Saturday, 27 July 2013 14:12

በሴቶች ፀጉር ላይ የተጠበቡት የ75 ዓመት አዛውንት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(6 votes)

የዛሬ 76 ዓመት በአድዋ አውራጃ የሃ በተባለ አካባቢ ነው የተወለዱት፡፡ እድሜያቸው እርፍ ጨብጦ ማረስ እስኪያስችላቸው ድረስ ከብቶች እየጠበቁ ነው ያደጉት፡፡ “እረኛ ነበርኩ” ይላሉ፡፡ ከዚህ በኋላ እድሜያቸው 23 ዓመት እስኪሆን ድረስ የተዋጣላቸው ገበሬ ሆነው ቤተሰባቸውን አገልግለዋል፡፡ ከዚያ በኋላ አዲስ አበባ የገቡት አቶ ገብረክርስቶስ ታረቀኝ፤ (ጋሽ ገብሬ) እንዴት አዲስ አበባ እንደመጡ፣ ወደ ውበት ባለሙያነት እንዴት እንደገቡ፣ በውበት ስራ ዘመናቸው ስላሳለፏቸው አስገራሚ ገጠመኞች፣ ስለትዳር ህይወታቸው እና በመሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡


ራስዎን ያስተዋውቁ
የሚያውቁኝ ሰዎች በአቋራጭ ገብሬ ብለው ነው የሚጠሩኝ፡፡ ደንበኛ ስሜ ግን ገብረክስርቶስ ታረቀኝ ነው የሚባለው፡፡ የተወለድኩት አድዋ አውራጃ፣ የሃ የተባለ ቦታ ነው፡፡
አሁን እድሜዎት ስንት ደረሰ?
ሰባ አምስተኛዬን ጨርሼ 76ኛ አመቴን ጀምሬአለሁ።
አዲስ አበባ ከመምጣትዎት በፊት ስለነበረው የልጅነት ጊዜዎ ያጫውቱኝ …
አስተዳደጌ እንግዲህ እድሜዬ ደርሶ እርፍ እስከምጨብጥ ድረስ የከብትና የፍየል እረኛ ነበርኩ፡፡ እድሜዬ ከፍ ሲል የቤተሰቤን መሬት እያረስኩ፣ ጥሩ ገበሬ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡
ለቤተሰብዎ ስንተኛ ልጅ ነዎት?
ሶስተኛ ልጅ ነኝ፤ ሁለት ታላላቆች አሉኝ፡፡ በቤታችን አምስት ሴትና ሰባት ወንዶች ነበርን፤ አሁን ከሰባቱ ወንዶች ሌሎቹ ሞተው እኔ ብቻ ነኝ የቀረሁት፡፡
እንዴትና እና ለምን አዲስ አበባ መጡ?
አዲስ አበባ የመጣሁበት ምክንያት የሚገርምም የሚያስቅም ነው፡፡ ምን መሰለሽ… በእኛ አገር ለጋብቻ ግንቦት ወር ተመራጭ አይደለም፡፡ ተመራጭ ወር ጥር ነው፡፡ በዛን ወቅት አባቴ አቶ ታረቀኝ ሀብታም ገበሬ ናቸው፡፡ አንዲት ልጅ ነበረች፤ ለጋብቻ ሶስት ቤተሰብ ይጠይቃታል…
ሶስት ቤተሰብ ጠየቃት ሲሉ እንዴት ነው?
በእኛ ጊዜ ለልጁ ሚስት የሚጠይቀው ቤተሰብ ነው፡፡ ለዚህች ልጅ የእኔን ቤተሰብ ጨምሮ ሶስት ቤተሰብ ሽማግሌ ላኩ፡፡ ከዚያም ከሶስቱ ቤተሰብ ለእኔ ቤተሰብ ተፈቅዶ፣ የእኔ ሚስት እንድትሆን ለቤተሰቤ ምላሽ ሰጡ ማለት ነው፡፡ አሁን ግንቦት ወር ላይ ቤታችን ውስጥ ጠላ ይጠመቃል፡፡ ከዚያ የአጎቴን ሚስት “ለምን ይህ ሁሉ ጠላ ይጠመቃል ስላት እጮኛህ እዚህ መጥታ ትከርምና ሰርግህ በሚመጣው አመት ነው የሚሆነው አለችኝ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ጠፍቼ ለመምጣቴ ምክንያቱ ይሄ ነው፡፡
ሚስት ማግባቱን ጠልተው ነው ወይስ?
እንደነገርኩሽ በእኛ አገር ደንበኛ የሰርግ ወቅት ጥር ወር ነው፤ እኔ ደግሞ አግባ የተባልኩት በግንቦት ነው፤ ለሰርግ ጥሩ የሚባል ወር አይደለም፡፡ እናም ጓደኞቼ በጥር እያገቡ የጫጉላ ጊዜያቸውን በደንብ ሲያሳልፉ፣ እኔ በግንቦት አላገባም ብዬ ነው ጠፍቼ የመጣሁት፡፡ እኛ አገር ጫጉላ ቤት በጣም የሚከበርና የሚወደድ ስርዓት ስለሆነ፣ ያ ነገር በሌለበት አላገባም የሚል አቋም ነበረኝ፡፡ በቃ ጠፍቼ እዚህ መጣሁ፡፡
ታዲያ የተደገሰው ድግስ እንዴት ሆነ?
