Saturday, 10 August 2013 11:17

ትውልድ የ" ማዛመድ "ዕዳው!

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

በዘመናዊነት አስተሳሰብ “ማዛመድ” ያለ ውዴታ የተጣለብን ፍዳ መሆኑን ቅንጣት አልጠራጠርም። ማዛመድ ማግባባት ብቻ አይደለም፡፡ ማዳቀልም ነው፡፡ የሚዳቀሉት ነገሮች ተቃራኒ መሆናቸው ግልፅ ቢሆንም፤ ተቃራኒነታቸው ተመጣጣኝ ካልሆነ ድቅያው ይቆረቁዛል እንጂ አያድግም፡፡
ለምሳሌ፤ ሴት እና ወንድ በፆታ ተቃራኒ ናቸው። ግን ተመጣጣኝ ተቃራኒዎች በመሆናቸው ይዛመዳሉ፡፡ ይፈላለጋሉ፡፡ ይፋቀራሉ፡፡ ይዋለዳሉ። ከሁለቱ ልዩነት ውስጥ አዲስ ፍሬ ይፀነሳል፡፡ ያመጣጠናቸው ተፈጥሮአቸው ነው፤ ፅንሱ ሲያድግ አዲስ ትውልድ ተብሎ ይጠራል፡፡
የሴቴ እና ወንዴውን ፆታ በሌላ ነገር መወከል እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ፆታዎቹን በአስተሳሰብ ልንወክላቸው እንችላለን፡፡ አንደኛው ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ (ፆታውን ከፈለግን ወንድ ብለን እንጥራው) … ሌላኛው የምዕራባዊያንን አስተሳሰብ ሊወክልልን ይችላል፡፡ ይችላል ብቻ ሳይሆን ነውም፡፡ ፆታውን ሴት ብንለው ተቃራኒነቱን አያዳክመውም፡፡ …
በጣሊያን ፋሽስታዊ ወረራ ከደረሰብን ሽንፈት አንስቶ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ ለማዳቀል የምንሞክረው እነዚህን … የሐሳብ፣ የባህል፣ የአመለካከት፣ የእምነት…ፆታዎችን ቅራኔ ነው፡፡ ከሽንፈታችን በፊትማ አለም ወደኛም እኛም ወደ አለም ሄደን መቀላቀልን አንሻም ነበር፡፡ የተሳካልን ግን አይመስለኝም፡፡ የሚዳቀሉት ማንኛቸውም ተቃራኒዎች ተመጣጣኝ ካልሆኑ የተሳካ ትውልድ ወይንም የትውልድ ማንነት አይፈጠርም፡፡
… ቴክኖሎጂን የተቀበለ እንጂ ያልፈለሰፈ አገራዊ አስተሳሰብ ቴክኖሎጂዉን ለማይመጣጠን አገልግሎት ሲጠቀምበት ቢገኝ… ተጠያቂው ትውልዱ አይደለም፡፡ ትውልዱ የራሱን አስተሳሰብ በራሱ ቋንቋ መግለፅ እየቻለ፣ በፈረንጅ ቋንቋ የአማርኛን ቅኔ ለመግለፅ ከሞከረ … ድቅያው ፍሬአማ የሚሆን አይመስለኝም፡፡
… ማዛመድ እና ማዳቀል ግን ለሰው ልጅ የተፈጥሮ ባህርይው ነው፡፡ አበሻም ሆነ ፈረንጅ የሰው ልጆች ናቸው፡፡ (እነ ፍራንስ ቦዋዝ እንደሚሉን ከሆነ!) መቅዳት እና ማስቀዳት ግዴታው በመሆኑ ያስፈልገዋል፡፡ ስለሚያስፈልገውም ደግሞ ለመቅዳት ይገደዳል፡፡ መቅዳት እና ከራሱም እንዲቀዳለት መፈለጉን በሚፈጥራቸው መልከ ብዙ ገለፃዎች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ የዘመኑ ትውልድ የዚህ አይነተኛ ምሳሌ ነው፡፡
