Saturday, 24 August 2013 10:50

ኢህአዴግም መለስን በደንብ አያውቃቸውም! (እንደኛ)

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(12 votes)

“ጠ/ሚኒስትርነት ምቾትም ነው፤ እስርቤትም ነው”
የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከሞቱ መንፈቅ ሞላቸው አይደል (ጊዜው እንዴት ይከንፋል!) እሳቸውን ተክተው እንዲመሩን ኢህአዴግ የሾማቸው ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ደግሞ በአዲሱ ዓመት ሥልጣን ከያዙ መንፈቅ ይሞላቸዋል፡፡ (ዓመት ገዙን ማለት እኮ ነው!) በነገራችን ላይ የመለስ ሙት ዓመት በችግኝ ተከላ መታወሱ አስደስቶኛል፡፡ (የአረንጔዴ ልማት ተሟጋች ነበሩ እኮ!) የአካባቢ ጥበቃ ቡድን ጭፍን ደጋፊ ግን አልነበሩም፡፡ የግድቡን መገንባት የተቃወሙትን ምን እንዳሏቸው እናስታውሳለን፡፡ እናላችሁ … ችግኝ ተከላው ጥሩ ሆኖ ሳለ አንድ ሃሳብ ግን አለኝ፡፡ ለሳቸው ሙት ዓመት በመላ አገሪቱ የተተከለውን የችግኝ ብዛት መተሳሰብ ያለብን ይመስለኛል፡፡ (የአገር ሃብት እኮ ነው!) በ2000 ዓ.ም የሚሊኒየሙ በዓል ጊዜ ተተክለው የነበሩ ችግኞች ይፅደቁ ይክሰሙ የምናውቀው ነገር የለም እኮ! (መረጃ የለንማ!) እርግጠኛ ነኝ ለመለስ የአንደኛ ዓመት መታሰቢያ የተተከሉት ችግኞች በዕድላቸው ይፅደቁ የምንላቸው አይደሉም (የአበሻ ልጅ ነው በእድሉ ያድጋል የሚባለው!) ስለዚህ ለከርሞ “የችግኝ ተከላው ሰምሯል አልሰመረም?” የሚለውን በመረጃ ላይ ተመስርተን እንድንገመግም የችግኞቹ ብዛት አሁኑኑ ይነገረን፡፡ (ለሃሜት በር ላለመክፈት እኮ ነው!) የጠ/ሚኒስትሩ ሙት ዓመት የተዘከረው ግን በችግኝ ተከላ ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ በዲስኩርም በግጥምም የዘከሩ አሉ፡፡ (ለካ የካድሬ ግጥም አይጥምም!!)
ትንሽ ያልተመቸኝ በመፈክር የታጀበው አዘካከር ነበር፡፡ ካልተሳሳትኩ የአዲስ አበባ መስተዳድር በመፈክር ነው ሙት አመቱን የዘከረው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ደግሞ መለስ የመፈክር ሰው አልነበሩም (በታጋይነታቸው አልወጣኝም) አራት ኪሎ ከገቡ በኋላ ግን መፈክር ሲሉም ሆነ ሲያስብሉ አላየንም (ጦሳቸውን!) እናላችሁ … የመፈክር ጋጋታው ከየት እንደመጣና ለምን እንዳስፈለገ ግርም ብሎኛል (ኢህአዴግ አብሾ አለበት እንዴ?) ምናልባት እኮ ለዶ/ር ነጋሶ “መሳቢያ ውስጥ ከተነዋል” ያላቸውን “ሶሻሊዝም” አውጥቶት እንዳይሆን ሰግቼ እኮ ነው (መፈክር የሶሻሊዝም ጣጣ ነው!) ወዳጆቼ… እኛ እንደ ዶ/ር ነጋሶ መታለል አንፈልግም፡፡ (እሳቸውም ግን ወደው አይደለም!) እኔ የምለው ግን ኢህአዴግ “ነጭ ካፒታሊዝም ነው የምከተለው” ሲል አልነበር እንዴ? (እሱማ ድሮ ቀረ!) ዛሬማ “ኢህአዴግ ነፍሴ” የልማታዊ መንግስት ቀንደኛ አቀንቃኝ ሆኖልናል፡፡ ለነገሩ እኛ ነን ያስቸገርነው እንጂ ወዳጅ አገራት ዘንድማ ዝነኝነት አትርፏል፡፡ (ለዚህ እኮ ነው “በአፍሪካ ኢህአዴግን የሚወዳደር ፓርቲ የለም” የተባለው!)
