Saturday, 24 August 2013 11:16

ዴቢ ስለ ማይክል ምን መሰከረች?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ማይክል ምንም አይነት ህመምን የማስተናገድ አቅም የሌለው ሰው ነው፡፡ ማመን በሚያስቸግር ደረጃ ህመምን ይፈራል፡፡ ህመምን ለማስወገድ ምንም አይነት መድሀኒት ይወስዳል፡፡ ዶክተሮቹም ለዚህ ፍርሐቱ መሳሪያ ሆነውለታል” ብላለች፡፡ ዴቢ ሮው ከማይክል ጃክሰን ጋር የተዋወቀችውም እዛው ሀኪም ቤት ነበር - የማይክልን ቆዳ በሽታ ከሚያክመው ከዶክተር አርኖልድ ክላይን ጋር በምትሰራበት ወቅት፡፡ እዛ ተዋውቀው ተጋቡ፡፡ በጋብቻ ጥምረት ሦስት አመት አብረው ኖሩ፡፡ ከ1996-1999 … የመጀመሪያዎቹን ሁለት ልጆቹን የወለደችለትም ዴቢ ሮው ናት፡፡ በፍርድ ቤት በሰጠችው ምስክርነቷ፡- ማይክል፤ ለቀዶ ጥገና ብቻ የሚወሰድ ማደንዘዣ ለእንቅልፍ ሲል ይወጋ እንደነበር ተናግራለች፡፡
“… ከሞት ይልቅ እንቅልፍ የማጣቱ ነገር በበለጠ ያስጨንቀው ነበር” ትላለች ዴቢ፡፡ “ምክንያቱም ያለ እንቅልፍ በመድረክ ላይ ሙዚቃዎችን ማቅረብ ስለማይችል ነው”
ለቀዶ ጥገና የሚወሰደውን ማደንዘዣ በ1997 (በፈረንጆቹ አቆጣጠር) መጠቀም ከማዘውተሩ በፊት … የሌላ ህመም ማጥፊያ መድሐኒት ሱሰኛ ነበር፡፡ በ1993 የፔፕሲን ማስታወቂያ ለመስራት ቀረፃ በሚያደርግበት ወቅት በተፈጠረ አደጋ፣ የራስ ቅሉ ላይ የቃጠሎ አደጋ ባጋጠመው ጊዜ ህመሙን ለማስወገድ “ዲሜሮል” የተሰኘ ማደንዘዣ ይወስድ ነበር፡፡ የዚህን መድሐኒት ሱስ መላቀቅ ሳይችል በላዩ ላይ “ፕሮፖፎል” የተባለውን ማደንዘዣ ለእንቅልፍ ሲል ደረበበት፡፡ የእነዚህ የህመም ማጥፊያ መድሐኒቶች መደራረብ በ2009 አለምን ላስደነገጠ ሞቱ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ሚስቱ በምስክርነቷ ፍንጭ ሰጥታለች፡፡ ዴቢ ሮው የከሳሹ ቤተሰቦች (በተለይ የማይክል ጃክሰን እናት ካተሪን) ከቀጠሩዋቸው ጠበቆች የሚቀርቡላትን መስቀለኛ ጥያቄዎች በፍርዱ ቀጣይ ሂደቶች እንደምትመልስ ይጠበቃል፡፡

Read 1862 times