Saturday, 31 August 2013 12:02

ለአክራሪነት የምንንበረከክበት ተጨማሪ ምክንያት

Written by  ዩሀንስ ሰ.
Rate this item
(7 votes)

አመቱን ሙሉ፣ ኢህአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስለ አክራሪነት አደጋ እና ስለ ሃይማኖት ነፃነት መላልሰው መላስሰው እየነገሩን ይሄውና ክረምቱ ሊገባደድ ደርሷል። አሳዛኙ ነገር፣ በደፈናው እያድበሰበሱና እያምታቱ ከመናገር ውጭ የአክራሪነትን ምንነት ከነምንጩ፣ እንዲሁም የሃይማኖት ነፃነትን ትርጉም ከነምክንያቱ በግልፅ አፍረጥርጦ የሚናገር አልተገኘም።
የሃይማኖት ነፃነት ማለት፣ እንደየምርጫችን የሃይማኖት እምነቶችን መቀበልና መደገፍ ማለት ብቻ አይደለም። የሃይማኖት እምነቶች አለመቀበልንና መተቸትንም ይጨምራል። እንደየእምነታችን የሃይማኖት ትዕዛዛትን እየተከተልን መፈፀም ማለት ብቻ አይደለም። ትዕዛዛትን እየተቃወሙ አለመፈፀምንም ሁሉ ያካትታል። በአጭሩ የሃይማኖት ነፃነት፣ የሃሳብ ነፃነት ውስጥ የሚጠቃለል አንድ ክፍል ነው።
ታዲያ፣ የሃይማኖት ነፃነት ማለት እምነትን መያዝ ብቻ ሳይሆን ከሃይማኖት ነፃ መሆንንም እንደሚጨምር በግልፅ የተናገረ የፓርቲ መሪ ወይም ተወካይ አጋጥሟችኋል? የሃይማኖት ነፃነት መከበር አለበት የሚባለው፣ ለሃይማኖት ተቋማት፣ ልዩና ከፍተኛ ቦታ በመስጠት አይደለም። ቀድሞ ይሰጣቸው የነበረውን ልዩ ስፍራ በማሳጣት እንደማንኛውም ማህበር፣ የግለሰቦችን ነፃነት ሳይጥሱ የሕግ ተገዢ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው የሃይማኖት ነፃነት የሚያስፈልገው። ይህንን እውነት ፊት ለፊት የሚያስረዳ ፖለቲከኛ ወይም ፓርቲስ አይታችኋል? የለም።
አክራሪነት በተፈጥሮው፣ ሃይማኖትን ከማጥበቅ እንደሚነሳ እቅጩን የተናገረ ፖለቲከኛ ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? እንዲሁ በደፈናው ለዘብተኛነትን ነው የሚሰብኩት። ለዘብተኛ መሆን ማለት ግን ሌላ ትርጉም የለውም። አንዳንድ የሃይማኖት እምነቶችንና ትዕዛዛትን በዝምታ አይተው እንዳላዩ ማለፍ ማለት ነው። የአክራሪነትና የለዘብተኛነትን ልዩነት በግልፅ ለማሳየት አንድ ምሳሌ ልጥቀስላችሁ።
እርስዎ እና ወንድምዎ ወይም ጓደኛዎ የአንድ ሃይማኖት ተከታይ ናችሁ። ወንድምዎ ወይም ጓደኛዎ፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሃይማኖቱን ቀይሮ እርስዎንም ለመስበክና ለማሳመን ቢሞክር ምን ያደርጋሉ? እስቲ፣ ቁም ነገር ይዞ ከመጣ ልስማው ብለው ያስተናግዱታል? ይከራከሩታል? ወይስ ዞር በልልኝ ይሉታል? ለእንደዚህ አይነት አጋጣሚ የሚሆን ነገር በሃይማኖት መፅሃፍዎ ውስጥ የሰፈረ ትዕዛዝ ቢኖርስ? እስቲ ይህንን እንመልከት፡
