Friday, 13 September 2013 12:31

የፖለቲካ ፓርቲዎች 2005ን እንዴት አሳለፉ?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ)

“የዓመቱ ትልቁ ፈተና የጐረቤት አገሮችን ሰላም ማስፈን ነበር”

በአጠቃላይ እንደ አገር በ2005 በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በዋናነት በድህነት ቅነሳ ላይ ነው ያተኮርነው፡፡ ትልቁ የዘመናት ችግራችን ድህነት በመሆኑ እሱን ለመቀነስ የተደረጉ እንቅስቃሴዎች ከሞላ ጐደል ቢሆንም ውጤታማ ነበሩ፡፡ ሌላው የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ላይ የተጀመሩ ስራዎች ሲሆኑ በዚህ ረገድም ስኬታማ ስራዎችን ሰርተናል፡፡ ግን ብዙ ርቀት ይቀረናል፡፡ ሰላምን በመላው ኢትዮጵያ ማስፈን ሌላው ስራችን ነበር፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማስፈንም ሆነ ድህነትን ለመቀነስ ሰላም መስፈን አለበት፡፡ መንግስት በውጭም በውስጥም የሚሰራቸው ስራዎች አሉ፡፡ በተለይ በውጭ ጉዳይ ደረጃ የትራንስፎርሜሽን እቅዱን ለማሳካት ከውጭ በንግድ ዘርፍ፣ በቴክኖሎጂ ዝውውር፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝምና መሰል ጉዳዮች ፋይናንስን ለመሳብ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ነገር ግን አሁን ካሉብን ችግሮች አንፃር፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ድህነትን ለመቅረፍና አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ ከፍተኛ ጥረቶች መደረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በግሌም ከነዚህ ጋር የተሳሰሩ ስራዎች ላይ ተሳትፌአለሁ፡፡ አጠቃላይ አመቱ ጥሩ ነበር፡፡
በ2005 ዓ.ም እንደፈተና የምናነሳው ከበፊት አመታት ተዛውሮ የመጣው የጐረቤት አገሮችን ሰላም የማረጋጋት ስራ ነበር፡፡ በሶማሊያ አዲስ መንግስት የመመስረትና አዲሱን መንግስትም የማረጋጋት እንዲሁም፣ የአካባቢው ችግር የሆነውን አል-ሸባብ የማስወገድና ሁለገብ ሰላምን የማስፈን ጉዳይ ትልቁ ፈተናች ነበር፡፡
ሆኖም ይህን ፈተና በብቃት የተወጣነው ይመስለኛል፡፡ ሌላው በሁለቱ ሱዳኖች መካከል ሪፈረንደሙ (ህዝበ-ውሳኔው) በሰላም እንዲሳካ ማድረጋችን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ድህረ-ሪፈረንደሙ ከሀብት ክፍፍል፣ ከህግ ጉዳዮችና ከጐረቤት አገሮች ጋር ተያይዞ ከበድ ያሉ ነገሮች ነበሩት፡፡ ይህንንም በጥሩ ሁኔታ ተወጥተነዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ በአጠቃላይ በውጭ ግንኙነት ትልቅ ትኩረትና ጥረት የጠየቀው የጐረቤት አገሮችን ሰላም ማስፈን ነበር፡፡ ምክንያቱም የጐረቤት አገሮች ሰላም የእኛም ሰላም ነው፡፡ የእነሱ ልማት የእኛ ልማት ነው። የእነሱ መረጋጋትም እንዲሁ የእኛ መረጋጋት ነው፡፡ እሱም ቢሆን በስኬት ተጠናቅቋል፡፡ ገና መጠናከር የሚገባቸውና ሊስተካከሉ የሚችሉ ግንኙነቶች ይኖራሉ፤ እነሱም በሂደት ይሳካሉ ብለን እናምናለን። በ2006 የበለጠ ብዙ ነገሮች ይስተካከላሉ፡፡ በ2006 በአለም ዙሪያ ከጋራ ጥቅማችን ጋር በተያያዘ አለም አቀፍ ህግና ስርዓትን በጠበቀ ሁኔታ ግንኙነታችን ማጠናከር ትልቁ እቅዳችን ነው፡፡ ለእናንተም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም መልካም አዲስ አመት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

