Saturday, 19 November 2011 14:17

“ሰውን ሰው ያደረገው Face book ሳይሆን Bank book ነው”

Written by  በፍቃዱ አባይ
Rate this item
(1 Vote)

ፌስ ቡክ የሃሳብ ማንሸራሸርያ መድረክ ነው ብል አገዘፍከው እባል ይሆን? በርግጥ ሃሳቡ ሁሌ ቁምነገር ላይሆን ይችላል፡፡ ቀልድና ዋዛ ፈዛዛ ሊበረክትም ይችላል፡ ግን ሁሉም ውስጥ የሆነ ሃሳብ አይጠፋም፡፡ በዚህ እሳቤ ነው አንዳንዶች ፌዝ ቡክ እያሉ የሚያፌዚበትን የማህበራዊ ድረ ገጽ መድረክ (ፌስ ቡክን) የምቃኘው፡ ከምን ልጀምር … እንግዲህ በፈቃዴ ከማህበራዊ ብሶት ጀምረናል፡፡ እንደሚታወቀው በአማርኛ ዓ.ነገር መስራት ገና ስንጀምር የሚቀርብልን ምሳሌ ነው- “አበበ በሶ በላ” በኛ የትምህርት ዘመን ማለቴ ነው እንጂ አሁንማ አቤ አይታወቅም፡፡ በሶ መብላቱንም ትቷል ይሉናል - የፌስ ቡክ ምንጮቻችን፡፡

ለምን ብላችሁ የምትጠይቁ ከሆነ የኑሮ ውድነቱ የሚል መልስ ታገኛላችሁ፡፡ በእርግጥ ይሄ ሊገርመን አይገባም፡፡ እንኳን ለምሳሌ ብቻ የሚጠቀሰው አቤ ቀርቶ ዓለምም በኑሮ ውድነቱ እየመሰቃቀለ ነው፡፡  
መቼም አገራችን የቅኔ አገር መሆኗን የሚክድ ያለ አይመስለኝም - ባንዳ ካልሆነ በቀር፡፡ የፌስ ቡክ አባላት በአብዛኛው ሃሳባቸውን የሚገልፁትም በግጥም ነው - ቅኔ ይቀናቸዋል፡፡
አንድ የፌስ ቡክ ፌዘኛ ፍቅረኛው ዕድሜዋ በየዓመቱ ካለበት ንቅንቅ የማይል ሆኖ ቢቸገር ሌላ ምርምር ውስጥ ሳይገባ የቋጠራትን ስንኝ ፌስቡኩ ላይ ለቅኦታል፡፡ እነሆ:-
ካቻምና ሳገኝስ ሃያ ነበር አመትሽ፤
ቀጠልሽም ሃያ አምና ለልደትሽ፡፡
ይጨምራል ብዬ ስጠብቅ ዘንድሮ፤
ለኩሰሽ አየሁሽ ሁለትና ዜሮ፡፡
እናም
ለእድሜሽ ማቆሪያ ካለሽ ገንዳ ነገር፤
ወጣት ሆኜ እንድኖር ገንዳሽን ልበደር፡፡
አሁን ደግሞ የፌስ ቡክን የቡሄ ጭፈራ ግጥም እንመልከት፡፡ ፌስቡክና ቴክኖሎጂ ባህላችን ላይ ያሳረፉትን ተጽእኖ እግረመንገዳችንንም እናያለን፡፡
ሆያ … ሆዬ በፌዝ ቡክ
ሎጊን በለው በሩን የፌስ ቡኩን
ሆያ ሆዬ፤ ሆ፤ ወዴት ልጠለል ሆ
ፌስ ቡክ ከፈትኩኝ ለመከላከል
እዛ ማዶ፤ ሆ፤ አንዱ ተጠምዶ፤ ሆ
በቻት ተጥዶ፤ ሆ
እዚያ ማዶ ሆ፤ አንዱ ተናዶ፤ ምላሽ አጥቶ፤
እዛ ማዶ ሆ፤አንድ ችግኝ፤ እዛ ማዶ ሆ፤ አንድ ችግኝ፤ የኔማ እንትና
አድ አድርጊኝማ
“እደጉ ልጆች ጭፈራውን ወደነዋል፤ ሙልሙሉን በኦንላይን እንልክላችኋለን!!!”
ይላል፡፡ እንግዲህ ቡሔ በያመቱ ሲመጣ ጅራፍ እያጮሁ ከመንደር መንደር ድምፁን በመቀባበል አውዳመቱን የሚያውጁት የሰፈር ልጆች ቡሔ በኦንላይን (Online) ከሆነ ምን ይውጣቸው ይሆን?
ፌስ ቡክ ላይ የማይነሳ ርዕሰ ጉዳይ የለም፡፡
ፍቅር፣ ፖለቲካ፣ ባህል፣ ማህበራዊ ህይወት ወዘተ…በቀልድም በቁምነገርም ይነሳል፣ ይተነተናል፣ ይብጠለጠላል፡፡ በትዳር ዙሪያ የተቀለደውን ላካፍላችሁ፡
ሚስት- የኔ ውድ፤ እኔ አሁን ብሞት ሌላ ሚስት ታገባለህ?
ባል - በፍጹም!
ሚስት- እርግጠኝ ነኝ ታገባለህ?
ባል - (በንዴት) በቃ አገባለሁ
ሚስት - ግን እኛ ቤት ውስጥ ትኖራለች?
ባል - እና ሌላ ቤት ልከራይ?
ሚስት - እሺ የእኔን ልብስ እንድትለብስ ትፈቅድላታለህ?
ባል - (ድንገት አምልጦት) ኧረ እሷ በቁመት ትበልጥሻለች!
የሥራ ባህልን አስመልክቶ ስለ ጃፓኖችና ስለመካከለኛው ምስራቅ ህዝቦች የሰፈረው ደግም ራሳችን እንድንመረምር የሚነሽጥ ነው፡፡ እንዲህ ይላል - ከፌስ ቡክ የተገኘው መረጃ፡፡
Japanese attitude for work
If one can do it, I can do it.
If no one can do it, I must do it.

