Saturday, 27 July 2013 14:19

ያልነገርኩሽ ነገር

Written by  አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(42 votes)

ሁለቱም ፍቅር ይይዛቸዋል ተብለው የሚጠረጠሩ አይነት አይደሉም፡፡ ‘እንዲህ የሚባል ነገር አለ እንዴ?’ ሊል ይችላል አንዳንድ ሰው፡፡ አዎ እንዲህ የሚባል ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ ፡- “እከሌ እኮ ፍቅር ይዞታል፡፡” ሲባል” “ተዉት እባካችሁ እሱ ልማዱ ነው፡፡” የሚል መልስ ይሰማል፡፡ አንዳንዴም፡- “እከሊት እኮ ፍቅር ያዛት፡፡” ሲባል “እሷን?! እንዴት ተደርጐ?! እሷ እኮ ጀግና ቢጠበስ አይሸታትም!” የሚባልላትም አለች፡፡ ሁለቱም “እንዴት ተደርጐ” የሚባልላቸው ናቸው፤ ግን ሁለቱም እንዴት ተደርጐዎች ፍቅር ያዛቸው፡፡
ሚና እና ሀሌሉያ ተፋቀሩ፡፡
ይህ የሚና እና የሀሌሉያ እውነተኛ የፍቅር ታሪክ ነው፡፡
ሚና ፀይም ናት፡፡ ፊቷ ክብ ነው፡፡ ፀጉሯ አጭር ሆኖ ከርዳዳ ነው፤ በደንብ የማይታይ የተፈጥሮ ስስ ከርል አለው፡፡ የአይኖቿ ቅዶች ያምራሉ፤ ከአንደበቷ ይልቅ ብዙ ነገር የምትናገረው በአይኖቿ ነው፤ በአይኖቿ ማድነቅ - መናቅ፣ መቆጣት - ማባበል፣ መጥራት - መግፋት፣ ማቀፍ - መገፍተር፣ ማመስገን - ማንኳሰስ…በአይኖቿ፤ ተራ ስሜቶች አታስተናግድም፡፡ አጭር ናት፤ ግን አያስታውቅባትም፤ የትከሻዋ ቀጥ ማለት፤ የአካሄዷ ስክነት እና ፍሰት ረዥም ያስመስላታል፡፡ የቆዳዋ ቀለም ይገርማል፤ ስም የለውም፤ አንዱ አንዴ “ቀለምሽ…” ብሎ ጀምሮ…ምን እንደሚል ግራ ገብቶት “ቆቅማ ነው፡፡” ብሏታል፡፡ ከዚያ በኋላ “ቆቅማ ቀለም፡፡” ይሏታል፡፡
ሚና ነፃ፣ ግለኛ እና ምክንያታዊ ሰው ናት፤ ያለ ምክንያት የምታደርገው አንድም ነገር የለም፤ ሁሉ ነገሯ በምክንያት እና በእቅድ የተቀነበበ ስለሆነ ሰዎች ይፈሯታል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች የባህሪ ድክመት ያለባቸውን ሰዎች ባያደንቋቸውም ይወዷቸዋል፤ እንደ ሚና አይነቶቹን ፍፁማውያኖች ግን ፈጽሞ አይወዷቸውም፤ ወይ ያከብሯቸዋል ወይ ይፈሯቸዋል፤ ጠና ሲል ይጠሏቸዋል፡፡ ሚናን ብዙዎች ያከብሯታል፤ የሚፈሯትም አሉ፤ የምር የሚጠሏትም ትንሽ አይባሉም፡፡ ሲወቅሷት፤ ሊያሟት ሲጀምሩ፡- “ሠው፤ ሠው አትሸትም…” ብለው ይጀምራሉ፡፡…
