Saturday, 17 August 2013 12:13

ክፍቱ መስኮት

Written by  ደራሲ ሳኪ ትርጉም፡-ሐዊ
Rate this item
(1 Vote)

ሄክቶር ሂዩ ሞንሮ (ሳኪ)በ1870 በበርማ ግዛት ተወልዶ በ1916 የሞተ ደራሲ ነው፡፡ አባቱ፤በበርማ መርማሪ ፖሊስ ነበር፡፡ ሳኪ በሎንዶን ጋዜጠኛ ሆኖ በመስራት የፅሁፍ ተሞክሮውን አሀዱ አለ፡፡ የመጀመሪያ የአጭር ልቦለድ ድርሰቶቹ “በዌስት ሚኒስቴር ጋዜት”ታተሙለት፡፡ በቀጣይ ህይወቱ በርካታ የአጫጭር ልብ ወለድ መድበሎች ለአንባቢዎቹ አበርክቷል፡፡ ይህ “ክፍቱ መስኮት” (the open window) የተባለው ነጠላ ልብ ወለድ “The Unbearable Bassington” ከተባለው መድበል የተወሰደ ነው፡፡
                                                  ***
“አክስቴ አሁኑኑ ትመጣለች ሚኒስተር ኔትል….፡፡ እስከዛው ከእኔ ጋር እየተጫዋወትክ እንድትቆይ ተገድደሀል” አለች አንድ “በራሴ ብቁ ነኝ” የምትል የምትመስል የአስራ አምስት አመት ልጃገረድ፡፡
ፍራምቲን ኔትል ፤ወጣቷን ልጃገረድ ባልደለለ፣ እስክትመጣ የምትጠበቀዋን አክስት ባላዋረደ አንዳች የጭውውት አዝማሚያ ሊጠመድ ራሱን አዘጋጀ፡፡ ግን፤ በግሉ እንደዚህ አይነቱ የእንግድነት ቆይታ በማይተዋወቁ ጎረቤቶች መሀል መደረጉ….ለአእምሮ ቀውስ ህመሙ የሚፈይደው ጠቃሚ ነገር መኖሩን ተጠራጥሯል፡፡ በእነዚህ ባይተዋር ሰዎች መሀል የተገኘው ለህመሙ መፍትሄ እንደሚያገኝ በማመኑ ነበር፡፡
“አዎ….አዎ አውቃለሁ ምን እዛ እንደሚጠብቅህ” ብላው ነበር እህቱ፤ አሁን መጥቶ ወዳረፈበት የገጠር መንደር ለመጓዝ ሲሰናዳ፡፡ “አዎ አውቃለሁ እዛ ራስህን ትቀብርና ከማንም ጋር አትገናኝም፡፡ ከብቸኝነትህ የተነሳ የአእምሮ ህመምህ ይብስብሃል፡፡ ስለዚህ እዛ ካሉ ሰዎች ጋር እንድትቀራረብ የትውውቅ ደብዳቤ ልፃፍልህ፡፡ ትዝ ይለኝ ከሆነ እኔ ወደዛ መንደር ስሄድ ከተገናኘሁዋቸው ሰዎች አንዳንዶቹ መልካም ነበሩ”
ሚሲስ ሳፕልተን፤ህመምተኛው ፍራምተን የትውውቅ ደብዳቤውን ይዞ ከተጠጋቸው የመንደሩ ሰዎች አንዷ ናት፡፡ በእህቱ “መልካም” ተብለው ከተጠሩት ሰዎች ምድብ ትሆን? ሲል ፍራምተን አሰበ፡፡
“እዚህ መንደር ካሉ ነዋሪዎች ብዙዎቹን ታውቃለህ?” ስትል የአስራ አምስት አመቷ ልጃገረድ ፍራምተንን ጠየቀችው፡፡
“አንድም ሰው አላውቅም፡፡ እህቴ ከዚህ ቀደም የመነኮሳቱ መኖሪያ ውስጥ ለእረፍት መጥታ ቆይታ አድርጋ ነበር፡፡ ከአራት አመት በፊት ገደማ፡፡ እና እዚህ ሳለች ታውቃቸው የነበሩትን ሰዎች መጎብኘት እንድንችል የትውውቅ ደብዳቤ ሰጠችኝ”