Middle Eastern attitude for work

Wallhi, if one can do it, I let him do it.
If no one can do it, ya-habibi how can I do it.
የእኛስ? ለስራ ያለን አመለካከት ለየትኛው ይቀርባል? ምናልባት ለሁለተኛው፡፡
አንድ ወዳጄ ደግሞ ባለቤቷን ሳይጠቅስ አንድ ማለፊያ ግጥም ፌስ ቡኩ ላይ አስፍሯል፡፡ እኔ ግን የባለቅኔው ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን እንደሆነ ደረስኩበት፡፡ ግጥሙ እንዲህ የሚል ነው:-
የማይነጋ ህልም ሳልም፣
የማይድን በሽታ ሳክም፣
የማያድግ ችግኝ ሳርም፣
የሰው ህይወት ስከረክም፣
እኔ ለኔ ሆኜ አላውቅም፡፡
ፌስ ቡክ በትክክልም ፌዝ ቡክ እንደሆኑ ማሳያ የሆኑ ጥቅሶችም ልታገኙ ትችላላችሁ፡፡ ርሀብ ቢያሰቃይህ በእንቅልፍ ያልፍልሐል፤ ማጣት ኮንዲሽን ነው፤ ያልጠረጠረ ጸጉሩን አበጠረ … ዓይነት ፌዝ አከል አባባሎች በሽ ናቸው፡፡ መሰል ፌዞችን ባነበቡበት አንደበትዎ ደግሞ መንፈስዎን የሚገዙ፤ በማራኪ ምስሎች ያሸበረቁ፤ ግብረ-ገብ ምክሮችን ሊያነቡ ይችላሉ፡፡ ልክ እንደዚህ፤
በገንዘብ የሚበልጥህን በዕውቀት ብለጠው
በዕውቀት የሚበልጥህን በፍቅር ብለጠው
በፍቅር የሚበልጥህን እርሱን ግን ውደደው፡፡
በሀገሩ ጉዳይ አንጀቱ ያረረ ስሜቱን በስድብም ሆነ በጥቅስ እንዲሁም በፌዝ እንደሚገልጸው ሁሉ የሀገር ፍቅር አንጀቱ ድረስ ዘልቆ የገባም ስሜቱን በፌዝ መጽሐፍ (ፌዝ ቡክ) ላይ ከመግለጽ የሚያግደው የለም፡፡ ቀጣዩን ግጥም አንብቡ፡፡
ኢትዮጵያዊነት
ስኖር እስከዛሬ … ደግሞም ስኖር ነገ
በውስጤ የሚሄድ ሁሌም እያደገ
አለኝ እኔ አንድ ስም
ዘላለማዊ የማንነት ዕትም
እናም ላንዱ ስሜ
እስከ ዘላለሜ!!!
ጥልቅ ጥብቅ ነው ክብሬ
በክፉም ሲያነሱት ይቆጣል ደም ስሬ
በሔድኩበት ዓለም ክብርና ኩራቴ
ኢ.ት.ዮ.ጵ.ያ.ዊ.ነ.ቴ
ስትል አንዲት እንስት የገጠመችውን ግጥም ሌላ ባለ ፌዝ ቡክ የራሱ ፌስ ቡክ ላይ ለጥፎት አንብቤያለሁ፡፡