“የእናትህ ልጅ ወንድምህ ወይም ወንድ ልጅህ፣ ሴት ልጅህ ወይም ሚስትህ፣ ወይም እንደ ነፍስህ ያለ ወዳጅህ፣ [በዙሪያህ ከቅርብ የሚገኙ ሕዝቦች ወይም ከምድር ዳር ከሩቅ የሚኖሩ ሕዝቦች የሚከተሉትን ሃይማኖት አምጥቶ፣ አማልክቶቻቸውን እናምልክ] ብሎ ቢያስትህ፣ እሺ አትበለው። አትስማው፤ ዓይንህም አይራራለት። አትማረው፣ አትሸሽገው። ይልቁንስ ግደለው። እርሱን ለመግደል የአንተ እጅ ይቅደም፣ ከዚያም በኋላ የሕዝቡ ሁሉ እጅ ይውረድበት። ከአምላክህ ሊያርቅህ ወድዶአልና እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገረው። ሕዝቡም ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ፣ እንዲህም ያለ ክፉ ሥራ እንደ ገና በአንተ መካከል አያደርጉም።
… ሌሎችን አማልክት እናምልክ ብለው የከተማቸውን ሰዎች አሳቱ ሲሉ ወሬ ብትሰማ፣ … ይህም ክፉ ነገር እንደ ተደረገ እርግጥ ሆኖ ቢገኝ፣ የዚያችን ከተማ ሰዎች በሰይፍ ስለት ፈጽሞ ትመታቸዋለህ። ከተማይቱን፣ በእርስዋም ያለውን ሁሉ፣ እንስሳውንም በሰይፍ ስለት ታጠፋቸዋለህ። …ከተማይቱንም ዕቃዋንም ሁሉ ለአምላክህ በእሳት ታቃጥላለህ፤ ለዘላለምም ወና ትሆናለች።”
የሃይማኖታዊ እምነት ሰባኪዎች፣ እነዚህን ትዕዛዛት በበርካታ አስገራሚ መንገዶች ሊተነትኗቸውና ሊተረጉሟቸው እንደሚችሉ አያጠራጥርም። በቀጥታ አንብበን የምንገነዘበው ጭብጥ ግን ብዙም የሚሻማ አይደለም። ካንተ አካባቢና ከተማ ውጭ፣ በሩቅና በቅርብ የሚኖሩ ሰዎች በሌላ ሃይማኖት ሌላ አምላክ ያመልኩ ይሆናል።
በቤተሰብህ፣ በአካባቢህና በከተማህ ውስጥ፣ ያንተው አይነት ሃይማኖት ሲከተሉ የነበሩ ሰዎች ሃይማኖታቸውን ሲቀይሩ ወይም ሲሰብኩ ግን፣ ምህረት የማይደረግለት ጥፋት ነው። (ዋናው ትኩረት፣ የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ አይደለም)
ሃይማኖታቸውን ቀይረው የሚሰብኩ ሰዎችን ትገድላለህ። ስብከቱን ሰምተው ሃይማኖታቸውን የቀየሩትንም ሰዎች፣ በከተማዋ ያሉትን እንስሳት ጭምር ትጨፈጭፋለህ። (ዋናው ትኩረት፣ ያንተ አይነት ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች ላይ ነው)
እንግዲህ ከላይ የተጠቀሱትን ትዕዛዛት ከምር ተቀብሎ ቀጥተኛ ትርጉማቸውን የሚከተልና የሚሰብክ፣ ከምር ተግባራዊ መደረግ አለባቸው ብሎ የሚያምንና የሚንቀሳቀስ ሰው ነው አክራሪ ማለት።
ሌሎቻችንስ ምን እናደርጋለን? ከአክራሪዎች የተለየ አማራጭ እናፈላልጋለና። ደግሞም፣ በርካታ የተለያዩ መንገዶች አሉ። “እነዚያ ትዕዛዛት፣ በቀጥታ ከሚያስተላልፉት ግልፅ መልዕክት የተለየ ሚስጥራዊ ትርጉምና ድብቅ መልዕክት ይኖራቸው ይሆናል” ብለን ማለፍ እንችላለን። አንድ ዘዴ ነው። ቀጥተኛውን ትርጉም ውድቅ የሚያደርጉ ተቃራኒ ሃይማኖታዊ ትዕዛዛትንና ጥቅሶችን መዘርዘርም ሌላ ዘዴ ነው። አንዱን ጥቅስ በሌላ ጥቅስ እናለዝበዋለን።