እኔ ምን አውቄ የራሳቸው ጉዳይ ነው፡፡
አዲስ አበባ ሲመጡ ዕድሜዎት ስንት ነበር?
ያኔ እድሜዬ 23 ነው፡፡ በ1950 ዓ.ም ነው አስታውሳለሁ፡፡
እዚህ መጥተው ማን ጋ አረፉ? ቤተሰብ ነበርዎት?
አመጣጤ ወንድሜ ጋር ነው፤ ወንድም ነበረኝ - ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ፡፡ ሀይለማርያም ታረቀኝ ይባላል፤ መምህር ነበር፡፡ እርሱ ጋ ትንሽ ጊዜ ተቀምጬ ስራ ፈልጌ ገባሁ፡፡ ለምን ብትይ እሱ ብዙ ቤተሰብ ስለነበረው፤ እኔን ጨምሮ ማስተዳደር ከባድ ነበር፡፡
ምን አይነት ስራ አገኙ?
ሰው ቤት ነው የተቀጠርኩት፤ ልብስ ማጠብ፣ ሸሚዝ መተኮስ እሰራ ነበር፤ ትልቅ ቤት ነው፡፡ እዚያ ቤት ሆኜ በጥሩ ሁኔታ የወጥ ቤት ስራ ተምሬ፣ አንድ አምስት አመት ከሰራሁ በኋላ ጋራዥ ቤት ስራ ገባሁ፡፡ ጋራዥ እየሰራሁ እያለ አንዲት ዘመዴ ታመመችና ደብረሊባኖስ ጠበል ይዣት ሄድኩኝ፡፡ አንድ ወር ተኩል ጠበል ቆይተን ስንመለስ፣ ከጋራዥ ሳላስፈቅድ ስለሄድኩኝ ወደ ስራዬ መመለስ አልቻልኩም፡፡ ወሩ የካቲት ስለነበር ከዚያን ጀምሮ ለአራት ወር ስራ አጣሁ፡፡ በወቅቱ የሚረዳኝ አልነበረም፤ ወንድሞቼም ራሱን ችሏል በሚል ትተውኝ ነበር፡፡ ክረምቱ እየመጣ ስለነበር የምበላው የምጠጣው አልነበረም፡፡ ከዚያ ደጃች ውቤ ሰፈር ሲስተር ሚዛን የሚባሉ የሴት ፀጉር ቤት ነበራቸው፡፡ እዛ ገባሁ፡፡
እንደሰማሁት ሲስተር ሚዛን ፀጉር ቤት ሊገቡ የቻሉት፤ ዝናብ ለመጠለል የተደገፉት በር ድንገት ተከፍቶ ወደ ፀጉር ቤቱ በመግባትዎ በዚያው እንደቀሩ ነው?
ሲስተር ሚዛን ከዚያ በፊት የሚያውቁኝ ሰው ቤት ተቀጥሬ ስሰራ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ረጅም ጊዜ አላዩኝም ነበር፡፡ እንዳልሽው ሀይለኛ ዝናብ ዘነበና፣ ፀጉር ቤቱ በር ላይ ለመጠለል ስጠጋው በሩ ወደ ውስጥ ተከፈተና ሳላስበው ገባሁ፡፡ ሲስተር ሚዛን ሲያዩኝ “ታረቀኝ አለህ እንዴ” ብለው በአባቴ ስም ጠሩኝ፡፡ “ከየት መጣህ” አሉኝ “ስራ የለህም እንዴ” ብለው ጠየቁኝ “የለኝም” አልኳቸው፡፡ “የለኝም” ስላቸው ግን ሌላ ቦታ ስራ የሚያስገቡኝ መስሎኝ ነው፡፡ “ቶሎ በሉ ሻይ ዳቦ አምጡለት” ብለው ለሰራተኞቹ ትዕዛዝ ሰጡና “አሁን እኛ ጋ ክረምና ባይሆን መስከረም ሲመጣ ስራ ፈልገህ ትወጣለህ” አሉኝ፤ ይህ የሆነው ሰኔ ላይ ነው፡፡ ሰኔና ሃምሌ፣ ነሀሴ እዚያው እየተላላኩ እያየሁ እየተማርኩ ቆየሁ፡፡ በወር 40 ብር ይከፈለኝ ነበር፡፡ ጳጉሜ ሲሆን ሠራተኞች እድገትና የተሻለ ደሞዝ እያገኙ ከአንዱ ወደ ሌላው ፀጉር ቤት ይሄዳሉ፡፡ የሲስተር ሚዛንም ሰራተኛ ሄደና በበዓሉ ባዶ ቀሩ፡፡ “አንተ ትችላለህ?” አሉኝ፤ “አዎ” አልኳቸው፡፡ ክረምቱን ስመለከት በከረምኩት መሰረት፣ ለቅዱስ ዮሐንስ በዓል የሚሰራውን ስራ ቀጥ አድርጌ ስሰራ ዋልኩኝ፡፡
ከዚያን ቀን በፊት ትንሽ ልምምድ አድርገው ነበር፤ ወይስ በመመልከት ብቻ?
