Print this page
Saturday, 10 August 2013 10:42

የአንድነት ፓርቲን 4 ጎማዎች ማን አተነፈሰው?

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(16 votes)

. ኢህአዴግ - ትንግርታዊ እድገት አስመዝግቤያለሁ!
. ተቃዋሚ - አላየንም፤ እድገቱ የውሸት ነው!
. ህዝብ - መሃል ተቀምጦ ቁልጭ ቁልጭ!

ከጥቂት ዓመታት በፊት ነው፡፡ አንድ ዘመናዊ ካፌ ውስጥ ቁጭ ብዬ ያዘዝኩትን ማኪያቶ እየጠበቅሁ ነበር፡፡ (የምንጠብቀው ነገር አበዛዙ!) መጠበቁ ሲሰለቸኝ ከያዝኩት ቦርሳ ውስጥ ያጋመስኩትን አዲስ መፅሃፍ አውጥቼ ማንበብ ጀመርኩኝ፡፡ አንድ አምስት ገፆች ካነበብኩ በኋላ ነው ማኪያቶው የመጣልኝ (“የዘገየ ማኪያቶ እንዳልተጠጣ ይቆጠራል”) አስተናጋጁ የዘገየበትን ምክንያት ሊነግረኝ ወይም ይቅርታ ሊጠይቀኝ አልፈለገም፡፡ (ይቅርታ መጠየቅ የማይወዱት ፖለቲከኞች ብቻ ይመስሉኝ ነበር!) እሱ እቴ! ማኪያቶውን ወርውሮልኝ እብስ አለ፡፡
ደግነቱ ባሪስታው ባለሙያ ነው፡፡ ግሩም ማኪያቶ ነው የሰራልኝ፡፡