ይሄ ሁሉ አላስኬድ ቢለን እንኳ፣ የትዕዛዛቱን ቀጥተኛ ትርጉም አይተን እንዳላየን ችላ የምንል እንኖራለን። ለዘብተኛነት ይሄው ነው። ሃይማኖታዊውን እምነትና ትዕዛዛቱን በጥቅሉ እንቀበላለን ብንልም፣ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም አንዳንዶቹን እምነቶችና ትዕዛዛት ቸል በማለት በሰላም ኑሯችንን ለመቀጠል እንሞክራለን። ችግር የሚመጣው፣ አክራሪዎች ሲያፋጥጡን ነው - ለዚያውም በሦስት ተከታታይ ማፋጠጫ ፈተናዎች።

አንደኛ፡ አማኝ ነህ
“አማኝ ሃይማኖተኛ ነኝ እስካልክ ድረስ፣ ሁሉንም እምነቶች መቀበልና ሁሉንም ትዕዛዛት ተግባራዊ ማድረግ የሃይማኖት ግዴታችሁ ነው” ለሚሉን አክራሪዎች፣ ምላሻችን ምን ይሆናል? ሰው መግደልና ከተማውን ሙሉ ህፃን ከአዋቂ ሳልል ማቃጠል አእምሮዬ አይቀበለውም ማለት እንችላለን። ነገር ግን፣ በዚህ መከራከሪያ መቀጠል የምንችለው፣ ከእምነት በፊት ለአእምሮ ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ ብቻ ነው።

ሁለተኛ፡ አገልጋይ ነህ
“ደግሞስ፣ ስለሌሎች ሰዎች ሃይማኖት ምን አገባኝ? እምነታቸውን ቢለውጡ ወይም ባይለውጡ የራሳቸው ምርጫ ነው” የሚል ሌላ መከራከሪያ ብናመጣ ያዋጣናል። የኔ አላማ በራሴ ጥረት ኑሮዬን ማሻሻልና ከቀና ሰዎች ጋር መገበያየት እንጂ፣ የሌሎች ሰዎችን ሕይወትና ኑሮ ለመምራት መሞከር አይደለም ብለን እንሞግታቸው። ግን እነሱም፣ የራሳችንን እምነት በመጠቀም ማጥመጃ ያዘጋጃሉ። “የሃይማኖት ትዕዛዛትን የምትፈፅም የፈጣሪ አገልጋይ እንደሆንክ ታምናለህ? ወይስ ለራስህ አለማዊ የግል አላማ ቅድሚያ ትሰጣለህ?” ብለው ያፋጥጡናል።
በእርግጥ፣ ሰባኪዎች “ፈጣሪን ለማገልገል ትዕዛዛቱን ፈፅም” ብለው ሲነግሩን፣ “የፈጣሪ ትዕዛዛት ወዳንተ የሚደርሱት በኔ በኩል ነው፤ አንተ በታዛዥነት ፈፅም” ማለታቸው እንደሆነ ይገባን ይሆናል። የፈጣሪ ቃል አቀባይ ሆነው መቅረባቸውም ላይዋጥልን ይችላል። ነገር ግን፣ ይሄ ማምለጫ አይሆነንም። “ለራሱ የግል አላማ ቅድሚያ የማይሰጥ አማኝ፣ ፈጣሪን ለማገልገል ትዕዛዛቱን ይፈፅማል” በማለት ሲያፋጥጡን፣ የሚያጠግብ ምላሽ ከሌለን እግራቸው ስር መንበርከካችን አይቀርም። “የፈጣሪን ትዕዛዛት መፈፀም ግዴታ ነው” ብለው ይጨምሩበታል።

ሦስተኛ፡ ግዴታ አለብህ
“ከራስ ጥቅም በፊት፣ ለአገር ልማትና ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት ግዴታ ነው” እንደሚባለው አይነት ነው። ብዙ ሰው፣ “የአገር አገልጋይ፣ የሕዝብ ባሪያ ነህ” ተብሎ ሲነገረው፣ ለመቃወም አይሞክርም፤ ይስማማል እንጂ።