እንዲህ ነክቼ አላውቅም ግን አትኩሬ እመለከት ነበር እንዴት ይሄ ያቅተኛል እያልኩ በጥንቃቄ እከታተል ነበር፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ ደሞዜ ከ40 ብር ወደ 90 ብር አደገና መስራት ጀመርኩ፡፡ ይሄው 45 ዓመት ሙሉ በዚሁ ስራ ላይ አለሁ፡፡ ይህ እንግዲህ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑ ነው፡፡
ሲስተር ሚዛን ፀጉር ቤት ስንት ዓመት ሰሩ?
ሲስተር ሚዛን ቤት አንድ አምስት አመት የቆየሁ ይመስለኛል፡፡ አሁን ያለሁበት ፀጉር ቤት በ1965 ዓ.ምአካባቢ ነው የመጣሁት፡፡
ከሲስተር ሚዛን ፀጉር ቤት የወጡት በአሁኗ የትዳር አጋርዎ በወይዘሮ ለገሠች ምክንያት ተጣልተው እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው?
እውነት ነው፤ በወቅቱ ወ/ሮ ሚዛን በጣም ሲያመነጭቋት መታገስ አልቻልኩም፤ ጥፋትም ካጠፋች መመከር ነው ያለባት፤ ልጅቱ ገና የ18 ዓመት ልጅ ነበረች፡፡ እንደዚያ ከፍ ዝቅ ሲያደርጓት ለምን ደሀዋን እንዲህ ያደርጓታል በሚል ተጋጨንና ለቅቄ ወጣሁ፡፡ እርግጥ ወ/ሮ ሚዛን የዋህ ሠው ናቸው፤ ግን አፋቸው ሰው ያስቀይማል፡፡ ካልመታኋት ሲሉ “አይችሉም” አልኳቸው፤ ተጣላን፡፡
በወቅቱ የፍቅር ግንኙነት ጀምራችሁ ነበር እንዴ?
አዎ ሌሎች ሰዎች አያውቁም እንጂ እኛ ጀምረናል፡፡ እሷ ቤት ተከራይታ ስለነበር አብዛኛውን ጊዜ አብረን ነበር የምናድረው፡፡
የፀጉር ስራ በጀመሩበት ዘመን ወንዶች የሴት ፀጉር ሲሰሩ አልተለመደም፡፡ ይሄስ ተጽእኖ አላሳደረዎትም?
በስራዬ ላይ ተጽእኖ ባያሳድርብኝም እኔ ግን የሴት ስራ ሰራሁ ብዬ የበታችነት
ይሰማኝ ነበር፡፡ “ለምንድን ነው እዚህ ስራ ውስጥ የገባሁት” ስልም አማርር ነበር፡፡ ሃይለማሪያም ያልኩሽ ወንድሜ ግን ገና አሁን ጥሩ ሙያ ጀመርክ ብሎ አጽናናኝ፡፡ እርግጥ እኔ የበታችነት ይሰማኛል ብዬ አልነገርኩትም፡፡ እርሱ ግን “ጥሩ ነው፤ በርታ ወደፊት ይጠቅምሀል” ብሎ አበረታታኝ፤ ትንሽ ቀለል እያለኝ መጣ፡፡
ከ40 ዓመት በላይ በዚህ ሙያ ላይ ሲያሳልፉ በርካታ ገጠመኞች ይኖሩዎታል፡፡ እስቲ ገጠመኝዎን ያካፍሉኝ… በተለይ የሚስቴን ፀጉር አሳጥረህ ቆረጥክ ብሎ ሽጉጥ የመዘዘ ደጃዝማች እንደነበረም ሰምቻለሁ…
ሰውየው ደጃዝማች ናቸው፡፡ ልጅቷ ዋግሹም ከተባለ ቦታ ከወሎ ነው ያመጧት፡፡ በጣም ቆንጆ ናት፡፡ ከእነ አሽከራቸው ይዘዋት መጡ፡፡ “አንተ ነህ ፀጉር ሰሪው” ሲሉኝ፣ አዎ አልኩኝ፡፡ “የኔ ጌታ እባክህ ልዕልት ተናኘ ወርቅ ቤት ግብዣ ይዣት ስለምሄድ ቆንጆ ከተሜ አድርገህ ስራልኝ አሉኝ፡፡ ልጅቷ ገና የ18 እና የ20 ዓመት ብትሆን ነው፤ በጣም ልጅ ናት፡፡ ሰውየው ደግሞ እኔ አሁን ባለሁበት እድሜ ይሆናሉ፡፡ በደንብ አድርገህ ስራልኝ” ስላሉኝ፣ ደክሜ ጥሩ አድርጌ ሰራኋት፡፡ እንደምታውቂው በካውያ ስጠቀልለው አጠረ፡፡ ካፊያ ስለነበር እንዳይበላሽ ከስር ሻሽ ከ
ላይ ላስቲክ አድርጌ፣ የአሽከሩን ካኪ ካፖርት ከላይ ደርቤ ከአሽከርዬወ ጋር ሰደድኩላቸው፡፡ ከግማሽ ሰዓት በኋላ መጡና መኪናቸውን ገጭ አድርገው ሲያቆሙ ጊዜ፣ ምንድነው ብዬ ሳይ፣ ሰውየው ሽጉጥ አውጥተው ሲያቀባብሉ አየኋቸው፡፡ በቃ ይሄ ሰውዬ ሊገድሉኝ ነው ብዬ ተናግሬ ሳልጨርስ፤ በሩን በሀይል ኳ ኳ ኳ…አደረጉት፡፡
እዚያው ቆመው ጠበቁ ወይስ ሸሹ?
