Friday, 13 September 2013 12:44

“ለአዲስ ዘመን ለኢትዮጵያ ሕዝብ የምናቀርበው ስጦታ የለንም!”

Written by  ሰለሞን አበበ
Rate this item
(22 votes)

(ደርግ፣ መስከረም 1967 ዓ.ም)
የ1967 ዓ.ም አዲስ ዘመን ሊብት የዋዜማው ዕለተ ምሽት ጀምሮ የጆናታን ዲንቢልቢን “ዘ ሂድን ፌሚን” በማሳየት፣ “ለአዲሱ ዘመን ለኢትዮጵያ ሕዝብ የምናቀርበው ስጦታ [ከዚህ ሌላ] የለንም” የሚል ዝግጅት፣ በጥቁርና ነጩ ቲቪ አቀረቡ፡፡ ሕዝብ አለቀሰ፡፡ ነገር አለ ማለት ነው፡፡
አዎን፣ አለ፡፡ መስከረም 1967 ዓ.ም ልክ እንደ ዘንድሮው ረቡዕ ዕለት ነበር ዘመን መለወጫው፡፡ ሐሙስ ዕለት መስከረም 2 ጧት የአፍሪካ አዳራሽ የሚባለው ኢሲኤ ፊት ለፊት ሕዝብ ግጥም ብሎ ወደ ኢዮቤልዮ ቤተመንግሥት አሻግሮ ይመለከታል። ታንክና ብረት ለበስ ጦር በዙሪያው ከብቧል፡፡ የዚያኑ ዕለትም ንጉሱ ከሥልጣን የመውረዳቸው ዓዋጅ ታውጇል፡፡ ጳጉሜ 5/1966 ማክሰኞ ዕለት ነበር ለማውረድ ሲያመነታቱ የነበሩትና የደርግ አባላትን የሚያሾሩት ኃይሎች ለመጨረሻ ጊዜ የገንዘብ ጥያቄ ለንጉሱ እንዲቀርብላቸው ያደረጉት፡፡
“በስዊዝ ባንክ ያስቀመጡትን ገንዘብ ይመልሱ” ተባሉ፡፡ የርሳቸው ምላሽ ከዚህ በፊት ሲመልሱላቸው ከነበረው የተለየ አልነበረም፡፡
“ገንዘብ የለንም፡፡ የነበረንንም ለልጆቻችን አውርሰናል፤” የሚለውን ቁርጥ ያለ መልሳቸውን አጥብቀው ገለጹ፡፡
በዚህ ወቅት ይሁን ወይም ከዚህ በፊት ባይለይም፣ ትልቂቱ ልጃቸው ልዕልት ተናኜ ወርቅም፣ “የምን ገንዘብ ነው፡፡ እኛም እኮ ልጆች ነን፡፡ ወራሾች ነን” ሲሉ በቁጣና በኃይለ ቃል እንደመለሱላቸው ይታወቃል፡፡
ምናልባትም፣ የደርጉ መሪ ተዋናይ የነበሩት ሻለቃ መንግሥቱ ኃ/ማርያም በፕሬዚዳንትነታቸው ዘመን፣ “እኔ እንዲያውም ርሳቸውን አከብራቸው ነበር፡፡ እንዲያ ያሉ አድርጌ አላስባቸውም ነበር፡፡ ነገር ግን የዚያን ጊዜ የተናገሩት ከርሳቸው የማልጠብቀውን ነበር፣” ሲሉ ስለ ልዕልቲቱ በይፋ የተናገሩትም እንዲህ ያለ ጥያቄም ሲያቀርቡላቸው የተናገሯቸውን ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል፡፡
ነገር ግን ሻለቃው ከንጉሱ ፊት ቀርበው እንደነበር የማይታሰብበት ታሪክን ስለምናገኝ፣ (እንደ ግብፁ ጋማል አብዱል ናስር ሌሎችን ፊት እያስቀደሙ የፈለጉትን ሲያስፈጽሙ የነበሩ ናቸውና) ምናልባት ንጉሱ ከወረዱ በኋላ፣ በተለይም ከ10 ወሮች በኋላ በኮ/ል ዳንኤል አስፋው የሚመራው የቅልቡ ነፍሰ ገዳዮቻቸው ቡድን ከደብረብርሃን አዲስ አበባ ገብቶ፣ እንዲገድሏቸው ከማዘዙ በፊት ይሆናል ከኝህ ጊዜ ጥሎአቸው እንኳ ይፈሯቸው ከነበሩት ግርማዊው አዛውንት ፊት የቀረቡት፡፡
ያ መቼም ይሁን፣ በጳጉሜ 5/67 ዓ.ም ለደርግ አስተባባሪ መልእክተኞች የመለሱት ምላሽ ግን ከወራት በፊት ጀምሮ በደርግ ሲብላላ የቆየው ንጉሱን የማውረዱን ሥራ ቁርጥ አደረገው፡፡ ወደዚያው፣ ሕዝቡንም ለማነሳሳትና ተገቢ ርምጃ እንደሆነ እንዲታሰብ፣ አዲስ አበባ ላይ ለነበሩ ባለቴሌቪዥኖች የጆናታን ዲንቢልቢ “ዘ ሂድን ፌሚን” የአዲስ አመት ስጦታ ሆኖ እንዲተላለፍ ተደረገ፡፡ “እኛ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመኑ መለወጫ የምናቀርብለት ስጦታ የለንም” በሚል ርዕስ ይህ የዲንቢልቢ ፊልም እና የንጉሠ ነገሥቱ የደግ ጊዜ ዓለም ጐን ለጐን እየተቀነባበረ፡፡ የዚያኑ ዕለት ምሽት (ለአዲስ አመት ዋዜማ ምሽት) ጀምሮ በጥቁር ነጩ ምስል ቀረበ፡፡