ተጨማሪ አምስት ገፆችን በማኪያቶዬ አወራረድኩና ሂሳብ ከፍዬ ለመሄድ፣ አስተናጋጁን በጭብጨባ ጠራሁት፡፡ ሂሳቡን ከተቀበለኝ በኋላ ጠረጴዛው ላይ ያስቀመጥኩትን ዳጐስ ያለ መፅሃፍ የጐሪጥ እያየ “ለቤቱ አዲስ ስለሆኑ ነው እንጂ ማንበብ ክልክል ነው” አለኝ፡፡ በትክክል የተሰማኝን ስሜት አላውቀውም፡፡ ንዴት… ግርምት… ግራ መጋባት… ሁሉም በአንድ ላይ የተደበላለቁበት ስሜት ሳይሆን አይቀርም፡፡ “አበዳችሁ እንዴ… እንዴት ማንበብ ትከለክላላችሁ?” አልኩት አስተናጋጁን፡፡
“እኔ የታዘዝኩትን ነው… ካላመኑኝ…” ብሎ ግድግዳ ላይ ወደተለጠፈ ማሳሰቢያ በእጁ ጠቆመኝ፡፡ ዓይኔ እጁን ተከትሎ ሄደ፡፡ “ጋዜጣ ማንበብ ክልክል ነው!” ይላል - ቃለ አጋኖው የደመቀው ማሳሰቢያ! ከአፌ አልወጣም እንጂ “ደንቆሮዎች!” ብያለሁ - በሆዴ፡፡ (ንዴት ነዋ!) “አንድ ሰሞን እኮ ቤቱ ላይብረሪ መስሎ ነበር… አንድ ማኪያቶ ይዞ መወዘፍ ነው!” አለኝ - የክልከላውን ምክንያት በግድምድሞሽ ሊያስረዳኝ የፈለገው አስተናጋጅ፡፡ “መቼ ይሆን ከክልከላ አባዜ” የምንላቀቀው? ለአፍታ ቆዘምኩ፡፡ ከመንግስት ጀምሮ እስከ እድር ቤት መጋዘን ኃላፊው መከልከል ብቻ ነው፡፡ በደንብ ሳስበው የሰነፍ መፍትሄ መስሎ ታየኝ፡፡ ፈጠራ ሲነጥፍ፣ አዕምሮ መስራት ሲያቆም የሚመረጥ ቀላል መፍትሄ፡፡ (ጦቢያን የሰነፎች አገር አድርገናታል!)
ይሄ የማንበብ ክልከላ ትዝ ያለኝ ለምን መሰላችሁ? አንድ ወዳጄ ሰሞኑን አንድ ምግብ ቤት ውስጥ ተለጥፎ ያነበበውን ማሳሰቢያ ነግሮኝ ነው፡፡ “ጉርሻ ክልክል ነው!” ይላል፡፡ (ጉድ ሳይሰማ… አሉ!) ይኸው “አትጐራረሱ!” የሚል ምግብ ቤት መጣና አረፈው! (“መሳሳም ክልክል ነው” የሚሉም አሉ፡፡) በእርግጥ እነዚህኞቹም ቸግሯቸው ነው፡፡ (ቢቸግር ጤፍ ብድር አሉ!) ምግብ ቤቱ ብፌ በማዘጋጀት ይታወቃል፡፡ አንዳንድ “ስማርት” ነን ባዮች ታዲያ ሁለት ሆነው ይገቡና የአንድ ሰው ምሳ አንስተው ይበላሉ - እየተጐራረሱ፡፡ ብፌ ላይ ደጋግሞ ማንሳት ስለሚፈቀድ፣ አንድ ምግብ ለሁለት ጥግብ እስኪሉ በልተው ይወጣሉ - የአንድ ብፌ ብቻ ከፍለው፡፡ ከምግብ ቤት ሃላፊዎቹ የተገኘ መረጃ ነው (from the horse’s mouth እንዲሉ) ሃላፊዎቹ ለዚህ ቢዝነስ የሚያቃውስ ችግር የመጣላቸው ፈጣን መፍትሄ ጉርሻን መከልከል ነው፡፡ የቢዝነስ ስትራቴጂ መሆኑ እኮ ነው! (ድንቄም ስትራቴጂ!)
አይገርማችሁም… ሁለቱም እኮ ጉርሻን “አቢዩዝ” እያደረጉ ነው - ተመጋቢውም መጋቢውም፡፡ አንዳንድ ብልጣ ብልጦች ጉርሻን ያለአግባብ ተጠቀሙበት ብሎ መጐራረስን መከልከል የሰነፎች መፍትሄ ነው፡፡ እንዴ… መጐራረስ እኮ “አንጡራ” ባህላዊ ሃብታችን ነው፡፡ (የውጭ ምንዛሪ ባያመጣም!) በነገራችሁ ላይ ፈረንጆች በጉርሻና በደቦ የአመጋገብ ባህላችን ይገረማሉ አሉ፡፡ (ጥሬ ስጋ መብላታችን እንደሚያስገርማቸው!) ጋዜጣ ማንበብ በይፋ የሚከለክል ካፌ እንዳለን ቢሰሙ ደግሞ የበለጠ ይገረሙ ነበር፡፡ (ኧረ “ዊርድ” ይሆንባቸዋል!) ምናልባትም የጥናትና ምርምር መነሻ ሊሆናቸውም ይችላል፡፡ (ሺ አመት ቢያጠኑን አያውቁንም!)
ይሄውላችሁ… አንድ ቀን አገር አማን ነው ብለን ካፌ ውስጥ ስንገባ ደግሞ “ሞባይል ማውራት ክልክል ነው!” የሚል ማሳሰቢያ እንዳናይና ተማረን ለስደት እንዳንነሳ (ስደቱም ካልተከለከለ እኮ ነው!) ሰሞኑን የጥላሁን ገሰሰ ልጅ በኢቴቪ “የማያውቁት አገር አይናፍቅም…” የሚለውን ዘፈን ሲያቀነቅን ሰምቼ አልዋጥልህ አለኝ፡፡ እንዴ… በዓመት ሩብ ሚሊዮን ገደማ ህዝብ አገሩን ጥሎ ወደማያውቀው አረብ አገራት እየሄደ እኮ ነው፡፡ የማያውቁት አገርማ በደንብ ይናፍቃል! ቢያንስ በጦቢያ
እኔ የምላችሁ…ሰሞኑን “አንድነት” ፓርቲ በሰላማዊ ሰልፍ ተንበሸበሸ አይደል? ምን ያድርግ? የስምንት ዓመት “ውዝፍ” አለበት እኮ! (የሰልፍ “ሃራራውን” እየተወጣ ነው!)