እኔ ግን ሁሌም ግራ የሚገባኝ ምን መሰላችሁ? የአብዮታዊ ዲሞክራሲና የልማታዊ መንግስት አንድነትና ልዩነት? አንዳንዴ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ? አብዮታዊ ዲሞክራሲ የልማታዊ መንግስት የቤት ስም! አንዳንዴ ደግሞ የሶሻሊዝም ከፍተኛ ደረጃ ኮሙኒዝም ነው እንደሚባለው የአብዮታዊ ዲሞክራሲም ከፍተኛ ደረጃ ልማታዊ መንግስት ይመስለኛል፡፡ (ነገሩ አልሸሹም ዞር አሉ ነው!) የልማታዊ መንግስት ዋና መለያው ኢኮኖሚው ውስጥ “አትርሱኝ” ማለቱ ነው አይደል? (እንድታስረዱኝ እኮ ነው!) ኢህአዴግ፤ “መንግስት አገር ያስተዳድር እንጂ ኢኮኖሚው ውስጥ ገብቶ “መቀወጥ” የለበትም” የሚሉ ወገኖችን ምን እንደሚላቸው ታውቃላችሁ? “ሞኛችሁን ፈልጉ!”
የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አንዴ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገሩ፤ መንግስት የዘበኝነት ሚና ብቻ እንዲኖረው (ኢኮኖሚው ውስጥ የማይገባ ህግ አስከባሪ!) የሚፈልጉት የኒዮሊበራል አስተሳሰብ አቀንቃኞች እንደሆኑ አስረግጠው መግለፃቸው ትዝ ይለኛል፡፡ (አንዳንድ ካድሬዎች “አገር ለማስተዳደር እንጂ ለዘበኝነት አይደለም የታገልነው” ብለዋል አሉ?)
በነገራችሁ ላይ ባለፈው ዓመት ጠ/ሚኒስትሩ ከሞቱ በኋላ አንድ የቻይና ፊት ያላቸው ምዕራባዊ ምሁር ስለመለስ ጉደኛ ነገር ተናግረዋል፡፡ እራሱ ኢህአዴግም የማያውቀውን! “ዓለም የመለስን የኢኮኖሚ መርህ (የመንግስት እጅ ያለበትን ማለት ነው) ቢከተል ኖሮ ከዓለምአቀፉ የኢኮኖሚው ቀውስ ይድን ነበር” ብለዋል ምሁሩ፡፡ (ነፃ ገበያ ቀለጠ!) እርግጠኛ ነኝ የእኚህ ምሁር አባባል ራሳቸው ኢህአዴጐችንም ሳያስደነግጣቸው አልቀረም፡፡ (እንዲህ አስበው አያውቁማ!) እውነቴን እኮ ነው … መለስ ዓለም አቀፉን የኢኮኖሚ ቀውስ ይታደጋሉ የሚለውን ማንም አስቦትም አልሞትም የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ (ቢያውቁማ ይነግሩን ነበር!) ሌላው ቀርቶ ኢህአዴግ መለስን… “የላቀ አዕምሮ ባለቤት”፣ “የፖለቲካ ሊቅ”፣ “የኢኮኖሚ ምሁር”፣ “የዲሞክራሲ ቀንዲል” … ወዘተ እያለ ማድነቅ የጀመረው የውጭዎቹ ወዳጆቻቸው ተናግረው ሲበቃቸው እኮ ነው! ስለዚህ ልክ እኛ ሲሞቱ “አናውቃቸውም ነበር” እንዳልነው ሁሉ ኢህአዴግም እንዲሁ የተቆጨ ይመስለኛል፡፡