በዚህ ፊልም የሚታየው የረሃቡ ሰለባዎች ሁኔታ አሳዛኝና ሰው ሆኖ መፈጠርን ሁሉ የሚያስጠላ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ በየጣልቃ ከሚገቡት በንጉሡ አካባቢ የነበሩ አንዳንድ ድግሦችና ፌሽታዎች ጋር፣ በተለይም አሠርተውት ከነበረ ሐውልት ጋር ሲቀናጅ ብዙዎችን አስለቅሶ እንደነበር የገለጹ አሉ፡፡
የሚገርም ነው! ደርግ በወሎ የነበረውን ወደ 1 ሚሊየን ሰው የተጠቃበትን ረሃብ ከንጉሡ ሐውልት ግንባታ ጋር በማቅረብ ሰውየው ላይ ዘመተባቸው። በእርሱ ዘመን ደግሞ የረሃብተኛው ቁጥር በ3 እጥፍ አድጐ የዓለምን ልብ ባሳዘነበት ወቅት፣ እርሱም ትግላችን ሐውልትን ይገነባ ነበር፡፡ የርሱ ተከታዮችም የንጉሱንና ይህን የደርጉን ዘመን የረሃብ ሰቆቃ እና የሐውልት ግንባታዎች ታሪክ እየተረኩም ነበር የቀሰቀሱትም የገቡትም፡፡ በሚያስገርም ተመሳሳይነት የረሃብተኛው ብዛት ከንጉሱ ዘመን ከስምንት እጥፍ በላይ በሚሆን ቁጥር ጨምሮ በነበረበት ጊዜ ደግሞ እነሱ የሰማዕታት ሐውልትን ግንባታ ላይ ነበሩ፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ በቅርብ ካለው ሕዝብ ሊገጥም የሚችል ተቃውሞም እንዳይኖር፣ ይልቁንም ድርጊቱን እንዲደግፉላቸው እንዲህ ተደርጐ ሲቀርብ አድሮና ውሎ፣ በቀጣዩ ቀን፣ መስከረም 2 ቀን ላይ ንጉሱን ከሥልጣን የማውረዱ ሥራ ተከናወነ፡፡ የማውረጃው ዓዋጅም ታወጀ፡፡ ሐሙስ ዕለት ጧት ላይ ነበር፡፡ ሰውም አስቀድሞ አውቆታል፡፡ አዋጁ በማለዳው ጧት እንደተሰማ ይታወቃል፡፡ ያም ሆኖ ይሆናል የአፍሪካ አዳራሽ ፊት ለፊት (ኢሲኤ) ጧቱኑ በብዙ የአዲስ አበባ ነዋሪም የተሞላው፡፡
በኢዮቤልዩ ቤተመንግሥቱ ውስጥ የ83 ዓመቱ ንጉሠነገሥት ከሚታወቅላቸው የዕለት ተዕለት የጧት መደበኛ ውሎአቸው በተለየ ሁኔታ ከዙፋናቸው ተቀምጠዋል፡፡ ለርሳቸው ከሚቀርቡት ልዑል ራስ እምሩም በዚያች ጧት ላይ በታዛቢነት እንዲገኙ አዛዥ - ናዛዥ የሆነው ደርግ በጠራቸው መሠረት ተገኝተዋል፡፡
ከደርግ የተመረጡ 13 አባላት የያዘው ቡድን አባላት፣ ከአሁን አሁን ወገቤን ሊያነክቱኝ ነው ብላ ተሸማቅቃ ቁልጭልጭ እንደምትል ውሻ ከፊታቸው ወደ ቀኝ ጐን፣ ትከሻ ለትከሻ ከመተዛዘል ብዙም ባልራቀ ሁኔታ ተጠራቅመው ቆመዋል፡፡
እንደ አንድ ፖላንዳዊ አገላለጽ፣ ፍርሃታቸው ያ የሞት ሽረት ደብዳቤ ለነሱው ራሳቸው የሚገለጽ ይመስል ነበር፡፡
የቡድኑ መሪ የነበሩት ሻለቃ ደበላ ዲንሳ የያዙትን ወረቀት አነበቡ፡፡
“የጦር ኃይሎች የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር ደርግ ለግርማዊነትዎ ደህንነትና ጤንነት በሰፊው እሚያስብ እንደመሆኑ መጠን፣ ለዚሁ ለጤንነትዎም ሆነ ለደህንነትዎ የተዘጋጀ ሥፍራ ስለ አለ ወደዛ እንዲሄዱልን በትህትና እንለምናለን፡፡”
እንደምንም ጨረሷት አንብበው፡፡
ንጉሡ ዝም ብለው ቆዩ፡፡ ከዚያ ያላንዳች ድንጋጤና መረበሽ ይጠይቋቸው ጀመሩ፡፡
“እንዴት ነው የሚኬደው?”