የፌስ ቡክ አንዱ መለያ ጽሑፎች የጋራ ሃብት መሆናቸው ነው፡፡ ፎቶዎች፣ ቀልዶች፣ ቁምነገሮች፣ ተረቦች፣ ወዘተ አንዴ ከተለቀቁ ማንም የራሱ ንብረት ያደርጋቸዋል፡፡ የአዕምሮ ሃብት ስርቆት (plagiarism) በፌስ ቡክ አይታወቅም፡፡
የፌዝ ቡክ አባል ሲሆኑ ሆደ ሰፊ መሆንን ይጠይቃል፡፡ በቅርቡ በተጀመረውና ተሟሙቆ በቀጠለው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዙሪያ የሚቀርቡ ፌዞች ሌሎቹ የፌዝ ቡክ ማድመቂያዎች ናቸው፡፡ በዚህ ውድድር አርሰናል በሜዳውና በደጋፊው ፊት በማንችስተር ዩናይትድ 8ለ2 ከተሸነፈ በኋላ ከአንድ እስከ አስር በሚጻፉ ቁጥሮች መሐከል በስምንት ቁጥር ፈንታ አርሰናል የሚል ስም በመጻፍ ማንቼዎች አርሴዎችን ሲያበሽቁ ከርመው ነበር፡፡ ታድያ ምን ያደርጋል? ይህ የፌዝ ቡክ ስላቅ ለማንችስተሮችም አልቀረላቸውም፡፡ በከተማ ተቀናቃኛቸው ማንችስተር ሲቲዎች የደረሰባቸው የ6ለ1 ሽንፈት በኋላ ስድስት ቁጥር በፈንታዋ ማንቼ ስትባል፣ አለቃ ፈርጉሰን ራሳቸውን ይዘው የተነሱትን ፎቶግራፍ በማስደገፍ “የእጄን ነው ያገኘሁት” ከሚል መግለጫ ጋር ሲሰራጭ ሰንብቷል፡፡
ቅድም ሳልጠቅስ ያለፍኳት አንድ የፌስ ቡክ ጥቅስን ሳልነግራችሁ ማለፍ ልቤ እሺ አላለምና እነሆ:-
“ሰውን ሰው የሚያደርገው Face book ሳይሆን Bank book ነው፡፡
መቼም ለባንኮች ጉደኛ ማስታወቂያ እንደምትሆን አልጠራጠርም፡፡ የፌስ ቡክ አባላት ግን ደጐች ናቸው - በነፃ እነሆ ብለዋል፡፡
ለልደት የተቋጠረች ስንኝም ያገኘሁት ከፌስ ቡክ ላይ ነው፡፡ እናንተም በልደት ቀናችሁ ብትለጥፏት ጠያቂ የለባችሁም፡፡ በሉ ደህና ሰንብቱልኝ፡፡
ዕድሜ ምሳሌ ነው የህይወት መኪና፤
ዘመንም መንገድ ነው የዕድሜ ጎዳና፤
እኛም ተጓዦች ነን ከአምና ካቻምና፡፡
መንገደኛው ጊዜ አይቀርም መድረሱ፤
መኪናም አይቀርም አንድ ቀን መፍረሱ፤
ዘመን ግን ይኖራል ውልፊት የለም በሱ፡፡
ተጓዦች ከሆንን በዚህች አለማችን፤
ዛሬ ነው መደሰት በልደት ቀናችን፡፡

 

Read 5354 times Last modified on Saturday, 19 November 2011 14:24