በርካታ የዩኒቨርስቲ ተመራቂዎች፣ የወደፊት አላማቸው ምን እንደሆነ ሲጠየቁ፣ “አገሪቱን ለማልማት፣ ሕዝቡ የሚጠብቅብኝን ሁሉ ለመስራትና ለመወጣት ዝግጁ ነኝ” ብለው ሲናገሩ ሰምታችሁ ይሆናል። ለምን? የግል አላማ መያዝ እንደ ወንጀል አልያም እንደ ነውር ይቆጠራላ። እንዲህ አይነቱ “ሕዝባዊ ስሜትን” የሚያመልክ አስተሳሰብ ነው፣ ከ50 አመታት በላይ በአገራችን ሰፍኖ የቆየው።
በእርግጥ፣ “ማንም ሰው ማንንም የማገልገል ግዴታ የለበትም” የሚል በሳይንሳዊ እውቀት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ በማምጣት፣ የሃይማኖት አክራሪዎችንና ሕዝባዊ ካድሬዎችን መከላከል ይቻላል። ከ230 አመታት በፊት ለአሜሪካ ምስረታ የተዘጋጀው የነፃነት መግለጫ ጥሩ ምሳሌ ነው።
የመንግስት ሃላፊነትና ስራ የእያንዳንዱን ሰው መብት ማስከበር እንደሆነ መግለጫው በአፅንኦት ያስገነዝብና፣ ከእነዚህ መብቶች መካከልም፣ የሕይወት መብት፣ የነፃነት መብትና ደስታን የመሻት መብት ይጠቀሳሉ ይላል። የቃላት አመራረጣቸው ድንቅ ነው። ሶስቱንም መብቶች በየተራ እንያቸው።
ከሁሉም በፊት፣ የአንድ ሰው ሕይወት የማንም ንብረት አይደለም - የራሱ የሰውዬው እንጂ። የራሱን ኑሮ የሚመራው ደግሞ በራሱ ነፃ አእምሮና ምርጫ እንጂ በሌላ ሰው ትዕዛዝ አይደለም። ይሄ ነው የነፃነት መብት። የእያንዳንዱ ሰው በጥረቱ የራሱን ሕይወት የማሻሻልና ደስታን የመቀዳጀት አላማውን እንዳያሳካ የሚያግደው ሃይል መኖር የለበትም - ማንንም የማገልገል ግዴታ የለበትምና። የራሱን ደስታ በራሱ ጥረቱ የመሻት መብት አለው። ለሳይንሳዊ እውቀት ከሁሉም የላቀ ክብር የሰጡ የአሜሪካ መስራቾች፣ በዚህ መንገድ ነው ስልጡን የፖለቲካ ስርዓትን የገነቡት። የሃይማኖት አክራሪነትን ለማሸነፍ የቻሉትም በዚሁ ምክንያት ነው። እኛም ሳይንሳዊ እውቀት የበላይነት እንዲይዝ በማድረግ አክራሪነትን መከላከል እንችላለን።
“አማኝ ሃይማኖተኛ ነኝ እያልክ፤ እንዴት ማንንም የማገልገል ግዴታ የለብኝም ትላለህ?” ብለው አክራሪዎች ሲያፋጥጡን የምንሰጣቸው ምላሽ ላይ ነው ቁልፉ ያለው።
የአክራሪዎች ማጥመጃ ግን ይሄ ብቻ አይደለም። በሃይማኖቶች መካከል ፉክክርና ተቀናቃኝነት በመፍጠር፣ ከዚያም አልፈው ቅራኔና ግጭት በመዝራት፣ “የኛ ወኪል፤ የሃይማኖታችን ጠበቃ” አድርገን በራሳችን ፈቃድ ዘውድ እንድንጭንላቸው ያደርጋሉ። ከዚያ በኋላማ ስለታቸውን ወደኛው ያዞሩብናል።
