Saturday, 17 August 2013 11:24

ሃናኔና ሃሊቴ የአምስት ሣንቲም ቅቤ ተካፍለው ሲቀቡ ውለው ወደማታ በአምስት ሣንቲም ጐመን ይጣላሉ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

(የሚከተለውን ተረት - መሰል ታሪክ ከዚህ ቀደም ትንሽ ለየት ባለ መልኩ ተርከነዋል፡፡ የሚሰማ ጠፍቶ ታሪክ ሲደገም በማየታችን ደግመን አቅርበነዋል፡፡)
አንድ ፀሐፊ እንዳለው “እኔን ቅር የሚለኝ ታሪክ መደገሙ ሳይሆን፤ በበለጠ አስከፊ መልኩ መደገሙ ነው” ይላል፡፡
ዕውነት ሆነው ከመቆየት ብዛት ተረት የሚሆኑ ታሪኮች አሉ፡፡
ባለፈው ሥርዓት፣ ከዕለታት አንድ ቀን የነበሩ፤ ሁለት የትግል ጓዶች ነበሩ አሉ፡፡ ከጊዜ ብዛት ተቃዋሚ ድርጅታቸውን ትተው ወደመንግሥት ለመግባት ተወያዩ፡፡
አንደኛው - “እረ ይሄ ድርጅታችን የሚመች አልመሰለኝም፡፡ አደጋው እየበዛ መጣ”
ሁለተኛው - “ዕውነትክን ነው፡፡ እኔም ከዛሬ ነገ ሁሉም ነገር ቅር እያለኝ መሆኑን፤ ልነግርህ
ሳስብ ነበር፡፡”
አንደኛው - “ታዲያ ከዚህ ወጥተን ለምን ወደመንግሥት አንገባም?”
ሁለተኛው - “ይሻለናል”
ተስማሙና ባንድ በሚያውቁት ሰው በኩል ወደ መንግሥት የፖለቲካ መዋቅር ገቡ፡፡ ጠርናፊያቸው አንድ የሚያውቁት ሻምበል ሆነ፡፡
የፖለቲካ ርዕዮተዓለምና አቋም ላይ ተወያዩ፡፡ ተዋወቁ፡፡ ተማማሉ፡፡ የትግሉ አካል ሆኑ፡፡ ንቃታቸው አስተማማኝ ነው፡፡ ቀድሞ በነበሩበት ድርጅት ውስጥ በቂ ንባብ አድርገዋል፡፡
እየነቁ እየተደራጁ ቀጠሉ፡፡ በመካከል ከሁለቱ አንደኛው ወደ ኪዩባ የመሄድ ዕድል ያጋጥመዋል፡፡
ኪውባ ሄዶ፣ ንቃቱን አዳብሮ፣ ትምህርት አበልጽጐ ወደሀገሩ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳል፡፡
ተንሰፍስፎ ያንን የትግል ጓዱን ይፈልገዋል፡፡ ተገናኙ፡፡
“እንዴት ነህ?” አለ ከኩባ የመጣው፡፡
“በጣም ደህና ነኝ፡፡ አንተስ?” አለ አዲሳባ የቆየው፡፡
“ኪውባ በጣም ድንቅ ነበር፡፡ ብዙ ጓዶች አፍርቻለሁ፡፡ የዳበረ ዕውቀት ይዤ መጥቻለሁ ብዬ አምናለሁ” አለው በነቃ ኩራት፡፡
“መልካም፤ በሚገባ ታወራኛለህ!”
“ለመሆኑ ሻምበልስ? ጤናውን እንዴት ነው?”
“ዉ! ሻምበልኮ ታሰረ” አለው እዚህ የቆየው፤ በሀዘንና እንጉርጉሮ ቃና አቀርቅሮ፡፡
ይሄኔ ከኩባ የመጣው በጣም ግራ ገባው፡፡ “እንኲን ታሰረ!” እንዳይል በሳል የማይል ጓዱ ነው፡፡ “ለምን ይታሰራል?” እንዳይል፤ የራሱንም ዕጣ - ፈንታ አያቅም፡፡ ስለዚህ ሲቸግረው፤
“አቤት የአብዮታችን ፍጥነት?!” አለ፤ ጭንቅላቱን በሁለቱ እጆቹ መካከል ቀብሮ፡፡
ጊዜ አለፈና እንደተባለው ሁለቱም ዕጣ - ፈንታቸው እሥር ቤት የሚከትታቸው ሆነና እሥር ቤት ተገናኙ፡፡ ለንፋስ ወጥተው የግል ጨዋታ ሲጨዋወቱ፤
አንደኛው - “እህስ ጓድ፤ አሁንስ የአብዮታችን ፍጥነት ምን ይመስልሃል?”
ሁለተኛው - “አይ ወዳጄ!! አሁንማ አንደኛውን ጄት ሆኖልሃል! ሁላችንንም ጠራርጐን
ገብቷል!” አለ፡፡
* * *
ከሁሉ ነገር በፊት ከመከዳዳት ይሰውረን፡፡ ስለሰው ትተን ስለአብዮታችን ፍጥነት የማናወራበት ጊዜ ይስጠን፡፡ ሁላችንንም ጠራርጐን ገባ የማንባባልበት፤ “ውሃ ሲወስድ አሳስቆን” የማንዘባበትበት ቀና ዘመን ያምጣልን፡፡
