Print this page
Saturday, 31 August 2013 11:56

“ነገር ለጫሪዋ ትተርፋለች ረግረግ የረገጣትን ታሰጥማለች

Written by 
Rate this item
(5 votes)

(ነገር ንአጓዲኣ ትልክም፣ ታኼላ ንኣታዊኣ ተስጥም)

ከእለታት አንድ የክረምት ቀን፣ አንዳች አውሎ ንፋስ በመጣ ሰዓት፤ ፈረስ፣ በሬ እና ውሻ አንዱን የሰው ልጅ እንዲያስጠልላቸውና እንዲያሳድራቸው ለመኑት፡፡ ሰውዬው መልካም ፈቃዱ ሆነ፡፡ የክረምቱ ብርድ በርዷቸዋልና ይሞቃቸው ዘንድ እሳት አነደደላቸው፡፡ የሚተኙበት ምቹ ስፍራም ሰጣቸው፡፡ ይበሉት እንዳይቸገሩም ለፈረሱ ገብስ ሰጠው፡፡ ለበሬው ጭድ ሰጠው፡፡ ለውሻውም ከራሱ ራት ከተረፈው ፍርፋሪ አቀረበለት፡፡
በነጋታው ነፋሱ ካቆመ በኋላ ሲለያዩ ምሥጋናቸውን ለሰውዬው ለማቅረብ አሰቡ፡፡
“እንዴት አድርገን እናመስግነው?” አለ ፈረስ፡፡
“የሰውን ልጅ እድሜ እናስላና፤ በየፊናችን ተካፍለን፣ ያለንን ጥሩ ጠባይ ብንሰጥስ?” አለ ውሻ፡፡
“እንዴት ማለትህ ነው?” ሲል ጠየቀ በሬ፡፡
ውሻም፤
“እያንዳንዳችን ልዩ ችሎታ አለን አይደል? ያንን የው ልጅ እድሜ፣ ከእድሜው ጋር በሚሄደው ፀባዩ አንፃር እናጤነዋለን” አለ፡፡
ፈረስ፤
“አሁንም ልትል የፈለግኸው በደንብ አልገባኝም”
ውሻ፤
“ልዘረዝርልህ እኮ ነው፡፡ ለምሳሌ በመጀመሪያ የህይወቱ ክፍል፣ የሰው ልጅ ወጣት ነው፡፡ ለዚህ የሚሆን ጠባይ ማን ይስጠው?” ሲል ጠየቀ፡፡
ፈረስ፤
“እኔ እሰጠዋለሁ” አለና ሰጠ፡፡ በዚህ ረገድ ወጣቶች ሁሉ ትእግስት-የለሽና ጉልበተኛ እንዲሆኑ ሆኑ፡፡
ውሻ ቀጠለና፣
“ቀጥሎ፣ ሁለተኛው የህይወቱ ክፍል የመካከኛ እድሜ ጐልማሳነቱ ነው - ለዚህስ የሚሆን ፀባይ ማን ይስጠው?” አለ፡፡
በሬ፤
“እኔ እሰጠዋለሁ፡፡ የእኔን ጠባይ ይውሰድ” አለ፡፡ እውነትም የሰው ልጅ በመካከለኛ እድሜው በሚሰራው፣ ሥራ ዘላቂ ምን ጊዜም ደከመኝ የማይል፣ ምንጊዜም ታታሪ የሆነ ባህሪ ኖረው፡፡
በመጨረሻም ውሻ፤
“የሽምግልና ጊዜ ጠባይን እኔ እለግሰዋለሁ” አለ፡፡ በዚህም መሰረት የሰው ልጅ በእርጅናው ጊዜ ነጭናጫና በትንሹ የሚያኮርፍ፣ “ውሻ በበላበት ይጮሃል” እንደሚባለው ምግብ ላበላውና ምቾት ለሀጠው የሚያደላና፤ ፀጉረ - ልውጥ ሰው ላይ ግን የሚጮህና የሚናከስ ሆነ፡፡
***
ትእግስት-የለሽና ጉልበተኛ ወጣቶች ለአደጋ ይጋለጣሉ፡፡ ዘላቂና ታታሪ ዜጐች ለሀገር ህልውና ዋና ቁምነገር ናቸው፡፡ የሽማግሌዎች መርጋትና መሰብሰብ፤ ለሀገር የረጋ ህይወት መሰረት ነው፡፡ በአንፃሩ ሽማግሌው ነገር ፈላጊ፣ ጉልቤ ልሁን ባይ፣ የማያረጋጋ ከሆነ የአገር አደጋ ነው፡፡ የፈረሱም፣ የበሬውም፣ የውሻውም ባህሪ በሰው ልጆች ህይወት ውስጥ ወሳኝነት ያላቸው ጉዳዮች እንደመሆናቸው፤ ህብረተሰባችንን ለመመርመር ያግዙናለ፡፡ በየሥራ ምድቡና በየሀብት መደቡ፣ እንዲሁም በአገር አመራር ደረጃ ባሉ ዜጐች ላይም ይንፀባረቃሉና፡፡