ከላይ የተጠቀሰው ሃይማኖታዊ ትዕዛዝ በደንብ አይታችሁት እንደሆነ፣ ዋናው ትኩረቱና ፀቡ፣ ሌላ ሃይማኖትን ከሚከተሉ ሰዎች ጋር አይደለም። የሃይማኖት አክራሪ ዋነኛ ኢላማም፣ ሌላ ሃይማኖት በሚከተሉ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ አይደለም። እንደሱ አይነት ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎችን በጅራፍ እየዠለጠ፣ በብረጥ እየቀጠቀጠ ሰጥ ለጥ አድርጎ መቆጣጠርን፣ እምቢ ያለውን ደግሞ እያቃጠለና እያረደ መጨፍጨፍን ነው የሚፈልገው።
በእርግጥ፣ ይህ ሁሉ የአክራሪ ጉድ በግላጭ ከመታየቱ በፊት፣ በቅድሚያ “የሃይማኖታችን ተቆርቋሪ!” ብለን በፈቃደኝነት እንድንሾመው በርካታ ዘዴዎችን መጠቀሙ አይቀርም። በየዘመኑና በየሃይማኖቱ የተፈጠሩ አክራሪዎችን በምሳሌነት እንጥቀስ።

የአይሁድ አክራሪ፣ አይሁዶችን ያሰቃየ
ከላይ የተጠቀሰው ሃይማኖታዊ ትዕዛዝ፣ ከኦሪት ዘዳግም በቁንፅል የተወሰደ ጥቅስ ቢሆንም፣ በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ የሚፈለፈሉ አክራሪዎች ተመሳሳይ ጥቅሶችን የታጠቁ ናቸው። ከሁለት ሺ አመታት በፊት፣ በእስራኤል አገር ገናና ለመሆን የቻለ አክራሪ የአይሁድ ቡድን፣ ከሃይማኖት መፅሃፍ ውስጥ እልፍ ትዕዛዛትን እየጠቀሰ ነው አማኞችን ሲያሰቃይ የነበረው። “ያንን ትዕዛዝ አፈረስክ፣ ይሄን ትዕዛዝ አጎደልክ” እያለ ይገርፋል፣ በድንጋይ ይወግራል፣ ይገድላል። “ገደል ውስጥ የገባውን በሬ አውጥተህ ያዳንከው በሰንበት እለት ነው” የሚለው ውንጀላ በጊዜው ተራ ውንጀላ አልነበረም። “በሰንበት እለት አንዳችም ነገር እንዳትሰራ ከፈጣሪ የተሰጠህን ትዕዛዝ አፍርሰሃል” ተብለህ ይፈረድብሃል።
ታዲያ አክራሪው ቡድን፣ እንዲህ የአገሬውን አማኝ ከማሰቃየቱ በፊት፣ በአማኞች ዘንድ ገናናነትን ለመቀዳጀት ዘዴ ማበጀት ነበረበት። ተሳክቶለታልም። በወቅቱ “እስራኤልን በቅኝ ግዛት ተቆጣጥሮ ሃይማኖታችንን ያረከሰውን የሮም ወራሪ ሃይል እንዋጋለን” በማለት የሃይማኖት ተቆርቋሪነት ዝናና ማዕረግ ከአማኞች ዘንድ አግኝቷል። ከዚያ በኋላ ነው፣ አክራሪው ቡድን ወደ ዋናው ትኩረቱ በመዞር፣ የአገሬውን አይሁዶች ቁምስቅላቸውን ያሳያቸው የጀመረው።

ግማሽ ያህሉን አማኝ የጨረሰ የክርስትና አክራሪ
ለሺ አመታት በተለያየ መልክ የተፈለፈሉ የክርስትና አክራሪዎችም እንዲሁ፣ ተቻኩለው በቀጥታ ክርስትያኖችን የማሰቃየት ዘመቻ አልጀመሩም። በቅድሚያ “የክርስትና ተቆርቋሪ” የሚል ማዕረግ ለማግኘት ተሯሩጠዋል። የሮምና የግሪክ እምነቶች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር፣ ከአይሁድ እና ከእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ጋር ግጭት ለመፍጠር ብዙ ደክመዋል።
