Saturday, 27 July 2013 13:57

‘አባባ ገፋ፣ ገፋ…’

Written by 
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…መቼም ጉዳችን አያልቅ! ብሎ፣ ብሎ የኬት መውለድና አለመውለድ ‘ጉዳያችን’ ሆኖ ይረፍ! እንደው አሰሳቸውንም፣ ገሰሳቸውንም ስንሰበስብ እያዩ… “እናንተ ብሎ ባለድሪምላይነር…” ቢሉን ምን ይገርማል! ለሶፍትዌር ባለሙያዎቻችን ሀሳብ አለን…ከመከረኛው ኢንተርኔት ላይ ለእኛ የሚሆነውና የማይሆነውን እየለየ ‘ፊልተር’ የሚያደርግ ሶፍትዌር ይሥሩልንማ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄኔ እኮ ጎረቤታችን ስትሰቃይ ከርማ የወለደችን ሴት አይደለም “እንኳን ማርያም ማረችሽ!” ልንላት…አለ አይደል… “አንድ ለራስ እንኳን በቀን ሁለቴ መመገብ አስቸጋሪ በሆነበት ጊዜ የምትወልደው… ሙጃ ልታበላው ነው!” ምናምን የምንል እንኖራለን። እናላችሁ… “ገንፎ ብሉ…” ባልተባልንበት… “እልል በሉ፣ ኬት ወንድ ልጅ ከእነቃጭሉ ዱብ አደረገች…” አይነት ነገር አሪፍ አይደለም፡፡
ስሙኝማ…የድሪምላይነሩን ነገር ተከትሎ ኢንተርኔት ላይ እየተሰጡ ያሉ አስተያያቶች…አለ አይደል…ዓለም አሁንም እንዴት ‘እንደሚተረጉመን’ አሪፍ ማሳያዎች ናቸው፡፡ “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች…” የሚሉት አዲስ አበባ ብቻ እንደሚቀር ልብ ይባልማ! በየስፖርቱም፣ በየምናምኑም “ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው…” ምናምን የምንለው ሁሉ ‘ሳይንስ ፊክሺን’ እንደሆነ ልብ ይባልልንማ! ቂ…ቂ…ቂ… (በተለይ…ግርም የምትለኝ ነገር ምን መሰላችሁ…የሆነ እኛን የሚመለከት ነገር በሆነ የኤፍ.ኤም. ፕሮግራም ላይ ይጠቀስና ምን ይከተላል መሰላችሁ…“ዓለምን እያነጋገረ ያለ ጉዳይ…” ይባላል። ዓለምማ አይደለም ‘ራዲዮናችን’… የኢትዮዽያ ድሪምላይነር አውሮፕላን… ምናምን ሲባል ምን ይል መሰላችሁ… አንዱ ‘ፈረንጅ’ በመከረኛው ፌስቡክ ላይ እንደለጠፈው… “Dreamliner! Ethiopia! You must be kidding me!” ይላል፡፡ የእኛ ነገር እንዲሁ ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ዘንድሮ የ‘መሳም’ና የ‘ማቀፍ’ ትርጉሞች እየተለዩላችሁ ነው፡፡ እናማ…በአደባባይ ‘መሳም’… ‘መታቀፍ’…ፍቅር ላይሆን ይችላል፡፡
የምር…ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡ ይቺን አገር የሚያሾሯት ነገሮች “አላዩንም፣ አልሰሙንም…” ተብለው የሚሠሩ ነገሮች መአት ናቸው፡፡ እናማ…በአደባባይ “ተሳምኩ” ተብሎ ከመጋረጃ ጀርባ ‘መነከስ’ አለላችሁ!
