Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 26 November 2011 08:37

አዲስ አበባ በኪራይ ሰብሳቢነት አልተቻለችም!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የዜጐችን “ቀለበት” የሚያስተጓጉል “ግምገማ” ....  
ወጋችንን ከመዲናችን ብንጀምር ምን ይመስላችኋል? ከአዲስ አበባችን ማለቴ ነው፡፡
ስምን መላዕክ ያወጣዋል የሚባለው ለካ እንዲህ ነው፡፡ “አዲስ”ም ያልሆነችው “አበባ”ም የሌላት መዲናችን ስሟ አዲስ አበባ ሲሆን ግርም ይላል፡፡ የከተማዋ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ሰሞኑን ለተወካዮች ም/ቤት ባቀረቡት መግለጫም፤ መዲናዋ በኑሮ ውድነትና በሌሎች ችግሮች የተተበተበች መሆኗን ተናገሩ እንጂ ስለ አዲስነቷም ስለ አበባነቷም ያሉት ነገር የለም፡፡

ለነገሩ እኮ የከተማዋ አዲስነት ለእቴጌ ጣይቱ እንጂ ለኢህአዴግ ሊሆን አይችልም፡፡ ከ100 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረች ከተማ በምን ተዓምር አዲስ ልትሆን ትችላለች? በእርግጥ ከንቲባው ከዚህ ቀደም ያልተናገሩት አዲስ ነገር ስለከተማዋ ተናግረዋል - አዲስ አበባ የኪራይ ሰብሳቢነት የበላይነት የሰፈነባት ከተማ ሆናለች በማለት፡፡
እሳቸው የተናገሩትን በ”ፖለቲካ በፈገግታ” ሳፍታታው፤ አዲስ አበባ የኪራይ ሰብሳቢ ከተማ ሆናለች የሚል አንደምታ ይሰጠናል፡፡ “በተለይ በመሬትና በግብር ጉዳዮች ላይ አትኩረን ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማስወገድ ሰፊ ጥረት ስናደርግ ብንቆይም፤ ሠራን ባልንባቸው በእነዚህ መስኮችም ቢሆን ዛሬም ከኪራይ ሰብሳቢነት አረንቋ አልወጣንም” ብለዋል - አቶ ኩማ ደመቅሳ፡፡ ከተማዋን በተመለከተ በከንቲባው የተሰጠው በችግሮች የተሞላ ሪፖርት፤ ከተቃዋሚዎች የመጣ ቢሆን ኖሮ “ጨለምተኛ” ብዬ ለማጣጣል አፍታም አይፈጅብኝ ነበር፡፡ ግን የእሳቸው ስለሆነብኝ በግዴ ዋጥ አደረኩት፡፡
የአቅም ግንባታና የመልካም አስተዳደር እጦት አሁንም ከባድ ፈተና ሆኖ የተጋረጠባት አዲስ አበባ፤ የኑሮ ውድነቱም የራሱን ተጽእኖ እያሳፈረባት የምትገኝ ከተማ ሆናለች ይላሉ - ከንቲባው፡፡
ይሄም በዋነኞቹ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ የተጀመሩትን የለውጥ እርምጃዎች በከፍተኛ ደረጃ እየተፈታተናቸው እንደሚገኝ አቶ ኩማ ተናግረዋል፡፡
የከንቲባው ሪፖርት ጨለምተኝነት ያየለበት ቢመስልም እውነት እንደሆነ ግን ማንም አይክድም - ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ፡፡ እንግዲህ እኔ እንደተረዳሁት አዲስ አበባን የኪራይ ሰብሳቢ ከተማ ያደረጓት በኑሮ ውድነት መከራቸውን የሚበሉት ነዋሪዎቿ አይደሉም፡፡ እኛ ነዋሪዎቿማ ልማታዊም ኪራይ ሰብሳቢም መሆን አቅቶን የሚሆነውን እየጠበቅን ነው፡፡ ከንቲባውም እንደገለፁት፤ ችግሩ ይበልጥ የሚታየው ከመሬትና ግብር ነክ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ደግሞ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮች እንደሆኑ አሳምረን እናውቃለን፡፡ በነገራችን ላይ ከንቲባው ደፍረው አልተናገሩትም እንጂ ኢህአዴግ ውስጥ ኪራይ ሰብሳቢዎች ሰርገው ገብተዋል፡፡ ቁጥራቸውም ቀላል አይመስለኝም፡፡ ያለዚያማ የበላይነት ሊኖራቸው አይችልም ነበር፡፡ እኔን የገረመኝ ግን ልማታዊ ኢህአዴጐች ነገሩ እንዲህ እስኪሆን ድረስ ምን ይጠብቃሉ? “ንቀውናል፤ ደፍረውናል” ማለት ይሄኔ ነው!