ሞኝሽን ፈልጊ! እንዴት ቆሜ እጠብቃለሁ፡፡ በመስኮት ዘልዬ ከወጣሁ በኋላ በሩን ከፈቱላቸው፡፡ ፀጉር ቤቱ (የሲስተር ሚዛን ፀጉር ቤት ማለቴ ነው) ከሳሎኑ ጋር ስድስት ክፍል ነው፡፡ ሁሉም ክፍል ውስጥ ፈልገው ፈልገው ሲያጡኝ “ደሙን ደመ-ከልብ ነው የማደርገው ይጠብቅ፡፡ እኔ ፀጉሯን አሳምረህ ስራልኝ አልኩ እንጂ እንዲህ ቆራጠህ ጣል አልኩት እንዴ” ሲሉ አንዲት ህይወት የምትባል ልጅ ነበረች፡፡ “ይሄው ወደ ውስጥ ተጠቅልሎ እንጂ አልተቆረጠም እኮ” ብላ አስረዳችልኝና ሰውየው ተነስተው ሄዱ እልሻለሁ፡፡
ሌላ ገጠመኝ…
አንድ ጊዜ ደግሞ ሌላ ያሳቀኝ ገጠመኝ ነበር፡፡ አንድ ኩመላ የሚባል ጓደኛዬ ነበር፤ ገና ፀጉር ቤት እንደተቀጠረ ነው ነገሩ የተከሰተው፡፡ እኔ እና እርሱ ጐን ለጐን እየሰራን ነው፡፡ እርሱ የሚሠራቸውን ሴት “ምን አይነት ልስራልዎት” ይላቸዋል፡፡ “ዞረህ እቀፈኝ” ይሉታል፡፡ በጣም ደነገጠ፤ እርሱ ገና አዲስ ስለሆነ አልገባውም፤ “ዞረህ እቀፈኝ” አንዱ የፀጉር ስታይል ነው በወቅቱ “ምን አሉኝ እመቤቴ” ይላቸዋል ደንግጦ “ጆሮህ አይሰማም ዞረህ እቀፈኝ አልኩህ እኮ” ይሉታል፡፡ “ዞረህ እቀፈኝ” የሚባለው የፀጉር ስታይል ሶስት ስም አለው… አንዱ ሽኞ ይባላል ሁለተኛው ዞረህ እቀፈኝ ይባላል፣ ሶስተኛው “ብኩል” ይባላል፡፡ “ዞረህ እቀፈኝ” የተባለው ፀጉሩ እርስ በእርሱ ስለሚተቃቀፍ ነው፡፡
በመጨረሻ ከድንጋጤው ሳይወጣ ጆሯቸው ላይ ተለጥፎ “ምናሉኝ እመቤቴ” ሲላቸው ተናደው ከመቀመጫቸው ብድግ አሉና “ዞረህ እቀፈኝ፤ አበጥርልኝ ነው የምልህ” ብለው ጮሁበት፡፡ እርሱ እቀፈኝ ያሉት መስሎት ደነገጠና መስራት ሲያቅተው፣ እኔ ተቀብዬ ለሴትዮዋ የሚፈልጉትን ሰራሁላቸው፡፡
“ዞረህ እቀፈኝ” ሲሉት ዞሮ ግጥም አድርጐ አለማቀፉም አንድ ነገር ነው …
እንዴ ምን ነካሽ! አድርጐት ቢሆንማ ስንት መዘዝ ይመጣ ነበር፡፡ የሰው ሰው ዝም ብሎ ማቀፍ አለ እንዴ?
ሙሽራ ሞሽሩ ተብለው ተጠርተው አንድ ብስጭት ገጥሞዎት ነበር ይባላል፡፡ እስኪ ይንገሩኝ…
አንድ ጊዜ ሙሽራ ፈሽንልን ተብዬ ተጠርቼ ሄድኩኝ፡፡ ስሄድ መኝታ ቤቱን ሚዜዎቿና ሌሎች ሴቶች ሞልተውታል፡፡ እኔ ልሠራ ጀመር ሳደርግ፣ አንዷ ተነስታ “እንደዚህ አይደለም፤ እንዲህ እንዲህ አድርገህ ስራ” አለች፡፡ እሺ ብዬ የተባለውን ስጀምር ሌላዋ ተነስታ ሌላ ትላለች፡፡ አንዷም ተነስታ ሌላ አይነት ስራት ትላለች፡፡ ይሄን ጊዜ ናላዬ ዞረ፤ ከዚያ ልብሴን ለበስኩና መሳሪያዬን ሸክፌ “በቃ እናንተ ስሩላት” ብዬ ብድግ ልሄድ ስል፣ ያ ሁሉ ሴት ጉልበቴ ላይ ወደቀ፡፡ ከዚያ “ሁላችሁም ውጡና ልስራት፤ በዚህ ካልተስማማችሁ ተውት” አልኳቸው፡፡ ከዚያ በተረጋጋ መንፈስ ጥሩ አድርጌ ሰራሁ፡፡ በጣም ተደሰተች፤ እነሱም ይቅርታ ጠየቁኝ፤ አመሰገኑኝ፡፡
በአንድ ወቅት እርስዎና ኩመላ የተባለው ጓደኛዎ “ሻለቃና ሀምሳ አለቃ ነን” እያላችሁ ተነቅቶባችኋል ይባላል፡፡ እውነት ነው?