ሀሌሉያ ሰው፣ ሰው ይሸታል፡፡ አልኮል ይወዳል፤ የሚጠጣው ከዊንስተን ቸርችል በላይ ነው፡፡ በሲጋራ ይመሰጣል፤ ከሲግመንድ ፍሮይድ በላይ ነው የሚያጨሰው፤ ለማያጨሱ ጓደኞቹ በሲጋራ ጦስ በመጣ ካንሰር የሞተውን የፍሮይድን አባባል ይነግራቸዋል ፡- “ሠው ሳያጨስ እንዴት ላለማጨስ ይወስናል?” ሴቶች ይወዳል፤ ሴቶችም ይወዱታል፤ ሲዘሙት እንደ ንጉስ ሠለሞን ነው፤ አምስት መቶ ሲደመር እቁባቶች አሉት፡፡ አይፈራም፤ እንደ ሄምንግዌይ ወንድ ተኩል ነው፡፡ ሙዚቃ ይወዳል፤ ሲደንስ አለም ሁሉ አብሮት ይደንሳል፡፡
ሚናን ለመጀመሪያ ጊዜ ያያት እሱ በሚያስተምርበት ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለመምህርነት ቅጥር ለቃለ መጠይቅ ቀርባ ነው፡፡ የቅጥር ኮሚቴ ውስጥ ነበረበት፤ ቃለ መጠይቅ ከሚያደርጉ አራት ሰዎች አንዱ እሱ ነበር፡፡ ጥያቄዎቹ ተደጋጋሚ ስለነበሩ እና ተወዳዳሪዎቹም ብዙ ስለነበሩ ሰልችቶት፣ አቋርጦ ሲጋራ ሊያጨስ ወጣ፤ ሲመለስ ሚና እየተጠየቀች ደረሰ፡፡ ስታየው ደነገጠች፤ ሲያያት ደነገጠ፡፡ እርጋታዋ ገርሞታል፤ በጣም ተረጋግታ ነው የምትመልሰው፡፡ ፍርሃትም የለባትም፤ ለመመሰጥም አትሞክርም፤ ትጠየቃለች፤ በእርጋታ ትመልሳለች፡፡
“ሚና ጥያቄዎቻችን አልቀዋል፤ እናመሰግናለን፤ ውጤቱን ደውለን እናሳውቅሻለን፡፡” አለ የኮሚቴው ሰብሳቢ፡፡
“ቆይ፤ ቆይ እኔ አንድ ጥያቄ አለኝ፤ ለሚና፡፡” አለ ሀሌሉያ፡፡
“ጥሩ እንግዲህ፡፡” አለ የቅጥር የኮሚቴው ሰብሳቢ፤ በቅሬታ፡፡
“ሚና?”
“እህ?”
“የወንድ ተማሪሽ የፍቅር ጥያቄ ቢያቀርብልሽ ምን ታደርጊያለሽ?”
ያልተጠበቀ ጥያቄ ነበር፡፡ መገረም እና ፈገግታ ሰፈነ፡፡ ሁሉም የሚናን መልስ እየጠበቁ ነው፡፡ ከረዥም ፀጥታ በኋላ፤
“የወንድ ተማሪዬ የፍቅር ጥያቄ ቢያቀርብልኝ ምን አደርጋለሁ ነው አይደል ጥያቄው?”