የሆነ ሆኖ ግን ችግሩን የመፍታት ሃላፊነቱን ለራሱ ችግሩን ላመጣው ኢህአዴግ እንተወው፡፡ ለክፋት እንዳይመስላችሁ … መላውን (ብልሃቱን) የሚያውቀው እሱ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር እስኪፈታ ግን የከተሞች የኪራይ ሰብሳቢነት ደረጃን የሚያወጣ ተቋም ብናቋቁም ምን ይመስላችኋል? መቼም የአንደኝነት ደረጃውን ከአዲስ አበባ ላይ የሚወስድ ማንም የለም፡፡ እንደውም የመዲናችን ቅፅል ስም “ኪራይ ሰብሳቢ” ወይም “Rent Seeker” ቢባልስ? ለመጪው ትውልድ የመዲናዋን ታሪክ ለማስተላለፍ ማለፊያ ብልሃት ይመስለኛል፡፡ አሁን በዚህች የኪራይ ሰብሳቢዎች ከተማ የተከሰተ አስደማሚ ታሪክ ላውጋችሁ፡፡
ሰሞኑን አንድ ወዳጄ የቀለበት ስነስርዓት ነበረበት፡፡ (ቀለበት ያስራል ለማለት ፈልጌ ነው፡፡) እንግዲህ ቀለበቱ ጠዋት እንደሚከናወን ጠቁሞኝ ነበርና ከምሽቱ 11 ሰዓት ላይ በሙሉ ልብስ ሽክ ብሎ ሳገኘው “ቀለበቱ እንዴት ነበር?” ስል ጠየኩት፡፡
“ባ’ክህ አልተሳካም” አለኝ፤ በቅሬታ የቀለበት ጣቱን እያሳየኝ፡፡ ደነገጥኩ፡፡ እውነትም አልተሳካም፡፡ ጣቱ ላይ ቀለበት አላሰረም፡፡
“ምነው ምን ተፈጠረ?” ቀጣዩ ጥያቄዬ ነበር፡፡
ወዳጄ መልስ እስኪሰጠኝ እኔ ስንቱን እንዳሰብኩ አልነግራችሁም፡፡ ቆይ እንዴት ነው ቀለበት ላይሳካ የሚችለው? ቀለበት የሚያስሩት ጥንዶች አሉ፡፡ ቀለበቱም ተገዝቷል፡፡ በአጠቃላይ ለሥነስርዓቱ የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች በሙሉ እንደተጠናቀቁ ወዳጄ ነግሮኛል፡፡ እኔ መቼም እስከዛሬ “የቀለበት ስነስርዓቱ አልተሳካም!” ያለኝ ሰው አልገጠመኝም፡፡
ምናልባት የፈጠራ ስራዎች (ፊልምና ልቦለድ) ላይ ሊኖር ይችላል፡፡ በተረፈ ግን እንጃ! ለዚህም ነው የደነገጥኩት፡፡
የሆነ ሆኖ ወዳጄ ጠዋት ላጤ ሆኖ ከቤቱ ወጥቶ ባለትዳር ሆኖ ሊመለስ ነበር ያሰበው -ቀለበት አስሮ፡፡ ግን አልተሳካም፡፡ በፍፁም! በጥንዶቹ መሃል ድንገተኛ ችግር ተፈጥሮ ይሆን ብላችሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ፡፡ በጥንዶቹ መሃል ፍቅር በሽበሽ ስለሆነ የፈለገ ችግር ቢፈጠር በፍቅር ይፈታል፡፡ የቀለበቱ ሥነስርዓት የተስተጓጐለው በምን መሰላችሁ? በስብሰባ ነው! የማን ስብሰባ ያላችሁ እንደሆነ መልሱ … የክፍለከተማ አመራሮች የሚል ነው፡፡ እኔ ስገምት ግን ስብሰባ ተባለ እንጂ ነገሩ ግምገማ ሳይሆን አይቀርም፡፡ (የከተማዋ አስተዳደር፤ ሃላፊዎችን እየገመገመና ሹም ሽር እያደረገም አይደል!) ስብሰባም በሉት ግምገማ ግን የወዳጄ የቀለበት ስነስርዓት ተስተጓጉሏል፡፡