ምን መሰለሽ... እሱን ጉድ ያመጣብኝ ኩመላ ነው፡፡ ጃንሆይ ወርደው ደርግ የገባ ሠሞን ዜና ለመስማት ቴሌቪዥን ያለበት መጠጥ ቤት ጐራ እንል ነበር፡፡ ያኔ ሁሉም ቤት ቴሌቪዥን አልነበረም፡፡ ታዲያ አንድ ጊዜ የሆነ ቢራ ቤት ገባንና ዜና ስንመለከት፣ ሁለት ዘናጭ ዘናጭ ሰዎች ተዋወቅን፡፡ አሁን ኩመላ ምን ይላል… እኔን ሲያስተዋውቃቸው “ሻለቃ ገብሬ ይባላል፤ እኔ ደግሞ ሃምሳ አለቃ ኩመላ እባላለሁ፤ ህዝብ ደህንነት ቢሮ ነው የምንሠራው” ይላቸዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከነዚህ ሰዎች ጋር ጓደኛሞች ሆንን፡፡ እነዚህ ሰዎች በወቅቱ ሲቪል አቪዬሽን የሚሠሩ የተማሩ ሰዎች ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ በየመጠጥ ቤቱ ስንገናኝ “ኖር ሻለቃ” ብለው ተነስተው ነው የሚቀበሉን፡፡ አንዳንዴ በእንግሊዝኛ ሲያዋሩን፣ እኛ ምንም ስለማናውቅ እንደ ደንቆሮ እም ….እም…እም እንላለን፡፡ ኩመላ ምንም አልተማረም፤ እኔ ገና ከገጠር እንደመጣሁ ሰው ቤት እየሠራሁ፣ ማታ ማታ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምሬያለሁ፤ ቢሆንም እነዚህ ሰዎች የሚያወሩትን እንግሊዝኛ መቋቋም አንችልም ነበር፡፡
ታዲያ እንዴት ተነቃባችሁ?
ወይ ጉድ! የዛን ቀን መሬት ተከፍታ ብትውጠኝ ደስ ባለኝ፡፡ ቀኑ እሁድ ነው፤ ጠዋት ስራ ገብተን እስከ ስድስት ሰራንና ወጣን፡፡ ያን ጊዜ እሁድ ከሰዓት በኋላ አንሰራም ነበር፡፡ አሁን እንዝናና ብለን በሲኒማ አምፒር በታች በኩል ወደ አንድ መጠጥ ቤት ስንገባ፣ ጓደኞቻችን ሽክ ብለው ለብሠው ቢራ ይጠጣሉ፡፡ ልክ ስንገባ “እንዴ! ሻለቃ መጣችሁ” ብለው ተቀብለው አስቀመጡን፤ ካልጋበዝናችሁ ብለው እምቢ አሉ፤ ምን እናድርግ አልንና ቢራ አዘዝን፡፡ ገና ቢራው እንደተከፈተ አንዲት ሂሩት የምትባል ደንበኛዬ ከየት እንደመጣች አላውቅም፤ ብቻ እዛ መጠጥ ቤት ተከሠተች፡፡ የረጅም ጊዜ ደንበኛዬ ናት፤ ልክ ስታየኝ “ገብርዬ እንዴት ነህ፤ የዛን ቀን እኮ ፀጉሬን በደንብ አልሠራኸኝም” ለምን እንደሆነ አላውቅም ቶሎ ተበላሸ ስትል ሁላችንም ደነገጥን፡፡ ከዚያ እኔ ወዲያውኑ ሽንት ቤት አለ ብዬ በጓሮ በር ወጥቼ ጠፋሁ፡፡ ኩመላ ግን እዛው ቁጭ ብሎ ቢራውን ጨረሠ፡፡ ይህን ሁሉ ውርደት ያመጣብኝ እርሱ ነው፡፡ በኋላ ስንገናኝ አንተ ነህ ይህን ቅሌት ያመጣኸው ብዬ ተጨቃጨቅን በቃ አለፈ፡፡
እስከ ዛሬ ምን ያህል ሙሽሮች ሞሽረው ድረዋል?
በቁጥር ይህን ያህል ነው ለማለት እቸገራለሁ፡፡ በርካታ ሙሽሮሽችን ሞሽሬያለሁ፤ ከመቶ እና ከ200 በላይ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ በስራዬ በጣም ተወዳጅ ነበርኩኝ፡፡ ነፍሳቸውን ይማረውና የዚህ ፀጉር ቤት ባለቤት ወ/ሮ ብርሀኔ፣ ስራ ስለሚበዛብኝ በእጃቸው ነበር የሚያጐርሱኝ፡፡
አሁን 76ኛ አመትዎ ነው፡፡ በጣም ጤነኛና ጠንካራ ነዎት፡፡ የጥርስዎ፣ የፀጉርዎና የጋውንዎ ንጣት እኩል ነው፡፡ አሁንም በጥንካሬ ውበትን እየተጠበቡበት ይገኛሉ፡፡ የጤንነትዎ ምስጢር ምንድን ነው?