የመጨረሻውን አረፍተ ነገር የተነፈሰበት ቅላፄ “ባትሰጠኝ ይሻለኝ ነበር” የሚል መታከት በውስጡ አዝሏል፡፡ በግልፅ፡፡
“ስለዚህ ስለ አክስቴ ምንም የምታውቀው ነገር የለም?” ብላ በጥያቄ ተከታተለችው፡፡
“ስሟን እና አድራሻዋን ብቻ” አለ እንግድየው፤ወይዘሮ ሳፕተልን ያገባች ትሆን? ወይንስ ባሏን የቀበረች? እያለ ከራሱ ጋር እየተጠያየቀ ነው፡፡ በክፍሉ ውስጥ የሰፈነ አንዳች መንፈስ ባል-ባል….ወንድ-ወንድ ያውዳል፡፡
“አክስቴ፤ ክፉ እጣ ፈንታ የተከሰተው ከሶስት አመታት በፊት ነበር” አለች ልጅቱ፡፡ “እህትህ እዚህ መጥታ ከሄደች በኋላ መሆኑ ነው”
“ክፉ አጋጣሚ?” ተገርሞ ጠየቃት፡፡ እረፍት በተመላው የገጠራማ መንደር ‹ክፉ አጋጣሚ› የሚከሰትበት ስፍራ አይመስልምና፡፡
“በኦክቶበር ወር መስኮቱ እንደዚህ ተደርጎ የተከፈተው ለምን ይመስልሀል?” አለች ኮረዳይቱ፤ወደ መስኩ የሚያመራውን ትልቁን የፍሬች መስኮት ለእሱ እያመለከተች፡፡
“በዚህ ወቅት በተለምዶ አየሩ ሞቃት ነው፡፡ ነገር ግን መስኮቱን ከተከሰተው መጥፎ አጋጣሚ ጋር የሚያገናኘው ምን ነገር አለ?” አለ ፍራምተን፡፡
“በዚህ መስኮት በኩል…ልክ የዛሬ ሶስት አመት….የአክስቴ ባል እና ሁለቱ ወንድሞቹ ለእለታዊ የተኩስ ልምምዳቸው ወጥተው….ሳይመለሱ ቀሩ፡፡ ገላጣውን ምድረ በዳ አቋርጠው ወደ ሚያዘወትሩት…ወደ ሚመርጡት የጠመንጃ መተኮሻ መስክ በማምራት ላይ ሳሉ…ድንገተኛ ደራሽ ወንዝ መጥቶ ጠራርጎ ወሰዳቸው፡፡ መጥፎ ዝናባማ ክረምት ነበር፡፡ አስክሬናቸው የት እንደወደቀ አልታወቀም፡፡ ከሁሉም የሚያሳዝነው የታሪኩ ክፍል ደግሞ በዚህ አኳኋን የደረሱበት ሳይታወቅ መቅረቱ ነው፡፡”
እዚህ ላይ የልጅቱ ድምፅ የቀድሞውን ጠንካራ አንድምታውን አጥቶ ሰብአዊ መሰለ፡፡
“ምስኪኗ አክስቴ አንድ ቀን ቧላ እና ወንድሞቿ ከጠፉበት ተመልሰው ይመጣሉ፤ ብላ ታምናለች፡፡ ከተሰወሩበት፡፡ እነሱ እና አብሯቸው የደረሰበት ያልታወቀው ባለ ቡናማ ፀጉሩ ውሻ አንድ ላይ ሆነው…በዚህ መስኮት በኩል እንደ አወጣጣቸው ተመልሰው ሲወጡ የምታያቸው ይመስላታል፡፡ ለዚህ ነው ፀሀይ እስክትጠልቅ ድረስ መስኮቱ ክፍት የሚተወው፡፡
“ምስኪን አክስቴ….ባሏ እና ወንድሞቿ ወጥተው ለመቅረት ሲሄዱ አኳኋናቸው እንዴት እንደነበር አይረሳትም፡፡ ደጋግማ ነግራኛለች፡፡
“ባለቤቷ ነጩን የዝናብ ካፖርቱን በክንዱ ላይ አድርጎ…..ሮኒ ታናሽ ወንድሟ “ብሬቲ ለምን ትዝያለሽ” የሚለውን ዜማ እያዜመ፡፡ አክስቴ በዛ ዜማ እንደምትበሳጭ ትናገር ስለነበር እሷን ለመተንኮስ ታናሽ ወንድሟ ዜማውን ያዘወትራል….. በዚህ መስኮት በኩል ከጠፉበት ተመልሰው ሲመጡ የማያቸው እየመሰለኝ እኔ እንኳን በፍርሀት ሽምቅቅ እላለሁኝ….”
