስ! ቂ…ቂ…ቂ… አሀ…ልክ ነዋ! ምነው እንክትክት ብለን አንስቅ! በየቦታው የተለያዩ ‘ግንዶች ከእነ ቅርንጫፎቻቸው’ ሲቆሙ መሀል ሜዳ ላይ የቀረነው ቁጥቋጦ ብንሆን መሆን አለበት ብዬ ነዋ!)
እናላችሁ…ይሄ ‘ልክ አለማወቅ’ ነገር…አለ አይደል…በመአት ነገር ታዩታላችሁ፣ ይሄ በሆነ ባልሆነው “ዓለም ያደነቀን…” “የዓለም መነጋገሪያ የሆንነው…” የሚሉ ‘ልብ ወለዳዊ ልብ ወለዶች’ (የሚባል ነገር ባይኖርም እንደ ሀሳብ የያዝልን) ልክን ያለማወቅ ችግሮች ይመስሉኛል፡፡
በቀደም በዓመቱ ውስጥ አፍሪካ ከመጡ ከሀምሳ ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች እኛ ዘንድ የመጡት አንድ ሚለዮን እንኳን አይሞሉም ሲባል ነበር፡፡ እናሳ…‘ያደነቁን’ ሁሉ ምነው ዶላሬውን፣ ፓውንዱን ምናምን ይዘው አይጎርፉ!
ለምሳሌ አሥራ ምናምነኛውን ምሥራቅና መካካለኛ አፍሪካ ዋንጫን የሰጠን አንድዬ ነገ ደግሞ… ‘ያምናን ቀን ረገምኩት…’ ምናምን የሚለውን ብሶታችሁን ከመቀጠላችሁ በፊት እስቲ ለዚች ሰንበት እንኳን ደስ ይበላችሁ…” ይለን ይሆናል፡፡
ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የኢትዮጵያና የናይጄርያን ግጥሚያ የዓለም መገናኛ ብዙሀን የሚዘግቡት ‘ልዩ ትኩረት’ ስለተሰጠው ሳይሆን…በቃ፣ ከምድቡ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች የመጀመሪያው ስለሆነ ነው፡፡ አለቀ! ይልቁንስ ያስገርምና “ጉድ” ያሰኝ የነበረው ባይዘግቡት ነበር፡፡
እናማ… ‘ልክ ያለማወቅ’ ለራስ የሚሰጥ ግምትን ያበላሻል፡፡ ዘንድሮ በተለይ በኪነ ጥበቡ፣ በስፖርቱ እና በሌላውም የምናየው “ከእኔ በላይ ላሳር…” ‘ባህል’ ምንም ሳይሆን ‘ልክን ያለማወቅ’ ነገር ነው። በዛ ሰሞን በአንድ ዝግጅት ላይ “አዲስ አበባ ኒው ዮርክን እየመሰለች ነው…” የሚል ነገር ስንሰማ…“ጎበዝ ኧረ እንዴት ነው ነገሩ!” ብለናል፡፡ እንዴ…ኮምፒዩተር ፊት ቁጭ ብለን ስለማንኛውም ነገር፣ ስለየትኛውም አካባቢ የፈለግነውን መረጃ ማግኘት በምንልበት ዘመን…እንዲህ አይነት ‘ልክን አለማወቅ’ አሪፍ አይደለም፡፡
ደግሞ አዲስ አበባ ዘመናዊ ለመሆን ከኒው ዮርክ፣ ቶክዮ… ምናምን መወዳደር አያስፈልጋትም። የስሟን ያህል እንኳን ‘አዲስ አበባ’ ብትሆን ይበቃታል፡፡
እግረ መንገድ…በተለይ ኤፍ.ኤሞች ላይ ለሚሠሩ…ይሄ አንድ ነገር በተነሳ ቁጥር አገራችንን ከሌላው ጋር ለማመሳሰል፣ ለማበላለጥ የሚደረገው ‘ማሳመሪያ’ ..አለ አይደል… እውነት ቢሆን እንኳን ከመሰልቸቱ የተነሳ እንዳይታመን ያደርገዋል፡፡ ይቺ አገር…የውጪ ሚዲያ፣ ዲፕሎማት ቅብፕርስዮዎች የማይናገሩላት ብዙ ነገሮች የነበሯት፣ ብዙ ነገሮች ያሏት አገር ነች፡፡
ማወዳደር ምናምን ሳያስፈልግ ራሷን ችላ መቆም የምትችል የነበረች አገር ነች፡፡ እናማ…በተደጋጋሚ የሚባለውን ለመድገም እናንብብ! እናንብብ! እናንብብ! የተለያዩ ድርሳናትን እያነበብን፣ እየፈተሽን በሄድን ቁጥር…እመኑኝ ደጋግመን የምንለው ነገር ቢኖር… “እውነት ይቺ አገር እንዲህ ነበረች!” የሚል ነው፡፡
በዛ ሰሞን እንዲሁ በአንድ የሚዲያ ዝግጅት ላይ… “አዲስ አበባን አሁን ሳያት ዱባይን ነው የምታስታውሰኝ…” ያለው ‘አስተያየት ሰጪ’…አለ አይደል… ‘ሌላ ዱባይ’ እንዳለች ስለጠቆመን አድናቂው ነኝ፡፡ ልክ ነዋ…መቼም ይቺ በየዓረብ ቻነሎች የምናያትን ዱባይ ሊሆን አይችልም!
እናላችሁ…ሳንጠይቅ፣ ሳናመዛዝን በተቀደደ ቦይ እየገባን በህልም ባህር ዋኝተን ወደ እውነተኛው ዓለም ስንመጣ ያለውን ድንጋጤ አያድርስብንማ! ድሮ በዘፈን ህንድ አንደኛ፣ ሱዳን ሁለተኛ፣ ኢትዮጵያ ሦስተኛ የሚባል ነገር ነበር፡፡ እናማ ሰዋችን እንክት አድርጎ ነው የሚያምነው፡፡ እናማ…ከህልም ባህራችን ብቅ ስንል…አይደለም ሦስተኛ ምናምነኛ መባል…“አገራችሁ የሙዚቃ ባንድ አለ?” አይነት ነገር ሲገጥመን ይታያችሁማ! እናማ…ልክን ማወቅ እየተሳነን ሁላችንም በአንድ ቦይ ስንፈስ አሪፍ አይደለም፡፡
ሁሉ በሽተኛ ሁሉ ራሴን ባይ
በቤታችን ደህና መጥፋቱ ነው ወይ፣
ከመባባል ይሰውረንማ!
እና ‘ልክን ማወቅን የመሰለ ነገር የለም፡፡
በዛ ሰሞን የሆነ ሰው በ‘ፈረደበት ሚዲያ’…አለ አይደለም… “ዓለም ያደነቀው ዲሞክራሲያችን…” ምናምን ሲል ሰምቼ ለራሴ ምን አልኩ መሰላችሁ…“አይ ይሄ ‘ዳስ ካፒታል’ ምናምን የሚባለውን መጽሐፍ ፈልጌ ማንበብ አለብኝ…” አልኩ፡፡ ‘ስለሚደነቁ ዲሞክራሲዎች’ የተጻፈው እሱ ላይ ነው…አይደል! ቂ…ቂ…ቂ…
እና ‘ልክን ማወቅን የመሰለ ነገር የለም፡፡
ፊቱን ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ፣
ተብሏል፡፡
ለቡድናችን መልካም ዕድል፡፡
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 2997 times