እኔ የጤንነቴ ምስጢር እግዚአብሔር ነው፡፡ ምግብ የሚከለክለኝ ነገር የለም፡፡ ግን አትክልትና ፍራፍሬ አዘወትራለሁ፣ ወተት እጠጣለሁ፣ በእግሬ በጣም እጓዛለሁ፡፡ ምግብ ላይ አትክልቱን ከእንጀራ ጋር ነው የምመገበው፡፡ ስጋ አልፎ አልፎ ካልሆነ አላዘወትርም፤ መጠጥ በዞረበት አልዞርም፤ ሳቅና ጨዋታ እወዳለሁ፤ እዚህ ፀጉር ሊሠሩ የሚመጡ ሴቶች ሳይስቁና ሳይዝናኑ አይወጡም፡፡ ማታም ይምጡ ጠዋት “Good morning” እላቸዋለሁ፡፡ በዚህ በዚህ ጤንነቴ ጥሩ ነው፤ አልፎ አልፎ ትንሽ ደም ግፊት አለኝ፤ በመድሀኒት እየተቆጣጠርኩት ነው፤ አይኔ ደህና ነው፤ መነፅር ግን አደርጋለሁ፤ ሌላ ችግር የለብኝም፡፡
ለብዙ ጊዜ ደጃች ውቤ ሠፈር ኖረዋል፡፡ የሲስተር ሚዛን ፀጉር ቤትም ደጃች ውቤ ሠፈር ነበር ይባላል፡፡ የደጃች ውቤን ጭፈራ ቤቶች ጐብኝተው ያውቃሉ?
እኔ በህይወቴ ደጃች ውቤ ጭፈራ ቤት የገባሁት አንድ ቀን ነው፡፡ ከዚያ በፊት አንድ ገጠመኝ ላውራሽ፡፡ የዛን ቀን ስሠራ ዋልኩና አንድ ልጅ ነበረች፤ ባል አላት፤ ባሏ ጉራው መከራ ነው፡፡ “እንዲህ አድርጌ፣ እከሌን ደብድቤ…” ብቻ የማይለው የማይቀባጥረው ነገር የለም፡፡ ሹፌር ነው፡፡ አንድ አርብ ቀን እኔ፣ እሱ፣ ሚስቱም፣ አንድ ከባላገር የመጣ ሠውም አለ፡፡ አብረን እየሄድን እያለ፣ መንገድ ላይ የሆኑ ብዙ ወንዶች ሚስቱን እንቅ ሲያደርጓት፣ ባሏ ሸሽቶ ጥሏት ሄደ፡፡ እኔ እንዴት ሴት ልጅ ለጐረምሳ ትቼ ብዬ ከነሱ ጋር ትንቅንቅ ጀመርኩ፡፡ በወቅቱ የደጃች ውቤ ሠፈር ጐረምሶች አትንኩኝ ባይ ነበሩ፡፡ እኔን ለሶስት ሆነው ያዙኝና ጣሉኝ ክንዴን መቱኝ፡፡ እርሷ “ኧረ ገደሉት” እያለች፣ ትጮህ ነበር፤ ባሏ ግን ቤቱ ሄዶ “ያዙኝ ልቀቁኝ” ይላል፡፡ በጣም የተናደድኩበት ጊዜ ነው ያ ቀን፡፡ “አንተ ጉረኛ፤ የኔ ሚስት መሠለችህ እንዴ” ብዬ ተጣላን፡፡ ደጃች ውቤ ውስጥ አንዴ ጭፈራ ቤት ገባሁ ያልኩሽ፣ አንድ ጓደኛዬ ከተኛሁበት ቀሰቀሠኝ፡፡ እኔ፣ ወንድሜና አንድ ጓደኛችን ነበር፡፡ አቤል ስዩም ይባላል፡፡ ጓደኛዬ የደጃች ውቤ ቤተሠብ ነው፡፡ ሩብ የአዲስ አበባ መሬት የእርሱ ነው፡፡ ዛሬ 40ሺህ ይሸጣል፤ ነገ 30ሺህ ይሸጣል፡፡ ብር እንደ አፈር ነበር፡፡ አሁን ያን ጊዜ ማታ ጠጥቶ መጥቶ “ና ተነስ” ብሎ ቀሰቀሰኝ፤ እሺ አልኩና ከወንድሜና ከጓደኛችን ጋር ተነስተን፣ አሰገደች አላምረው ቤት ገባን፡፡ ዳንስ ቤቱ “ፓትሪክ ሉሙምባ” ይባላል፡፡ እዚያ ቤት ቅልጥ ያለ ጭፈራ አለ፡፡ አሁን አቤል ለእኔ 700 ብር ሰጠኝ፡፡ ያኔ ሠባት ሺህ ብር በይው፡፡ ገብረክርስቶስ፤ “ይህን ብር ይዘህ የማዝህን ታደርጋለህ” አለና እርሱ መድረኩ ላይ ወጥቶ በማይክራፎን ለሁሉም ቢራ አዝዤላችኋለሁ አለ፡፡ በዚያ ምሽት እነ ማህሙድ አህመድ፣ እነ ጥላሁን ገሰሰ ነበሩ፡፡ ጥቁር ቢራ ለሁሉም አዘዘ፡፡
ጥቁር ቢራ የሚባለው የትኛው ቢራ ነበር? ሜታ ነው ወይስ…
እኔ ስሙን አላስታውስም ግን ጥቁር ቢራ እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ ጠርሙሱ የአሁኑን የጊዮርጊስ ቢራን ጠርሙስ ይመስላል፡፡ እና ያን ሁሉ ሰው ጋብዞ፣ ሂዱና ሂሳቡን ከገብረ ክርስቶስ ጋ ውሠዱ ሲል እጄ ላይ ከ700 ብር 25 ብር ብቻ ቀረ፡፡ ሀያ አምስት ብር ስትቀረኝ ወጥቼ ሄድኩኝ፡፡
እርስዎስ ስንት ቢራ ጠጡ?