“አዎ፡፡” አሉ አራቱም አንድ ላይ፡፡
“በመጀመሪያ ጆሮውን እቆነጥጠዋለሁ፡፡” ሁሉም ሳቁ፡፡
“እሺ ከዛስ?” አላት ሀሌሉያ ሲስቅ ያነባውን እንባ ከአይኑ እየጠረገ፡፡
“ከዚያ ባልቆነጠጥኩት ጆሮው በኩል አርፎ እንዲማር እነግረዋለሁ፡፡” ሳቅ፡፡
አሁን ሚና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ የትምህርት ክፍልን ተቀላቅላ የመምህር ሀሌሉያ የስራ ባልደረባ ሆናለች፡፡ ሚና ስትቀጠር ሀሌሉያ ካቀረበላት አስቂኝ ጥያቄ ወዲህ አውርተው አያውቁም፡፡ ያኔ መጠየቅ የፈለገው ጥያቄ “ተማሪሽ የፍቅር ጥያቄ ቢያቀርብልሽ መልስሽ ምን ይሆናል?” ሳይሆን “የስራ ባልደረባሽ የፍቅር ጥያቄ…” እንደሱም አይደለም፡፡ መጠየቅ የፈለገው “እኔ፣ ሀሌሉያ የፍቅር ጥያቄ ባቀርብልሽ መልስሽ ምን ይሆናል?” ብሎ ነው፡፡ ሁለቱም ተግባብተዋል፤ ሁለቱም ተዋደዋል፡፡
እሷ “ሀሌሉያ የፍቅር ጥያቄ ቢያቀርብልኝ፤ በሀሴት ይህን ጥያቄ ያቀረበውን አፉን ድብን አድርጌ እስመዋለሁ፡፡” ብትለው ነበር ፍላጐቷ፤ ግን - “ጆሮውን እቆነጥጠዋለሁ፡፡” ብላ አሾፈችበት፡፡ የሚገርመው ይህን መልሷን ሲሰማ ሀሌሉያ እየሳቀ በግራ እጁ፤ ቀኝ ጆሮውን ሲያሽ ነበር፡፡ ይህ ፍቅር ይሉት ነገር ሁሌ ይገርማል፡፡ ሁለቱም ልጆች በዚያ ቅጽበት ተዋደዋል፤ በጣም የሚገርመው ደግሞ እንደተዋደዱ ማወቃቸው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በመጀመሪያ እይታ የሚከሰት ፍቅር ጣዕሙም፤ ጥልቀቱም፤ እርቀቱም፣ አንደኛ ነው፡፡ ከመላመድ የሚመጣ ፍቅር፣ ፍቅር አይደለም፤ ኑሮ ነው፡፡
ሚና ሥራ ከጀመረችበት ቀን አንስታ ተስፋ ነበራት፡፡ ይህ ዋዘኛ የስራ ባልደረባዋ አንድ ቀን፣ በቅርብ ቀን ጥያቄውን እንደሚያቀርብላት እርግጠኛ ነበረች፡፡ እንዲያውም መልሷን አዘጋጅታለች፤ ምን እንደምትል ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደምትለውም ተለማምዳለች፤ ግን ብትጠብቅ፤ ብትጠብቅ፤ ብትጠብቅ…ምንም የለም፡፡ ሀሌሉያ ካለችበት አካባቢ ግን ጠፍቶ አያውቅም፡፡ ከእለት፤ እለት እየወደዳት ነው፡፡…እየወደዳት በመጣ ቁጥር፤ ፍርሃቱም እየጨመረ መጣ፡፡ ሠላም እንኳ መባባል ተአምር ሆነበት፤ ሆነባቸው፡፡
የሆነ ቀን እንዲህ ሆኖ ነጋ፡- የሀሌሉያ ቤት በክርክር ጦፏል፡፡
“ብትጠየቅ ምን አባቷ ታመጣለች?”
“ምንም!”
“እና ታዲያ?!”
“መጠየቅ ነዋ!”
“መቼ?!”
“ዛሬውኑ!”
