Saturday, 27 July 2013 13:57

የ”ቃጭሉ” ሥነ-ልቦና

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(45 votes)

የነጭ አክራሪዎችን ያስቆጣ ጥቁሮቹን ደግሞ ያስደሰተው ሪፖርት እንደሚያሳየው በርዝመት ብልጫ የጥቁሮቹ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ከአፍሪካ ኮንጐ አንደኛ ናት በአማካኝ 7.06 ኢንች ርዝመት ያላቸው ባለ “ቃጭሎች” አፍርታለች፡፡ ኢኩዋዶር (7.0)፣ ጋና (6.81)፣ ኮሎምቢያ (6.7)፣ ካሜሩን (6.56)፣ ጃማይካ (6.42)…

ወንድ ልጅ ሲወለድ ሰባት እልልታ ውልደቱን ተከትሎ የሚያስተጋባ የብስራት ድምፅ ነው፡፡ ከእልልታው ጋር “ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ” የሚል አገላለፅም የፆታ ማንነቱን ማረጋገጫ ዘይቤአችን ነው።
ከወንድነት ጋር ዘወትር ተያይዞ ስለሚታሰበው “የቃጭሉ” ስነ-ልቦና በጥናት የተደገፈ እይታ ለማቅረብ ወጠንኩ፡፡ “የቃጭሉ” የመጠን ርዝመት ወይንም እጥረት ወንድነትን እና የፆታዊ ግንኙነትን በምን ረገድ ይጠቅማል? ወይንም ይጐዳል… ወይንስ ወንድነት ከብልት መጠን ጋር ምንም ንክኪ የለውም? የሚለውን ጭንቀት አዘል ስነ-ልቦና ከወንዶች የጓዳ አስተሳሰብ በምክንያታዊነት መዝኖ ለማቅለል… በዛውም ሳይንሳዊ ግንዛቤ ለማስጨበጥ… የታቀደ ፅሁፍ እነሆ፡-
የመጣጥፉ ዳራ ይሄ ቢሆንም፤ መነሻ የሆነኝ ዜና ግን በዚህ ሳምንት በ”ሴክሹዋል ሜዲስን” ጆርናል አማካኝነት የተፃፈ የጥናት ወረቀት ነው፡፡ በአሜሪካ ሀገር የወንዶች ብልት ርዝመት መጠን በአማካኝ 14.2 ሴንቲ ሜትር መሆኑ ይፋ ሆነ፤ ይላል ዜናው። በመቀጠል፤ “ሁሉም ወንዶች ብልታቸው በመጠን ረጅም እንዲሆን ምኞታቸው ቢሆንም፤ በተፈጥሮ ከታደሉት መጠን በላይ ጨምረው የሚዋሹት በምን ምክንያት እንደሆነ ግን ግልፅ አይደለም” ይላል፡፡
ለምንድነው ወንዶች ትልቅ መጠን ያለው “ቃጭል” እንዲኖራቸው የሚፈልጉት? በሴቶቹ ምርጫ ምክንያት ነው? የተፈጥሮን ተልእኮ ከመወጣት (የዘር ፍሬን በሴቷ መሀፀን ከማኖር) አንፃር የመጠን ርዝመት እና እጥረት የሚያመጣው ፋይዳ ምንድነው? በመጠን ማነስ ምክንያት የሚመጡ የስነ-ልቦና መንጋደዶችን ለማካካስ የሚወሰዱ መፍጨርጨሮች ምን ይመስላሉ? “ቃጭሉ” ከሌላው የሰውነት አካል በተለየ ድብቅ እና በነውር ስነ-ልቦና የታጠረ የመሆኑ ምክንያት ምንድነው?... የሚሉ ጥያቄዎች ይህንን የሰውነት ክፍል ለስነልቦና ምርምር ብቻ የተፈቀደ እንዲሆን አድርገውታል፡፡
ከታሪክ አንፃር