“የክርስትና ተቆርቋሪነታቸውን” ካስመሰከሩ በኋላ ግን፣ ወደ ዋና አላማቸው በመዞር፣ ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት፣ ኦርቶዶክስ፣ መናፍቅ … ምናምን እያሉ በእሳት ማቃጠል፣ በሰይፍ መቅላት፣ በድንጋይ መውገር… ያልተፈፀመ የጭፍጨፋ አይነት የለም። ቀላል እንዳይመስላችሁ። በእያንዳንዱ ሃይማኖታዊ ዘመቻና ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አልቀዋል።
በ17ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ ወደ 20 ሚሊዮን ገደማ የነበረው የጀርመን ህዝብ ቁጥር፣ በጥቂት አመታት ውስጥ ወደ 10 ሚሊዮን የወረደው፣ የክርስትና አክራሪዎች በክርስትያኖች ላይ በለኮሱትና ባካሄዱት ሃይማኖታዊ ዘመቻና ጦርነት ነው። ፈረንሳይ ውስጥ በ16ኛው ክፍለዘመን ማብቂ ላይ ለ30 አመታት በተካሄደ ሃይማኖታዊ ግጭትና ጦርነት 3 ሚሊዮን ሰዎች ተቀጥፈዋል። በክርስትና አክራሪዎች ነው፣ ክርስትያኖች ያለቁት።

በእስልምና አክራሪዎች ያለቁ ሙስሊሞች
በየዘመኑና በየአገሩ የተፈለፈሉ የእስልምና አክራሪዎችም እንዲሁ፣ ከክርስትና ወይም ከአይሁድ እምነት ተከታዮች ጋር በመጋጨት የሃይማኖት ተቆርቋሪነታቸውን ካሳወጁ በኋላ፣ እንደተለመደው ሙስሊሙን ነው መጨፍጨፍ የቀጠሉት። ባለፉት አመታት ኢራቅ ውስጥ በአክራሪዎች የተፈፀመውን የሽብር ዘመቻ ማየት ይቻላል። ፀረ አሜሪካ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት በኢራቅ ውስጥ ገናናነትን ለማግኘት ዘመቻ ካካሄዱ በኋላ ነው፣ ኢራቃውያን ላይ ሰይፋቸውን የመዘዙት። ሺዓ ትክክለኛ እስልምና አይደለም ብለው ገደሉ። ከዚያም ለዘብተኛ ሱኒዎች ከሃዲዎች ናቸው ብለው ጭፍጨፉውን ገፉበት።
የጥንቶቹ አክራሪዎችም በተመሳሳይ መንገድ፣ ሺዓ፣ ሱኒ፣ ሱፊ … እያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞችን ጨርሰዋል። በ14ኛው ክፍለዘመን መገባደጃ ላይ ቲሙር ወይም ቲመርሌን ተብሎ የሚታወቀውና ራሱን እስላማዊ ሰይፍ ብሎ የሚጠራው ገዢ ባካሄዳቸው ወረራዎች ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አልቀዋል። በጦርነት የተቆጣጠራት አንዲት ከተማ ውስጥ፣ ለመቀጣጫ ብሎ ከመቶ ሺ በላይ ሰዎችን አንገታቸውን ቆርጦ፣ 50 የጭንቅላት ክምር ፒራሚዶችን ሰርቷል። በአክራሪ ሙስሊሞች ጭካኔ ነው፣ ብዙ ሙስሊሞች የተጨፈጨፉት።
ሰዎች አትሳሳቱ! የሃይማኖት አክራሪነት ብዙዎቻችን እንደምናስበው ቀላል አደጋ አይደለም። ባለፉት መቶ ወይም ሁለት መቶ አመታት፣ በአለማችን ውስጥ የአክራሪነት አደጋና እልቂት እንደ ጥንቱ ገንኖ ሳይወጣ የቆየው፣ ሃይማኖታዊ እምነት የበላይነቱን አጥቶ ስለቆየ ነው። የመቶ አመታት ታሪክ ውስጥ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ እንደሰደድ እሳት የሚንሰራፋ የአክራሪነት አደጋ ስላላየን፣ ዛሬም ከቁጥጥር ውጭ አይሆንም ብለን የምንፅናና ከሆነ፣ ተሳስተናል።
