Saturday, 03 August 2013 10:37

“የእናተንስ እኛ፤ የእኛን ማን ገደለው…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(13 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

አንድ ወዳጄ በሚኒባስ ላይ አየኋት ያላት ጥቅስ ምን ትላለች መሰላችሁ… ‘ስኮፒዮ የሌለው መኪናና ታሪኩን የማያውቅ ሰው አንድ ናቸው…’ አሪፍ አይደል! ዘንድሮ ታሪክ አዋቂና ‘ትሪክ’ አዋቂ ተምታታብንሳ! የምር ግን ምን መሰላችሁ…አንዳንድ ጊዜ ታሪክ እየተባሉ የምናነባቸውና የምንሰማቸው ነገሮች…አለ አይደል… የሆነ የፍርድ ቤት የ‘ክስ መዝገቦች’ እየመሰሉን ተቸግረናል፡፡ የምር ግን ዘንድሮ ሁሉም ነገር “እነሱ ናቸው…” አይነት ‘ጦስ፣ ጥምቡሳስ’ን ወደሌላ ማስተላላፍ እየሆነ አገራችን መካሰሻ፣ መነካካሻ እየሆነች ነው፡፡ ይቺን እውነተኛ ታሪክ ስሙኝማ… በአገራችን አንድ አካባቢ የሆነ ነው አሉ፡፡ ጎረቤታሞቹ ለረጅም ጊዜ አብረው ኖረዋል፡፡ አንድ ቀን ታዲያ የአንደኛው ቤተሰብ ልጅ ህይወቱ ያልፋል፡፡ ይሄኔ ታዲያ ነገር ይመጣላችኋል፡፡ የሟች ዘመዶች ውስጥ ውስጡን የጎረቤቶቻቸውን ስም እያነሱ “እነሱ በልተዉት ነው ህይወቱ ያለፈው…” ምናምን እያሉ ወሬው ተነዛና መንደረተኛው ጆሮ ሁሉ ደረሰ፡፡

ከጥቂት ወራት በኋላ ‘በልተዉት ነው’ ከተባለው ቤተሰብ አንድ ልጅ ይቺን ዓለም ይሰናበታል፡፡ ይሄኔ ከዘመዶቹ አንዷ ምን ብለው አለቀሱ አሉ መሰላችሁ… አንድ አምላክ ነው እንጂ የሚያደላድለው እግዚአብሔር ነው እንጂ የሚያደላድለው መድኃኔዓለም ነው እንጂ የሚያደላድለው የእናተንስ እኛ የእኛን ማን ገደለው? እናላችሁ…በሆነ ባልሆነው ጣት እየተቀሳሰርንና “እነሱ ናቸው…” እየተባለ “የእናተንስ እኛ፤ የእኛን ማን ገደለው…” የምንባል ቁጥራችን እየበዛ ነው፡፡ በልጅነት ጊዜ… ኩኩ መለኮቴ እሷ በበላችው በእኔ ላከከችው… የምትባል ነገር ነበረች፡፡ ብዙ ነገሮች ‘ኩኩ መለኮቴ’ እየሆነብን ተቸግረናል፡፡ ታዲያላችሁ…ነገረ ሥራችን ሁሉ ‘ኩኩ መለኮቴ’ አይነት ሲሆን፣ “የእኔ ጥፋት ነው፣ አስተካክላለሁ…” የሚል ሲጠፋ አሁን በየቦታው እንደምናየው ወሬያችን ሁሉ ስለ ችግርና ችግር ብቻ (እንዲሀ አይነት ‘ቃላት አጣጣል’ ሲገባባኝስ’!) ብቻ ይሆናል፡፡