በተለያዩ ዘመናት የበቀሉ ጥንታዊ ስልጣኔዎች ለራሳቸው ያላቸውን ግምት (ጥንካሬያቸውን፣ ሃያልነታቸውን፣ የብዙ ዘር ሀረግ መፍለቂያ መሆናቸውን) ለመግለፅ የወንድ ብልትን እንደ ምልክት ይጠቀሙ ነበር፡፡ ከዚህ የአካል ክፍል መነሻነት ምስሎች እና ሐውልቶችን ቀርፀዋል፡፡
ለምሳሌ በጥንታዊቷ ግሪክ፡- የተገረዘ እና በመጠን አነስ ያለ ብልት በወንዶች ላይ ተስማሚ/ትክክለኛ ተደርጐ ይታሰብ ነበር፡፡ ሮማዊያኑ ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ የሆነውን መጠን ለወንድነታቸው መለኪያ ይፈልጉ ነበር፡፡ …በሁሉም ውስጥ ግን ይህ በተፈጥሮ በተሰጣቸው የመራቢያ አካል አማካኝነት ለራሳቸው ያላቸውን ግምት ከሌላው ጋር የሚያነፃፅሩበት የራስ አክብሮት መለኪያ መሆኑ ጐልቶ ይታያል፡፡
የጥንት ግሪካዊያን መጠነኛ ብልት ለአማልክቶቻቸው ሰጥተው፣ በመጠን ከፍ ወይንም ረዘም ያለውን “ግማሽ እንስሳ እና ግማሽ ሰው ለሆኑት እንደ Satyr (ግማሽ ፍየል ግማሽ ሰው) ይሰጣሉ፤ ወይንም ኋላ ቀር ብለው ለሚንቋቸው፣ ላልሰለጠኑ አረመኔዎች የተገባ እንደሆነ በቅርፃቅርፅ ጥበባቸው ያመለክታሉ፡፡ ከስልጣኔ በታች መሆንን ከመራቢያ አካል ግዝፈት ጋር ያያይዙታል፡፡
አረቦች በቀደምት ስነ-ፅሁፎቻቸው አማካኝነት የወንድ ልጅ “ቃጭል” ረዘም ቢል የተሻለ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ ጥንታዊው የተረት መፅሐፋቸው “አረቢያን ናይትስ” ለዚህ ምሳሌ ማጣቀሻ ሊሆን ይችላል፡፡ “አል ጃሐዝ” የተባለው የአፍሮ - አረብ ፀሐፊ “ትልቅነት በረዘመ ቢሆን ኖሮ አህያ ነበር ትልቅ የምትሆነው” ይላል፡፡ ከወንድነት አዎንታዊ ጥንካሬዎች ጋር ሳይሆን ርዝመትን ከሴሰኝነት ጋር ያያይዘዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ በተለያየ ስልጣኔ እይታም “የቃጭሉ” ነገር አወዛጋቢ መሆኑን ልብ ማለት ይቻላል፡፡

ከዝንጀሮ ቤተሰቦች (Primates) አንፃር
ከጦጣ ዝርያዎች አንፃር ከታየ የሰው ልጅ (ወንድ) የመራቢያ አካል በርዝመትም በድድርነትም የላቀ ነው። የላቀበት ምክንያት ግን ለአጥኝዎቹ ግልፅ አይደለም፡፡ በጋርዮሽ የዝግመት ዘመኑ ይፈፅም የነበረው የጋርዮሽ ወሲብ ለዚህ ልቀቱ ምክንያት እንደሆነ የአካል ለውጥ አጥኝዎቹ ይገምታሉ፡፡ ምናልባትም የብልት መጠኑ ከቦታ ቦታ እንደዚሁም ከዘር ዘር የተለያየበት ምክንያቱ ይህ ሊሆነ ይችላል ይላሉ፡፡
የጦጣ ዝርያዎች ከአላቸው ግዝፈት አንፃር በጣም ያነሰ የመራቢያ አካል አላቸው፡፡ ሰው ግን ከአካላዊ መጠኑ አንፃር ሲገመገም “ወንድነቱ” የረዘመ ነው፡፡
በሐገሮች መሀል ያለ የቁመት ልዩነት