አንድ የንግድ ሽርክና ተቋቁሞ ተቃቅፈው ከተለያዩ፣ ሻምፓኝ ከተቃመሱ በኋላ… በአምስተኛ ወሩ ከአምስቱ ሸሪኮች ሦስቱ የ“አላዩንም፣ አልሰሙንም…” የመጋረጃ ጀርባ ‘ግዝገዛ’ ይጀምራሉ። እናማ… ደበቅ ይሉላችሁና ሁለቱን ፈንግለው እንዴት ድርጅቱን እንደሚጠቀልሉ ይመክራሉ፡፡ ግን ምን መሰላችሁ…ቆይቶም ቢሆን ‘ነቄ’ መባሉ አይቀርም፡፡
እናማ ምን መሰላችሁ…ዘንድሮ ብዙ ነገራችን በአደባባይ ‘ጉንጭ ላይ’…ከመጋረጃ በስተኋላ ‘ጀርባ ላይ’ ሆኗል፡፡ የምር ቀሺም ነው…አሀ ልክ ነዋ! በኤድዋርድ ስኖውደን ዘመን “አላዩንም፣ አልሰሙንም…” ብሎ ነገር ቀሺም ነው፡፡
እናላችሁ…ሙሉ ኮሚቴው፣ ሙሉ ሥራ አስፈጻሚ…ምናምን ሳያውቃቸው በ“አላዩንም፣ አልሰሙንም…” የሚተላለፉ ውሳኔዎች መአት ናቸው፡፡ ማለት…በ“አላዩንም፣ አልሰሙንም…” የ‘አባባ ገፋ፣ ገፋ’…‘ታክቲክና ስትራቴጂዎች’ የሚተላለፉ፡፡
እኔ የምለው…የ‘አባባ ገፋ፣ ገፋ’ ነገር ካነሳን አይቀር… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይቺን በከተማችን የሆነ ቦታ የተደረገች እውነተኛ ነገር ስሙኝማ፡፡ እናላችሁ…ባልና ሚስቱ የአራት ዓመት ልጅ አላቸው፡፡ ባል ደግሞ ሥራ ነው የሚውለው። ለካስ ሰውየው ሥራ ሲሄድ አንድ መንደር ውስጥ የሚታወቁና ራሳቸውን ‘ሪቻርጅ’ በማድረግ ተወዳዳሪ የሌላቸው ሰው ቤቱ ብቅ ይላሉ፡፡ እናማ… ልጁ “ህጻን ነው፣ አያየንም፣ አይሰማንም…” ብለው እሳቸውና እሜቲት ሚስት ‘እነሆ በረከት’ ምናምን ይባባሉላችኋል፡፡
አንድ ቀን ታዲያ “አያየንም፣ አይሰማንም…” የተባለው ልጅ እየተኮላተፈ ለአባቱ የሰውየውን ስም እየጠቀሰ “አባዬ፣ አንተ ሥራ ስትሄድ አባባ…..ቤታችን ይመጣሉ” ይላል፡፡ አባትየውም ሰውየው መጥተው ምን እንደሚሠሩ ይጠይቀዋል፡፡ ልጁ ምን አለ መሰላችሁ…“ከእማዬ ጋር ገፋ…ገፋ…ገፋ….ያደርጋሉ፣” ሲል ይመልሳል፡፡ የእንቅስቃሴውንም አይነት ለአባቱ በሚችለው መልኩ ያሳያል፡፡
እናላችሁ… ወሬው መንደር ውስጥ ተዛመተና ሠፈርተኛው መካካል የሰውየው መጠሪያ ማን ሆነ መሰላችሁ…“አባባ ገፋ፣ ገፋ…” አሪፍ አይደል!
እናማ… “እነሱ አያዩም፣ አይሰሙም…” እየተባለ የሚደረገው ‘ገፋ፣ ገፋ’ ሁሉ አንዳችን ባናይ ሌላችን እንደምናይ ይታወቅልንማ!
የባልና ሚስት ነገር ካነሳን ይቺን ስሙኝማ…ባል ሆዬ ሚስቱ በሆነ ባልሆነው እየጨቀጨቀችው ለካስ ነገረ ሥራዋ ‘አፍንጫው ጫፍ’ ደርሶበታል፡፡ ታዲያላችሁ…አንድ ቀን እሷ ለቁርስ እንቁላል እየጠበሰች እያለ ማብሰያ ቤት ዘው ብሎ ይገባና ጮክ ብሎ ትዕዛዞች መስጠት ይጀምራል፡፡ “ተጠንቀቂ… ተጠንቀቂ! ትንሽ ቅቤ ጨምሪበት! ኧረ በእግዜሐር! ይሄን ያህል እንቁላል ለምን ጨመርሽ! ያንን ያህል ቅቤ ከየት እናመጣለን! ይጣበቅብሻል ነው እኮ የምልሽ! ተጠንቀቂ… ተጠንቀቂ! ተጠንቀቂ እያልኩሽ እኮ ነው! ምግብ ስታበስይ እኔን አታዳምጪኝም! ሁልጊዜም አታዳምጪኝም! እንቁላሉን ገልበጥ፣ ገልበጥ አድርጊው እንጂ! አንቺ ሴትዮ ነካ ያደርግሻል እንዴ! ያምሻል! ደግሞ ጨው አታብዢ፡፡ ሁልጊዜ ነው እንቁላል ስትጠብሺ ጨው የምትሞጅሪው! ጨው ጨምሪ! ጨው!”