የቀዳው ነገር ከምንጩ ውጭ ሲሆን ነው ችግሩ። ለምሳሌ … የብሎን መንጃ (Screw driver) ከባህር ማዶ ወደ አበሻ ማንነቱ አስገብቶ ሲቀዳ … ብሎን መንጃውን “ጠመንጃ” መፍቻ ብሎ ነበር ለራሱ ትርጉም ሲል የሰየመው፡፡ ስያሜ እና ቋንቋ ስለ ነገርየው ያለንን እውቀት እና አስተሳሰብ በአጭሩ ጨምቀን የምናስቀምጥበት (abstract) ማዛመጃችን ነው፡፡ … ብሎን የሚባል ነገር በሌለበት ሀገር ላይ ከብዙ ብሎኖች እና ሜካኒካል የአሰራር ቅንብር የተሰራ አንድ እቃ መግባቱን ሳይሆን ነገርየውን “ለጠብ” አላማ ብቻ በመዋሉ የሚፈለግ መሆኑን ቃሉ ገላጭ ነው፡፡ ቃሉ “ጠብ መንጃ” ነው። ብሎን ማጥበቂያውን ወይንም ማላያውን እቃ ሊያውቀው የሚችለው ከዚህ የጠብ ፍላጐቱ ጋር አያይዞ ነው። ምንም ነገር አጥብቆም ሆነ አላልቶ አያውቅም። ባለማወቁ ጠብ መንጃን መፍቻ ብሎ ጠራው። “መፍቻ” ማለቱ ራሱ ትርጉሙ ወዲህ ነው፡፡ ከመስራት፣ ማፍረስ … ከመግጠም መንቀል እንደሚቀርበው የሚያሳይ ነው፡፡
ስለ ኮምፒውተር ያለው እውቀትም “ከጠመንጃ መፍቻው” የተለየ አይደለም፡፡ ኮምፒውተሩን ይፈልገዋል፡፡ ፊደሎቹን በብራና የጥንታዊ ጥበቡን ተጠቅሞ መጠረዝ አይችልም፡፡ መፅሐፍት ለማተም “የጉተምበርግን” ፈጠራ ይፈልገዋል። ስለሚያስፈልገው፡፡ ከባህር ማዶ ያስመጣዋል፡፡ ካስመጣው ስልጣኔ ጋር የራሱን ጥንታዊነት ደባልቆ አዲስ ድቅያ ለማፍራት ይሞክራል፡፡ … “ጥንቸል ዘላ ዘላ ከመሬት” እንደሚባለው እድሜ ልኩን ሲያዳቅል ኖሮ በስተመጨረሻ … ጥንታዊ አባቶቹ ወደ ቆረቆሩት ገዳም ገብቶ ይመንናል፡፡
ከአለም ጋር ለመዛመድ የሚያደርገው ሙከራ ራስ ምታት ሆኖበት እያለም ሌላ ሀገራዊ ግጭቶችም ልዩነቱን ያበዙበታል … በራሱ እና በሀገሩ ላይ ያሉ ብሔሮች መሀልም ያለው ተቃርኖ የመዛመድ ፍላጐት ይቀሰቅስበታል፡፡ … ግን ተቃራኒዎቹ ተመጣጣኝ ካልሆኑ መደባለቅ አይኖርም። ተመጣጣኝነት ማለት አንዱ የበለጠ፣ ሌላው ያነሰ ባለመሆናቸው እርስ በራስ እንዲቀላቀሉ፣ እንዲዛመዱ የሚያደርጋቸው ስበት ነው፡፡ ካልሆነ መደባለቅ አይቻልም፡፡ ቢደባለቁም አይዛመዱም። ያልተዛመደ ግን የተዛመደ የሚመስል ማንነቱ…በቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት…እየተሳከረበት በመግባባት ስም ሳይግባባ እንቆቅልሽ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
… የደራሲ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር ዜና እረፍት ሲሰማ (በአለማየሁ ገላጋይ) ገፋፊነት የፃፍኳት አንድ ግራ የተጋባች መጣጥፍ ነበረችኝ፡፡ መጣጥፏ አሁን ከሌሎች መጣጥፎች ጋር ተዛምዳ “መልክዐ ስብሐት” የተሰኘች መፅሐፍ ሆና ተጠርዛለች፡፡
በመጣጥፏ ለመቀላቀል ወይንም ለማዛመድ የሞከርኩት ደራሲ ስብሐት ገ/እግዚአብሔርን ከአሜሪካዊው ደራሲ ኧ.ሄሚንግዌይ ጋር ነበር። መጣጥፏ ግራ የተጋባች የሆነችው ዝምድናው የተሳካ ባለመሆኑ ነው፡፡ እኔ የሞከርኩትን ሙከራ በኔ ትውልድ ስም የሚጠራ ወጣት በሙሉ የሚሞክረው ይመስለኛል፡፡ በተለያየ ዘርፍ እና አቅጣጫ ሙከራው ይከናወናል፡፡ … ሁሉም የትውልዱ አባል ለመሆን የሚፍጨረጨርለት፣ የሚሰደድለት አንድ የባህር ማዶ ማንነት አለ፡፡ ለማዛመድ ይጥራል፡፡ እኔ በደራሲ ረገድ ስብሐትን ከሄሚንግዌይ ጋር ለማዛመድ ሞከርኩ፡፡ በደንብ ካልተዛመዱ ሁለቱም ተቃራኒዎች ለየብቻቸው መኖር ቢቀጥሉ ይሻላል፡፡ ምክንያቱም ከድቅያው አዲስ እና ከሁለቱ ተቃራኒዎች የበለጠ የጠነከረ ውህድ (synthesis) አይገኝምና ነው፡፡ ካልተገኘ ደካማው ከውህዱ ውስጥ ይሞታል፡፡ ከድህነት እና ከብልጽግና የትኛው ነው ጠንካራ?