“ወደተዘጋጀ ሥፍራ…ሥፍራ አለ፡፡ በተለይ ያዘጋጀነው፡፡ ከኛ ጋር እንሄዳለን”
“በጠቅላላው መቼም የተናገራችሁትን ሰምተናል፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ስንሆን ስም ብቻ አይደለም፤ ሕዝቡም አገሩም በሰላም ጊዜ የሚሰራለትን፣ ጠላትም ቢመጣ የሚመክትበትን በማሰናዳት ነው እንጅ፡፡ ይኸው ቢሆንም፤ በየጊዜው የሚለዋወጠው ነገር ደግሞ ላገር የሚጠቅም ነገር እስከአለበት ያገርን ጥቅም በሌላ ለመለወጥ አይቻልምና ይህ ያነበባችሁትን ሰምተናል፤ አሁንም እንደዚህ ነው፡፡ ማቆም ነው፡፡
“የኔ ታሪክ እዚህ ያበቃል፡፡ የናንተ ታሪክ እዚህ ይጀምራል፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት በመጠበቅ ዳር ድንበሯን ማስከበር ካቃታችሁ፣ ያን ጊዜ የናንተ ታሪክ ይሞታል፤ የኔ ታሪክ ደግሞ ያኔ ይጀምራል፡፡
አሁንም ዝም ብለው ቆዩና “መጻሕፍት ይዤ መሄድ ይፈቀድልኛል?” ሲሉ ጠየቁ፡፡
“አዎን” ለማለት አላመነታሁም ይላሉ፣ ደበላ ዲንሳ በምሥክርነት መጽሐፍ ላይ፡፡
“አሽከርስ ከእኔ ጋር መሄድ ይቻላል ወይ?” አሏቸው፡፡
“ግርማዊ ሆይ! ማንን ነው የሚፈልጉት?” - ደበላ ዲንሳ፡፡
“አሽከር ብዬኻለሁ! ምን አማረጠህ” ብለው ተቆጡ፡፡
በዚያን ጊዜ ከደበላ ዲንሳ ጀርባ “ወሰኔ ወሰኔ” የሚል ስም ተጠርቶም ነበር፡፡
ከደቂቃዎች ዝምታ በኋላ ደግሞ “ለመሆኑ ወዴት ነው የምንሄደው፣” ብለው ጠየቁ፡፡ ትክክለኛ የቦታውን ስም ሊገልፁላቸው ባይችሉም ከአዲስ አበባ ውጭ እንደማይሆን ደበላ ዲንሳ ገለጹ፡፡
አሁንም ረጅም ዝምታ፡፡ ይኼኔ ደበላ ወደ ልዑል ራስ እምሩ ተናገሩ፣ “ልዑል ሆይ፣ ለጃንሆይ ይንገሩልን፣ ወደተዘጋጀላቸው ቦታ…” እንዳሉዋቸው፣
“ተነሳና ሂድ መቸስ ምን ይደረግ፣” በማለት ልዑሉም ወደ ንጉሡ ተናገሩ፡፡
ይኼኔ ብድግ አሉ፡፡ ቀጥታ ወደ ደበላ ዲንሳ ተራመዱና ከፊታቸው ቆመው፣ የመሣሪያ አያያዛቸውን ተመለቱላቸው፡፡ እናም፣ “ለምንድነው መሣሪያውን እንዲህ የያዝከው” አሏቸው፡፡ “ለአያያዝ ይመቸኛል ብዬ”
”እኛን ለመያዝ?”
“የለም፣ ግርማዊ ሆይ ጠመንጃውን”

Read 7730 times Last modified on Friday, 13 September 2013 12:49