ሀሌሉያ ነው ከራሱ ጋር እየተነታረከ ያለው፡፡ “ምንም”፤ “መጠየቅ ነዋ”፣ “ዛሬውኑ”
የሚሉት መልሶቹ ጠንካሮች አልነበሩም፤ ሲደጋግማቸው ካሰባቸው በላይ ጠነከሩለት፡፡ የዚያን ቀን እንደሚያወራት ወሰነ፡፡
በባህር ዳር ጫፍ አንደኛው ቤት ደግሞ አንዲት ቆቅማ ቀለም ያላት ልጅ ንጋቷን እንዲህ እያሰበች ጀመረች፡፡
“…ለምንም አይደለም የምፈልገው፤ በቃ ጓደኛዬ ቢሆን ምን ችግር አለው? ደግሞም እኔ ለከተማውም፤ ለሥራውም አዲስ ነኝ፤ እሱ አይደለም፤ አንዳንድ ነገሮች ሊረዳኝ ይችላል፤…ሠላም እለዋለሁ…ከዚያ ሻይ ብንጠጣስ? እለዋለሁ…ከዚያ ሻይ እየጠጣን ጐበዝ አስተማሪ እንደሆነ መስማቴን እነግረዋለሁ…አይ እንደሱ አይደለም…እንዴት ነው ታዲያ?...ለማዋራት የሚከብድ ልጅ አይደለም…ታዲያ ለምንድነው እኔን የማያዋራኝ ግን?...ቆይ ሻይ እንጠጣ እለዋለሁ…እንደዚያ ማለት ችግር አለው?...የለውም…ምን ችግር አለው?...ከዚያ ሻይ እየጠጣን ጐበዝ አስተማሪ እንደሆነ መስማቴን እነግረዋለሁ…ከዚያ ለምን ብዙ እንደሚያጨስ፣ ለምን ከሰኞ እስከ ሰኞ እንደሚጠጣ፣ …ለምን፣ ለምን፣…ለምን እንደሚሸረሙጥ እጠይቀዋለሁ…ምን አገባሽ? ቢለኝስ? ይለኛል ደግሞ! ግን ዝሙት ደግሞ ሀጢአት ነው፤ እና የሱ ነፍስ ገሃነም ውስጥ ብትቃጠል ማን ይጠቀማል? ማንም…ስለዚህ …ማናገር አለብኝ፤ ዛሬ አናግረዋለሁ…”
እዚህ ሀሳቧ ጋ ስለሀሌሉያ የሰማችው የማይታመን ነገር ትዝ አላት፡፡ የህግ ትምህርት ክፍል ሀላፊው፤ ዲኑ፤ የአስተዳደር እና የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚደንቶች እና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ተሰብስበው፤ “ባስቸኳይ ትፈለጋለህ…” ብለው ደወሉለት…ሄደ፡፡
“ከሴት ተማሪዎች ጋር ያለህ ቅርበት ጤናማ አይደለም!”
“ጤናማ ነው፡፡” ነገሩ ወዲያው ነው የገባው፡፡ “ደደብ ሁላ” አለ በሀሳቡ፡፡
“በጣም ትቀርባቸዋለህ ነው የሚባለው!”
“ብዙዎቹን እንዲያውም ተኝቼያቸዋለሁ፡፡”
“ምን!?”
“ከወደድኳቸው እና ከፈቀዱኝ ሴት ተማሪዎች ጋር ሁሉ ተኝቻለሁ፡፡”
“ይህ እኮ ለጆሮ የሚከብድ፣ ለጆሮ የሚቀፍ የዲሲፕሊን ጥሰት ነው፡፡”
“አይደለም፡፡”
“ነው !!!!” እያንዳንዱ ቃለ - አጋኖ አራቱን ተሰብሳቢዎች ነው የሚወክለው፡፡
“ቆይ አንድ ጥያቄ አለኝ፤ አንድ መምህር ከሴት ተማሪው ጋር አይተኛ የሚባለው ለምንድነው?”