በነገራችን ላይ ስንት ዓመት አብረዋቸው የታገሉ የትግል አጋሮቻቸው እንኳን መለስን እንደፈረንጆቹ አልገለጿቸውም (አያውቋቸውማ!) በዚህ የተነሳም ፓርቲው የውጭ ሰው ስለመለስ እንዲናገር ወይም እንዲመሰክር ላለመጋበዝ ወስኗል የሚል “ሃሜታ” ሰምቻለሁ፡፡ (ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ ሆኑባቸዋ!) ባለፈው ዓመት ፕሮፌሰር ይስሃቅ፤ መለስ እንዳረፉ የተናገሩት ነገርም ከኢህአዴግ እውቀት ውጭ ይመስለኛል፡፡ (የማናውቀውን ስብዕናቸውን እኮ ነው የነገሩን!) በዚህ አጋጣሚ ኢህአዴግ የአሁኑን ጠ/ሚኒስትርና ከፍተኛ አመራሮች ማንነት (ስብዕና፣ ብቃት፣ ፍልስፍና ወዘተ) መርምሮ በቅጡ ቢጠቀምባቸው ይበጀዋል እላለሁ (አሁንም እንዳይቆጭ እኮ ነው!)
እንግዲህ ሰሞኑን የመለስ ሙት ዓመት በችግኝ ተከላ የተዘከረው የችግኝ ፍቅር ስለነበራቸው አይደለም፡፡ ለአረንጔዴ ልማት በዓለም አቀፍ መድረክ ያደረጉትን አስተዋጽኦ ለመዘከር ተብሎ ነው፡፡ እግረመንገዴን መለስ “አረንጓዴ ልማት” ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ በቅጡ መረዳት እንዳለብን ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ (ዕውቀታችን ጥራዝ ነጠቅ ሆኖ ነገር እንዳናበላሽ!)
እኛ ደግሞ በዚህ አምድ አንዳንድ ንግግራቸውን እያስታወስን ትንሽ ብንዘክራቸውስ፡፡ (የአቅማችንን ያህል ማለቴ ነው!) እኔ የምለው…ፓርላማው ኮስተር ብሎ ሥራ የጀመረው የሳቅ ድርቀት ስላጠቃው ነው እንዴ? (ጥያቄ እንጂ ሽሙጥ አይደለም!)
ሰሞኑን ከዩቲዩብ ላይ የተገኘ ቪዲዮአቸውን ስመለከት ከማረኩኝ ንግግሮች አንዱ የጠ/ሚኒስትርነት ሥራቸውን ይወዱት እንደነበር የገለፁበት ነው (አብዛኛው እኮ የሚሰራው እንጀራ ሆኖበት ነው!) እናላችሁ … በትርፍ ጊዜያቸው ምን እንደሚሰሩ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ “የተሰጠኝን ሥራ እወደዋለሁ፤ ኮንትራቴ ስምንት ሰዓት ነው፤ ነገር ግን ሥራውን ስለምወደው ከስምንት ሰዓት በላይ ነው የምሰራው፤ ስለዚህ ብዙ ትርፍ ጊዜ አለኝ ብዬ አልወስድም” ብለው ነበር፡፡ (የሚወደውን የሚሰራ እኮ የታደለ ነው!) አንዱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር የጠ/ሚኒስትሩን ንግግር ሰምተው ምን እንዳሉ ታውቃላችሁ? “እኔም የሳቸውን ሥራ እወደዋለሁ!” (ነውጠኛ አባባል እኮ ነው!)