ስለዚህ የማቀላቀል ሙከራዬን እምገፋበት ይመስለኛል፡፡ ማዛመዱ በድርሰት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን … በሙዚቃ፣ በቲያትር፣ በፍልስፍና፣ በፊልም፣ በሳይንስ … በሐይማኖት … ወዘተ እያለ የሚቀጥል ነው፡፡ ማዛመድ የቻልኩ እንደሆነ፤ የሁለቱ ተቃራኒዎች ዝምድና … ተመጣጣኝ እና አንዱ ሌላውን የመሸከም አቅም ያለው ሆነው እናገኛለን፡፡
እስቲ ሙከራዬ ላይ ትንሽ ቅርፅ ልጨምርበት። ቅርፅ ይዘትን የመሸከም አቅም አለው፡፡ ሀሳቡ እስካለ ድረስ የሚገለፅበት ቁልጭ ያለ መንገድ መገኘቱ አይቀርም፡፡ እኔ ዛሬ መግለፅ የሞከርኩት “ዝምድና” የተባለውን እሳቤ ነው፡፡ በዘርፋችን እና በዘርፋቸው፡፡ በእኛ እና በአለም መሀል፡፡ የዚህን ሀሳብ ለመግለፅ ትምህርት ቤት ስንማር ፈተና እንፈተንባት የነበረችውን የጥያቄ ቅርፅ ለመጠቀም ወሰንኩ፡፡
አዛምድ (ለሙዚቃ)
h ሀ. ጃኖ ባንድ (ሊድ ጊታር) a. ውልፍጋንግ
አማዴዮስ ሞዛርት
b ለ. አለማየሁ እሸቴ b. ጄምስ ብራውን
e ሐ. ቴዲ አፍሮ c. አሊ ፋርካ ቱሬ
f ሠ. ማሕሙድ አህመድ d. ፍራንክ ሲናትራ
g ቀ. አስቴር አወቀ e. ሮበርት ኔስታ
ማርሊ
a በ. ፕ/ር አሸናፊ
(እረኛው ባለ ዋሽንት) f. ሁሊዮ ኢግሌስየስ
d ተ. ጥላሁን ገሠሠ g. ሻዴ
c ቸ. አሊ ቢራ h. እስቲቭ ሬይቫን
ማዛመዱ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ውልፍጋንግ አማዲየስ ሞዛርትን ከፕሮፌሰር አሸናፊ ጋር በማዛመዴ የስህተት ምልክት (X) የሚሰጠኝ ካለ … ስህተቱ ከእኔ የመነጨ አይደለም፡፡
ስህተቱ ከእኔ ያልሆነው፡- የተሳሳትኩት የቱ ጋር እንደሆነ ባለማወቄ አይደለም፡፡ ላውቅ የምችለው ከብዙ መቶ አመታት የስልጣኔ ጉዞ በኋላ መሆኑ ላይ ነው፡፡
ማዛመድ ሲያቅተኝ … የራሴን ታላቅነት እፈክርና ወደ አባቶቻችን እምነት እና ትውፊት ስለማፈግፈግ እሰብካለሁ፡፡ … የፈረንጆቹን ስልጣኔ በኮምፒውተር ላይ እጭንና አደምጣለሁ፡፡
አዛምድ (ፍልስፍና)
----ሀ. ? a. ፍሬድሪክ ኒቼ
----ለ. ? b. ቶማስ አኳይነስ
----ሐ. ? c. ኢማኑኤል ካንት
----መ. ? d. ሐሮደርጋር
-b-ሠ. ዘርዐ-ያዕቆብ e. ፕሌቶ
----ረ. ? f. አሪስቶትል
----ቀ. ? g. ቅዱስ አጉስጢኖስ
“ሀ-ለ-ሐ-መ”ን ከ “A,B,C,D” ጋር ለማዛመድ ከመሞከር … “ጠብ መንጃን” ፍቅር እንዲነዳ መፀለይ ሳያዋጣ አይቀርም፡፡ “ጥንቸል ዘላ ዘላ ከመሬት” እንዲሉ ወደ አባቶቻችን የሚስጢር እና ቅኔ ጉድጓድ መመለስ በንፅፅር ቀላል ነው፡፡ ወደ ድግምቱ … ምቀኝነቱ … መተቱ፡፡

 

Read 3635 times