ልጃገረዲቱ ድንገት እንደ መንቀጥቀጥ ብላ ወሬዋን አቋረጠች፡፡ አክስትየው መዘግየቷን ይቅር እንዲልላት እንግዳዋን እየጠየቀች ወደ ሳሎን ቤቱ ገባች፡፡ አክስትየው በመምጣቷ ፍራምተንን ግልግል ተሰማው፡፡ በልጅቷ ወሬ ተጨንቆ ቆይቶ ነበር፡፡
“ቬራ እያጫወተችህ እንደቆየች እገምታለሁ” አለችው፤ወይዘሮ ሳፕልተን፡፡
“መሳጭ ነበረች” አለ ፍራምተን፡፡
“መስኮቱ ክፍት በመሆኑ እንደማትረበሽ ተስፋ አደርጋለሁ” አለች ወይዘሮ ሳፕልተን ጠበቅ ባለ ቅላፄ፡፡ “ባለቤቴ እና ወንድሞቼ ከተኩስ በቀጥታ ወደ ቤታችሁ የሚመለሱት በመስኮቱ በኩል ነው፡፡ ወደ ረግረጉ ቦታ ወርደው ስለሆነ የሚመለሱት በጨቀዩ ጫማዎቻቸው ምንጣፌን ማበላሸታቸው አይቀርም፡፡ የእናንተ ወንዶች ነገር እንደዛ ነው አይደል?”
ስለ ተኩስ ልምዳቸው …..እየተመናመኑ ስለመጡት የአደን ወፎች… እንደዚሁም በክረምት ዳክዬዎች እንደሚበዙ… እና ወዘተ በማውራት ተንጣጣች፡፡ ለፍራምተን ይህ ሁሉ ወሬዋ አሰቃቂ ሆነበት፡፡ የወሬዋን አቅጣጫ ወደ ሌላ አርዕስት ለመቀየር በፅኑ ተፍጨረጨረ፡፡ ግን ስኬታማ አልሆነም፡፡ ወይዘሮዋ፤ ለፍራምተን ጭንቀት ቁብ እንዳልሰጠች አስታወቀባት፡፡ አይኖቿ በተደጋጋሚ በእርሱ ላይ አልፈው፣ በተከፈተው መስኮት፣ ከመስኮቱ ባሻገር ወዳለው መስክ ይማትራሉ፡፡ ከሶስት አመት ባሻገር ወደነበረው ጊዜ፡፡
ክፉው አጋጣሚ በሚዘከርበት ሶስተኛ አመት፣ ፍራምተን በዚህ ቤት ውስጥ እንግዳ ሆኖ መገኘቱ መጥፎ አጋጣሚ ሆነበት፡፡
“ዶክተሮቼ ሙሉ እረፍት ማድረግ እንዳለብኝ በአንድ ላይ ተስማምተዋል፡፡ ተስማምተው እረፍት አዝዘውልኛል” አለ ፍራምንተን፡፡ “ሥነ ልቦናዬን ከሚያስጨንቅ ማንኛውም አይነት የሥሜት ጡዘት እንድታቀብ ወይንም ሀይል የሚጠይቅ ምንም አይነት የአካል እንቅስቃሴ እንዳላደርግ አስጠንቅቀውኛል” በማለት የጤና እክሉን ይፋ አደረገ፡፡ ከቁጥጥሩ ውጭ ለመውጣት የሚታገለውን ግራ መጋባት ለማረጋጋት እየጣረ፡፡
ከአጋጣሚ ትውውቅ የተገኙ ሰዎች አንዱ የሌላውን ሰው ህመም እና ድክመት…..ለማወቅ ጉጉት እንዳላቸው ያውቃል፡፡
“ምን አይነት ምግብ እየተመገብኩ ማረፍ እንዳለብኝ ግን ሀኪሞቹ እርስ በእርስ ስላልተስማሙ ትዕዛዝ አልሰጡኝም”ብሎ ፍራምተን ቀጠለ፡፡
“ነው?” አለች ወይዘሮ ሳፕልተን ማዛጋትን እንደ ማፈን በመሰለ ድምፅ፡፡
ቀጥላ ግን ድንገት ፈካ አለች፡፡ በንቁ አስተውሎት፡፡ ፍራምተን እያወራት ላለው ነገር አልነበረም የነቃችው፡፡
“ይኸው መጡ በስተመጨረሻ!” ብላ ጮኸች፡፡ “ልክ ደግሞ ሻይ በመጠጫችን ሰአት፣በጭቃ እስከ አይናቸው ድረስ የተዘፈቁ አይመስሉም!”