አሁን ሁሉም ግራ ተጋቡ፡፡ ጥያቄውን አስበውበት አያውቁም፡፡ ጉዳዩን ብዙ ያሰቡበት፣ ጠልቀው የሚያውቁት ይመስላቸው ነበር ግን፤ አሁን ጥያቄውን ይዘው ጭንቅላታቸው ውስጥ መልስ ቢፈልጉ ምንም የለም፡፡
“ቆይ እኔ እነግራችኋለሁ፤ አንድ መምህር ከተማሪው ጋር እንዳይተኛ የሚፈለገው፤ ልጅቷን ሲወዳት እንዳይጠቅማት፣ ሲጠላትም እንዳይጐዳት ነው፤ በትምህርቷ፡፡ አንድ መምህር የወደዳት ተማሪ እሺ ስትለው የማይገቡትን ጥሩ ውጤት ካልሰጣት፤ ወይም እምቢ ስትለው የሚገባትን እስካልነፈጋት ድረስ አስተማሪ ከተማሪው ጋር እንዳይተኛ ሊያሳምን የሚችል ምንም አይነት መከራከሪያ አይኖርም፤ እኔ ደግሞ ሁለቱን፣ ምን ሁለቱን ብቻ ምንም አይነት ስህተት ሳልፈጽም ነው ከወደድኳቸው እና ከፈቀዱኝ ተማሪዎች ጋር የምተኛው፤ ይሄን ሁሉም ያውቃል፡፡”
ይሄን ሁሉም ያውቃሉ፤ አራቱም በየተራ ተያዩ፡፡ ከአራቱ ሶስቱ፣ ማለት ከህግ ትምህርት ክፍል ሃላፊው በቀር ፕሬዚደንቱ እና ሁለቱ ምክትል ፕሬዚደንቶች ያገቡት ተማሪዎቻቸውን ነው፡፡
“አንዴ ውጭ ቆየን፡፡” አለው ፊተ ረዥሙ፣ ጀልጋጋው፣ እና አመዳሙ፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት፡፡
ሀሌሉያ ወጥቶ፣ ሲጋራውን እያጨሰ፣ ጥሏቸው በዚያው ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ሁሉ ነገር በዚሁ አበቃ፡፡
“ለምን ታመነዝራለህ?” ብላ ልትመክረው የከጀለችው ሚና፤ ይህን ስታስብ ተደነቀች፡፡ “ለምን ግን ከሥራው አላባረሩትም እስከዛሬ?” አለች ለራሷ፣ ደስ የሚል ፈገግታ ፊቷ ላይ አብርታ፡፡ “ጉድ የሆነ ሰው ነው!” አለች፤ “ሰይጣን ነው!” አለች አሁንም፤ ሁለመናዋ እየሳቀ፡፡
በዚያን ቀን ሚና፤ ሀሌሉያ ይወድልኛል ብላ ያሰበችውን ልብስ ለብሳ ከቤቷ ወጣች፡፡ ሀሌሉያ፤ ሚና ትወድልኛለች ብሎ ያሰበውን ሙሉ ጥቁር ሱፍ ልብስ እና ነጭ ሸሚዝ በጠዋት ወጥቶ ገዛ፤ ሙሉ ሱፍ ልብስ ኖሮት አያውቅም፡፡ ሚና የምታዘወትረውን ቤት ያውቃል፤ ወደ ስራ ከመሄዷ በፊት ቡናዋን የምትጠጣው ፓፒረስ ሆቴል ነው፤ ከስራ መልስም ቡናዋን እየጠጣች ከቦርሳዋ የማይጠፋውን መጽሐፍ ቅዱስ የምታነበው፣ ከቦርሳዋ የማይጠፋው ማስታወሻ ደብተር ላይ ግጥሞች የምትሞጫጭረው ፓፒረስ ሆቴል ነው፡፡ ሀሌሉያ ቀን ቡናውን፣ ማታ ቢራውን የሚጠጣው ክላሲክ የምትባል ቤት ነው፡፡
እሷም እንደዛተችው፤(“ዛሬማ አናግረዋለሁ…”) እሱም እንደፎከረው ምንም አታመጣም፤ ዛሬውኑ ምን መጠየቅ) እሱ እሷን ፍለጋ ወደ ፓፒረስ ሆቴል ሲሄድ፣ እሷ እሱን ፍለጋ ወደ ክላሲክ ባር ስትሄድ መንገድ ላይ ተገናኙ፤ ጊዮን ሆቴል ጋ ተገናኙ፡፡ ሁለቱም ሁሉ ነገር በግልጽ ታውቋቸዋል፡፡ ፍቅር እንደዚህ ነው፡፡ ሚና፣ ሀሌሉያ እሷን ፍለጋ እየመጣ እንደሆነ አውቃለች፡፡ ሱፍ ለብሶ አይታው አታውቅም፤ “እስኪ አሁን ምን ሱፍ የሚያስለብስ ነገር መጣ?” ሀሌሉያም ሚና እሱን ፍለጋ ወደ ክላሲክ እየመጣች እንደሆነ ገብቶታል፡፡ “ቆይ እስኪ አሁን በአዘቦት ቀን ፀጉር ላይ ጽጌረዳ አድርጐ መዋብ ምን የሚሉት ነገር ነው? ደሞ እንዴት፣ እንዴት ሆና ነው የዘነጠችው?”