============
“የኢህአዴግ አምባገነንነት ተጠናክሯል”
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (“የአንድነት” ፓርቲ ሊቀመንበር)
በ2005 ዓ.ም ስብሠባዎችና ሠላማዊ ሠልፎችን ለማካሔድ ከመንግስት ፍቃድ የመጠበቅ አዝማሚያ ታይቷል፡፡ ይሔ ግን ትክክል አልነበረም። ስብሠባዎችንና ሠላማዊ ሠልፎችን ለማካሔድ የሚያስፈልገው ፍቃድ መጠየቅ ሳይሆን ማሳወቅ ብቻ ነው፡፡ በህገ መንግስቱ ላይም ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቅ እንጂ ማስፈቀድ ያስፈልጋል አይልም፡፡ መንግስትም እውቅና መስጠት ነው እንጂ የመከልከል መብት እንደሌለው ህጉ ይገልፃል። አሁን አሁን በፖለቲካ ድርጅቶች በኩል ይሔ ግንዛቤ ተፈጥሮ በህገመንግስቱ መሠረት በማሳወቅ (እውቅና ቢያገኙም ባያገኙም) ህዝባዊ ስብሰባና ሰልፎች ማካሄድ ጀምረዋል፡፡ በፓርቲዎች ውይይት የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ተሰጥተዋል፡፡ ሠማያዊ ፓርቲ ሠላማዊ ሠልፍ አድርጓል፡፡ ያንን ተከትሎም አንድነት፤ በርካታ ሠላማዊ ሠልፎችና ስብሠባዎች አካሒዷል። ስለዚህ ተግባራዊ የሠላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ተጀምሯል ማለት ይቻላል፡፡ የህዝቡ ችግር አፍንጫው ላይ ደርሷል። ይህንም ችግር በህዝባዊ ስብሠባዎች እና ሠላማዊ ሠልፎች ላይ እያንፀባረቀ ነው፡፡ ከ2004 ዓ.ም የተለየ ለውጥ ያየሁት ይሄ ነው፡፡ ኢህአዴግ ላይ ደግሞ አምባገነንነቱ እየጨመረ መምጣቱን አይቻለሁ። በ2005 ዓ.ም የተካሔደው ምርጫም ኢህአዴግ አምባገነንነቱን ምን ያህል እንዳጠናከረ የሚያሳይ ነው፡፡ 2006 ዓ.ም እነዚህ ችግሮች ተቀርፈው የምናይበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ ያለዚያ ህዝቡ ኢህአዴግ ላይ ተነስቶ ችግር እንዳይፈጠር ስጋት አለኝ፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ያጠበበውን እና የዘጋውን የፖለቲካ ምህዳር እንዲያሰፋና እንዲከፍት ነው የምጠይቀው፡፡ ህዝቡም የተጠናከረ ትግል የሚያደርግበት፣ መብቱን የሚያስከብርበትና ለነፃነቱ የሚታገልበት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

===========

“ኢህአዴግ ራሱን መፈተሽ አለበት”

