Saturday, 27 July 2013 14:10

የባዮሎጂ ምሩቁ ከብት አርቢ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(8 votes)

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በባዮሎጂ የትምህርት ዘርፍ በዲግሪ እንደተመረቁ በወለጋና በአዲስ አበባ በመምህርነት ለ11 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ማስተማሩን በመተው በወተት ላም እርባታ በግል ሥራ ላም ተሰማርተዋል፡፡ ከትምህርትና ከሥራ ያገኙትን ዕውቀት ለሌሎች ለማካፈል በማለም “ከወተት ላይ እርባታ ለመጠቀም” በሚል ርዕስ 776 ገፆች ያሉት መጽሐፍ አሳትመው ባለፈው ወር በአዲስ አበባ ግብርና ቢሮ አዳራሽ አስመርቀዋል፡፡ ጋዜጠኛ ብርሃኑ ሰሙ ከመፅሃፉ አዘጋጅና ከከብት አርቢው ከአቶ ፋሲካ በቀለ ጋር ያደረገው ቃለምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ዲግሪ ይዞ ወደ ከብት በረት መግባት ለብዙዎች የሚከብድ ይመስላል፡፡ እርስዎ እንዴት ወደ ላም እርባታ ገቡ?
ትውልድና ዕድገቴ በአዲስ አበባ ከተማ ነው። ጉለሌ አካባቢ በነበረው ቤታችን፣ ወላጆቼ ከብት የማርባት ሥራ ያከናወኑ ስለነበር፣ በዘርፉ ያለኝ የሥራ ዕውቀትና ፍቅር ከልጅነቴ አንስቶ ያደገ ነው። ከዩኒቨርስቲ ከተመረቅሁ በኋላ በመምህርነት ብቀጠርም ሕልሜ የግል ሥራ መሥርቶ መምራት ስለነበር፣ ከማስተማር ወጥቼ ወደ ከብት እርባታ ገባሁ፡፡
መምህር ሳሉ ለተማሪዎች የተለያዩ እንስሳትን እያቀረቡ በማሳየት የተግባር ትምህርት ይሰጡ ነበር ይባላል...
በወለጋ ሻምቡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለዘጠኝ ዓመታት ነው ያስተማርኩት፡፡ ትምህርት ቤቱ የበጎ አድራጎት ድርጅት አሟልቶ ያደራጀው ላቦራቶሪ ነበረው፡፡ ማዕከሉ ያለ አገልግሎት ተዘግቶ መቀመጡን ሳስተውል፣ መምህራንና ተማሪዎችን በማስተባበር አገልግሎት እንዲሰጥ አደረግሁ፡፡ ትምህርቱን በተግባር ማሳያ ስሰጥ፣ ተማሪዎቹም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ተማሪዎቹ ጥንቸል፣ እባብ፣ ኤሊ፣ ዓሳ … ያመጡ ነበር፡፡ የተለያዩ ኬሚካል በመጠቀም እንስሳቱን እያደረቅን እናስተምርበት ነበር፡፡ ኤግዚቢሽን ያሳየንበትም ጊዜ አለ፡፡ በዚህ ሥራችን ትምህርት ቤቱ ተሸላሚ ሆኗል።
ከቅጥር ሥራ ወጥተው የግል ሥራ ሲጀምሩ የገጠምዎት ችግር ነበር?
ከብት እርባታ ከልጅነቴ ጀምሮ እያየሁ ያደግሁት ሥራ ቢሆንም የእናቴን አራት ላሞች እንደ መነሻ ካፒታል ይዤ መስራት ፣ ያልጠበቅሁት ብዙ ችግሮች ገጥመውኛል፡፡ ለነገሩ በዘርፉ ውስጥ ያሉ ችግሮች ናቸው በእኔም ላይ የተከሰቱት፡፡ ከአመጋገብ፣ ከማለብና ከሆድ ዕቃ ችግር ጋር ተያይዞ በተከታታይ ላሞች ሞተውብኛል፡፡ ለእንስሳቱ ህመም መድሐኒትና ሐኪም ማግኘቱም እራሱን የቻለ ትልቅ ችግር ነው፡፡ የጤና ባለሙያው ወደ እኛ ለመምጣት ፈቃደኛ ባይሆን ወይም ባይመቸው ላሟን ወደ ሐኪሙ መውሰጂያ መንገድ የለም፡፡ ሰው ቢታመም በኮንትራት ታክሲ ወይም በሸክም ሐኪም ዘንድ ማድረስ ይቻላል፡፡ ላሞች ግን… እነዚህ ችግሮች ናቸው መጽሐፍ እንዳዘጋጅ ያነሳሳሱኝ። ዘርፉ አዋጭና ብዙ ሰዎች ያልገቡበት ቢሆንም ችግሮቹ በቶሎ መፍትሔ የሚገኝላቸው አይደሉም፡፡
የላምና የወተት ዋጋ ድሮና ዘንድሮ ምን ይመስላል?