የወንድ የመራቢያ አካል በሀገራችን ለምርምር የቀረበ አይደለም፡፡ የፈረንጆቹ ግን ሁሉን አየነት ምርምር ያደርጉበታል፡፡ ምክንያቱም በነውር የተተበተበ የአካል ክፍል ቢሆንም እንደ ማንኛውም የሰውነት ክፍለ ምርምር ስለሚያስፈልገው ነው፡፡
ከምርምሮቹ መሀል በተለያዩ አለም ክፍል ያሉ የሰው ዘሮችን የብልት መጠን በመለካት ዳታ መመዝገብ አንዱ ነው፡፡ ምዝገባወ የሚካሄደው በሳይኮሎጂስቶች ነው፡፡
ምናልባት ልክ እንደ ሌሎቹ የሰውነት ክፍሎች (ልብ፣ አይን፣ ጆሮ) ያልታየው ከመሰረታዊ የተፈጥሮ ባህሪ ጋር ስለተሳሰረ መሆኑ ይገመታል፡፡
በመለካቱ ስራ ላይ ሳይኮሎጂስቶቹ የሚገጥማቸው ዋና ችግር ትክክለኛ ልኬትን ማግኘት አለመቻል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ መዝጋቢው፤ የቃጭሉን ባለቤት የብልቱን ትክክለኛ ርዝመት ለክቶ እንዲነግረው ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም ነገርየው ነውር በመሆኑ ሁሉም የራሱን “ቃጭል” ለክቶ የሚሰጠው ልኬትን ከመቀበል ውጭ አማራጭ የላቸውም - ባለሞያዎቹ። ተመዝጋቢው ሲመልስ በአማካኝ 1.0 ኢንች በእውነተኛው ልክ ላይ ጨመሮ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተለያዩ ሀገሮች ተደጋግሞ የተሞከረና በተደጋጋሚ ተዛብቶ የተገኘ ውጤት ነው፡፡ መጨመሩ ያስፈለጋቸው ወንድነታቸውን ከሌላው ለማስበለጥ በመሻት እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡
በሰሜን አየርላንድ የሚገኝ የሳይኮሎጂ ፕሮፌሰር ከ116 ሀገሮች የሰበሰበውን ዳታ በጥናታዊ ሪፖርት መልክ ይፋ ሲያደርግ ለጭቅጭቅ እና ለተለያዩ አመለካከቶች መንስኤ ሆኖ ነበር፡፡ ሪፖርቱ የቀለም ዘረኝነት አዝማሚያ ያላቸውን አስቆጥቶም ነበር፡፡
የነጭ አክራሪዎችን ያስቆጣ ጥቁሮቹን ደግሞ ያስደሰተው ሪፖርት እንደሚያሳየው በርዝመት ብልጫ የጥቁሮቹ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ከአፍሪካ ኮንጐ አንደኛ ናት በአማካኝ 7.06 ኢንች ርዝመት ያላቸው ባለ “ቃጭሎች” አፍርታለች፡፡ ኢኩዋዶር (7.0)፣ ጋና (6.81)፣ ኮሎምቢያ (6.7)፣ ካሜሩን (6.56)፣ ጃማይካ (6.42)…
እዚሁ የበለጡ ርዝመቶች ዝርዝር ውስጥ “አይስ ላይንድ” በደረጃ ዘጠነኛ አካባቢ መቀመጧ “እንዴት?” የሚል ግራ መጋባት እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል፡፡ (ጥቁሮች በተቆጣጠሩት የረጅም ርቀት ሻምፒዮና ነጮቹ እንዴት ገቡ? ማለት ይሆን ግራ መጋባቱ?)