ቀድሞ በማዘጋጃ ቤት ይፈፀም የነበረው የጋብቻ ውል (ቀለበት) በየክፍለከተማው መፈፀም ከጀመረ ቆየት ሳይል አልቀረም፡፡ እናም ስንቱ ጋብቻ ፈፃሚ በስብሰባ ሰበብ ቀለበት ሳያስር ሥነስርዓቱ ለሌላ ቀን ተላልፎበት እንደተመለሰ ቤቱ ይቁጠረው፡፡
አንድ ጥያቄ አለኝ - አገር አማን ሆኖ የሰው ቀለበት የሚያስተጓጉል አስቸኳይ ስብሰባ ከየት መጣ? በመረጃ አልተረጋገጠም እንጂ በዕለቱ ሁሉም ክ/ከተሞች በስብሳባ ተወጥረው እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ በዚያን ዕለት በመዲናዋ አንድም ቀለበት ያሰሩ ጥንዶች የሉም እንደማለት ነው፡፡ ለምን ብትሉ … ክፍለከተሞቹ እየተገማገሙ ስለነበር! ለምን እንደሆነ አላውቅም… የኢህአዴግ ሹመኞች በር ዘግተው ግምገማ ላይ ነን ሲሉ ደስ አይለኝም፡፡ የግምገማውን ውጤት ስለማይነግሩን ይሆን? ብቻ ግምገማ … ስብሰባ … አይመቸኝም (ኪራይ ሰብሳቢዎችን ያበዛብን እሱ ቢሆንስ?)
… የወዳጄስ ቀለበት ስለሆነ ችግር የለውም፡፡ ዛሬ ባይሳካ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ ያስራል - ቀለበቱን፡፡ ጊዜ የማይሰጥ የሆድ ነገር ቢሆን ኖሮስ? ለምሳሌ ስኳርና ዘይት የሚቸረችረው መንግስት እንደመሆኑ መጠን ነዋሪዎች እንደአቅሚቲ አንድም ሁለትም ኪሎ ለመሸመት በየቀበሌያቸው ጐራ ሲሉ የቀበሌ ሱቅ ደጃፉ ተጠርቅሞ ግምገማ ላይ ናቸው ቢባልስ? አያድርገውና ዳቦ ቤቶች በክ/ከተማ ስር ቢሆኑና ዳቦ ለመግዛት ስንሄድ “ዛሬ ዳቦ የለም፤ ግምገማ ነው ያለን” ብንባልስ? አሁንም አያድርገውና የመዲናዋ ሆስፒታሎች በሙሉ በክ/ከተማ ስር ቢሆኑና ቀኗ የደረሰ ነፍሰጡር ወደ አንዱ ሆስፒታል ለእርዳታ ስትሄድ… ሆስፒታሉ በግምገማ በሩን ዘግቶ ብታገኘውስ? ልጁ የሚወለድበት ቀን እንደቀለበቱ ሊተላለፍ ነው? የግድ ነው! ከግምገማ የሚበልጥ ነገር የለማ!
እስቲ አስቡት… የቀብር ሥነስርዓት ለመፈፀም ወደ ክ/ከተማ መሄድ የግድ ቢሆን ምን ሊፈጠር እንደሚችል? በእርግጥ እኔ ሞቼ ስለማላውቅ ጉዳዩ ክ/ከተሞችን ይመልከት አይመልከት አላውቅም፡፡ ግን ባይመለከት ፀሎቴ ነው!