የሃይማኖት አክራሪነትና እልቂቱ የረገበው፣ በ17ኛውና ከዚያም በ18ኛው ክፍለ ዘመን፣ በሃይማኖታዊ እምነት ፋንታ ሳይንሳዊ እውቀት የበላይነት እየያዘ ስለመጣ ነው። “የብርሃነ እውቀት ዘመን” ወይም “የአእምሮ ዘመን” ተብሎ በሚታወቀው በዚያ ዘመን ነው፣ የግለሰብ ነፃነት ክብር አግኝቶ ስልጡን የፖለቲካ ስርዓት ስር መስደድ የጀመረው።
የአሜሪካ ህገመንግስትን ተከትሎ፣ በየአገሩ ለግለሰብ ነፃነት ዋጋ የሚሰጡ ጭላንጭሎች ብቅ ብቅ እያሉና ህገመንግስቶች እየተበራከቱ፣ ኢትዮጵያ ውስጥም የነፃነት ጠብታዎች መታየት እየጀመሩ ነበር። ለግለሰብ የንብረት ባለቤትነት እውቅና የሚሰጥ፣ የግለሰቦች የደብዳቤ ልውውጥ እንዲሁም መኖሪያ ቤትን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መደፈር እንደሌለበት የሚገልፅ የአገራችን ህገመንግስት የፀደቀው በ1923 ዓ.ም ነው። ይህችው ትንሽዬ ጅምር እየተስፋፋች አልሄደችም።
ሳንይሳዊ እውቀት ቀደም ሲል በሃይማኖታዊ እምነት ምትክ የበላይነትን እንደተቆጣጠረው ሁሉ፣ በ20ኛ ክፍለ ዘመን ደግሞ የሶሻሊዝምና የፋሺዝም ሕዝባዊ መፈክር የበላይነት አግኝቶ ስለነበር፣ ሃይማኖታዊ እምነት እንደድሮው የመግነን እድል ሳያገኝ ቆይቷል። ዛሬ ግን በሩ ተከፍቶለታል።
የግለሰብ ነፃነት የሚከበርበት ስልጡን የካፒታሊዝም ስርዓት እየተጠናከረ የሚጓዝበት ዘመን ላይ አይደለንም - ሳይንሳዊ እውቀት የበላይነቱን አጥቷል። በአገርና በሕዝብ፣ በጭቁኖችና በብሄር ብሄረሰብ ስም፣ የሶሻሊዝምና የፋሺዝም አምባገነንነት እየተስፋፋ የሚሄድበት ዘመን ላይም አይደለንም - “ሕዝባዊ መፈክር” የበላይነቱን አጥቷል። የአስተሳሰብ ኦና በመፈጠሩም ነው፣ ሃይማኖታዊ እምነት ቦታውን ለመሙላትና የበላይነቱን ለመቆጣጠር እየሞከረ ያለው።
ይህን የአክራሪነት ማዕበል በቀላሉ መመለስ የሚቻለው፣ ሳይንሳዊ እውቀት የበላይነት እንዲይዝ በማድረግ ነው። ነገር ግን ይህንን እያደረግን አይደለም። አስፈሪነቱም እዚህ ላይ ነው። አክራሪዎች ሃይማኖታዊ እምነትን ታጥቀዋል። ሌሎቻችን ግን፣ ኢህአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጨምሮ፣ በተበረዘና በተከለሰ፣ በተቀየጠና በተዘበራረቀ ቁርጥራጭ አስተሳሰብ ግራ ከመጋባትና ከመደናበር ውጭ የጠራ አስተሳሰብ አልታጠቅንም። ፓርቲዎቹ ስለ አክራሪነትና ስለ ሃይማኖት ነፃነት በተደጋጋሚ እያወሩ፣ ነገርን ከማድበስበስ በስተቀር አንዳች የሚጨበጥ ቁም ነገር ጠብ ሲላቸው የማናየውም በዚህ ምክንያት ነው።

 

Read 3651 times