በጣም አጫጭር “ቃጭል” በተፈጥሮ የተቸራቸው ሀገራት ወደ ሩቅ ምስራቅ ያሉት ናቸው፡፡ ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ (3.8 ኢንች)፣ ካምቦዲያ (3.95)፣ ታይላንድ (4.0)፣ ህንድ (4.03)፣ ታይዋን (4.24)… እያለ ይቀጥላል፡፡ (N.B አንድ ኢንች 2.5 ሳንቲ ሜትር ነው) በልኬቱ ውስጥ አንዳንዴ በሀገሮች መሀል ያለ የፖለቲካ ፍጭትም ለደረጃ ምደባው ሚዛናዊነት ሳንካ ሲሆን ይታያል፡፡ ለምሳሌ ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ በአማካይ ያኙት ነጥብ (3.8) አንድ አይነት ቢሆንም፣ የአሜሪካ ሚዲያ ዜናውን ስያሰራጭ፤ ሰሜን ኮሪያን “ውራ” እንደወጣች ተናግሮ ነበር፡፡
ይሄንን መርዶ መሰል ዜና በሰሜን ኮርያ ላይ ያስወራችው ታላቋ አሜሪካ ራሷ በደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ዘጠና ስድስተኛውን ስፍራ ነው የያዘችው፡፡ 5.08 ኢንች በአማካይ “የቃጭሎቿ” ርዝማኔ ነው፡፡
ጥናቱ ከተሰራባቸው 116 ሀገሮች 26ቱ በዶክተር አማካኝነት በትክክለኛው ዘዴ የተለኩ ናቸው። በትክክለኛው መንገድ የሚደረግ ልኬት ራሱ ባለ አካሉ ከሚለካው የተለየ ነው፡፡ የመራቢየ አካሉ ባለቤት በትክክለኛው መጠን ላይ አሻሽሎ መጨመሩ አይቀርምና፡፡ለምሳሌ ጥቁሮች (Black men) 7.9 ኢንች ለክተናል ካሉ በኋላ በትክክሉ ሲለኩ 6.9 ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ላቲኖች 7.7 ለካን ካሉ በኋላ 6.5 በእቅጩ ሆነዋል፡፡ ጥቁሮቹ በአንድ ኢንች ላቲኖቹ በ1.2 ኢንች አጋንነዋል፤ ዋሽተዋል፡፡ ኢስያ ያሉት ደግሞ የውሸታቸው መጠን ከፍ ይላል… 1.4 ኢንች ከሆኑት በላይ ጨምረው ተገኝተዋል፡፡ የተፈጥሮ መጠኑ አጭር የሆነ “ቃጭል”… በራሱ እጅ ራሱን በራሱ ሲለካ ጨምሮ የሚኘውም የውሸቱ ርዝመት መጠን የበለጠ ይሆናል፡፡ ከሁሉም የሰው ልጆች በእውነተኛ የብልት መጠናቸው ላይ በጣም ጨምረው በመዋሸት አቻ ያልተገኘላቸው ነጮቹ ናቸው፡፡ በአማካኝ 7.8 ኢንች ለካን ቢሉም በእርግጡ 6.1 ሆነው መገኘታቸው አይገርምም… ወይንም ሊያሸማቅቃቸው አይገባም፡፡
የኢትዮጵያን መጠን እንደ ዳታው ማወቅ የፈለጋችሁ ካላችሁ… መሀከለኛ በማለው ብትይዙት ጥሩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አይነት ልክ ያላት ሀገር ፈረንሳይ ናት፡፡ ሁለቱም በአማካይ 5.33 ተለክተዋል፤ የዜጐቻቸው “የቃጭል” ርዝማኔ መጠን…፡፡
የኤርትራ ስንት ነው? የግብፅስ? ብላችሁ እንዳትጠይቁኝ። የእኛ በለጠ ማለት ምንም ትርጉም የለውም። የሚያመለክተውም ነገር የለም፡፡ … የመራባት አዝማሚያን አመልካችም አይደለም፡፡ በህዝብ ብዛት መጠን በአንደኝነት ደረጃ አለምን የሚመሩ ቻይኖች፣ በመራቢያ አካል ርዝመት መጠን ግን የመጨረሻው እርከን ላይ ናቸው፡፡
የወንድነት መጠን እምነት በሴቶች እይታ