አቶ ሙሼ ሰሙ (የኢዴፓ ሊቀመንበር)
በ2005 ዓ.ም በፖለቲካው የተሻሻለ ጉልህ ነገር አላየሁም፡፡ አመቱ መገባደጃ ላይ በውንጀላ የታጀቡ ሠላማዊ ሠልፎች ቢካሄዱም ያንን እንደ ፖለቲካ ለውጥ አላየውም፡፡ ከዚህ ቀደም በነበሩ ምርጫዎች ለፖለቲከኞች የአየር ሠአት ይሰጥ ነበር፤ ዘንድሮ ግን አልተሠጠም፡፡ ለምርጫ ቅሰቀሳ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ለመስጠትም መንግስት ፍቃደኛ አልነበረም። ከሁሉም እጅግ አሳዛኙ ነገር በተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ላይ ብዙ ችግሮች መድረሳቸው ነው፡፡ መታሠር፣ መደብደብ፣ የመሳሰሉ፡፡ ችግሮቹን ማጣራት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ነገር ግን እሮሮ ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ አይመጣም፤ ደረጃውን መለየት ቢያቅተኝም፡፡
ነፃ ፕሬሱም ያለ ጭንቀትና ያለ ውጥረት መስራት የሚችልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት እላለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር ኢህአዴግ ቆም ብሎ ራሱን መፈተሽ አለበት፡፡ ዲሞክራሲ እያደገና እየጐለበተ መምጣት ያለበት ነገር ነው፡፡
በሠነድ ላይ ብቻ መስፈሩ በቂ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በተግባር መታየት አለበት፡፡ ኢህአዴግ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያስከብሩ ህጐችን አውጥቻለሁ ሊል ይችላል፡፡ ግን እነዛን ህጐች በሌላ ህግ በመሻር እንደሽብር ህጉ መብትን ሲነፍግ ደግሞ አይተናል፡፡
ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ተወግደው አዲሱን አመት በአዲስ ለውጥ እንደምሳናልፈው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

============

“አዲሱን ዓመት በስጋትና በተስፋ እንጠብቀዋለን”
አቶ አስራት ጣሴ (የ“አንድነት” ፓርቲ ዋና ፀሃፊ)

በ2005 ዓ.ም የገዢው ፓርቲ የሠብአዊ መብት ጥሠት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡ ከፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ አንፃር ከፍተኛ ወከባና ማስፈራራት ደርሷል፡፡
የዲሞክራሲያዊ መብት ነጠቃው አይሏል። ከምንጊዜውም በላይ የኢትዮጵያን ህዝብን መብት ያለአግባብ ለመጨፍለቅ በማን አለብኝነትና በአምባገነንነት የፈለገውን ሲያከናውን ታይቷል። ሁለንተናዊ የሆነ ጭቆናና በደል በህዝቡ ላይ ተፈፅሟል። “አንድነት” ፓርቲም ሆነ 33ቱ ፓርቲዎች የህዝቡን ችግሮች ለመፍታት ከፍተኛ እንቅስቃሴዎችን እያደረግን ያሳለፍንበት ዓመት ነው፡፡ ህዝቡም ትጥቁን አጠናክሮ ለሠላማዊ ትግል የተነሳሳበት ጊዜ ነበር፡፡ የህዝቡ ጥያቄዎች በአደባባይ በግልፅ ቀርበው ከመንግስት ጋር የተፋጠጡበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ በ2006 ዓ.ም የታሰሩ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች እንዲሁም የሃይማኖት መብት ጥያቄ በማንሳታቸው ወህኒ የገቡ ግለሰቦች የህግ የበላይነት ተረጋገጦ እንዲለቀቁ እመኛለሁ፡፡ “በእኔ ጎዳና ከተጓዝክ በአውራ ጎዳናው ተጓዝ፤ አለበለዚያ ግን አትጓዝም” የሚለው የአምባገነኖች አይነት አካሄድ እንዲቆም እመኛለሁ፡፡ አዲሱን ዓመት በስጋትና በተስፋ የምንጠብቀው ቢሆንም ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይባርካት፡፡ ሰላም የሰፈነባትና የዜጎቿ ጥያቄ በአስቸኳይ የሚመለስባት አገር ትሁን፡፡