እናማ… ስለ ቦተሊካ ችግር… ስለአገልገሎት አሰጣጥ ችግር… ስለ መከዳዳት ችግር… ምን አለፋችሁ፣ የችግር ዝርዝራችን ከህዝብ ቁጥር ዝርዝራችን ሊስተካከል ፉክክር ላይ ያለ ይመስላል፡፡ እናማ…አብዛኛው ችግር የሚመጣው የራሳችንን ሸክም ራሳችን ከመሸከም ይልቅ ወደ ሌላው የምናስተላልፍ እየበዛን ስለሄድን አይመስላችሁም! እናላችሁ…እንዲሁ አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር “እነሱ ናቸው…” ብሎ ጣት መቀሳሰር የዘመናችን ‘ሆቢ’ ነገር ሆኗል፡፡ ነገሮች ሲበላሹ፣ በቀኝ መሄድ የሚገባው ወደ ግራ ሲንጋደድ…“እነሱ ናቸው…” ባልበላው የሚላከክበት መአት ነው፡፡ የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… “የእኛ ጥፋት ነው…” “ችግሩን የፈጠርኩት እኔ ስለሆንኩ ይቅርታ…” ምናምን የምንባባልበት ጊዜ አልናፈቃችሁም! ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ምንጊዜም የተቀረው ዓለም እኛን ድባቅ ለመምታት እንዳሰፈሰፈ አድርጎ የማሰብ ነገር የህይወታችን አካል ሆኗል፡፡ ስሙኝማ…ባልና ሚስት አካባቢ “የእናተንስ እኛ፤ የእኛን ማን ገደለው?” አይነት ነገር መአት ጊዜ ይከሰታል ይባላል፡፡

“መብራቱን ሳታጠፊ ተኝተሽ አምፖሉን አቃጥለሽው አረፍሽ!” ሲላት “አንተ አይደለህ እንዴ ሌሊት፣ ሌሊት አሥሬ እየተነሳህ ስታበራና ስታጠፋ የምታድረው!” ትለውና የት ይደርሳል የተባለ ትዳር በአንዲት የ‘ቻይና አምፖል’ መቃጠል ድብልቅልቁ ይወጣል፡፡ (እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ሳምንት የማይበሩ አምፖሎች አምጥቶ የበተነብን ማነው! አሀ…በአሥርና አሥራ ምናምን ብር እየተገዙ በጥቂት ቀናት ‘ኤክስፓየር’ የሚያደርጉ አምፖሎች ‘ደምፕ’ ተደርገውብን ግራ ገብቶናላ! …ለነገሩማ…አለ አይደል…ብዙ ነገር አንድ ‘ሳምንት የማይበራ አምፖል’ እየሆነብን አይደል!) እናላችሁ…“እኔ አጥፍቻለሁ…” ማለት ‘ካፒታል ፐኒሽመንት’ ምናምን አይነት ፍርድ ‘በራስ ላይ’ እንደማሳለፍ አይነት እየተቆጠረና ነገርዬው ሁሉ… “የእናተንስ እኛ፤ የእኛን ማን ገደለው?” እየሆነ መአት ቤተሰቦች ይታመሳሉ፡፡ የባልና ሚስት ነገር ካነሳን አይቀር…ስማኝማ ወዳጄ…ባሏ ማታ እቤት ሲገባ “ምን እያደረግሽ ነው?” ሲላት “ራትህ ስለቀዘቀዘ እያሞቅሁ ነው…” ስላለችው ሴት ዛሬ እናውራ እንዴ! (ለ‘አደባባይ አይበቃም’ ብዬ ነው…) ስለ ባል፣ ሚስት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን የሆነ ቦታ ያነበብኳትን ስሙኝማ…ከጋብቻ በኋላ መኝታ ቤቱ ምን አይነት ጠረን ይኖረዋል? ለሚለው ጥያቄ የተሰጡ መልሶች ናቸው፡፡

በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት የሽቶና የአበባ መአዛ ይኖረዋል፡፡ ከአሥራ ሁለት ወራት በኋላ የቤቢ ፓውደር፣ ክሬም፣ ዳይፐርና ቤቢ ሎሽን አይነት መአዛዎች ይኖሩታል፡፡፡ ከሰባት ዓመታት በኋላ የሚኖረው ሽታ ምን መሰላችሁ…የህመም ማስታገሻ ኪኒኖች ሽታ! የቁርጥማት…ወዘተ. ደግሞላችሁ…ደግነቱ የዲ.ኤን.ኤ. ዘመን ሆነና ነው እንጂ…“ልጁ የአንተ፣ የራስህ ነው፣” “ያኔ ለምነህ እንትን ብለህ ደግሞ የእኔ አይደለም ልትል ነው!” አይነት ‘ኩኩ መለኮቴ’ መአት ነው፡፡ “የትም እንትን ብለሽ ያመጣሽውን… አባቱን እዛው ሄደሽ ፈልጊ!” አይነት ‘አንዱ በበላው፣ በሌላው ማላከክ’ መአት ግንኙነቶችን አፍርሷል፡፡ ይቺን ስሙኝማ…ሴትዮዋ ለሆነ የሬድዮ ቶክ ሾው ስልክ ትደውልና ምን ትል መሰላችሁ… “ሦስት ልጆቼን ይዞ ባዶ ቤት ጥሎኝ ለጠፋው ባለቤቴ መልእክት እንድታስተላልፉኝ ነበር፡፡” “እሺ አድማጫችን፣ መልእከትሽ ምንድነው?” ይሏታል፡፡ ይሄኔ እሷ ሆዬ ምን ብትል ጥሩ ነው… “እባክህ ከሦስቱ ልጆች ሁለቱን መልስልኝ፣ አንደኛው ብቻ ነው የአንተ ልጅ በሉልኝ፡፡” እንዲህም አለላችሁ! እናላችሁ…ብዙ ጊዜ የሆነ ነገርን ማን እንዳበላሸው “ፀሐይ የሞቀው፣ አገር ያወቀው…” ነገር ነው፡፡ ታዲያላችሁ…ነገርዬውን ማን እንዳበላሸው እየታወቀ… “እነሱ ናቸው…” ምናምን ሲባል ስትሰሙ…አለ አይደል…መግባባት ችለን ‘የቄሳሩ ለቄሳር’ የሚሆንበት ዘመን ለምን ቀን በቀን ጭርሱን እየራቀን እንደሚሄድ ግራ አይገባችሁም! ስሙኝማ…የዚህ አገር ‘ቦተሊካ’ ትልቁ ችግራችን (አንዳንዴ “ችግራቸው…” ለማለት ዳር ዳር አይላችሁም!)…በቃ ትናንት ለነበረውም፣ አሁን ለሚፈጠረውም ችግር ሁሉ …“እነሱ ናቸው…” የሚሉት አባዜ ነው፡፡ እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንዳንድ ጊዜ “ምንም ነገር አለማወቅ ይሻል ይሆን!” ያሰኛል፡፡ ጭንቀት የለ…“ይቺ አገር ወዴት እየሄደች ነው?” አይነት ነገር የለ…በቃ፣ ዋናው አጀንዳ “ይሄን የቢራ ዋጋ መቼ ነው የሚያወርዱልን?” የሚል ይሆንና ቢያንስ፣ ቢያንስ ለአሞክሲሊን የምንመድበው በጀት ይቀንስልናል፡፡

እናላችሁ… ዛሬ ከሰዓት በኋላ ‘ውሀ’ አካባቢ ተሰብስባችሁ…አለ አይደል…ከመሀላችሁ …“በቀደም በአፍሪካ ዋንጫ ተካፈልን ነበር ሲሉ የሰማሁት እውነት ነው እንዴ?” ወይም “እናንተ ሙባረክን ገለበጡት አሉ…” የሚላችሁ ሰው…ምን አለፋችሁ… ‘የሸረሪት ድር ያደራበት ጭንቅሌ ይዞም ቢሆን’ ለሽ ብሎ ይተኛል፡፡ እናላችሁ…አንድ ነገር ሲፈጠር “ጠላቶቼ ናቸው እንዲህ የሚያስወሩብኝ…” “ምቀኛ ጎረቤት ጠቁሞብኝ ነው…” “የፔርሶኔሉ ጸሀፊ ስለማትወደኝ ሹክ ብላ ነው እየተባለ…” አንዱ በበላው በሌላ እየተላከከ የአገሪቱ ጣቶች በሙሉ የሚጠቁሙት ወደ ሌሎች ብቻ ሆኗል፡፡ “የእናተንስ እኛ፣ቀ የእኛን ማን ገደለው?” አይነት አባባልን ‘ታሪክ’ የሚሆንበትን ዘመን ያፍጥልንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5515 times