ሲገናኙ ምንም አልተፋፈሩም፤ አልተፈራሩም፡፡
“ሀሌሉያ እንዴት ነህ?” አለችው ሚና፡፡
“ታዲያስ ሚና?”
“ሻይ…” አለች እሷ፡፡
“እንጠጣ፡፡” አላት እሱ፡፡
ተያይዘው ጊዮን ሆቴል ገቡ፡፡ ሁለቱም ሻይ አዘዙ፡፡
“ይኸውልህ፣ ያኔ እኔ ለስራ ስወዳደር ከተጠየኳቸው ጥያቄዎች አንተ የጠየከኝ ጥያቄ እስከዛሬ…” አፍራ አቋረጠች፡፡
“እኔም ያኔ፣ አንቺ ለስራ ስትወዳደሪ የጠየኩሽን ጥያቄ ደግሜ ልጠይቅሽ አስቤ፣ አንቺን ፍለጋ ወደ ፓፒረስ እየመጣሁ ነበር፡፡”
“ያኔ የጠየከኝ ጥያቄ ይገርማል፡፡”
“አይገርምም፡፡”
“ማለቴ ደስ ይላል፡፡”
“መልስሽ ምንድን ነው?”
“ጥያቄው ምን ነበር?”
ሁለቱም ሳቁ፤ በቃ ፍቅረኛሞች ሆኑ፡፡
እስከዛሬ ድረስ ሰዎች ይከራከራሉ፡፡ አንዱ ወገን፡- “ታውቃለህ ይኼን እብድ፣ ሰካራም እኮ ለፍቅር የጠየቀችው እሷ ነች፡፡” ይላል፤ ሌላው “ኧረ ባክህ የመጀመሪያ ቀን እሷን ለማናገር ብቻ ብሎ ሱፍ የገዛው እሱ ነው፡፡”
“እሷ ናት የጠየቀችው!”
“እሱ ነው የጠየቃት!”
እስከአሁን ሰዎች ይከራከራሉ፡፡
እየተጫወቱ እያለ፡- (አሁን ሀሌሉያ ቢራ ነው እየጠጣ ያለው፤ ምን ቢሆን ቆንጆ ነው? ሚናም እሱን አይታ ጠጥታ የማታውቀውን ቢራ አዛለች፤ ይገርማል፤ ጠጣችው፤ አልመረራትም፤ ይሄም ይገርማል፡፡)
“ምን አይነት ሴት ነው ግን የምትወደው?” አለች ሚና፤ ሁለተኛውን ቢራ ካጋመሰች በኋላ፡፡
“ሴቶች በሚለው ይስተካከልልኝ፡፡”
“እንዳሉት ይሁን፤ ተስተካክሏል፡፡”
“ሶስት አይነት ሴቶች ነው የምፈልገው፤ አንድ ሚስቴ የምትሆን፣ ድል ባለ ሠርግ የማገባት፣ ብር አምባር ሰበረልዎ የማስብልላት፣ የእናትነት ባህሪ ያላት፣ የልጆቼ እናት የምትሆን፣ ልጆቼን ጡት አጥብታ፣ በስነ - ምግባር አንፃ የምታሳድግ፤ ሽሮ ወጧ ጣት የሚያስቆረጥም፤ ሸሚዜን የምትተኩስልኝ፣ ከረባቴን የምታስርልኝ፣ የቤቴ እመቤት…ይህቺ ዋነኛዋ ናት፡፡ ሁለተኛዋ ሴት አንደኛ ደረጃ ጭንቅላት ያላት መሆን አለባት፤ ኢንተለክቹዋል መሆን አለባት፤ ይኺችኛዋ ፊልም፣ ትያትር፣ ስዕል