እኔማ ምን እጠጣለሁ፤ አንድም አልጠጣሁ፤ ሂሳብ ተቆጣጣሪ ሆኜ ወንድሜና ጓደኛዬ ግን እየጠጡ ሲደንሱ ነበር፡፡ ከዚያ ሲፈልጉኝ የለሁም፡፡ በማግስቱ ጠዋት አቤል ያደርኩበት ቤት መጣና “ብሬን አምጣ” አለኝ፡፡ “የምን ብር” ስለው “700 ብር ነው የወሠድከው” አለኝና እንሂድ ብዬ ጭፈራ ቤት ወሠድኩት፡፡ ሂሳቡ ሲተሳሠብ፣ 25 ብር ብቻ ነው የቀረው፡፡ እሺ 25ቱን አምጣ አለኝ፡፡ “አልጋ ይዤ ነው ያደርኩበት፤ የለኝም” አልኩት፡፡ ከዚያን ቀን በኋላም በፊትም ደጃች ውቤ ዳንስ ቤት ገብቼ አላውቅም፡፡
ብዙ ሰዎች ከአንጋፋው ደራሲ ስብሀት ገ/እግዚአብሔር ጋር ያመሳስልዎታል…
ብዙ ሠው ስብሀት ነህ እያሉ መኪና ሁሉ እያቆሙ ይጠይቁኛል፤ “አይደለሁም” ስላቸው “ወንድሙ ነህ” ይሉኛል “አይደለሁም” እላለሁ፡፡ “ዝምድናም የላችሁ” ይላሉ “የለንም” እላለሁ፡፡ አቶ ስብሀት ከሞቱ በኋላም “ወንድሙ ነህ” ወይ ይሉኛል፡፡
ስብሀትን በአካል አግኝተውት ያውቃሉ?
በፍፁም፡፡ እርሳቸው በጋዜጣ በመፅሄት የሚፅፉትን አነብ ነበር፡፡ ስለ እርሳቸው ታሪክም አንብቤያለሁ፤ በአካል ግን አላገኘኋቸውም፡፡
ከመጀመሪያ ባለቤትዎ ከወይዘሮ ለገሠች ጋር እስካሁን አብራችሁ እንዳላችሁ አውቃለሁ፡፡ ስንት ልጆች ወለዳችሁ?
በሁለት ሆዷ ሶስት ልጆች ወልደናል፡፡
በሁለት ሆዷ ሲሉ?
ያረገዘችው ሁለት ጊዜ ነው፤ የወለደችው ሶስት ልጆችን ነው፡፡ በመጀመሪያው እርግዝናዋ አብርሀምና ይስሀቅ የተባሉ ሁለት ወንዶች ልጆች ሠጥታኛለች፡፡ በቀጣይ ምህረት የተባለች ሴት ልጅ ሰጥታኝ፣ ምህረት አሁን ወልዳ የልጅ ልጅ አሳይታኛለች፡፡ አያት ሆኛለሁ፡፡ አንዱ ልጄ ከ5 ኪሎ ዩኒቨርስቲ ማስተርስ አለው፡፡ ፔኤችዲ ለመስራት ጃፓን ነው ያለው፡፡ መስከረም ላይ ይመረቃል፡፡ ኢንጂነር ነው፡፡ በዩኒቨርስቲ ስኮላርሺፕ አንድ ተማሪ ላኩ ሲባል ተወዳድሮ ነው ጃፓን የሄደው፡፡ ይስሀቅ እዛው አምስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ነው የሚሠራው፡፡ መምህር ነው፡፡ ምህረት ከጐንደር ዩኒቨርስቲ በኮምፒዩተር ሳይንስ ተመርቃለች፡፡ 25 ዓመቷ ነው፤ አምስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ የማታ ተምራ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተመርቃለች፡፡
መጀመሪያ ሲስትር ሚዛን ቤት 90 ብር ነበር ደሞዝዎ፡፡ እዚህ ፀጉር ቤት ሲገቡ በስንት ተቀጠሩ? አሁንስ ደሞዝዎ ስንት ደረሠ?