እውነቱን ለመናገር ሰውየው የተዋጣላቸው ተናጋሪ ነበሩ፡፡ ተናግረው ሲያሳምኑ የሚያህላቸው አልነበረም፡፡ አላምንም ያለውን ደግሞ ቢያንስ በሳቅ ይሸኙታል (ባለማመኑ የታሰረ የለም!)
አንድ ጊዜ አገራቸው ላይ ኢንቨስት ሊያደርጉ የመጡ ዳያስፖራዎችን ሰብስበው ሲያነጋግሩ ብዙ ቅሬታና ወቀሳ ከቤቱ ተሰነዘረ - ወደ መለስ ወይም መንግስታቸው፡፡ በዚያ ላይ አብዛኛው ዳያስፖራ ከኢህአዴግ ጋር ሆድና ጀርባ ነው (በጥናት ሳይሆን ከምናየው ከምንሰማው!) እናም የያኔው መለስ ሁሉንም ከግምት ውስጥ አስገብተው ሲያበቁ፣ ለዳያስፖራው “ስሞተኞች” የሰጡት ምላሽ አዳራሹን በጭብጨባ አናጋው፡፡ ብልሃትና ብልጠት የተደባለቁበት የመለስ ንግግር የዳያስፖራውን ልብ እንደረታ መገመት አያዳግትም፡፡ እንዲህ ነበር ያሉት “ይሄ የእናንተ አገር ስለሆነ በቢሮክራሲው መልካም ፈቃድ ኢንቨስት የምታደርጉበት፣ የቢሮክራሲው መልካም ፈቃድ ሳይኖር ሲቀር ደግሞ አኩርፋችሁ የምትሄዱበት ሊሆን አይችልም፤ አማራጭ የላችሁም፤ አገራችሁ ነው፤ በእልፍ እስከመጨረሻው ድረስ መግፋት አለባችሁ፤ ማንም ሊያሰናክላችሁና ሊያስቆማችሁ አይገባም፡፡ እናንተን ከውጭ ኢንቨስተር የሚለየው ይሄ ነው፡፡ የውጭ ኢንቨስተር 190 ምናምን አገር አማራጭ አለው፤ እናንተ አማራጭ የላችሁም፤ አንድ አገር ብቻ ነው ያላችሁ …” እስቲ አስቡት … ይሄ ንግግር እንኳንስ ያለጠብ ያኮረፈ ዳያስፖራን ቀርቶ ደም ሊቃባ ያሰበን ባላጋራ እጅ አያሰጥም እንዴ? አንዳንዴ ሳስበው … አቶ መለስ ፓርቲያቸውን ኢህአዴግን ፈርተው እንጂ (ወይ አክብረው?) በዚህ ተናጋሪነታቸው የተቃዋሚ ጐራውን ሰብስበው ከጐናቸው ያሰልፉት ነበር፡፡ (በ97 ምርጫ ለቅንጅት ሊወዳደሩ ነው ተብሎ አልነበር?)
አንዱ የግል ሚዲያ ጋዜጠኛም ደሞዛቸው ስንት እንደሆነ ጠይቋቸው የሰጡት መልስም የሚያስገርም ነበር፡፡ “ደሞዜን በተመለከተ ፀረ-ሙስና የሁሉም ባለስልጣኖችን ደሞዝ አውጥቷል ይመስለኛል፤ ካላወጣ ግን እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የነበረው 6400 ነው፤ የአሁኑ ጭማሪ ግን እኔ ጋ አልደረሰም፤ ሲደርስ የሚጨመር ነገር ካለ አሳውቃለሁ” እርግጠኛ ነኝ ብዙዎቻችን ይሄንን ንግግራቸውን አልተቀበልነውም፡፡ (ባይዋሹ እንኳ ያሾፉ ነው የመሰለን!) እሳቸው ካረፉ በኋላም ግን ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ ያንኑ ደግመው ተናግረውታል፡፡ ክፋቱ ግን እሳቸውንም ሳንጠረጥራቸው አልቀረንም፡፡ እንዴ… ብናምናቸውማ ኖሮ የጠ/ሚኒስትር ደሞዝ ይሻሻል ብለን ሰልፍ እንወጣ ነበር፡፡ (የአገር ገፅ ግንባታ ያበላሻል እኮ!) እኔ የተቃዋሚ ፓርቲ ቢኖረኝ ኖሮ ይሄን ጥያቄ አንዱ የትግል አጀንዳዬ አደርገው ነበር (ከፀረ ሽብር ህጉ ቀጥሎ!)