===========

“በህዝብ በኩል መነቃቃት ተፈጥሯል”
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)
በ2005 ዓ.ም የታዩት ለውጦች በሦስት መንገድ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ለውጥ በመንግስት በኩልና ለውጥ በተቃዋሚዎች በኩል፡፡ ለውጥ በህዝቡ በኩል በኢህአዴግ በኩል ወደ ኋላም ወደ ፊትም ለመሔድ ፈራ ተባ እያለ፣ ቆራጥ የፖለቲካ ውሳኔ መስጠት ባለመቻሉ እጁ ላይ ያሉ ችግሮች ከዕለት እለት እየተባባሱ ሄደዋል፡፡ ለምሳሌ የእስልምና ዕምነት ተከታዮችን በተመለከተ የተፈጠረው ችግር ይጠቀሳል፡፡ በሚዲያው ላይ የደረሰው አፈናና አስተዳደራዊ በደል ሚዲያዎችን ከጨዋታው አስወጥቷቸዋል፡፡ በማህበራዊ ጉዳይም ቢታይ የኑሮ ውድነቱ፣ ሙስናው፣ የትራንስፖርት ችግሩ፣ የመብራት፣ የውሃና ሌሎች ችግሮች ፍፁም ባልተጠበቀ ሁኔታ ተባብሰው ህዝቡ በኢህአዴግ ላይ ያለውን እምነት እንዲያጣ አድርጎታል፡፡ በኢህአዴግ በኩል ምንም መሻሻል አልታየም፡፡ በህዝቡ በኩል ግን መነቃቃት ተፈጥሯል፡፡ ጋዜጦችን የማንበብ ፍላጐት፣ በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ መሳተፍ፣ በድፍረት የመነጋገር፣ ፓርቲዎች በሚያቀርቧቸው መድረኮች ላይ የመገኘት ሁኔታዎች ታይተዋል። ትንሽም ቢሆን ተስፋ የማድረግና የመለወጥ አዝማሚያ አለ፡፡ ለውጥ የሚያመጣ አመራር ቢያገኝ ህዝቡ ለመለወጥ ዝግጁ ነው፡፡
ተቃዋሚዎችም ኢህአዴግ በሚያደርስብን በደል ከማለቃቀስ ተላቀን ችግሮችን በአደባባይ ከህዝብ ጋር መወያየት ጀምረናል፡፡ ይሄ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ፖለቲካ የሀገር ጉዳይ ነው፤ ኢህአዴግ የዚህን አገር ችግር በራሱ “ተዓምር” ሊፈታው አይችልም፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚዎች፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለመብታቸው እንዲቆሙ እና መብታቸውን ለማስከበር እንዲጥሩ የጀመሩትን እንቅስቃሴ አጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል፡፡ 2006 የመልካም ስራ፣ የፍቅርና የጓደኝነት ዘመን ይሁንልን፡፡


===========

“አፈናና ጭቆና የበዛበት ዓመት ነው”
አቶ አበባው መሳይ (የመኢአድ ሊቀመንበር)

በተጠናቀቀው ዓመት የተለወጠ ነገር አለ፡፡ ወደ መልካም ሳይሆን ወደ ባሰ ሁኔታ ነው የገባነው፡፡ እስር እና የተለያዩ ጭቆናዎች የበዛበት አመት ነበር። በእርግጥ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድነት ለመስራት ተንቀሳቅሰዋል፡፡
የኢህአዴግ መንግስት በህዝባችንም ሆነ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ከፍተኛ አፈናና ጭቆና ያደረሠበት ዓመት ሆኖ አልፏል፡፡
ወደድንም ጠላንም ሁላችንም ኢትዮጵያኖች ነን፡፡ አገራችንን ወደ ሠላማዊ መንገድ ለማምጣት የገዢነት ሳይሆን የአመራር ስሜት ያስፈልጋል፡፡ ኢህአዴግ በ2006 ዓ.ም ህዝቡን አሳታፊ የሚያደርግ ሁኔታ በመፍጠር አገራችንን ወደ ጥፋት ከመምራት ይልቅ ወደ ሠላም ለማምጣት እንደሚሰራ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ይሔንን ባያደርግ ግን ሁኔታዎች ወደ ከፋ ሁኔታ እንደሚሔዱ እገምታለሁ፡፡

Read 2034 times