Saturday, 31 August 2013 12:08

በምርጫ ያጣነውን የፓርቲዎች ክርክር በ”ፀረ ሽብር ህጉ” አገኘነው!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(17 votes)
  • የአንድነት “ጥይት ተናጋሪ” በኢህአዴግ “የተገፋ” ነው ተባለ
  • ዶ/ር` መረራ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የበላውን ቡዳ ይጠይቃሉ?

እናንተዬ፤ የሰሞኑን የፖለቲካ ድባብ እንዴት አገኛችሁት? (የአውራው ፓርቲና የተቃዋሚዎችን ማለቴ ነው!) ድንገት ሳናስበው ተሟሟቀ አይደል? (ዕድሜ ለፀረ - ሽብር ህጉ!) በእርግጥ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎችም ምስጋና ይገባቸዋል (ልብ ስለገዙ!) እንዴ…ዋናውን ተመስጋኝ ዘነጋሁት እኮ! (ብራቮ ኢቴቪ!) እውነቴን ነው የምላችሁ…ባለፈው ሳምንት በኢቴቪ “የፀረ ሽብር ህጉና የፓርቲዎች አቋም” በሚል ርዕስ የተላለፈው ውይይት ተወዳጅ እንደነበር መረጃዎች ደርሰውኛል (ኤልፓ ግን አሻጥር ሰርቷል!)
በነገራችሁ ላይ ከ97 ምርጫ ወዲህ የታየ ትልቅ የዲሞክራሲ ጭላንጭል እኮ ነው (የሰይጣን ጆሮ አይስማብን!) ግን ደስ አይልም …ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በትልቅ የአገር ጉዳይ (አዋጅ) ላይ ህዝብ ፊት ሲሟገቱ! (Live ባይሆንም አናማርርም)
አንድ ምስጢር ልንገራችሁ፡፡ ለኢህአዴግ እንዳትነግሩብኝ ታዲያ! (promise?) በጣም ጥሩ! ለአንድ ዓመት በጠ/ሚኒስትርነት የመሩን የተከበሩ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ገና ሥልጣን ሲይዙ አስረግጠው እንደተናገሩት “የመለስን ሌጋሲ” በእርግጥም እያስቀጠሉ ነው፡፡ ራዕያቸውንም እያሳኩ ነው፡፡ ይሄውላችሁ… ዝም ብሎ የካድሬ ዲስኩር እንይመስልብን መረጃና ማስረጃ እየጠቀስን ብናወጋስ… (እንደሰሞኑ የፓርቲዎች ውይይት!) በአንደኛ ደረጃ የሚጠቀሰው ምን መሰላችሁ? ጠ/ሚኒስትሩ በሙስና ላይ የወሰዱት ቁርጠኛ እርምጃ ነው፡፡ በአንድ ዓመት ብቻ ስንት ተጠርጣሪ ሙሰኛ እንደተያዘ እስቲ ቁጠሩት… (እኔማ መቶ ከደረስኩ በኋላ መቁጠሩን ትቼዋለሁ!) ጠ/ሚኒስትሩ የገቡትን ቃል የፈፀሙት በሙስናና በሙሰኞች ላይ ብቻ አይደለም፡፡ በፓርላማና በኢቴቪ ያየናቸው በጐ ለውጦችም የመለስን ሌጋሲ ለማስቀጠል በአቶ ኃ/ማርያም አስተዳደር የተከናወኑ ተግባራት አካል ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተቃዋሚዎች የጨዋታ ሜዳ (እነሱ ምህዳር ይሉታል!) እየሰፋ መምጣቱን ማንም ሊክደው አይችልም፡፡ (ከ97 ምርጫ ወዲህ ሜዳው ጠብቦ ነበር አልተባለም?) አንድነት ፓርቲ ብቻውን በአንድ ወር ያካሄደውን ሰልፍ ብቻ መቁጠር በቂ ነው፡፡ አንዳንድ የ”ከፋፍለህ ግዛ” ስትራቴጂ አቀንቃኞች ምን እንደሚሉ ታውቃላችሁ? እነዚህ ሁሉ በጐ ለውጦች ከኢህአዴግ ሳይሆን ከአዲሱ ጠ/ሚኒስትር የፈለቁ ናቸው ይላሉ (ከፋፋዮች በሏቸው!) እነዚህ ወገኖች ያልገባቸው አንድ ነገር አለ፡፡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ሥልጣን እንደያዙ ከውጭ ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፣ ምን ራዕይ እንዳላቸው ተጠይቀው፤ የሳቸው ራዕይ የፓርቲያቸውን ራዕይ ማስፈፀም እንደሆነ በማያሻማ ቋንቋ ተናግረዋል፡፡ ስለዚህ ማናቸውም ለውጦች ከግለሰብ ሳይሆን ከፓርቲው እንደሚመነጩ ማወቅ ብልህነት ነው፡፡ (እኛ ከለውጡ እንጂ ከባለቤቱ ምን አለን?)