እኔ የምለው ግን… አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲህ ሙስና እላያቸው ላይ ያናጠጠው፣ “ደሞዝ እያነሳቸው ቢሆንስ?” ብላችሁ ታውቃላችሁ? (የመንግስት ባለስልጣናት እኮ የመላዕክ ስብስብ አይደሉም!)
ጋዜጠኛ መቼም ዕድል ካገኘ የማይጠይቀው ነገር የለውም (እንጀራው እኮ ነው!) አንዱ ጋዜጠኛ የጠ/ሚኒስትርነት ሥልጣናቸውን እንዴት እንደሚያዩት ጠይቋቸው እንዲህ አሉ “እንደ አመለካከቱ ነው … እንደምቾትም ማየት ይቻላል፤ እንደ እስር ቤትም ማየት ይቻላል” (አንዳንዱ ይሄኔ “ቃሊቲን አላዩ” ብሏቸው ይሆናል - በሆዱ!) “ለምሳሌ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሳነፃፅረው የምቾት ነው … የቆሸሸ ልብስ አልለብስም፣ አልራብም፣ አልጠማም፣ በቂ መጠለያ አለኝ ወዘተ ወዘተ … ነገር ግን ከዚህ ሥራ ወጥቼ ሌላ አማራጭ ብፈልግ እራባለሁ የሚል ግምት የለኝም” በማለት ስለ ምቾቱ ገለፁ፡፡ በመቀጠል እስር ቤት የሚያሰኘውን ተናገሩ “በዚህ ሥራ ላይ በምትሆንበት ወቅት የመሰለህን መናገር፣ የመሰለህን ማድረግ አትችልም፡፡ አንድ ነገር ብል ምንድነው ትርጉሙ? በአገር ላይ ምን ጉዳት ያስከትላል? ድርጅቱ ላይስ … ምናምን የሚል መታሰብ አለበት … በሀገሪቱ በጣም ብዙ ችግሮች አሉ፤ የመጨረሻው ሃላፊነት ያንተ ነው፤ እነዚህን ነገሮች በምታስብበት ወቅት በተወሰነ ደረጃ እስር ቤትም ነው” እውነታቸውን እኮ ነው፤ ነፃነት ከሌለው ያው እስር ቤት ነው፡፡ (ተቃዋሚዎች ሰማችሁ አይደል!) በመጨረሻ ከመላው ኢህአዴግ እሳቸውን (መለስን) ብቻ የሚወድና የሚያደንቅ የተቃዋሚው ጐራ ደጋፊ ሰሞኑን ሹክ ያለኝን ሹክ ልበላችሁና ልሰናበት፡፡ “መለስ በህይወት ከነበሩበት ጊዜ ይልቅ ከሞቱ በኋላ በመንግስት ሚዲያዎች የበለጠ ሽፋን እንዳገኙ ታውቃለህ? … እኔ በደንብ ነው ያጠናሁት … ዳታ ሁሉ አለኝ … በስልጣን ላይ በቆዩባቸው 20 ዓመታት እንዲህ ትኩረት አልተሰጣቸውም”፤ ታፍነው ነበር እኮ!” አለኝ፡፡ (“እውነትም ጠ/ሚኒስትርነት እስር ቤት ነው!” አልኩ-ለራሴ)

 

Read 3436 times