Print this page
Saturday, 13 July 2013 11:21

ተቃዋሚዎችም እኮ እየተሰደዱ ነው!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(16 votes)

ዲሞክራሲው ያመጣው ነው

እናላችሁ --- ኢቴቪ ያነጋገራቸው ምሩቃን በሙሉ “በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተን --- የዶሮ ወይም የንብ እርባታ አሊያም ኮብልስቶን እንሰራለን” ሲሉ ዋሉ (በከንቱ ነዋ ጥይት የባከነው!) እኔ የምለው ግን--- ዶሮ ለማርባት የአራት ዓመት ድግሪና ማስተርስ ምን ይሰራላቸዋል? ወይስ የዛሬ ድግሪና ማስትሬት እንደ 100 ብራችን በኢንፍሌሽን ተጠቅቷል! (ኢህአዴግ ቁምነገሩን ሁሉ ፖለቲካ እያደረገብን ተቸገርን እኮ!) የሆኖ ሆኖ ግን 40ሺ የጦቢያ ተማሪዎች ከዩኒቨርስቲ ተመርቀዋልና “ኮንግራ!” ብለናቸዋል (ቢደራጁም ባይደራጁም!)

ያለፈው ሳምንት ፌሽታ እንዴት ነበር? (አልገባንም እንዳትሉኝ ብቻ!) ስንት ሚኒስትሮች እንደተሾሙ ዘነጋችሁት ማለት ነው? (“ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም” ብትሉ አልሰማችሁም!) ከአስር በላይ ሹመት እኮ ነው የተሰጠው! ያውም የአዲስ አበባ ከንቲባና ሌሎች ሹመቶችን ሳይጨምር (በሙስና ከስልጣን መነሳቱም ቀጥሏል!) ፌሽታው ግን የሹመት ብቻ አልነበረም፡፡ 

የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ምርቃትስ? እሱም እኮ ከሹመት አይተናነስም፡፡ 40ሺ ገደማ ተማሪ እኮ ነው የተመረቀው፡፡ ችግሩ ግን ምን መሰላችሁ? ለኢቴቪ በሰጡት ቃለምልልስ አንዳቸውም እንኳን “በተማርኩት ትምህርት እንዲህ እፈጥራለሁ” ወይም “አንድ አዲስ ነገር እፈለስፋለሁ” የሚል የተስፋ ቃል አልሰጡንም (ምናለ ለአፋቸው እንኳ ቢሉት) አብዛኞቹ ከካድሬ ማሰልጠኛ ኮሌጅ የወጡ ይመስል “ተደራጅተን --” እያሉ ሲናገሩ እኮ ነው የሰማነው፡፡
(“ተደራጅተን እንታገላለን” ግን አላሉም) ቢሉስ ከማን ጋር ነው የሚታገሉት? (ብድር ከሚሰጣቸው ፓርቲ ጋር? አይሞከርም!) በዚያ ላይ እኮ የዜጎች መብትና ነፃነት ከተከበረ 2O ዓመት ገደማ አለፈው (ለህዝብ ጥቅም ሲባል አንዳንዴ ቢጣስም!) አንዳንዶቹማ መደራጀታቸውን እንጂ ተደራጅተው እንኳን ምን እንደሚሰሩ አያውቁም፡፡ (የመደራጀት ድግሪ ተጀመረ እንዴ?)
እናላችሁ --- ኢቴቪ ያነጋገራቸው ምሩቃን በሙሉ “በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተን --- የዶሮ ወይም የንብ እርባታ አሊያም ኮብልስቶን እንሰራለን” ሲሉ ዋሉ (በከንቱ ነዋ ጥይት የባከነው!) እኔ የምለው ግን--- ዶሮ ለማርባት የአራት ዓመት ድግሪና ማስተርስ ምን ይሰራላቸዋል? ወይስ የዛሬ ድግሪና ማስትሬት እንደ 100 ብራችን በኢንፍሌሽን ተጠቅቷል! (ኢህአዴግ ቁምነገሩን ሁሉ ፖለቲካ እያደረገብን ተቸገርን እኮ!) የሆኖ ሆኖ ግን 40ሺ የጦቢያ ተማሪዎች ከዩኒቨርስቲ ተመርቀዋልና “ኮንግራ!” ብለናቸዋል (ቢደራጁም ባይደራጁም!)
እኔ የምለው--- ከአስር በላይ ሚኒስትሮች ተሹመው “እንዴት ሹመት ያዳብር” አትልም ብላችሁ ታዘባችሁኝ አይደል? እንዲህ ያለው ጥያቄ ግን በዋናነት የሚመነጨው ከምን መሰላችሁ? የኢህአዴግን ባህርይ ካለማወቅ ነው፡፡ ኢህአዴጎች ሲሾሙ እኮ “ኮንግራ” ምናምን አይወዱም፡፡ (የፓርቲው ባህል አይፈቅድማ!) ዝም ብሎ አይፈቅድም ብቻ ሳይሆን ሚዛን የሚደፋ ምክንያትም አላቸው፡፡ አያችሁ ---- ለኢህአዴግ አባል የትኛውም ተጨማሪ ሥልጣን ወይም ሹመት ተጨማሪ መስዋዕትነት ማለት ነው (ራሳቸው ያሉትን እኮ ነው) መቼም ሥልጣንን እንደ “መስዋዕትነት” የሚቆጥር ብቸኛው የዓለማችን ፓርቲ ኢህአዴግ ሳይሆን አይቀርም፡፡ (ሌላ ፓርቲ አለ የምትሉ መረጃና ማስረጃችሁን ይዛችሁ ከች በሉ!)
እኔ የምለው---- ኢቴቪ በደቡብ ክልል በህገወጥ ስደትና ደላሎች ዙሪያ ያካሄደውን ውይይት አያችሁልኝ? ዝም ከተባለ እኮ ዜጎች ሁሉ ሄደው ጋራና ተራራው ብቻ የሚቀር ነው የሚመስለው፡፡ (ማን ነበር አገር ማለት ጋራና ተራራው አይደለም ያለው?) እንዴ --- አስተማሪው፣ ተማሪው፣ የኤክስቴሽን ሠራተኛው፣ ፖሊሱ -- የቀሩ እኮ የለም! በነገራችን ላይ ኢቴቪ በዚህ አሳሳቢ የአገር ጉዳይ ላይ ከደቡብ ነዋሪዎች ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ማድረጉን ሳላደንቅ አላልፍም (አድናቆቴ የጋዜጠኛዋን ፕሮፓጋንዳ አይመለከትም !) ኢህአዴግ ግን ለምን አንዳንዴ እንኳ ሰው የሚለውን እንደማይሰማ ግራ ግብት ይለኛል (ተቃዋሚዎች ትዝ እያሉት ይሆን!) ይታያችሁ --- በደቡብ በተደረገው ውይይት ላይ ነዋሪዎች ለምን ብዙ ሺ ብሮች እየከፈሉ ባዕድ አገር እንደሚጓዙ ተጠይቀው፣ ቁልጭ ባለ አማርኛ መልሰዋል - “የምንሰራበት በቂ መሬት የለንም”፣ “ተደራጅተን ብድር ስንጠይቅ የሚሰጠን አናገኝም”፣ “ለመነገድ ስንሞክር ፖሊስ ያሳድደናል” ወዘተ -- እያሉ፡፡ የኢቴቪ ጋዜጠኛ ተዘጋጅታ የሄደችው ግን ልትከራከራቸው እንጂ ልትሰማቸው አልነበረም፡፡ ለዚህ እኮ ነው አንድ አዛውንት “ስደቱ ጊዜው ያመጣው ነው!” ሲሉ ኢህአዴግ ያመጣው ነው እንዳሉ ቆጥራው ሙግት የያዘችው፡፡ እናላችሁ --“አሁን እኮ ጊዜው ተለውጧል! ኢትዮጵያ እያደገች ነው! የሥራ እድል ተከፍቷል!” ወዘተ-- ስትል ከእድሜ ጠገቡ ባለእውቀት አዛውንት ጋር ጉንጭ አልፋ ክርክር ውስጥ ገብታ አረፈችው (ያለእዳው ዘማች! አሉ) እሳቸው እንግዲህ ምን ያድርጉ? ሃቁን ነው የተናገሩት - ኖረው ያዩትን እውነት! እሷ ደግሞ ፕሮፓጋንዳ ካልቀላቀለች አይሆንላትም (የባቢሎን ቋንቋ!) ለነገሩ በጋዜጠኛዋም እኮ መፍረድ አይቻልም (አትፍረድ ይፈረድብሃል ነው!) እሷ የምታውቃትን “ኢትዮጵያ” ዜጎች ሁሉ የሚያውቁ እየመሰላት እኮ ነው፡፡ በነገራችን ላይ “ኢትዮጵያ አድጋለች--ሥራ በሽበሽ ነው!” የሚል ፕሮፓጋንዳ ስለአገሩ ጠንቅቆ ለሚያውቅ ነዋሪ መስበክ ብዙም አያዋጣም፡፡ ምናልባት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በሚደረግ የምርጫ ክርክር ላይ ይጠቅም ይሆናል (ይሄኛው የፖለቲካ ጨዋታ ነዋ!) በቅርቡ ጠ/ሚኒስትሩ ከነጋዴዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ስለስደተኞች ጉዳይ ሲናገሩ፣ ቀደም ሲል የአረብ አገራትን የቤት ሰራተኞች ፍላጎት የሚሞሉት እንደ እነፊሊፒንስ ያሉ አገራት እንደነበሩ ጠቅሰው፣ አሁን ግን እነሱ ስላደጉና ዜጎቻቸውን በየአገራቸው ለመቅጠር ስለቻሉ ተረኞቹ የእኛ አገር ዜጎች ሆነዋል” በማለት ካስረዱ በኋላ “መፍትሄው እንደ እነ ፊሊፒንስ ማደግ ብቻ ነው” ብለዋል (ይሄ ነው ከፕሮፓጋንዳ የፀዳ መልስ ማለት!) እስከዛ ግን የኢቴቪ ጋዜጠኛዋ እንዳደረገችው ቢያንስ በህገወጥ ደላሎች አማካኝነት የሚደረገውን ጉዞ ለመግታት ብዙ ውይይቶች፣ ብዙ ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች በማድረግ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ ይቻላል፡፡ ይሄኔ ፕሮፓጋንዳ ከእነአካቴው አያስፈልግም፡፡ መርሳት የሌለብን ምን መሰላችሁ----በአገሩ የሥራና የእድገት እድል እያለ ደቡብ አፍሪካም ሆነ አረብ አገር ለመጓዝ የሚመርጥ ማንም የለም (“ከማያውቁት መላዕክ የሚያውቁት ሰይጣን” ይባል የለ!)
በነገራችሁ ላይ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም እኮ እየተሰደዱ ነው፡፡ እነሱ ግን በህገወጥ ደላላ ተታለው አይደለም፡፡ የስደት ምክንያታቸውም እንደሌሎች ዜጎች ኢኮኖሚያዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነው፡፡ እኔ ግን በተቃዋሚዎች ስደት የአንዳንድ ኒዮሊበራል መንግስታት (ኢህአዴግ arm twister ወይም “እጅ ጠምዛዥ” የሚላቸውን ማለቴ ነው) እጅ አለበት ባይ ነኝ፡፡ ለምሳሌ የኦባማን አገር አማሪካን እጠረጥራታለሁ፡፡ ለምን መሰላችሁ? አብዛኞቹ የኢህአዴግ ተቃዋሚዎች እኮ እዚያ ነው የከተሙት፡፡ (አሜሪካ ባትኖር ኖሮ የት ያኮርፉ ነበር!) ተቃዋሚዎች ግን ለአመራሮችም ሆነ ለአባላቶቻቸው ስደት ተጠያቂው ማነው ሲባሉ ጣታቸውን የሚሰነዝሩት ኢህአዴግ ላይ ነው፡፡ እንዴት ሲባሉም--- ገዢው ፓርቲ እያደረሰብን ነው የሚሉትን በደል ዘርዝረው ያስረዳሉ፡፡ ከተለመዱት እስርና ወከባ በተጨማሪ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብታችንን ተነፍገናል የሚሉት ተቃዋሚዎች፤ በአገራቸው ጉዳይ ባይተዋር መደረጋቸውንም ይናገራሉ (“በህዳሴው ግድብ ዙሪያ አላማከረንም” የሚል ቅሬታቸውን ልብ ይሏል) “ኢህአዴግ ከህዝብ ጋር ከተገናኘን አሲረን ሥልጣን የምንቀማው ስለሚመስለው መፈናፈኛ አሳጥቶናል” የሚሉት ተቃዋሚዎች፤ ለዚህ ነው አመራሮችም ሆኑ አባላት የሚሰደዱት ባይ ናቸው፡፡ “ዲሞክራሲ ለኢህአዴግ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው” የሚለው ኢህአዴግ ግን የተቃዋሚዎች ስደት ዲሞክራሲው ያመጣው ነው ይላል፡፡ (እድገቱ ያመጣው ነው እንደሚለው መሆኑ ነው!)እኔ ግን የስደት ነገር በጣም የሚያሳስበኝ መቼ መሰላችሁ? ቱባ ቱባ የኢህአዴግ ባለስልጣናት መሰደድ የጀመሩ ዕለት ነው (ምን አጥተው እንዳትሉኝ ብቻ!) ለነገሩማ የተቃዋሚዎችን ያህል አይሆኑም እንጂ ስንቶቹ ለኮንፍረንስና ለህክምና እያሉ ተሰደው የለ፡፡ (የኢህአዴግ አባላትም ሲሰደዱ ተቃዋሚ ይሆናሉ አይደል?) ወዳጆቼ--- መሪዎች ስደት ከጀመሩ እኮ ሃይለኛ ቀውስ ነው የሚፈጠረው፡፡ (ተሰደው ካላየን አናምን እንዳትሉኝ!)
ኢህአዴግን በመዝለፍ ስማቸው የገነነ አንድ የተቃዋሚ አመራር ምን ቢሉኝ ጥሩ ነው ---- “ኢህአዴግ አውራ ፓርቲ ሳይሆን አውራ ዶሮ ነው!” አባባላቸው ፈገግ ቢያሰኘኝም ለምን እንዲያ እንዳሉ ስላልገባኝ ማብራሪያ ጠየኳቸው፡፡
እሳቸውም ፈገግታቸውን በማስቀደም “ከተማዋን እያት እስቲ --- እንደ አውራ ዶሮ ቆፋፍሮ ቆፋፍሮ--” አሉኝና አረፉት፡፡ እኔማ “በእርግጥ በየቦታው ቁፋሮ አለ ግን የእድገት ቁፋሮ ነው!” ልላቸው ዳድቶኝ ነበር፡፡ ግን ደግሞ “የኢህአዴግ ካድሬ” ብለው እንዳይፈርጁኝ ፈርቼ አፌን ዘጋሁ (“በተዘጋ አፍ ---” ይባል የለ!)

Read 5068 times