እስቲ አሁን ደሞ አንዲት ቁምነገር አዘል ቀልድ ጣል ላድርግላችሁ፡፡ (ዘና እንድትሉ እኮ ነው!)
ዶክተር ጌታቸው ቦሎዲያ የዩኒቨርስቲ የባዮ-ኬምስትሪ አስተማሪ ነበር፡፡ ተጨዋች፣ እንደልቡ የሚናገር፣ በህይወት ሳለ ለመንግሥት ባለስልጣናት ግድ የሌለው፣ በራሱና በእውቀቱ የሚተማመን ሳይንቲስት ነበር፡፡ (እንዲህ ያለ ምሁር እንደ ዳይኖሰር ጠፍቷል ልበል?) አንድ ጊዜ ከስድስት ኪሎ ወደ አራት ኪሎ ሲመጣ አንድ የስድስት ኪሎ ተማሪ ጭኖ (lift ሰጥቶ) ይመጣል፡፡ አራት ኪሎ ወደ ሳይንስ ኮሌጅ እየተቃረቡ ሲመጡ ተማሪውን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡፡ ዶ/ር ጌታቸው ወንድንም ቢሆን አንቺ ማለት ይቀናዋል፡፡
“የት ነው የምትማሪው?”
ተማሪው - ስድስት ኪሎ
ቦሎዲያ - ስንተኛ ዓመት ነሽ?
ተማሪው - አራተኛ ዓመት፤ ዘንድሮ እጨርሳለሁ
ሳይንስ ኮሌጅ አጠገብ አቁሞ እያወረደው፡
ቦሎዲያ - ቆይ ቆይ፤ ምንድነው የምታጠኚው ለመሆኑ?
ተማሪው - ፖለቲካል ሳይንስ
ቦሎዲያ - በይ በይ፤ ሳይንሱን ለእኔ ተይና ፖለቲካሽን ይዘሽ ውረጂ! (ምንጭ - አዲስ አድማስ)
ምሁሩ እኮ እውነታቸውን ነው፡፡ ፖለቲካ ብሎ ሳይንስ እኮ የለም - በተለይ በጦቢያ ምድር! ፖለቲካ እኮ እኛ አገር ሃሜትና አሉባልታ ነው፡፡ ፖለቲካ እኮ እኛ አገር ጠብና መጠላለፍ ነው፡፡ ፖለቲካ እኮ እኛ አገር የቀውስና የጥርጣሬ ምንጭ ነው፡፡ ፖለቲካ እኮ እኛ አገር መካካድና መዘላለፍ ነው፡፡
በነገራችሁ ላይ የመድረክ አመራር አባል የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅ ጉዞና የህይወቴ ትዝታዎች” በሚል ርእስ በቅርቡ ለንባብ ያበቁት ጉደኛ መጽሐፍ አላቸው፡፡ እናላችሁ… መፅሃፉን ብታነቡት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መመደብ እንዳለበት ትገነዘባላችሁ፡፡ (ዶ/ር መረራ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራርነታቸው በተጨማሪም የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ናቸው፡፡) በመፅሃፋቸው ጀርባ ላይ ስለ ዶ/ር መረራ የፖለቲካ ህይወት የቀረበው አጭር መረጃ እንዲህ ይላል ፡- “በፖለቲካው ዓለም፤ ከ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ እስከ ዛሬ በዘለቀው የኢትዮጵያ ሕዝቦች የመብት ትግል ውስጥ በመሳተፍ ሦስት መንግሥታትን ታግሏል፡፡ በደርግ ዘመን ለሰባት ዓመታት የፖለቲካ እስረኛ ሲሆን፣ ከ1997 እስከ 2002 የሀገሪቱ ፓርላማ አባል ነበር፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስና የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ የሚባሉ ድርጅቶችንና የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረትና መድረክ የሚባሉ ጥምረቶች በሊቀመንበርነት መርቷል”