ይሄን ጊዜ ሚስት ብው ትላለች፡፡ “አንተ ሰውዬ ያምሀል እንዴ! እኔ እንቁላል መጥበስ ያቅተኛል!” ብላ ትጮህበታለች፡፡
ባል ሆዬ ምን አለ መሰላችሁ…“መኪና ስነዳ አጠገቤ ሆነሽ ስትጨቀጭቂኝ የሚሰማኝን ስሜት እንድታውቂው ነው!” አለና አረፈው፡፡
እናማ…በየመሥሪያ ቤቱ እነኚህ የፈረደባቸው ‘ዓላማና’…. ‘ግብ’ ምናምን የሚሉ ነገሮች ግድግዳ ሙሉ ተጽፈው ታያላችሁ፡፡ ታዲያላችሁ…ሁሉም ላይ ደግሞ ‘ግልጽነት’ የምትለዋ ነገር አትጠፋም፡፡ ያው እኛም እያየን “ድንቄም ግልጽነት!” እንላለን፡፡ የ“አባባ ገፋ፣ ገፋ…” ዘመን ነዋ!
እዚህ አገር “አያዩንም፣ አይሰሙንም…” ሳይባል የሚሠራ ነገር ምን መሰላችሁ…መንገድ ላይ ፊኛ ማቃለል! የምር…አሳፋሪ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አሀ…ጥግ መፈለግ፣ ከግንብ ጀርባ መዞር ምናምን ቀረ እኮ! (አንዳንዴም እነኚህ ነገሮች ከመረሳታቸው የተነሳ… “ጎጂ ባህል…” ምናምን የተባሉ አይመስላችሁም!) በአደባባይ መጸዳዳት ትክክል አለመሆኑን ለልጆቹ ማስተማር የሚገባው ‘ሱፍ በከረባት ግጥም’ ያደረገው ሰው በጠራራ ጸሀይ ትራፊክ መብራት ላይ ዚፕ ሲፈታ ታገኙታላችሁ፡፡ እናላችሁ… አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያየን ነው፡፡ አንዳንዴ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ከተማዋ በሙሉ ሳንቲም ሳይከፈልባት እንትን መባያ የሆነች ይመስለኛል፡፡
እናላችሁ…በፊት ለፊት ግጥም አድርገን ከሳምን በኋላ ዘወር ሲልሉን ምላሳችንን የምናወጣ አይነት ሰዎች እየበዛን ስንሄድ አሪፍ አይደለም፡፡ እናማ…እንዲህ፣ እንዲህ ሆነን እንዴት መግባባት እንደምንችል…አስቸጋሪ ነው፡፡
ስሙኝማ…የመስማት ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ… ሰውየው ምን አለ መሰላችሁ…“ሽማግሌዎቹ ምን ጊዜም ሰርግ ላይ ሲያገኙኝ አጠገቤ ሆነው ጎኔን ነካ ያደርጉና ‘ቀጥለህ አንተ ነህ’ እያሉ ይጨቀጭቁኛል፣” ይላል፡፡
እሱ ምን እንደሚያደርግ ሲጠየቅ ምን አለ መሰላችሁ…“እኔ ደግሞ ቀብር ላይ አጠገባቸው እሆንና ጎናቸውን ነካ እያደረግሁ ‘ቀጥሎ እርሶ ነዎት’ እላቸዋለሁ፡፡”
እናማ…“አያዩንም፣ አይሰሙንም” እየተባለ የሚደረጉ ‘አባባ ገፋ፣ ገፋ…’ ነገሮችን የሚያስቀር ተአምር አንድዬ ይላክልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3137 times