አንዳንድ ፖለቲካ - ቀመስ እንዲሁም ኢህአዴግ ዘመም ሰዎች፤ ተቃዋሚዎችን ሲተቹ “እነሱ ደሞ ያለተቃውሞ ሥራ የላቸውም” ይላሉ፡፡ እንዴ … ድሮም የተቋቋሙት ለ“መቃወም” አይደለም እንዴ? (ፈቃዳቸው እኮ የተቃውሞ ነው!) ያለዚያማ የኢህአዴግ “አጋር” ድርጅት መሆን ይችሉ ነበር፡፡ እናላችሁ… ጥያቄው መሆን ያለበት ለምን ተቃወሙ ሳይሆን “ምንድነው የተቃወሙት?” የሚለው ነው፡፡ (“ተቃውሞ ለተቃውሞ ሲባል” ወይስ? … የሚል ክርክር በኢቴቪ ቢጀመር ጥሩ ነበር!) ሌላው ደሞ “ለሚቃወሙት ነገር አማራጭ አላቸው ወይ?” የሚለው ጥያቄ ነው - ለተቃዋሚዎች የሚቀርብ፡፡ እንጂማ… መቃወም፣ መሰለፍ፣ መሰብሰብ፣ መቀስቀስ፣ መደራጀት፣ ማደራጀት፣ ማስፀደቅ ማሰረዝ… ሥራቸው እኮ ነው፡፡ (ህገመንግስቱ ያጐናፀፋቸው መብትም ጭምር!) ለምሳሌ የአንድነት ፓርቲው አቶ አስራት ጣሴ፤ በሰሞኑ የተቃውሞ ሰልፍ “እድገቱ የውሸት ነው!” ብለዋል (ሥራቸውም መብታቸውም ነው!) ኢህአዴግ ደግሞ እድገቱን በአሃዝና በዲጂት አስልቶ “የምር ነው” ይለናል፡፡ (እሱም መብቱ ነው!) እኛ ደሞ (ሰፊውን ህዝብ ማለቴ ነው!) መሃል ሆነን ቁልጭ ቁልጭ እንላለን (እኛም መብታችን ነው!)
“አንድነት” በሰሞኑ ሰልፍ ደረሰብኝ ያለውን ችግር ሰምታችኋል? ቅስቀሳ የሚያካሂድበት መኪና አራቱም ጐማዎች ባልታወቁ ግለሰቦች ተንፍሰው ተገኝተዋል፡፡ አንዳንዶች የኢህአዴግ ሴራ ነው ቢሉትም እኔ ግን ለመቀበል አቃተኝ (ኢህአዴግ መንግሥት እንጂ “አሸባሪ” ነው እንዴ?)
እኔ የምለው ግን… የፓርቲዎች “ሥነምግባር ኮድ” ምርጫ ከሌለ (election ማለቴ ነው!) አይሰራም እንዴ? (ሥነምግባር እኮ ለራስ ነው!) አንድነትም ግን መጠንቀቅ ነበረበት፡፡ ለምንድነው ለመኪናው ጠባቂ የማያቆመው? (ላቷን ውጭ እያሳደረች ጅብን ነገረኛ ታደርጋለች አሉ) በነገራችሁ ላይ ሰሞኑን ተቃዋሚዎች የሚያካሂዱት እንቅስቃሴ ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለኢህአዴግም ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው የልምድ ፖለቲከኞች (የልምድ አዋላጅ እንደሚባለው) ተናግረዋል፡፡ እኔም እስማማለሁ (እኔም እኮ የልምድ ፀሃፊ ነኝ) አያችሁ… እንቅስቃሴው ዲሞክራሲ እንዳለና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ እየተጧጧፈ መሆኑን የሚያሳይ ነውና (የባቡር መስመር ዝርጋታውን ባያህልም!) ለመንግሥትም ሆነ ለኢህአዴግ የገፅ ግንባታ ያግዛቸዋል፡፡
ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ፤ ባለፈው እሁድ በኢቴቪ “120” መዝናኛ ፕሮግራም ስለ ፖለቲካ የተናገረውን ሰማችሁልኝ? እኔማ ምን አልኩ መሰላችሁ? “ኃይሌ አምርሯል!” እውነቴን እኮ ነው! የኃይሌ ወደ ፖለቲካ መግባት እርግጥ መሆኑን ያወቅሁት የዛን እለት ነው፡፡ (በኢቴቪ ደገመዋ!) ምን እንዳለ አልሰማችሁም? የፖለቲካ “እሳት አደጋ አጠፋለሁ” እኮ ነው ያለው፡፡
“ፖለቲካ እሳት አይመስለኝም፤ ከሆነም ገብቶ ማጥፋት ነው” ብሏል-አትሌቱ፡፡ (ችግሩ ውሃ እኮ ነው!) ውሃው ከተገኘ ግን እንደ ኃይሌ አይነት ብዙ የ“ፖለቲካ እሳት” አጥፊዎች ያስፈልጉናል፡፡ “የፖለቲካ አምቡላንስ” እና የ “የፖለቲካ ቀይ መስቀል”ም ቢገኝ … ሻርን ነበር፡፡ ጦቢያ ከ“ፖለቲካ እሳት አደጋ” ትድናለች ማለት እኮ ነው! (ቢያንስ ቃጠሎው ይቀንሳል!) ዜጐች በፖለቲካ እሳት ከመለብለብም ይድናሉ፡፡
ቀስ በቀስ ፖለቲካ እሳት ሳይሆን ውሃ ይሆናል - የበረደ፣ የሰከነ፣ የረጋ፡፡
የፖለቲካችን ባህርይው ብቻ ሳይሆን መልኩም ይለወጣል - ከ“ቀይ” ወደ “አረንጓዴ”፣ ከ“እሳት” ወደ “ውሃ”፣ ከብጥብጥ ወደ ሰላም፣ ከ “ሽብር” ወደ ልማት ይቀየራል፤ ያድጋል፤ ይሻሻላል፡፡ ለአረንጓዴው ፖለቲካ ያብቃን! (ከአትሌት ኃይሌ ጋር ወደፊት!)

Read 3005 times