አንዲት ላም በ700 ብር የምትሸጥበት ዘመን እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ አሁን እስከ 40ሺህ ብር ታወጣለች፡፡ በሣንቲም ቤት ይከፈልበት የነበረው አንድ ሊትር ወተት አሁን 16 ብር ገብቷል። ለወተት ዋጋ መጨመር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ የመኖ መወደድና፣ የወተት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የወተት ሊፈጠር ከሚችልባቸው ምክንያቶች አንዱ በወተት አስተላለብ የሰለጠኑ ባለሙያዎች አለመኖር ነው፡፡
የሁለቱን ግንኙነት ያብራሩልኝ…
የግል ከብት አርቢዎች ለአላቢ የምንቀጥረው ያለ ምንም መመዘኛ ነው፡፡ ተቀጣሪው ከገጠርም ይምጣ የከተማ ሰው ይሁን በሚያውቀው መልኩ ወይም የተነገረውን ነው የሚሰራው፡፡ ላም የምትሰጠው ወተት ውጤታማ እንድትሆን በወሊድ ወቅት የምታገኘው እንክብካቤ፣ የበረቷ ንጽሕና አያያዝ፣ የአመጋገብ ሁኔታዋ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የተፈጥሮ ፀባይና ፍላጎቷ እንዲጠበቅላት ትፈልጋለች፡፡ ይህንን ካጣች የምትሰጠው የወተት መጠን ይቀንሳል፡፡
የላሞችን ተፈጥሮና ባሕሪ እንዴት ይገልፁታል?
ላሞች ንቁ ናቸው፡፡ በድግግሞሽ ይማራሉ። የሰዓት ግንዛቤ አላቸው፡፡ ዛሬ በረቱን የጠረግንበትንና ወተት ያለብንበትን ሰዓት ጠብቀን፣ በማግስቱም በተመሳሳይ ጊዜ ያንን እንድንፈጽም ይፈልጋሉ። አንድን ነገር ካስለመድናቸው ሰዓት 30 ደቂቃ ዘግይተን ብንፈጽምላቸው ይቆጣሉ፣ ይነጫነጫሉ፣ ይበሳጫሉ፡፡ ከላሞች ባሕሪ ጋር ተስማምተን ካልሰራን ሥራችን ለኪሳራ ይዳረጋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከብት አርቢዎች ማህበር አላችሁ?
በፊት አንድ አጠቃላይ ማህበር ነበር፡፡ አሁን ግን አባላቱ በሚገኙበት አካባቢ እየተሰባሰቡ ለችግራቸው መፍትሔ ለማግኘት እየጣሩ ነው። በአቃቂ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ወዘተ … በማህበር ለመደራጀት እየሞከሩ ያሉ አርቢዎች አሉ፡፡
የመድሐኒት እጥረት ከመኖሩ የተነሳ ጊዜ ያለፈበትን መርፌ የምትወጉበት ጊዜ አለ ይባላል፡፡ እውነት ነው?
ከፍተኛ የመድሐኒት ችግር አለብን፡ እንዳልከው ስንቸገር ጊዜ ያለፈበትም ቢሆን የምንጠቀምበት ጊዜ አለ፡፡ የግብርና ቢሮ የእንስሳት መድሐኒት መሸጫ መደብር እንዲከፍት ጠይቀን ነበር፡፡ የ30 ብር አንድ ብልቃጥ መድሐኒት፣ 900 ብር ድረስ የምንገዛበት ጊዜ አለ፡፡
የኮንዶሚኒየም ሕንፃዎች የከተማ ከብት እርባታን እያጠፋ ነው ስለሚባለው ምን ይላሉ?
ነባር የመኖሪያ መንደሮች ለልማት ሲፈርሱ፣ ሕልውናቸው ያበቃላቸው በረቶችን አውቃለሁ። ከብት ኮንዶሚኒየም ሕንፃዎች ላይ ሊወጣ አይችልም፡፡ የወተት አስፈላጊነትና ጥቅምን እያስተማርን የበረቱን ሕልውና መጠበቅና መከላከል አለመቻል፣ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ጉዳይ ስለሆነ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
“ከወተት ላም እርባታ ለመጠቀም” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፍዎ ውስጥ የላም ዝርያዎችን በአምስት ነው የመደቧቸው፡፡ ቁጥሩን ከዚህ ከፍ አድርገው የሚገልፁም አሉ፡፡ የልዩነቱ ምክንያት ምንድነው?