የሀገር መሪዎች ወደ አመራሩ ቡድን ፊታቸውን ሲያዞሩ፤ ለህዝቡ ጀርባቸውን መስጠታቸው አይቀሬ ነው ይላሉ የፖለቲካ ፀሐፍት፡፡ ”ከጭምብሉ በስተጀርባ” በተባው መፅሐፍ ደራሲው ባድዊን፤
“ኦርኬስትራውን ለመምራት የሚፈልገው ኅብረ-ዜማ - አቀናጅ (Conductor) ጀርባውን ለተመልካቹ ህዝብ ይሰጣል” ይለናል፡፡
ኦርኬስትራው መስመር ከያዘ በኋላ ግን ወደ ህዝቡ መዞር ያስፈልጋል፡፡ ኦርኬስትራውም የሚያነጣጥረው ተመልካቹ ላይ ነው፡፡ የኅብረ-ዜማውን ቃና ማጣጣም ያለበት ህዝቡ ነው፡፡ ኦርኬስትራውም ሆነ መሪው ኅብረ-ዜማው ለኅሩያን ኅዳጣን (ለጥቂቶች ምርጦች እንዲሉ) ብቻ እንዲሰማ ከሆነ የታቀደው፤ አዲዮስ ዲሞክራሲ!
በሀገራችን እንደተመላላሽ በሽተኛና አልጋ ያዥ በሽተኛ ተብለው ሊከፈሉ የሚችሉ አያሌ ችግሮች አሉ፡፡ አንድኞቹ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሳይገባ በፊት ሲነገሩ፣ ሲመከሩ የሚሰሙ ዜጐች “እሺ፤” ጐርፍ ከመጣም ሲደርስ እናቋርጠዋለን” የሚሉ የሚፈጥሩት ነው፡፡ ሁለተኞቹ ጐርፍ እሚባል ከነጭራሹም ሊመጣ አይችልም፤ የሚሉቱ የሚፈጥሩን ችግር ነው፡፡ ሦስተኞቹ ሀሳቡን ወይም መረጃውን ያመጡትን ክፍሎች “በሬ ወለደ ባዮች” ብለው የሚፈርጁ በመሆናቸው የሚፈጠር፡፡ አራተኞቹ ግን በጣም ጥቂቶቹ ምክር ተቀብለው፤ ድምፅ የላቸውም እንጂ፣ እንጠንቀቅ እያሉ ጥሩ ደወል ቢያሰሙም የመደማመጥ ችግር ነው፡፡ ደጋግመን በከበደ ሚካኤል ልሳን እንደተናገርነው፡- ዛሬም “…አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ የባሰ ደንቆሮ”
እንላለን፡፡
እንሰማማ፡፡ ችግሮች ይግቡን፡፡ ቀድመን ሁኔታዎችን እንይ! የቅድመ-አደጋ ጥሪ ማዳመጥን ትተን፤ ጐርፉ ሲመጣ አንጩህ፡፡ ጉዞ እሚሰምረው ነገር ማጣጣም ሲኖር ነው፡፡ ጉዞ ይሳካል እሚባለው ቅድመ-እንቅፋትን ማየት ሲቻል ነው፡፡
እንቀሰቅሳለን ያልነው መንገድ ውሎ ሲያድር ምን እሳት ይዞ እንደሚመጣ እናስተውል፡፡ “እዚያም ቤት እሳት አለ!” ጨዋታ ንግገር አይደለም፡፡ ቀድሞ ማስላት ጉዳት የለውም፡፡ የቀደሙ ስህተቶችንም አውቆ ማረም ነውር አይደለም፡፡ እሳቱ ሲለኮስ ማገዶ ሲጫር ያልነቃ ልቦና፤ ብዙ ጊዜ አደጋ ያስተናግዳል፤ ይባላል፡፡
የተዳፈነ እሳትን ለማንቃት መሞከር አላግባብ ድካም ነው፡፡ ያ እሳት ከተንቀለቀለ ደግሞ ራስንም ጭምር ያነዳል፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ፤ እንደትግሪኛው ተረት፤ “ነገር ለጫሪዋ ትተርፋለች፣ ረግረግ የረገጣትን ታሰጥማለች” ማለት ነው፡፡

Read 3438 times
Administrator

Latest from Administrator