ለምን መሰላችሁ? የክ/ከተሞች ሃላፊዎች ስብሰባ ባማራቸውና በተገማገሙ ቁጥር ሃዘንተኞች ለቅሶና ሀዘኑ ሳያንሳቸው፣ በክ/ከተሞች ይንገላቱ ነበራ! “ዛሬ ቀብር የለም ግምገማ ነው” ካሉ ሃዘንተኛው አስከሬኑን ይዞ ወደ ቤቱ ከመመለስ ውጭ ምን አማራጭ አለው?
ወዳጄ ቀለበቱ አለመሳካቱን ከነገረኝ በኋላ ለጉዳዩ ተጠያቂው ማን ሊሆን እንደሚችል ሳወጣና ሳወርድ ነበር - ለብቻዬ፡፡ ከጥቂት የአዕምሮ ጅምናስቲክ በኋላ ግን ደረስኩበት፡፡
አዎ ለወዳጄ ቀለበት መስተጓጐል ተጠያቂውን አግኝቼለሁ፡፡ ወዳጄንና ፍቅረኛውን (ባለቤቱን) በደስታ ቀናቸው መውቀስ አይሁንብኝና ለቀለበታቸው ሥነስርዓት መስተጓጐል ዋነኛ ተጠያቂዎቹ ራሳቸው ናቸው፡፡ እንዴት ብትሉኝ… የቀለበት ቀናቸውን በዚህ ቀን ነው ብለው ከመወሰናቸው በፊት “የሰፈር ካድሬ” ወይም “ውስጥ አዋቂ” ፈልገው በክ/ከተማው ስብሰባ ወይም ግምገማ መኖር አለመኖሩን ማሰለል ነበረባቸው፡፡ አያችሁ… ስለላ ለፖለቲካና ለጦርነት ብቻ ሳይሆን ለቀለበትና ለሠርግም ወሳኝ እየሆነ መጥቷል፡፡ እናም በቅርቡ ቀለበት ለማሰር ዕቅድ ያላችሁ ጥንዶች፤ ጉድጉድ ከመጀመራችሁ በፊት በክ/ከተማችሁ መቼ ስብሰባና ግምገማ እንደሌለ አሰልሉ፡፡ መረጃውን በቀጥታ እናገኛለን ብላችሁ ካሰባችሁ ግን ተሸውዳችኋል፡፡
በመጨረሻ ግን ለኢህአዴግ ትንሽዬ ምክር አለችኝ፡፡ ለሹመኞቹ የግምገማ ፕሮግራም ያውጣላቸው፡፡ እንዴ … ለምን ከሥራ ውጭ በትርፍ ጊዜያቸው አይገማገሙም? ጉዳዩ ዝም ከተባለ እኮ የከተማዋ ነዋሪ ህይወት ይመሳቀላል፡፡ ዛሬ የዜጐች የቀለበት /ፕሮግራም/ በሹመኞቹ ከተወሰነ፤ ነገ ደግሞ የቁርስና የምሳ ሰዓትም በእነሱ ውሳኔ ስር መውደቁ አይቀርም፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ የእኛን የነዋሪዎችን ፕሮግራም ማዛባት ይሆናል፡፡ የሆነ ሆኖ ግን ወዳጄ በነጋታው ክ/ከተማ ሄዶ፣ ግምገማ ስላልነበረ የቀለበት ሥነስርዓቱን ፈጽሟል፡፡ ነገ ደግሞ ሰርጉን ይፈጽማል፡፡ በእርግጥ የሰርግ ሥነስርዓቱ ከክ/ከተማ ጋር የተያያዘ ስላልሆነ የሚያሰጋ ነገር የለም፡፡ ወዳጄ ጋብቻው የአብርሃምና የሣራ ጋብቻ እንዲሆንላት ተመኝቼ ብሰናበትስ … ወይስ “ፖለቲካ በፈገግታ” ላይ መልካም ምኞት መግለፅ አይቻልም?

 

Read 5232 times Last modified on Saturday, 26 November 2011 08:45