አያችሁልኝ… ፖለቲካ በእኛ አገር ሙያ (career) ሳይሆን ትግል ነው - ሲከፋ ለሞትና ለዝንተዓለም እስር ይዳርጋል፡፡ ካልከፋ ደግሞ ከአገር ያሰድዳል (ስደት እኮ ሰፊ ወህኒ ቤት ነው!) ዛሬ እንደው ላጓጓችሁ ብዬ እንጂ የዶ/ር መረራን መፅሃፍ የመቃኘት ዓላማ የለኝም፡፡ እንጂማ ስንት አጀብ የሚያሰኙ ታሪኮችና ገጠመኞችን እንደያዘ አልነገራችሁም፡፡ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡ በባዶ ከምንለያይ ግን እስቲ አንዲት ነገር ከመጽሐፉ ላጋራችሁ፡፡ የኢትዮጵያዋና ችግሮች ሦስት ናቸው ይላሉ - ምሁሩ፡፡ አንደኛው - የትግራይ ልሂቃን “ስልጣን ወይም ሞት” ብለው ሥልጣንን የሙጥኝ ማለታቸው (የአባታቸው ርስት አደረጉት ለማለት ይመስላል)፣ ሁለተኛው - የአማራው ልሂቃን የኢትዮጵያዊነት ሰርተፊኬት (ሊቼንሳ) ሰጪ ነን ባይነት (የዜግነት ብቃትና ደረጃ አውጪ ማን አደረጋቸው ማለታቸው ነው) ሦስተኛው - የኦሮሞ ልሂቃን ብዙ ህዝብ ይዞ ልገንጠል ማለት (ግንድ እንዴት ይገነጠላል እያሉ ነው!)… እነዚህ ሦስት ጉዳዮች ካልተለወጡ አደጋው ይቀጥላል ባይ ናቸው - ዶ/ር መረራ፡፡ (የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ስለሆኑ እመኗቸው!)
የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንትና የአሁኑ የአንድነት ፓርቲ ሊ/መንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ስለመፅሃፉ በሰጡት አስተያየት፤ “ዶ/ር መረራ ጉዲና የኦሮሞ ህዝብ የመብት ትግል ከተቀሩት የኢትዮጵያ ህዝቦች የመብት ትግል ጋር በማቀናጀት ሰፊ ሚና በመጫወት ላይ የሚገኝ ታጋይ ምሁር ነው፡፡ በህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር የሚመኝ ሁሉ ሊያነበው የሚገባ መፅሃፍ ነው” ብለዋል፡፡ ከዶ/ር ነጋሶ ሃሳብ ጋር እስማማለሁ፡፡ ግን የምጨምረውም አለኝ፡፡ ከ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ እስከዛሬ የዘለቀውን የጦቢያ የመጠላለፍ ፖለቲካ ፍንትው አድርጐ የሚያሳይም መጽሐፍ መሆኑን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ፡፡
በዚያ ላይ ዶ/ር መረራ አዋዝተው ስለፃፉት በእርግጥም መነበብ ያለበት የፖለቲካ መፅሃፍ ነው ባይ ነኝ፡፡ (ኮሚሽን የተከፈለኝ እንዳይመስላችሁ!) አንድ የገረመኝ የዶ/ር መረራ አባባል አለ - መጽሐፋቸው መጨረሻ ላይ፡፡ “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቡዳ ማነው” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ (ፖለቲካ ሳይንስ አይደለም አላልኳችሁም!)