እዚህ ያስመጡኝ የዛሬ 41 ዓመት በ130 ብር ነው፡፡ ወደ ሁለት መቶ አደገና ከዚያ 300 ብር ላይ ቀጥ ብሎ ቆመ፡፡ ደንበኞቻችን ይመጣሉ እና ወ/ሮ ብርሃኔ በትርፍ ጊዜህ ለምን ከደላሎቹ ጋር እየተሻረክ አትሠራም አሉኝ፡፡ እሺ አልኩልሽና ጀመርኩ፡፡ ሰዎች የፀጉር ቤት ሠራተኛ ፈልግልን ማለት ጀመሩ፡፡ እስከ ስንት ትከፍላላችሁ ስል፣ ስምንት መቶ፣ ዘጠኝ መቶ፣ አንድ ሺህ ብር ይላሉ፡፡ የሁለት ወር ቅድሚያ ይቀበላሉ፡፡ ሴትየዋ እዚያ ቁጭ ብለው (ባለቤቷ) እንደዚያ ማስቀጠር ጀመርኩ፡፡ ይህን የማደርገው ከእርሱ ያነሠ እውቀት ያላቸው እንደዚህ ሲቀጠሩ፣ ለምን ለእሱ አልጨምርለትም የሚሉ እየመሠለኝ ነው፡፡ ብል ብል አልጨምር አሉ፡፡ አንድ ቀን አንዷ መጥታ ሠራተኛ ፈልግ ስትለኝ እኔን ውሠጂኝ” አልኳት፡፡ እሺ ብላ የሁለት ወር አንድ ሺህ ስምንት መቶ ብር ሠጠችኝ እና ለባለቤቴ ሰጥቼ ሄጄ ገባሁ፡፡ ከዚያ አበራ የሚባል ጓደኛዬ፣ ወንድሜና ራሳቸው ባለቤቷ ወ/ሮ ብርሀኔ ሆነው የምሰራበት ላሊበላ ሬስቶራንት ፎቅ ላይ ይመጡና ጐትተው ይዘውኝ ወጡና ተመልሼ ገባሁ፡፡ ከዚያ በኋላ 700 ብር እከፍለዋለሁ አሉ፡፡ ወሬ አልሞላም ነበር፤ ኪሳራውን ከፍለው አመጡኝ፡፡
አሁን ስንት ደረሠ ታዲያ?
አሁን 850 ብር ነው ደሞዜ፤ ነገር ግን ደንበኞቼ በሚሠጡኝ ጉርሻ ነው የምኖረው ማለት ትችያለሽ፡፡ ደንበኞቼ ውለው ይግቡ፡፡ ልጆቼም በደንብ ይጦሩኛል፡፡
መቼ ነው ጡረታ መውጣት የሚፈልጉት?
ልጆቼ አሁን ውጣ እያሉኝ ነው፡፡ እኛ የግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ መክፈል ከጀመርን ሁለት አመት ሊሞላን ነው፡፡ ልጁ፤ የፀጉር ቤቱ ባለቤት ጥሩ ነው፤ እናቱ ከሞቱ በኋላ እርሱ ነው የሚያሠራን፡፡ በጣም ጥሩ ሠው ነው፤ ሠው አይጨቁንም፡፡ በዓል ሲሆን ጉርሻ ይሠጠናል፤ ካናዳ 20 ዓመት ኖሮ ነው የመጣው? ሰለሞን ይባላል፡፡ እርሱ “ከእህቴ ጋር ተመካክሬ የአገልግሎት ክፍያ ሰጥተንዎት እረፍት ቢያደርጉ ደስ ይለኛል” ብሎኝ ነበር፡፡ እህቱ ለእናቷ 7ኛ ሙት አመት መጥታ ተመልሳ ሄደች፤ “እሷ ሄዳለች፤ ተመካክረን የአገልግሎት ክፍያ እከፍላለሁ፤ አማካሪ ሆነው ይቀጥላሉ” ብሎኛል፡፡ ከዚያ በኋላ አልጠየቅኩትም፤ ሠዎች ደግሞ ከምትቀመጥ ስራ፤ ያለበለዚያ እርጅና ይጫንሀል ይሉኛል፡፡
ከዚህ በኋላ ስንት አመት መኖር ይፈልጋሉ?
እኔ አሁን 76 አመቴ ነው፤ 80 ብሞላ ደስ ይለኛል፤ ከዚያ በላይ እንዲንዛዛ አልፈልግም፤ ቶሎ ቀልጠፍ ማለት ያስፈልጋል፡፡
አሁን የቀበሌ ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት… ኮንዶሚኒየም ተመዝግበዋል?
ባለሁለት መኝታ ቤቱን ተመዝግቤያለሁ፡፡
10/90 ነው ወይስ 20/80 ነው?
እሱን አላውቅም፤ ብቻ ሁለት መኝታ ነው የተመዘገብኩት፡፡ አሁን ሳስበው ኮንዶሚኒየም ለእኔ ምኔ ነው፤ አርጅቻለሁ እላለሁ፡፡
መልካም ጊዜ እመኝልዎታለሁ
እኔም ታሪኬን ለማስቀረት ስለታተራችሁ አመሠግናለሁ፡፡ እድሜና ጤና ይስጥልኝ፡፡

Read 7007 times