ቀላል የማይባል መንቀጥቀጥ ፍራምተንን ሰበቀው፤በመቀጠል ወደ አስራ አምስት አመቷ ልጃገረድ ዞረ “ምንድነው እየተከሰተ ያለው?” የሚለውን ጥያቄ ከነመልሱ እንድትለግሰው የሚለማመጥ አሳዛኝ የእይታ ተማጽኖ ወረወረባት፡፡ ልጃገረዲቱ ከመስኮቱ ውጪ እየተመለከተች ነበር፡፡ በድንጋጤ ክው ብላለች፡፡
ፍራምተን ስም አልባ በሆነ የፍርሀት ጥፊ ተመትቶ ከመቀመጫ ተጠማዝዞ ዞረ፡፡ ወደ መስኮቱ ተመለከተ፡፡ ልጅቱ እየተመለከተችበት ወዳለው አቅጣጫ፡፡
እየጠለቀች ባለችው የጀንበር ውጋገን ሶስት ሰዎች ወደ መስኮቱ አቅጣጫ በማምራት ላይ ናቸው፡፡ ሶስቱም በብብታቸው ጠመንጃ ይዘዋል፡፡ ከመሃከላቸው አንዱ በትከሻው ላይ ነጭ ካፖርት ደርቧል፡፡ የተዳከመ የሚመስል ቡና አይነት የፀጉር ቀለም ያለው ውሻ፣ ከእግራቸው ስር ኩስ-ኩስ ይላል፡፡
ሦስቱ ሰዎች ያለ ምንም ድምፅ ወደ ቤቱ ተጠጉ፡፡ ሸካራ የጎረምሳ ድምፅ “ብሬቲ ለምን ትዘያለሽ?” ብሎ በጩኸት አዜመ፡፡ ፍራምተን በእውር ድንብር ከዘራውን እና ባርኔጣውን ካስቀመጠበት አነሳ…. በኮሪደሩ በኩል ወደሚያስወጣው በር….ከዛ በጠጠራማው የደጅ ጥርጊያ በኩል አድርጎ ፈረጠጠ፡፡ ብስክሌት እያሽከረከረ በመግቢያው የሚያልፍ ሰው ከፍራምተን የሽምጥ አመጣጥ ጋር በግንባር እንዳይላተም ቁጥቋጦ ውስጥ አቅጣጫውን ስቶ ለመግባት ተገደደ፡፡
“ይኸው መጣን የኔ ውድ!” አለ ነጩን ካፖርት የደረበው ሰውዬ፤በፍሬንች መስኮቱ በኩል ገና ከመግባቱ፡፡ “ጭቃም ነበረ፣ነገር ግን አብዛኛው መሬት ደረቅ ነው፡፡ ማነው ይሄ እኛ ስንመጣ ፈርጥጦ የወጣው ሰውዬ?”
“በጣም የተለየ እና ግራ የሚጋባ ሰውዬ ነው፡፡…… ፍራምተን ኔትል ይባላል” አለች ወይዘሮ ሳፕልተን፡፡ “ስለ ህመሙ ብቻ ነው ማውራት የሚችለው፡፡ እና እናንተ ስትመጡ …..አንድም ጥሩ አሊያም የይቅርታ ቃል ሳይተነፍስ …..ፈርጥጦ ጠፋ፡፡ የሆነ የሙት መንፈስ ያየ እኮ ነው የሚመስለው….”
“ምናልባት በውሻው ምክንያት ሊሆን ይችላል” አለች ልጃገረዲቱ ረጋ ብላ፡፡ ቀጠለችና “ውሻ እንደሚፈራ አጫውቶኛል….በአንድ ወቅት በጋንጃ ሀይቅ አቅራቢያ ውሾች አሳድደውት መቃብር ቤት ለመሸሸግ ገብቶ ነበረ፡፡ እና ሌሊቱን ለመቃብር በተቆፈረ ጉድጓድ ገብቶ ለማደር ተገድዶ ነበር፡፡ ውሾቹ በጉድጓዱ አፍ ዙሪያ ከበው ሲጮሁ፣ ሲያጓሩበት እና አረፋቸውን ሲደፍቁበት….ነጋለት፡፡ ማንንም ሊያቀውስ የሚችል ነገር እኮ ነው ያጋጠመው…” አለች ልጃገረዲቱ፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ዝግጅት ታሪክ ፈጥራ መናገር ልዩ ተሰጥኦዋ ስለሆነ፡፡

 

Read 3528 times