እኔ የምላችሁ… ባለፈው ረቡዕ ማታ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በኢቴቪ የሰጠውን መግለጫ ሰምታችኋል? “አገልግሎቴን አሻሽያለሁ” እኮ ነው ያለን! ባለፈው ሳምንት በመብራት መቋረጥ የተነሳ በኢቴቪ የተላለፈውን የፀረ ሽብር ውይይት አልተከታተልንም ለሚሉ ዜጐች ምላሹ ምን ይሆን? እኔማ ለእነዚህ ተበዳዮች የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ጀምሬአለሁ - ኤልፓን ለመክሰስ፡፡ (እኔ እንደ “አንድነት” ሚሊዮን ድምጽ አልፈልግም፤ 100 ይበቃኛል!) አንዲት ወዳጄ ስለ “ኤልፓ” ተነስቶ (ስለእሱ ሳይነሱ ውሎ ማደር እኮ አልተቻለም!) ያወጋችኝን ላካፍላችሁ፡፡
“ልጄ አፏን የፈታችው በምን እንደሆነ ታውቃለህ?”
“በምንድነው?”
ያው “አባ፣ እሚ” በሚለው መስሎኝ ነበር፡
“በራ… ጠፋ… በሚሉት ቃላት ነው”
(አይገርምም!)
ገባችሁ አይደል… መብራቱ አስሬ እየጠፋ ሲመጣ “በራ ጠፋ” እያለች አፏን ፈታች ማለቷ እኮ ነው፡፡ ይሄ መቼም አሳዛኝ ክስተት ነው አይደል? ምናልባት ኤልፓ በዚህ መልኩ መገለፁ “ያኮራኛል!” ሊለን ይችላል፡፡ (ይኩራ፤ መብቱ ነው!) ለእኛ ግን “አገልግሎቴን አሻሽያለሁ” የሚለውን “የአንደበት ግልጋሎቱን” (ከሰሞኑ የኢህአዴግ ሹመኛ ንግግር ቃል በቃል የቀዳሁት ነው!) ይተወንና መብራቱን እንደድሮው በፈረቃ ያድርግልን! ሰሞኑን ካመለጠን የፓርቲዎች ውይይት በተጨማሪ በመብራት ድንገተኛ መቋረጥ በየቤታችን የተቃጠለውን ቲቪ፣ ሬዲዮና ሌሎች ቁሳቁሶች “ሆድ ይፍጀው” ብለናል፡፡ (የፒቲሺን ዘመቻው እስኪጠናቀቅ!)
ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ ላይ የወጣውን “የኢንጂነር ሃይሉ ሻውልና የኖርዌይ ኤምባሲ ውዝግብ” የተመለከተ ዜና አንብባችኋል? ለብዙ አመታት መኢአድን በሊ/መንበርነት የመሩት ኢንጂነሩ፤ የፓርቲያቸውን የእርስ በርስ ፉክቻ ተገላገልኩ ሲሉ የኤምባሲ ንትርክ ደግሞ ገጠማቸው፡፡ (የአገራቸውን ጉዳይ ሲገላገሉ የቤታቸው ጠበቃቸው!) እኔ ግን ስጠረጥር ኤምባሲው ኢንጂነሩን በደንብ ያወቃቸው አልመሰለኝም፡፡ እንዴ…ያፈነገጡ የመኢአድ አመራሮችን ተጋትረው ሲበቃቸው ሲሉ እኮ ነው ከፖለቲካ ጡረታ የወጡት፡፡ (ውዝግብ ብርቃቸው አይደለም ለማለት ነው!) “በፀባይ ቤቴን ካለቀቁ ከጐን አጥሩን አፍርሼ እገባለሁ” ያሉት ነገር ግን አልተመቸኝም፡፡ ኤምባሲ ማለት አገር ማለት ነው ይባል የለ፡፡ በኋላ የኖርዌይን ግዛት ደፈራችሁ ብንባልስ? (ኢንጂነሩ ለጦቢያ ክብር ሲሉ ቢታገሱ ጥሩ ነው!) በነገራችሁ ላይ የመኢአዱ የቀድሞ ሊ/መንበር ከኖርዌይ ኤምባሲ ጋር ሲወዛገቡ፣ የአንድነት ሊ/መንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ደግሞ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር ተወዛግበዋል ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ (ተቃዋሚዎችንና ኤምባሲዎች የበላቸው ቡዳ አልታወቀም!) ኤምባሲው ለፓርቲው ሊ/መንበርና ለህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ቪዛ ተጠይቆ ለዶ/ር ነጋሶ እንጂ ለህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አልሰጥም ማለቱ ነው ውዝግቡን ያስነሳው፡፡ (አሜሪካ ኤምባሲ መኪናና ቪላ ለሌለው ቪዛ አይሰጥም እኮ!)