አብራኝ የምታይ ናት፤ እና አይታ የምታደንቅ፣ የምትተች፣ የምትንቅ ሙዚቃ ሰምታ የምታደንቅ ወይም የምትንቅ፣ በሙዚቃ የምትደንስ፤ ስለ ደስቶይቭስኪ፣ ስለ ክርስቶስ፣ ስለ ክርስቶስ ሰምራ፣ ስለ ሶቅራጦስ፣ ስለ ቡድሃ፣ ስለ ኒቼ፣ ስለ ቶሪዮ፣ ስለ ሮበርት ፒርሲግ፣ ስለ አየን ራንድ…የምታወራኝ…ጂን የሚጠጣ፣ በሲጋራ የምትመሰጥ፣…ሶስተኛዋ የምፈልጋት ሴት ምን አይነት መሰለችሽ ባለጌ የሆነች ሴት፤ አልጋ ላይ ሁሉን የምትሆን፣ የባለጌዎች አለቃ የሆነች፣ አልጋ ላይ ሚስቴን የማልጠይቀውን ሁሉ የምጠይቃት፤ እና ለዚሁ ጉዳይ ብቻ የምንፈላለግ…እ…ለጊዜው ሶስቱን ካገኘሁ ይበቃኛል፡፡”
“እኔ ሶስቱንም አሟላለሁ፡፡” አለች ሚና፤ በችኮለ ግን በእርግጠኝነት፡፡ “እኔ ሶስቱንም መሆን፣ ማሟላት እችላለሁ I am all in one፤ እናት፣ ሀሳቢ፣ እና “ባለጌ” አይደል ያልከው? እኔ ሶስቱንም መሆን እችላለሁ፡፡”
“ለዚያ አይደል እንዴ ታዲያ የወደድኩሽ፡፡”
“እንዴት አወቅህ? ሶስቱንም ሴቶች ማለት እናት፣ ሃሳቢ፣ እና “ባለጌ” መሆን እንደምችል እንዴት አወቅህ?”
“ውቃቢዬ፣ ቆሌዬ፤ ቀልቤ ነገረኝ፡፡”
“ስለ እናት ያልከው…ስለ ሶስቱም ሴቶች ያልከው ደስ ይላል፡፡ ከሁሉም ግን የቷ ትበልጥብሃለች?”
“እናት የሆነችዋ ናታ፤ ብዬሻለሁ እኮ ዋነኛዋ እሷ ናት፡፡”
“ለምን”
“አንዴ አንዲት ሴት ሳደንቅ ምን እንዳልኩ ታውቂያለሽ? ልንገርሽ፤ “የልጆቼን ነፍስ በእሷ እጅ አምናለሁ” አልኩ፡፡ እንዲህ ያስባለችኝ ሴት የጓደኛዬ ሚስት ባትሆን ኖሮ ልወዳት ምንም ጉዳይ ነበርኩ፡፡”
“እኔ ስለራሴ ሰው ጠይቄ አላውቅም፤ አንተ ግን ስለ እኔ ስለምታስበው እጨነቃለሁ፤ ማወቅ እፈልጋለሁ፤ በጣም ስለወደድኩህ ይመስለኛል፡፡ እንዳትታዘበኝ፤ ምን አይነት ሰው አድርገህ ነው የምታስበኝ?”
“እሚገርምሽ እኔም ስለ እራሴ ተመሳሳይ ጥያቄ ልጠይቅሽ ነበር፡፡ ጥያቄውን ካነሳሽ አይቀር ልንገርሽ፤ አንቺ አብርሃም ነሽ፡፡”
“ምን?!” ግራ ተጋብታለች፡፡
“ይህን ነገር አታውቂም?”
“ምኑን?!”