መንግሥት ዘርፉን ለማገዝ የፈረንጅ ላሞችን ከተለያዩ አገራት እያስመጣ፣ ከአገር ውስጥ ላሞች ጋር እንዲዳቀሉ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ እኔ በ5 መድቤ ያቀረብኩት የወተት ላሞቹን ነው፡፡ የሥጋ ላይ ዝርያዎች ቁጥር ብዙ ነው፡፡
በመጽሐፍዎ ውስጥ “የጥጆች ነርሰሪ” ይቋቋም የሚል ሀሳብ አንስተዋል፡፡ ምክንያትዎ ምን እንደሆነ ቢነግሩኝ…
የወተት ላም አርቢው የመጨረሻ ግቡ በሚያልበው ወተት ውጤታማ መሆን ነው። መንግሥት የወተት ላሞችን ከውጭ እያስመጣ ከአገር ውስጥ ላሞች ጋር እንዲዳቀሉ የሚያደርገውና ከብት አርቢዎችም በበረታቸው የወተት ላም እንዲኖራቸው የሚተጉት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የላም አርቢዎች ግብ ይህ ከሆነ እርባታውን ከነርሰሪ መጀመር የመጨረሻ ውጤቱን ያሳምረዋል፡፡
ይህ ለወተት ላም እንክብካቤ ብቻ ሳይሆን ወንድ ጥጆችንም ከአደጋ ለመታደግ ይረዳል፡፡ የላም ወተት አርቢዎች ለትርፍ ስለምንሰራ፣ ወንድ ጥጆች ሲወለዱ ተንከባክቦ የማሳደግ ፍላጎትና ትዕግስት የለንም፡፡ በዚህ ምክንያት ወንድ ጥጆች ከተወለዱ ከጥቂት ቀናት በኋላ ለሥጋ ፈላጊዎች እንሸጣቸዋለን። በዚህ አሰራር ውስጥ ያለው አንዱና ትልቁ ችግር የተለያዩ ዝርያዎች ተዳቅለው የተወለዱት ወንድ ጥጆች አድገው ዘራቸው እንዳይስፋፋ እንቅፋት ይሆናል፡፡ የጥጆች ነርሰሪ ቢቋቋም ግን ተጨማሪ የሥራ ዕድል ከማስገኘቱም ባሻገር ከጥጆች ጋር በተያያዘ የጠቀስኳቸው ችግሮችን ይቀርፋል፡፡
የጥጆች ነርሰሪ የማቋቋም ሀሳብ አለዎት?
ነርሰሪ ሳይሆን የማለቢያ ስልጠና የሚሰጥ ማዕከል በቅርቡ የማቋቋም እቅድ አለኝ፡፡ የልምድ አላቢዎች በሚፈጥሩት ችግር የተነሳ፣ ላሞች የትምህርት መርጃ መሳሪያ ሆነዋል፡፡ ይህ ችግር ካልተቀረፈ በግል በረት አቋቁመው ከብት የሚያረቡ ሰዎች ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ ይቀጥላል፡፡ በውጭ አገራት ከልማዳዊ አለባ በመውጣት አሰራሩን (የማለቢያ ማሽን ባይኖር እንኳ) ዘመናዊ ለማድረግ ብዙ ስልጠናዎች ይሰጣሉ፡፡ በልማዳዊ አለባ ወቅት ጎተታና ጨበጣ የሚባሉ የአስተላለብ ዘዴዎች አሉ። ይህንንም ቢሆን መቼ፣ እንዴትና ለምን መጠቀም እንዳለብን ካላወቅን፣ የመጨረሻ ውጤቱ ጉዳት ይሆናል፡፡ ለዚህ ነው የማለቢያ ስልጠና የሚሰጥ ማዕከል ለማቋቋም ያሰብኩት፡፡
በመጨረሻ የሚያነሱት ሐሳብ ካለ …
እዚህ ደረጃ እንድደርስ ቤተሰቦቼና ጓደኞቼ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገውልኛል፡፡ ዛሬ 12 የሚታለቡ ላሞች አሉኝ፡፡ እዚህ ደረጃ የደረስኩት እናቴ በሰጠችኝ አራት ላሞች በመጀመር ነው፡፡ አባቴ ኢንጂነር በቀለ በትምህርትና በሥራ ልምድ ያገኘሁትን ዕውቀት ወደ መጽሐፍ እንድለውጠው አበረታቶኛል፡፡ የልጆቼ እናትና የትዳር አጋሬ በየዕለቱ ከእኔ ጋር በበረት ውላ በሥራ ባታግዘኝ ኖሮ ዛሬ፣ የደረስኩበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ተጨማሪ ዓመታት ይወስድብኝ ነበር፡፡

Read 7409 times