በሴቶች ላይ የወንዶች የብልት መጠን ምን ትርጉም ወይንም የምርጫ ለውጥ ያመጣል? በሚለው ጥያቄ ላይ የተደረጉ ብዙ ጥናቶች የሉም፡፡ በቴክሳስ ፓን አሜሪካን ዩኒቨርስቲ ላይ በBMC Womans Health ጥምረት በ50 የኮሌጅ ሴት ተማሪዎች ላይ የተጠና ጥናት የሚነግረንን እንመልከት፡፡
50ዎቹ ሴት ተማሪዎች ሁለት የወንድ አትሌቶችን በተመለከተ ምርጫቸውን እንዲጠቀሙ ተጠየቁ፡፡
የወንድን ብልት በተመለከተ ከርዝመት ይልቅ የነገርየው ውፍረት ለወሲባዊ እርካታ እንደሚመርጡ አብላጫዎቹ መልስ ሰጥተዋል፡፡
“ሳይኮሎጂ ቱዴይ” የተባለ መፅሔት 1500 ለሚጠጉ አንባቢዎቹ ባቀረበው ጥያቄ፤ መፅሔቱን የሚያዘወትሩ ወደ 1000 ገደማ ከሚጠጉ ሴቶች መሀል 71% ፐርሰንቱ የወንድ ብልት የርዝመት መጠን ለፍቅር ምርጫቸው ምክንያት እንዳልሆነ አረጋግጠዋል፡፡ ለብልቱ መጠን ትልቅ ቦታ ሰጥቶ የሚጨነቀው ራሱ ወንድየው እንጂ ሴቶቹ እንዳልሆኑ መመስከራቸው ነው፡፡ የሴቶቹ ምርጫ እንደሚጠቁመው ከሆነ ለወንድየው ተክለ ቁመና ረጅምነት እንጂ የሚጨነቁት… ለመራቢያ አካል ተክለ ቁመና ርዝመት ብዙም ግድ የላቸውም፡፡ እንዲያውም፤ ርዝመት ካለው “ቃጭል”… ውፍረት ያለው ለአልጋ እንደሚመቻቸው ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
የአውስትራሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርስቲ በ2013 አጥቢያ ባወጣው ጥናቱም ያሳየው ተመሳሳይ ውጤት ነው፡፡
ከብልት ርዝመት የተክለ ቁመና ዘለግ ማለት ሴቶቹን ያማልላቸዋል፡፡ ለዘግ ባለ ተክለ ቁመና ላይ ግን ተንጠልጣዩም ዘለግ ቢል አይከፋቸውም፡፡ ትንሹ ቁመና (የብልት) ግን ያለ ትልቁ ሚዛን አይደፋም - እንደ ሴቶቹ ምርጫ፡፡
ወንድነት እና የማንጠልጠል ስነ ልቦና
የብልቱን መጠን እየመዘነ የሚሸማቀቅ ወይንም የሚኩራራ ወንድ ብዙ ነው፡፡ ብልጫ አለኝ ባዩ የሚኩራራው አነስ ካሉት አንፃር ራሱን እየመዘነ ነው። የመራቢያ አካል በወንዶች ዘንድ በቁመት፣ ርዝመት እና ቅርፅ ብዙ አይነት ቢሆንም የተፈጥሮ ተልእኮውን በመወጣት ረገድ ከታየ የመጠን ልዩነቱ ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡
የወንዶች ብልት አንደሚለያየው ሁሉ የሴቶቹም መራቢያ አካል ከወንዶቹ በተመሳሳይ ሁኔታ ከሀገር ሀገር፣ ከዘር ዘር፣ በአንዷ እና በሌላዋ መሃል ልዩነት አለ፡፡
በወንዶች ዘንድ ግን የነገርየውን ቁሻሻ ማስወገጃ እና መራቢያ ከመሆን ባሻገር ማንነትን፣ ለራስ የሚሰጥን ከፍ ያለ ስፍራ በመጠን አማካኝነት የሚገልፅ ተደርጐ በመወሰዱ… ለፉክክር ከፍተኛ መድረክ ይከፍታለ፡፡ ፉክክሩ ድልም ሆነ መሸማቀቅን በወንዱ ላይ ሊፈጥር ይችላል፡፡የተፈጠረልኝ ነገር ትንሽ ነው ብለው የሚያስቡ ትንሽነታቸውን ለማሳደግ ብዙ መፍጨርጨር ውስጥ ይገባሉ፡፡
ይህንን የዝቅተኛ Self esteem ስነ ልቦናቸውን ለማከም፡፡ ስኬታማ ውጤት እና የማያሻማ ተፈጥሮን የመለወጫ መንገድ ግን እስካሁን እንዳልተገኘ ባለሞያዎቹ ይናገራሉ፡፡በወንድ ልጅ እና ቃጭሉ… መሃል ስለሚካሄድ የስነ ልቦና ጦርነት እናንተስ ምን ታስባላችሁ? በአንድነት በሚጓዙበት ህይወት ላይ የቃጭሉ ድምፅ ለተሸካሚው ወንድ ነው ወይንስ የቃጭሉ ድምፅ ለምታደምጠው ሴት?

 

Read 30278 times