የሮጠ ሁሉ እንደማያሸንፍ የሰሞኑ አትሌቲክስ ያስተምረናል፡፡ ድል፤ ሰዓት ጠብቆ ሊቀያየር እንደሚችልም የሰሞኑ አትሌቲክስ ያስተምረናል፡፡ አንዳንዱ ገና ከጅምሩ ሊያቋርጥ እንደሚችል የሰሞኑ አትሌቲክስ ይነግረናል፡፡ ብዙውን የሩጫ ክፍል ሄዶ ሄዶ ማብቂያው ግድም መሸነፍ ሊኖር እንደሚችልም የሰሞኑ አትሌቲክስ አሳይቶናል፡፡ ቢደክሙም፣ ቢዝሉም፣ ውጣ - ውረዱ ከባድ ቢሆንም፤ ሳይታክቱ፤ በጽንዓት ሮጦ እድሉ አምባ ለመድረስ እንደሚቻልም የሰሞኑ አትሌቲክስ ያለጥርጥር አመልክቶናል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ ራስን በማዘጋጀት፣ በልበ - ሙሉነትና በብልህነት ጊዜና ቦታን ማወቅ ያለውን ፈትልና ቀስም የሆነ፤ ግንኙነትና ትስስር በአጽንኦት እንድናስተውል ታላቅ ተመክሮን አጐናጽፎናል፡፡ ሩጫ ትንፋሽ እንደሚጠይቅ፤ ትግልም ትንፋሽ ይጠይቃል፡፡ ሩጫ ጉልበት እንደሚፈልግ ትግልም ጉልበት ይፈልጋል፡፡ ሳይዘጋጁ የገቡበት ሩጫ ተሸናፊ እንሚያደርግ፣ ሳይዘጋጁ የገቡበት ትግልም ከተሸናፊነት ጐራ ያስፈርጃል፡፡ ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል፤ ይሏል፡፡ ተዘጋጅቶ የሩጫው ሰንበር ላይ ወጥቶም መቼ ማፈትለክ እንዳለብን ካላወቅን፤ የተሻለ ብልጠት ያለው እንደሚቀድመን ሁሉ፤ በትግል ሠፈርም ተዘጋጅቶ ገብቶ ጊዜን ባለማወቅ ሳቢያ፤ ብልጡ ይቀድመናል፡፡ ከሩጫው ሜዳ የተፎካካሪን ብስለትና ጥንካሬ አንዳንዴም ተንኮል ከቁጥር መጣፍ ወሳኝ ነው፡፡ አንዳንዱ ተንከባክቦ የያዘው ጥንካሬ አለው፡፡
ተጋትሮም ተስፈንጥሮም ኬላውን ሰብሮ፣ በጥንካሬው ይዘልቃል፡፡ አንዳንዱ በልምድ ያዳበረው ብስለት አለው፡፡ ስለዚህም የተፎካካሪውን አቅምና በብልህነት የሚጠቀምበትን የጊዜ ሰሌዳ፣ ይመዝናል፡፡ አንዳንዱ የሌሎችን የመሮጫ ረድፍ በመዝጋት፣ ሲመች ጭራሹን በመገፋተር በብልጠትና በተንኮል ይሮጣል፡፡ የባሰበት እስኪነቃበት ዕፅ ይጠቀማል፡፡ እነዚህ የሩጫ ስልቶች የፖለቲካ ስልቶቻችን ተመሳሳይ ገጽታዎች ናቸው፡፡ ሩጫችን ለድል ያበቃን ዘንድ ግብዓቶቹን ሁሉ በአግባቡ ማጤን ዋና ነገር ነው፡፡ “ፈጣን ነው ባቡሩ” እንደምንል ሁሉ፤ “ያልተመለሰው ባቡርን”፤ አልፈን ተርፈንም፤
“እልም አለ ባቡሩ
ወጣት ይዞ በሙሉ” ማለታችንን አንርሳ፡፡
“አወይ መሶሎኒ፤ አወይ መሶሎኒ
ተሰባብሮ ቀረ፣ እንደጃፓን ስኒ” የሚለውም አንድ ሰሞን መዝሙር ነበር፡፡
ይድነቃቸው ተሰማ አንድ ጊዜ ስለሱዳን የእግር ኳስ ቡድን መሻሻል ተጠይቀው፤ “ሱዳን ዘግታ ስትለማመድ ቆይታ፣ ራሷን አጠናክራ፣ ወደፊት መጣች፡፡ እኛ እንደዱሯችን ነው የቆየነው፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር “ቆመን ጠበቅናቸው፤ ጥለውን አለፉ!” ብለዋል፡፡ ራስን ማጠናከር ዋና ነገር ነው፡፡
በህመምም፣ በአቅም ማነስም፣ “አውቀው በድፍረት ሳያውቁ በስህተት” ጥፋት ያጠፉም፣ በበላይ ተንኮልና ጥላቻም፣ በፓርቲ ምሥረታም፣ በመተካካትም ሰበብ ሰዎችን ስናገልል ከአጠቃላይ የአገሪቱ ዕጣ - ፈንታ ስዕል አኳያ ማየት ብልህነት ነው፡፡ በተዘበራረቁና በተወሳሰቡ ፖለቲካዊ ምክንያቶች ቂም መያዝ፣ መከፋፈል፣ አንድነትን ማናጋት፣ ወይም መሰነጣጠቅና “የትልቁ አሣ ትንሹን አሣ መዋጥ አባዜ” ማስተናገድ ክፉ ልማድ ነው፡፡ ይህ ልማድ እንዳይደገም “ሃናኔና ሃሪቴ የአምስት ሣንቲም ቅቤ ተካፍለው ሲቀቡ ውለው፣ ወደማታ በአምስት ሣንቲም ጐመን ይጣላሉ” የሚለውን የወላይታ ተረት ማስተዋል ደግ ነው፡፡

Read 2666 times