“ይኼውልሽ ሰዎችን ሁሉ በባህሪ ብንከፍላቸው በአራት ምድብ ይወድቃሉ፤ ወይ አብርሃም ወይ ሙሴ ወይ ጳውሎስ ወይ ጴጥሮስ ናቸው፡፡ የጥንት ምድብ ነው፡፡ ሄፓክራተስ ነው በመጀመሪያ ምድቡን ያወጣው፡፡ ሳይኪያትሪስቶች ለህክምና፣ ፀሐፊዎች ለገፀ ባህሪ ቀረፃ የሚጠቀሙበት የባህሪ ጐራ ድልድል ነው፡፡”
እንዲህ ብሉይ የሆነ የባህሪ ምድብ አለማወቋ አናዷታል፡፡
“ሄፓክራተስ ከክርስቶስ ልደት በፊት አይደል የኖረው? ስለጴጥሮስ እና ጳውሎስ ምን ያውቃል?” አለች አለማወቋ ያላናደዳት እየመሰለች፡፡
“አይ እሱ ባህሪያቱን የከፋፈለው phlegmatic, melancholic, choleric እና sanguine ብሎ ነው፤ በጥቅሉ The four Temperaments ነው የሚባሉት፤ በኋላ የመጡ አዋቂዎች ብዙዎች በቀላሉ እንዲረዱዋቸው ብለው አብርሃም፣ ሙሴ፣ ጳውሎስ እና ጴጥሮስ ብለው ከፋፈሏቸው፤ እንደ የባህሪው ዝርዝር አይነት፡፡”
“አብርሃም ቁጥብ፣ ጥንቁቅ፣ ሃሳብ የሚያዘውትር፣ ሠላማዊ፣ ራሱን የሚገዛ፣ እምነት የሚጣልበት፣ ባህሪው የማይዋዥቅ እና ጭምት ነው፡፡”
ፊቷ ፈካ፡፡
“እኔም ይሁን ሁሉ ነኝ?!”
“በተጨማሪም ውብ ነሽ፡፡”
ልትስመው ከጅላለች፤ ሊስማት ፈልጓል፡፡ ሁለቱም አፈሩ፡፡
“አንተስ ማነህ? አብርሃም፣ ሙሴ፣ ጳውሎስ ወይስ ጴጥሮስ?”
“ገምቺ፡፡”
“እምቢየው፣ እራስህ ንገረኝ!”
“የኔ ለየት ይላል፤ እኔ የሙሴ እና የጳውሎስ ቅይጥ ነኝ፤ እኔ እንደ ሙሴ ጭንቀታም ነኝ፤ አይታወቅብኝም እንጂ ጭንቀታም ነኝ፤ እናም የሚገርምሽ አሁንም አይታወቅብኝም እንጂ እንደ ሙሴ ግትር እና ጨለምተኛ ነኝ፤ እነዚህ የማይታወቁ ድብቅ ባህሪያቶቼ ናቸው፡፡
በተረፈ እንደ ጳውሎስ ስሜታዊ፣ እረፍት የለሽ፣ ሀይለኛ፣ በቀልቤ የምመራ፣ ቀልጣፋ እና ንቁ ነኝ፡፡ … እንደ አንቺ የአብርሃም አይነት ባህሪያት ያሉዋቸው ሰዎች ወይም አብርሃሞች ጥሩ ሀኪሞች፣ የማይረቱ ጠብቆች፣ የሚደመጡ ሸምጋዮች እና ዲፕሎማቶች፣ ምርጥ ፀሀፍት፣ ወደር የሌላቸው መምህራን፣ ይሆናሉ፤ በጣም ይገርማል፤ የአንቺን አሁን ተመልከቺ፤ የተማርሽው ህግ፣ የመረጥሽው ሙያ ደግሞ መምህርነት ነው፤ ትምህርትሽን በጥሩ ውጤት ነው ያጠናቀቅሽው፤ አሪፍ መምህር እንደምትሆኚ ደግሞ አልጠራጠርም”
“አመሰግናለሁ፤ ትገርማለህ፤ እራስህንም ሠዎችንም በደንብ ታውቃለህ”
“ይኼውልሽ ለኔ የሰው ዘር የተረገመው ቀፋፊው እርግማን ጥረህ፣ ግረህ፣ በላብህ ወዝ ኑር የሚለው ሳይሆን ጥረህ ግረህ እራስህን ፈልገህ እጣ ይመስለኛል፡፡” ሁለቱም በቀልዱ ሳቁ፡፡
የዚያን ቀን የጊዮን ውሎአቸው ይኸው ነበር፡፡
ፍቅር አሀዱ ተባለ፡፡
(ይቀጥላል)

Read 26247 times