Print this page
Saturday, 28 September 2013 11:06

“ትላንትና ማታ ቤትህ ስትገባ እንቅፋት የመታህ ድንጋይ ዛሬ ማታም ከደገመህ፤ ድንጋዩ አንተው ነህ!

Written by 
Rate this item
(5 votes)

             ከዕለታት በአንዱ ዝናባማ ቀን አንድ ሰው በአንዲት ቀጭን መንገድ እየሄደ ነበር። ዝናቡ ብዙ የዘነበ ስለሆነ አካባቢውን ሁሉ አጨቅይቶታል፡፡ በተለይ ያቺ ቀጭን መንገድ፤ ለአንድ ጊዜ የምታሳልፍ ሲሆን እጅግ አድርጋ ጭቃ በጭቃ ከመሆኗና በጣም ከመሟለጧ የተነሳ፤ የረገጡትን እግር ሁሉ ታዳልጣለች፡፡ ሰውየው በጣም ይቸኩል እንጂ በጥንቃቄ መራመድ እንዳለበት ገብቶታል፡፡ ከኋላው ያለ አንድ ሰው ከኋላው እየተከተለ ነው፡፡ እንግዲህ ተከታትለው እየሄዱ ነው፡፡ የመጀመሪያው ሰውዬ ጥቂት እንደተራመደ፤አዳለጠውና ዘጭ አለ፡፡ ወድቆ ጭቃው ላይ አረፈ፡፡ እንደ እልህም እንደቁጭትም ያዘውና፤ “እቺን ይወዳል?!” አለ፡፡

ሆኖም፤ እንደምንም ተሟሙቶ ተነሳ፡፡ ተስተካከለና እንደገና ለመራመድ ሞከረ፡፡ እንደገና ወደቀ፡፡ ሙሉ በሙሉ ጅው ብሎ ነው ከጭቃው የተደባለቀው፡፡ አሁንም፤ “እቺን ይወዳል?!” አለና እንደምንም መሬት ቧጦ ተነሳ፡፡ ከኋላው ለማለፍ የፈለገው ሰውዬ ትዕግስቱ እያለቀ መጥቷል፡፡ ወድቆ የተነሳው ሰው ለሶስተኛ ጊዜ ሙከራ ለማድረግ ሲራመድ፤አሁንማ ከስሩ ያለው ጭቃ ጭራሽ ላቁጧልና ባንድ ጊዜ አዳልጦት ዘጭ አደረገው፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ፤ “እቺን ይወዳል?!” አለ ጮክና ቆጣ ብሎ፡፡ ይሄኔ ከኋላ ሆኖ ይህንን እየሠማ ትርዒቱን የሚያስተውለው፤ ለማለፍ የሚፈልገው ሰውዬ ተናደደና፤ “ስማ የእኔ ወንድም፤አንተ ከወደድከው ተንደባለልበት! ለእኔ መንገድ ልቀቅልኝ!” አለው፡፡

                                                    * * *

በማንኛውም የህይወት እንቅስቃሴ ውስጥ መውደቅም ሆነ ማዳለጥ ያለ ነው። መነሳት አንድ የጠንካራ ሰው ነገር ነው፡፡ ደግሞ መውደቅ ፣ሆኖም እዚያው ቦታ ላይ መውደቅ አሳዛኝ ነው፡፡ ቀጭንና አዳላጭ የሆኑ የትግል መንገዶች ብዙ ናቸው፡፡ መሳለጫ እየመሰሉ የማያሳልፉ መኖራቸውን ያልተገነዘበ ታጋይ፣ ደጋግሞ መውደቅ አይቀርለትም! እንግሊዙ የታሪክ ተመራማሪ ስለፈረንሳይ የንጉስ ናፖሊዮን ሶስተኛው እንዲህ ሲል ፅፏል፡- “የአንድ አገር መሪ አደገኛ ነገር ነው ብዬ የማስበው የታሪክ ተማሪ መሆኑን ነው። እንደታሪክ ተማሪዎች ሁሉ መሪውም ካለፈው ስህተቱ የተማረው እንዴት አዲስ ስህተት እንደሚሰራ ነው!” ይላል፡፡ ለእኔ ብለህ ስማ ነው፡፡ ገጣሚው፣ፈላስፋውና ሃያሲው ሳሙኤል ቴይለር ኮልሪጅ፤ ደግሞ፤ “ሰዎች ከታሪክ ለመማር ቢችሉ ኖሮ፤እንዴት ያለ ትምህርት ባገኙ! ሆኖም አንድን ነገር ሙጭጭ ብሎ ከመውደድና በይዞታነት የያዝነው ፓርቲ ዐይናችንን ከማሳወሩ የተነሳ፤ ልምድ የሚያበራልን ማሾ ያለፍነውን ማዕበል ብቻ ይሆናል” ይለናል፡፡ ለእኔ ብለህ ስማ ነው ጐበዝ!

ሔገል የባለው ጀርመናዊ ፈላስፋ በበኩሉ፤ “ልምድና ታሪክ የሚያስተምሩን አንድ ነገር አለ፡፡ ይሄውም ህዝቦችና መንግሥታት ከታሪክ በፍፁም እንደማይማሩ ነው፡፡ አሊያም ደግሞ ከታሪክ ባገኙት ትምህርት መሠረት ምንም እርምጃ አለመውሰዳቸው ነው፤ ይለናል፡፡ ለእኔ ብለህ ስማ ነው ጐበዝ! “ህይወት ሰዎች ሲሞቱ አስቂኝ መሆኗን የማታቆመውን ያህል፤ ሰዎች ሲስቁም ህይወት ኮስታራ መሆኗን አታቆምም፡፡” በርናርድ ሾው ነው ይሄን ያለው፡፡ ዕውነቱን ነው፡፡ የዛሬው መስቀል ደመራ በየትም ወደቀ በየት፤ ከላይ የጠቀስናቸው ጥቅሶች የበዓሉ ስጦታ ይሁኑ! “ትላንትና ማታ ቤትህ ስትገባ እንቅፋት የመታህ ድንጋይ ዛሬ ማታም ከደገመህ፤ ድንጋዩ አንተው ነህ!” - የምንለው ዓመቱን በፍቅር፣ ሰላምና በብርሃን እንድንገፋው ነው! መልካም የመስቀል በዓል! ”

Read 3261 times
Administrator

Latest from Administrator