እኔ የምላችሁ…በነገው ዕለት ሁለት ሰላማዊ ሰልፍ ያዘጋጁ ቡድኖች “እኔ ነኝ የቀደምኩት” በሚል ተፋጠዋል የሚባለው ከምር ነው እንዴ? እኔ እኮ ሰሞነኛ ቀልድ መስሎኝ ነበር፡፡
በጣም እኮ ነው የሚገርመው… (ለቀልድም እኮ አይመችም!) በአገር አመራር ደረጃ የምናስባቸው ወገኖች “እኔ ነኝ የቀደምኩት” የሚል ንትርክ እንዴት ይገጥማሉ? (የልጆች ፉክክር አስመሰሉት እኮ!) በሰላማዊ ሰልፎች የሚቀርቡ ጥያቄዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ፈጣን ምላሽ ቢሰጣቸው እንኳ “እሺ ይሁን” ብለን እናልፈው ነበር፡፡
ግን ደግሞ እውነታው እንዲያ እንዳልሆነ አሳምረን እናውቃለን፡፡ በዚያ ላይ የጊዜ እጥረት እንደሌለብን እንኳን እኛ ነጮቹም ያውቁታል፡፡ (እዚህ አገር ርካሹ ነገር ምን ሆነና?) ታዲያ ለምኑ ነው እልህ መገባባቱ (ጐበዝ አገር በእልህ አትመራም!) እናላችሁ ሰልፉ ዛሬም …ነገም…ሳምንትም…የዛሬ ወርም ቢደረግ ችግሩ ምንድነው? (ወይስ አዋቂ ነግሮአቸው ነው!) በተለይ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች…የሚያምርባችሁ እንደሰሞኑ የሃሳብ ፍልሚያ ስታደርጉ እንጂ እልህ ስትጋቡ አይደለም፡፡ (ከነገ በኋላ ሰላማዊ ሰልፍ ይታገዳል ተባለ እንዴ?)
እኔ የምለው… በፀረ ሽብር ህጉ ላይ ፓርቲዎች ባደረጉት ክርክር ማን የረታ ይመስላችኋል? አንዳንዶች “ተቃዋሚዎች አስገቡለት” ሲሉ ሰምቻለሁ - ለኢህአዴግ መሆኑ ነው፡፡ ለእኔ ግን ሁለቱም አሸናፊዎች ናቸው፡፡ ቁጭ ብለው መነጋገራቸው በራሱ ባለድል ያደርጋቸዋል፡፡ እኔ የምለው ግን አንድነት ጥይት የሆነ ወጣት ተናጋሪ ከየት አመጣ? ቀድሞ ኢህአዴግ የነበረና “ተገፍቶ” (ፖለቲካዊ በደል ደርሶበት ማለቴ ነው) የተቃዋሚውን ጐራ የተቀላቀለ ወጣት ነው የሚል አሉባልታ ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ከሆነ ኢህአዴግ እንዴት እንደሚቃጠል አስቡት! (በራስ ጥይት መመታት እኮ ነው!) ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ… በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እየተገፉ ተሰደው ለሌላ አገር የሚሮጡ አትሌቶቻችን! በየውድድሩ እያሸነፉ የሌላ አገር ባንዲራ ሲያውለበልቡ አልተቆጨንም? (በእጅ ያለ ወርቅ እየሆነብን እኮ ነው!)
በመጨረሻ አንድ ሃሳብ ላቅርብና ልሰናበት (የሚሰማኝ ካለ) በሰሞኑ የፓርቲዎች ውይይት ኢህአዴግ “ፖለቲካዊ ውሳኔ” በሚል ባነሳው ጉዳይ ላይ ሌላ የውይይት ፕሮግራም ቢዘጋጅስ?
(ነገሮች እንዲጠሩ እኮ ነው!) አያችሁ ይሄ የውይይት ባህል ከዳበረ መፍትሔዎች ከውይይት መወለድ ይጀምራሉ፡፡ ኢቴቪም በዚያው አንድ ተወዳጅ ፕሮግራም ፈጠረ ማለት እኮ ነው፡፡ (ይሄም “ፖለቲካዊ ውሳኔ” ይፈልጋል እንዳትሉኝ?)

Read 4137 times